Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት​አበረታች ንጥረ ነገርና መዘዙ

​አበረታች ንጥረ ነገርና መዘዙ

ቀን:

በኢትዮጵያውያን የአትሌቲክስ ደጋፊዎች ዘንድ 1994 ዓ.ም. የማይረሳ ጊዜ ነው፡፡ ይኼ ዓመት ለስምንት ዓመታት ያህል የርቀት ሩጫ ንጉሥ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ጉዞ ላፍታ የተገታበት ዓመት ነበር፡፡ በኮመንዌልዝ ስታዲየም የተደረገውን ይሔንን ዓለም አቀፍ ሻምፒዮና ሩጫ ብዙ ኢትዮጵያውያን ሌላ ጊዜ እንደሚያደርጉት በጉጉት መከታተላቸውን ቀጥለዋል፡፡ ማሸነፉን ለቅጽበትም ያህል የማይጠረጥሩት ብዙ ኢትዮጵያውያን የመጨረሻውን ደወልና የኃይሌ አፈትልኮ መውጣትን ይጠባበቃሉ፡፡

ከትልቁ ቡድን ተለይተው ኃይሌ ገብረ ሥላሴ አሰፋ መዝገቡና ኬንያዊው ቻርለስ ካማቲ እየተመራሩ ሩጫቸውን ተያይዘውታል፣ የመጨረሻው ደወል ሲደወልና የቻርለስ ካማቲ ተስፈንጥሮ መውጣት ያልተጠበቀ ነበር፡፡ እንደ ሲድኒ ኦሊምፒክ ኬንያዊውን ሯጭ ፖል ቴርጋትን በሚያስገርም ሁኔታ ተናንቆ ያሸነፈበት ሁኔታ ይደገማል ብለው ብዙዎች ቢያስቡም ያልተጠበቀው ሆነና ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ተቀደመ፡፡

በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የኃይሌ ከአንደኛ ደረጃ መውረድ እንደ ሽንፈት በሚታይበት ሁኔታ ብዙዎች ለማመን ተቸግረው ታይተዋል፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሻምፒዮኖች አሸናፊ፣ በበርካታ የወርቅ ሜዳሊያ ኢትዮጵያን ያንቆጠቆጣትን የርቀት ሩጫ ንጉሥ በዚህ ውድድር ላይ ሦስተኛ መውጣት ለማመንም የተቸገሩ ብዙዎች ነበሩ፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም ‹‹ለካ ኃይሌም ሰው ነው›› የሚል የሚገርም ጽሑፍ ይዘው መውጣታቸውን አንዳንዶች ያወሱታል፡፡ ውጤቱን ብዙዎች አዝነው በፀጋ ቢቀበሉትም አንዳንድ ዜናዎች ቻርለስ ካማቲ አበረታች ንጥረ ነገር በመውሰዱ ምክንያት ከውድድሩ ውጭ በመሆኑ አሸናፊነቱ ለኃይሌ እንደሆነ ተወርቷል፡፡ ትንሽ የዚህ ዜና ሁኔታ የሚያስገርመው ሁለተኛ የወጣው አሰፋ መዝገቡን በምን መንገድ አልፎ አንደኛ መሆኑን አለመግለጽ አለመቻሉ ነው፡፡

የዚህ ሁሉ ስሜታዊነት ምንጩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአትሌቱ ያለው ፍቅር ነው፡፡ ትልልቅ እናቶች እንኳን ሳይቀሩ ውድድሮች በሚካሄዱበት ጊዜ ለማመን በሚደንቅ ሁኔታ ኢትዮጵያውያን ሯጮች እንዲያሸንፉ ስለት ይሳላሉ፡፡

በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የኢትዮጵያን ባንዲራ ከፍ አድርገው በማውለብለባቸው የኢትዮጵያ ባለውለታ ተደርገውም በብዙዎች ዘንድ እነዚህ አትሌቶች ተሥለዋል፡፡ በባዶ እግሩ ማራቶንን ካሸነፈው አበበ ቢቂላ ጀምሮ የመጀመሪያዋ ጥቁር አፍሪካዊት ወርቀኛ የሆነችው ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ ብዙዎቹ አትሌቶች የማይረሳ አሻራ ማሳረፍ ችለዋል፡፡ ከኃይሌ መሸነፍ አንድ ዓመት በኋላ ብዙዎች ያልሰሙት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ ይህም የርቀት ሩጫ ተወዳዳሪ የሆነው አለነ እመረ ናንድሮሎን የሚባለውን አበረታች ንጥረ ነገር በመውሰድ ለሁለት ዓመት ያህል ታገደ፡፡

ይኼ ንጥረ ነገር ጡንቻን ማጐልበት፣ የምግብ ፍላጐትን ማነቃቃት፣ የቀይ የደም ሴልን ቁጥር መጨመር፣ የአጥንትና ጥንካሬ ይጨምራል፡፡ ይሔንን አበረታች ንጥረ ነገር መውሰዱ ከአሥር ዓመት በላይ ዕድሜ ቢያስቆጥርም ለብዙ ኢትዮጵያውያን ጉዳዩ ዱብ ዕዳ ነው፡፡ የሰሞኑ የስድስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአበረታች ንጥረ ነገሮች ጋር ተያይዞ መነሣትም ለብዙዎች አስደንጋጭ መርዶ ሆኗል፡፡ ብዙዎችም በኢትዮጵያ አትሌቲክስ አደጋ የተጋረጠበት መሆኑን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ ዶ/ር አያሌው ጥላሁን በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የሕክምና ዲፓርትመንት ኃላፊ ስድስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አበረታች ንጥረ ነገር በመውሰድ ተጠርጥረው ምርመራ ላይ እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡ የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) በአትሌቶቹ ላይ የተገኘውን መረጃ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ልኳል፡፡ አይኤኤኤፍ በዘረጋው ፕሮግራም አትሌቶች ከውድድሮች በፊትና በኋላ እንዲሁም በየአገሮቹ ውስጥ በሚያደርጉት ምርመራ መሠረት እነዚህ አትሌቶች ምርመራ እንደሰጡ ዶ/ር አያሌው ገልጸዋል፡፡ በአይኤኤኤፍ የምርመራ አካሄድ መሠረት አትሌቶቹ ‹‹ኤ›› እና ‹‹ቢ›› የሚል ሁለት የምርመራ ናሙናዎችም ሰጥተዋል፡፡ አትሌቶቹ ተገኝቶባቸዋል የሚባለውን ንጥረ ነገር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የዓለም አቀፍ የፀረ አበረታች ንጥረ ነገር ኤጀንሲ (ዋዳ) በዚህ ዓመት ውስጥ በዋዳ ከተከለከሉ ንጥረ ነገሮች ዝርዝር ውስጥ መኖሩን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማመሳከር የመጀመሪያ ሥራ እንደነበር ዶ/ር አያሌው ይገልጻሉ፡፡ ከዚያም በመቀጠል አትሌቶቹን ጠርተው ያነጋገሩ ሲሆን፣ አይኤኤኤፍ በላካቸው ጥያቄዎች መሠረትም እነዚህን ንጥረ ነገሮች መውሰዳቸውን፣ ከወሰዱም የት ቦታና እነዚህንም አበረታች ንጥረ ነገር የሰጧቸውንም ግለሰቦች ማንነት የመሳሰሉ ጥያቆዎችንና መልሳቸውን በማካተት ለአይኤኤኤፍ ልከዋል፡፡ ይሔ ምርመራ ቀጣይነት ያለውና ምርመራውን አይኤኤኤፍ አጠናቆ እስከሚጨርስ ድረስ የአትሌቶቹ ማንነትና ዝርዝር ጉዳዮች በምስጢር መያዝ እንዳለበት የዋዳ ሕግ ስለደነገገ ይሔንን አካሔድ ፌዴሬሽኑ እንደተከተለ ዶ/ር አያሌው ይገልጻሉ፡፡

የዚህን አካሔድ ያልተረዱ ሰዎች የአትሌቶቹ ማንነት እንዲገለጽ በጥብቅ እየተከራከሩ መሆናቸውንም ዶ/ር አያሌው አልደበቁም፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የዋዳን ሕግ ጥሶ የአትሌቶቹን ማንነት ቢገልጽ ፌዴሬሽኑ እስከመታገድ ሊያደርሰው እንደሚችልም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከምርመራው በኋላ የመጀመሪያ መልስ ከአይኤኤኤፍ የተላከ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት ሦስቱ አትሌቶች ጊዜያዊ ዕገዳ ተጥሎባቸዋል፡፡ የዕገዳውም ጭብጥ እነዚህ አትሌቶች በማንኛውም አገር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ ውድድር እንዳይሳተፉ የሚከለክል መሆኑን ዶ/ር አያሌው ገልጸዋል፡፡ የመጨረሻው ውሳኔ የሚታወቀው የቢ ናሙና ውጤት ሲታወቅ ሲሆን፣ አትሌቶቹ በራሳቸው ወጫቸውን በመሸፈን ምርመራው የሚካሄድበት ሎዛን ከተማ በመሄድ ማየት እንደሚችሉ አክለው ገልጸዋል፡፡ በዘርፉ ላይ ዕውቀት ያላቸው ሰዎች የቢ ናሙና ውጤት ከኤ ናሙና ምንም ልዩነት እንዴለለው ይገልጻሉ፡፡ የመለያየት አጋጣሚው በጣም ኢምንት እንደሆነም ጨምረው ይገልጻሉ፡፡ የቅጣት ውሳኔውም ከቢ ናሙና ውጤት በኋላ ሲሆን፣ የቅጣት መጠኑም በወሰዱት አበረታች ንጥረ ነገሮችና ሌሎችንም ጉዳዮች የሚያጤን መሆኑንም ዶ/ር አያሌው ይገልጻሉ፡፡

ዘንድሮ አስደንጋጭ የሆነው የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ስም በአበረታች ንጥረ ነገሮች መነሣት ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም የአበረታች ንጥረ ነገሮች ቅሌት የተጋለጠበት ዓመትም ነው፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እንደዘገቡት፣ የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ከፍተኛ ኃላፊዎች ከአበረታች ንጥረ ነገር ጋር በተያያዘ ቅሌት ውስጥ መግባታቸው አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ከሙስናና ጉቦም ጋር በተያያዘም ማዕቀብ መጣሉ ትልቅ ዜና ነበር፡፡

በአይኤኤኤፍ ውስጥ ያሉ ከፍተኛ  ኃላፊዎች የሕይወት ጊዜ ገደብ የተጣለባቸው ከአበረታች ንጥረ ነገር ተያይዞ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙት አትሌቶችን ጉቦ በመጠየቅ የመሸፋፈን ሥራ በመሥራታቸው ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የቀድሞው የአይኤኤኤፍ ፕሬዚዳንት የላሚንዲያክ ልጅ ፓፓ ማሣታ ዲያክ አንዱ ነው፡፡ በአይኤኤኤፍ ውስጥም በአማካሪነት ሲያገለግል የነበረ ነው፡፡ ሌላው አስደንጋጭ ዜና የነበረው የራሱ የዓለም አቀፉ ፀረ አበረታች ንጥረ ነገር ዳይሬክተር ገብርኤል ዶል ከቅሌቱ ጋር በተያያዘ ከኃላፊነቱ ለአምስት ዓመት እንዲታገድ ውሳኔ ላይ መደረሱ ነው፡፡

እነዚህ ግለሰቦች ቅጣቱ የተላለፈባቸው እ.ኤ.አ. የ2010ሩ የለንደን ማራቶን አሸናፊዋ ሩሲያዊት አትሌት ሊሊያ ሾቡኮቫ ከ450 ሺሕ ዩሮ በላይ ጉቦ በመስጠት በውድድሩ ላይ ተካፋይ እንድትሆን በመፍቀዳቸው እንደነበርም ተዘግቧል፡፡  

ከለንደን ማራቶን አሸናፊነቷ ቀጥሎ በቺካጐ ማራቶንም ለመሳተፍ የበቃችው ከዚህ ጉቦ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ አትሌቷ የኋላ ኋላ በተደረገባት ተደጋጋሚ ምርመራ አበረታች ንጥረ ነገር ተጠቅማ በመገኘቷ ለ38 ወራት ያህል ከምንም ዓይነት ስፖርታዊ ውድድር ታግዳ እንድትቆይ ብትገደድም ለዋዳ ባሳየችው ትብብር ቅጣቱ ወደ ሰባት ወራት ዝቅ እንዲልላት ተደርጓል፡፡

ባለፈው የፈረንጆች ዓመትም የጀርመን ቴሌቪዥን ባቀረበው ጥናታዊ ዘገባ 99 በመቶ የሚሆኑት የሩሲያ አትሌቶች በአበረታች ንጥረ ነገር መጠርጠራቸውንና ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸውን ዘግቧል፡፡ ይህን ተከትሎም ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከአምስት ዓመት በፊት በመቶ የሚቆጠሩ የተጠረጠሩ የደም ናሙናዎችን ተከታትሎ የምርመራ ውጤታቸውን ይፋ ባለማድረጉ ከሩሲያውያኑ አትሌቶች የአበረታች ንጥረ ነገር ቀውስ ጋር ተያይዞ ሌላ የመነጋገሪያ አጀንዳን ከፍቶ ነበር፡፡

እንዲህ አነጋጋሪ ሆኖ የቀጠለው የአበረታች ንጥረ ነገር አጠቃቀም ዛሬ ላይ ዱብ ያለ ሳይሆን በጥንቱ ጊዜም የሚታወቅ መሆኑና በተለይም እ.ኤ.አ. በ1920ዎቹ አካባቢ በተደጋጋሚ የተከሰተ ጉዳይ እንደነበር በዘርፉ ጥናቶችን ያካሄዱ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ እንደ ዶ/ር አያሌው ገለጻ ዘጠኝ የሚሆኑ የተከለከሉ መድኃኒቶችን የሚያግዱ ምድቦች ሲኖሩ፣ ከእነዚህ መካከል አነቃቂ የሚባሉትና ከሆርሞኖች ጋር የተያያዙት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ‹‹እነዚህ አደገኛ ንጥረ ነገሮች ሲሆኑ፣ የሰውነት ህዋሳትን በማዳከምና ዲኤንኤንና ጂኖችን በመጉዳትም በልብ ጡንቻዎች ላይ የሥራ ጫናንና ሌሎች ችግሮችን በማስከተል አጠቃላይ የሰውነት አካላትን የሚመርዙ መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡

በአበረታች ንጥረ ነገር አጠቃቀም የዓለም መነጋገሪያ የሆኑ ስመጥር ስፖርተኞች ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2013 ከስፖርቱ ዓለም በጡረታ የተገለለውና የቱርደፍራንስ ውድድርን በተደጋጋሚ ያሸነፈው አሜሪካዊው ብስክሌተኛ ላርስ አርምስትሮንግ አንዱ ሲሆን፣ ከኦፕራ ዊንፍሬ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ አበረታች ንጥረ ነገር መውሰዱን አምኖ ነበር፡፡ ከቃለ ምልልሱ በኋላ በዓለም አቀፉ የፀረ አበረታች ንጥረ ነገር ወኪል ሰባት የቱርደፍራንስ ድሎቹ ተሰርዘውበት ከስፖርታዊ እንቅስቃሴዎቹ ለዘላለም መታገዱ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች አበረታች ንጥረ ነገር ጋር በተያያዘ ስማቸው ሲነሳ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ከዚህ በፊትም በአበረታች ንጥረ ነገር ተጠርጥረው ዕገዳ የተጣለባቸው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ነበሩ፡፡

ኢየሩሳሌም ኩማና ሽታዬ ገመቹ ኢፒኦ ከተባለ የአበረታች ንጥረ ነገር (መድኃኒት) ጋር በተያያዘ ምርመራቸው ፖዘቲቭ ሆኖ በመገኘቱ ለሁለት ዓመታት ዕገዳ ተጥሎባቸው ነበር፡፡ ዶ/ር አያሌው ንጥረ ነገሩ በሰውነት ውስጥ በተፈጥሯዊ መንገድ የሚመረት ቢሆንም አትሌቶቹ ግን በፋብሪካ የተመረተውን በመጠቀም በመጠርጠራቸው ዕገዳው እውን ሊሆን እንደቻለ ይናገራሉ፡፡ ይህ ንጥረ ነገር የቀይ ደም ህዋሳትን በብዛት እንዲመረቱ ከማድረግም በላይ ለአትሌቶቹ የበለጠ ጥንካሬን ከማላበስ ባሻገር ጡንቻን እንደሚገነባም ዶ/ር አያሌው ያብራራሉ፡፡

የማራቶን ሯጩ አምበሴ ቶሎሳም ሞርፊን የተሰኘ አበረታች ንጥረ ነገር እንደተጠቀመ በመረጋገጡ የዕገዳው ሰለባ ቢሆንም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳዩ ለሕዝብ ይፋ እንዳይሆን ወስኗል፡፡ እንደ ዶ/ር አያሌው አስተያየትም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዚህ ዜና ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ በመግባቱ ጉዳዩ ተዳፍኖ እንዲቀር መምረጣቸውን ያስረዳሉ፡፡

‹‹የፅናትና የጥንካሬ ተምሳሌት ለሆኑ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይህ ምን ማለት እንደሆነ ማሰብ ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ የመረጥነው በምስጢር መያዝ ነበር፤›› ሲሉ የፌዴሬሽኑን ጭንቀት ይገልጻሉ፡፡

ዛሬ ላይ እየተባባሰ የመጣውን ችግር ግን ሲመለከቱት  ‹‹በጣም ትልቅ ስህተት ነው የሠራነው፤ ዛሬ ላይ ዋጋ እያስከፈለን ነው፤›› ሲሉ ያለፈውን ጉድ መታፈን ከጥቅሙ ጉዳቱ ማመዘኑን ዶ/ር አያሌው ይገልጻሉ፡፡

በብዙ መልኩ የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች በረዥም ርቀት ሩጫ አሸናፊዎች መሆናቸውን የሚያሳዩ ጥናቶች ድሉን ከአካባቢያዊ ተፅዕኖ ጋር ያያይዙት ነበር፤ አሁን ግን እነዚህ ዘገባዎች ይህንን አንድምታ የሚያጠይሙት ሆነዋል፡፡

እንደ ታዋቂው አትሌትና የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት ስለሺ ስህን አስተያየት ይህ ጉዳይ ከአትሌቶቹ ገንዘብ የማግኘት ጽኑ ፍላጎት ጋር እንደሚያያዝ ነው፡፡ በየወቅቱ በዓለም አቀፍ መድረኮች የሚካሄዱ ውድድሮች ሁሉ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር የሚታፈስባቸው ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ አትሌቶቹን ስለሚያጓጓ በየትኛውም መንገድ ገንዘቡን የማግኘት ጥረት ይጀመራል በማለት ለሪፖርተር ሐሳቡን ገልጿል፡፡ በዚህ የተነሳም ስለሺ አበረታች ንጥረ ነገሮች ባለፉት ሁለት ዓመታት ከኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጋር በተያያዘ መነሳታቸውን ይገልጻል፡፡

እንደ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከገጠር አካባቢ የሚመጡ በመሆናቸው ስለእነዚህ አበረታች ንጥረ ነገሮች ግንዛቤ ስለማይኖራቸውና ሕይወታቸውን በመቀየር ላይ ስለሚያተኩሩ ለስህተት ተጋላጭነታቸው እንደበዛ ይገመታል፡፡ በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ ያሉ አትሌቶች ዶ/ር አያሌውን ሳያማክሩ ምንም ዓይነት መድኃኒት እንደማይወስዱ የሚጠቁመው ስለሺ በግላቸውና በሥራ አስኪያጆቻቸው ሥር የሚሠለጥኑት ግን ከዚህ በተቃራኒ የሚያምኗቸው ግለሰቦች ዕጣ ፈንታቸው ይወሰናል ይላል፡፡ በመረጃ ክፍተት ምክንያት በታገዱ ንጥረ ነገሮች ላይ በሚፈጠረው አናሳ ግንዛቤ ምክንያት አትሌቶቹ በቀላሉ ሊደለሉ እንደሚችሉ ስለሺ ያምናል፡፡    

ይህንን የስለሺን እምነት የሚጋሩት ዶ/ር አያሌው በጣም የሚገርመኝ የግልፀኝነት ችግሩ ነው በማለት በአትሌቶቹ፣ በአሠልጣኞቹና በሌሎችም ግለሰቦች መካከል ሊኖር የሚገባውን ግልጽነት ያነሳሉ፡፡ በምርመራው ወቅት በአትሌቶቹ የሚሞላ ፎርም መኖሩን በመግለጽ፤ ፎርሙ ከተሞላ በኋላ አትሌቶቹ መልሶቻቸውን እንደገና ሊያስቡበት የሚችሉበት የ14 ቀን ጊዜ ያለ ቢሆንም፣ በዘፈቀደ አሉታዊ ምላሻቸውን እንደሚሰጡ ዶ/ር አያሌው ይገልጻሉ፡፡ አትሌቶች ሕክምና ሲያደርጉ መድኃኒቶችን ሊወስዱ የሚችሉባቸው ዕድሎች መኖራቸውን በመጠቆም፣ አትሌቶቹ በዚህ ወቅት የአትሌቲክስ ፌዴሬሽናቸውንና የዓለም አቀፉን አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሊያሳውቁ እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡

በተወሰኑ አጋጣሚዎች አትሌቶቹ በይፋዊ ማስጠንቀቂያ የሚታለፉበት ዕድል መኖሩን የሚገልጹት ዶ/ር አያሌው ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች አትሌቶቹ ማንኛውንም መድኃኒት ቢወስዱም ወሰድን እንደማይሉ ጨምረው ያስረዳሉ፡፡ ለዚህም በቅርቡ የተሰማውን የአትሌት ስንታየሁ መርጊያን ጉዳይ ያነሳሉ፡፡ አትሌቱ የታይፈስና የታይፎይድ መድኃኒቶችን መውሰዱን ሲያምን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ድጋፍን እንዳልሰጠው በመጥቀስ አማሯል፡፡ ይህን ጉዳይም በመረጃ በማስደገፍ ፌዴሬሽኑ ለዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አቅርቧል፡፡ ውጤቱ ከዚህ ተቃራኒ ሆኖ የምርመራ ውጤቱ ያሳየው ግን የተጠቀሰው መድኃኒት ሳይሆን ሌላ የተከለከለ ንጥረ ነገር መውሰዱን ነበር፡፡ ከዚህ አትሌት በቀር ሌሎች አምስቱ ግን ተባባሪ ሆነው አስፈላጊውን ሁሉ መረጃ በመስጠታቸው ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በተጨማሪ አይኤኤኤፍንም መረጃው እንዳረካ ገልጸዋል፡፡

‹‹ባለፉት ዓመታት ከአምስት በላይ አትሌቶች ታግደዋል፡፡ ነገር ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ከአትሌቶቹ ዘርዘር ያለ መረጃ ያገኘነው›› በማለት ዶ/ር አያሌው ገልጸዋል፡፡ በተለያዩ ዓለማት አደገኛ የሆኑ አበረታች ንጥረ ነገሮች ይወሰዳሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ‹‹ብለድ ዶፒንግ›› በመባል ይጠራል፡፡ አትሌቶች ደም በመርፌ ከሰውነታቸው መጠው ማቀዝቀዣ ውስጥ የሚያስቀምጡት ሲሆን፣ በኋላ ውድድር ሊጀምሩ ሲሉ ደሙን መልሰው በመርፌ ወደሰውነታቸው ይወጉታል፡፡ ይሔም የኦክስጅንን መጠን ይጨምራል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቶችም ከዓለም አቀፉ ክስተት ብዙ እንደማይለዩ የሚገልጹት ዶ/ር አያሌው በጣም ውድ፣ በቀላሉ ሊገኙ የማይችሉና አደገኛ የሚባሉ አበረታች ንጥረ ነገሮችን እንደሚጠቀሙ አስረድተዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የጾታ ሆርሞን የሆነው ቴስቴስትሮን፣ ስቴሮይድና ስታንዞሎል ይገኙበታል፡፡ በቅርቡ የተጠረጠሩትም ስድስት አትሌቶች መካከል ስቴሮይድ የሚባለውን አበረታች ንጥረ ነገር እንደተጠቀሙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እነዚህ አበረታች ንጥረ ነገሮች አትሌቶች በከፍተኛ አቅም እንዲሠለጥኑ፣ በቀላሉ ከጉዳቶች እንዲያገግሙ እንዲሁም የሰውነት ጡንቻዎች በቀላሉ እንዲገነቡ የሚረዱ ናቸው፡፡ የእነዚህ አበረታች ንጥረ ነገሮች የጐንዮሽ ጉዳት ከፍተኛ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ የኩላሊት መታወክ፣ ራሰ በራነት፣ የወንዶችን የዘር ፍሬ መቀነስ እንዲሁም በሴቶች ፊት ላይ ፀጉር ማብዛትና ድምፅ እንዲጐረንን የማድረግ ጉዳት እንደሚገኙበት የተለያዩ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡

ከፍተኛ ጉዳት ከሚያመጡት ከእነዚህ አበረታች ንጥረ ነገሮች በተጨማሪ መካከለኛ የሚባሉና ለውድድሩ ብቻ ያተኮሩ ንጥረ ነገሮች የኢትዮጵያ አትሌቶች እንደሚጠቀሙ ዶ/ር አያሌው ያስረዳሉ፡፡ ብዙ አስተያየት ሰጪዎች እነዚህ አትሌቶች አበረታች ንጥረ ነገሮቹን የወሰዱት ካለማወቅ ነው የሚሉ ቢሆንም ከውድነታቸውና በቀላሉ መገኘት ካለመቻላቸው ጋር ተያይዞ እነዚህን ንጥረ ነገሮች እንዴት አገኟቸው የሚሉ ጥያቄዎች እየተነሡ ነው፡፡

በቅርቡ ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ በነበረው ውይይት የአትሌቶቹ ዘመዶች፣ ሥራ አስኪያጆች፣ አሠልጣኞች፣ የሕክምና ባለሙያዎችና በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እነዚህን አበረታች ንጥረ ነገሮች በመሸጥና በማቅረብ ሥራ እንደተሳተፉ ዶ/ር አያሌው በአግራሞት ይገልጻሉ፡፡ በከፍተኛ ደረጃ እነዚህን አበረታች ንጥረ ነገሮች በማቅረብ በቱሪስት ቪዛ አማካይነት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የውጭ አገር ዜጐች መሆናቸውን እንደተደረሰባቸው ዶ/ር አያሌው ይገልጻሉ፡፡ በዚህም አጋጣሚ የቱርክ ዜግነት ያለውና በማናቸውም ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ እንዳይሳተፍ በአይኤኤኤፍ የታገደው ከፍተኛ አቅራቢው ይህ ሰው እንደሆነ መረጃዎች እንደደረሳቸው ዶ/ር አያሌው ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች በበቆጂ፣ በባሌ ተራራዎችና በሱሉልታ ቤት ተከራይተው እንደሚኖሩና እነዚህን አበረታች ንጥረ ነገሮች ለአትሌቶቹ በማቅረብ እንደተሰማሩ አትሌቶቹ የሰጧቸውን መረጃ በመያዝ ዶ/ር አያሌው ገልጸዋል፡፡

‹‹የውጭ አገር ዜግነት ያላቸውና በሙያቸው ምንም ዓይነት የሕክምና ዕውቀት የሌላቸው ሰዎች ለአትሌቶቹ የሕክምና አገልግሎት ሲሰጡ ይታያሉ፡፡ በከፍተኛ አደጋ ውስጥ ነው ያለነው፣ ጦርነት እንደታወጀብን ነው የምንቆጥረው፡፡ እነዚህን አትሌቶች ማጣት ለእኛ ውድ ነው፤›› በማለት ዶ/ር አያሌው በቁጭት ይገልጻሉ፡፡

የብዙ አትሌቶች መፍለቂያ እንደመሆኗ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ብዙ ፈረንጆች አትሌቶቹን በማሠልጠንና በሥራ አስኪያጅነት እንደተሳተፉ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ይሔ ሁኔታ ከፍተኛ አደጋ እንዳለው የሚገልጸው የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት ስለሺ ስህን ነው፡፡ ‹‹አትሌቶቹ ስለእነዚህ ሰዎች በቂ መረጃ አይኖራቸውም፡፡ የእነዚህን ሰዎች ማንነትና የሙያ ብቃት ሊያረጋግጥ የሚገባው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ነው፤›› በማለት ስለሺ ይገልጻል፡፡

ምንም እንኳን የአትሌቶቹ መረጃ የማግኘት ዕድላቸው አናሳ መሆኑ ለዚህ ችግር መንስኤ መሆኑን ቢያምንም ከዚህ በተጨማሪም አትሌቶቹ በአቋራጭ ሀብታም የመሆን ጉጉት ለዚህ ችግር አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይገልጻል፡፡ ብዙዎች የአትሌቶቹን ሥራ አስኪያጆች ለችግሩ ዋና መንስኤ እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡ ይሔንን አስተያየትም ገመዱ ደደፎ የጃኒ ዲያማዶን ወኪልና የኢማነ መርጊያ፣ ለሚ ፀጋዬና ፀጋዬ መኮንን አሠልጣኝ በጽኑ ይቃወማል፡፡

ማናጀሮች ጥቅም ለማግኘት በማሰብ የአትሌቶቹን ጤና አደጋ ላይ ለመጣል ብዙም እንደማይደፍሩም ይገልጻል፡፡ በሰሞኑ የመነጋገሪያ ርዕስ መወዛገቡን የሚገልጸው አሠልጣኙ ዋናው ችግር ግን የአትሌቶቹ የመረጃ ክፍተቱና የግንዛቤ እጥረቱ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ ለዚህ እንደ ማሳያ የሚጠቅሰው አንዳንድ አትሌቶች የተቀጡበትን ሜልዶኒያም የተሰኘውን አበረታች ንጥረ ነገር በዋዳ የተከለከሉ ዝርዝር ውስጥ የተካተተው ታኅሣሥ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. (ጃንዋሪ 1 ቀን 2016) መሆኑን ነው፡፡

አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከታኅሣሥ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. (ከጃንዋሪ 5) በኋላ ምርመራ ማድረጋቸውን በመጠቆም በሕክምናው ላይ ያላቸው ዝቅተኛ ግንዛቤን ጨምሮ በመረጃው ላይም ዝቅተኛ ግንዛቤ እንደነበራቸው ይገልጻል፡፡ ‹‹እኔ እንኳን ይህን መድኃኒት በዕገዳ ዝርዝር ውስጥ መኖሩን አላውቅም ነበር፡፡›› የሚለው አሠልጣኙ ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች በዚህ ጥፋተኛ መሆን አይገባቸውም፡፡ ሆኖም ግን ጉዳዩ እጅግ የሚያጸጽት ነው ይላል፡፡ ገመዱ ብዙዎቹ አትሌቶች ፈሪ ከመሆናቸው የተነሳ ለሚወስዱት ቀላል ኪኒን እንኳ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያደርጉ መሆናቸውም ሳይገልጽ አላለፈም፡፡ ይሁንና ከፍተኛ ጥንቃቄ ቢደረግም ስህተት ግን አይኖርም ለማለት እንደማያስደፍርም ይናገራል፡፡ ካለው የአትሌት ቁጥር ብዛት አንፃር እነዚህን አበረታች ንጥረ ነገሮች መጠቀም በኢትዮጵያ አለ ብሎ ለመናገር እንደሚቸገር የሚገልጸው ገመዱ አንዳንድ ጊዜ አትሌቶቹ እነዚህን የተከለከሉ ንጥረ ነገሮችና መድኃኒቶች እንደ ቫይታሚን ሊጠቀሙ እንደሚችሉም ይገምታሉ፡፡

በሁኔታው እጅግ መደናገጡን የሚገልጸው ገመዱ፣ የአትሌቶቹን ቁጥር ከግምት በመውሰድ አትሌቶቹ ተጠቀሙ የተባለውን ንጥረ ነገር ለመውሰድ ሊያነሳሳቸው የሚችለው ምክንያት ቢኖር እንኳ፣ አትሌቶቹ ካላቸው ባህርይና ጥንቃቄ አንፃር እነዚህን ንጥረ ነገሮች በማወቅና በድፍረት ተጠቅመዋል ብሎ እንደማይገምት ይናገራል፡፡

አሠልጣኝ ገመዱ እንደሚናገረው በተለያዩ አገሮች ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱና የተወሳሰቡ ሕገወጥ ጉዳዮችን አትሌቶቹ እንደሚፈጽሙ ይናገራል፣ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ዋዳ እ.ኤ.አ. በ2009 ዓ.ም. አበረታች ንጥረ ነገሮች ለምርመራ በጀመረው ‹‹ባዮሎጂካል ፓስፖርት›› በሚባለው ሥራ ውስጥ ጣልቃ ለመግባት መሞከር እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ይህ የመመርመሪያ ዘዴ የአትሌቶቹን የዓመታት እንቅስቃሴዎች የሚመዘግብ ሲሆን፣ በተለያዩ ምርመራዎች ወቅትም አትሌቶቹ አበረታች ንጥረ ነገሮች ከተጠቀሙ ይሔ መሣሪያ ለውጥ ያሳያል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች የረቀቁ የማታለል ሥራዎችም እንዳሉ ዶ/ር አያሌው ይገልጻሉ፡፡

የስድስቱ አትሌቶች ማንነትም ጋር ተያይዞ አንደኛው አትሌት ፀጋዬ መኰንን መሆኑ በሚዲያ በመገለጡ ሳይጣራ መሆኑ የአትሌቱን ስም ሊያበላሸው እንደሚችልም ይገልጻሉ፡፡ ከማንነታቸው በተጨማሪ በብዙዎች ዘንድ አጠያያቂ የሆነው ቅጣቱ በውድድር ወቅት ያፈሩትን ንብረትን መወሰድ ያካትት ይሆን የሚል ነው፡፡ ይሄንንም አስመልክቶ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ አትሌቶቹ ገንዘብ ያገኙት ከግል ውድድሮች በመሆኑ የመቀማታቸው ሁኔታ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአገሪቷ የአትሌቲክስ ገጽታ፣ እንዲሁም የፌዴሬሽኑ ዕጣ ፈንታ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡ ሩሲያ አበረታች ንጥረ ነገሮችን የሚጠቀሙ አትሌቶች በመሸፋፈኗ መታገዷ የሚታወስ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ፀረ አበረታች ንጥረ ነገር ኤጀንሲ አባል ስትሆን በአባልነቷም ከፍተኛ የሆነ ሥራ እንደሚጠበቅባት ብዙዎች ይገልጻሉ፡፡ ስለሺም ፌዴሬሽኑ በሚፈለገው መልኩ እንዲተባበርና ያሉትን ሕጎችን መተግበር እንዲሁም በአጥፊዎች ላይ የማያዳግም ዕርምጃ እንደሚያስፈልግም ይገልጻል፡፡ ምንም እንኳን የአገሪቷ የአትሌቲክስ ገጽታ ቢያሳስበውም ከዚህም በላይ የተተኪ አትሌቶች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሊታሰብበት እንደሚገባ አበክሮ ይገልጻል፡፡ ለዚህም መፍትሔው ዘላቂ የሆነ ትምህርትና ጉትጐታ እንደሆነ የገለጹት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ ናቸው፡፡

በቀደመው ጊዜ ይሔ ጉዳይ ለኢትዮጵያ አሳሳቢ እንዳልነበር የሚገልጹት አቶ ቢልልኝ በአሁኑ ሰዓት ግን በአገራዊ ደረጃ የማንቂያ ሥራ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይሔ ክስተት የአገሪቷ አትሌቲክስ ያለበትን አደጋ የሚያሳይ ነው ከማንቂያ ሥራው በተጨማሪ ዋናው መሥራት ያለብን አትሌቶቹ ያለምንም ተፅዕኖ ማሸነፍ እንደሚችሉ ማሳመን ነው፤›› ይላሉ አቶ ቢልልኝ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ከውጭ አገር በቱሪስት ቪዛ ያለምንም የሙያ ማረጋገጫ የሚያሠለጥኑትንም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የማያዳግም ዕርምጃ እንደሚወሰድም ጨምረው ገልጸዋል፡፡   

(ለዚህ መጣጥፍ ደረጀ ጠገናው አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡)      

     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...