Thursday, December 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የመስፍን ኢንጂነሪንግና የጀርመኑ መኪና አምራች ጥምረት

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከኢፈርት ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ በ1985 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡ በወቅቱ ሰባት ሚሊዮን ብር ካፒታል ይዞ ወደ ሥራ እንደገባ የድርጅቱ ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡ ባገለገሉ የእጅ መሣሪያዎችና ማሽነሪዎች ሥራ የጀመረው ይህ ኩባንያ ደረጃ በደረጃ እያደገ በአሁኑ ወቅት የትላልቅና ከባድ ተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ ፋብሪካ ወደመገንባት መሸጋገሩን የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብተ ሓዱሽ ይገልጻሉ፡፡

በር፣ መስኮት፣ የከሰል ማንደጃና የመሳሰሉትን በመሥራት ወደ ሥራ የገባው መስፍን ኢንጂነሪንግ፣ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የብረታ ብረትና የመኪና መገጣጠሚያ ሥራዎች ውስጥ በመሳተፍ ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ምርቶችንም ፈብርኮ ለማቅረብ እየተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡

ኩባንያው ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሮበታል የተባለውን አዲስ ምርት ባለፈው ዓርብ፣ መቀሌ በሚገኘው የፋብሪካው ቅጥር ግቢ ውስጥ በተደረገ የምረቃ ሥርዓት ወቅት ይፋ አድርጓል፡፡

ከ22 ዓመታት በኋላ ኩባንያውን ወደ ሌላ የዕድገት ምዕራፍ ያሸጋግረዋል የተባለው አዲሱ ተግባር ከባድ ተሽከርካሪዎችን በመገጣጠም ለገበያ ማቅረብ መጀመሩ ነበር፡፡ ኩባንያው መገጣጠም የጀመራቸው ለተሽከርካሪዎችም በከባድ ተሽከርካሪዎች አምራችነቱ ከ100 ዓመታት በላይ ልምድ ያለው የጀርመኑ የኤምኤኤን (MAN) ተሽከርካሪዎች ናቸው፡፡

የመስፍን ኢንጂነሪንግ የምርት ሒደትን ወደፊት ያራምዳል የተባለው ይህ የተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ ፋብሪካ፣ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ምርት የሆነ ከባድ ተሽከርካሪ የሚገጣጠምበት ቀዳሚ ኩባንያ እንዲሆን ማሽቻሉም በምረቃ ሥርዓቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡

ኩባንያው እያሳየ ያለውን ዕድገት ግምት ውስጥ በማስገባት ማሻሻያዎችን እያደረገ በመምጣት የተለያዩ ምርቶችን የሚያመርቱ፣ አገልግሎት የሚሰጡና ራሳቸውን ችለው በአራት የቢዝነስ ዩኒቶች የተዋቀረ መሆኑን የገለጹት አቶ ሀብተ፣ አንዱ የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካው ነው ብለዋል፡፡

በአራት ተከፋፍለው ራሳቸውን ችለው የተዋቀሩት ዘርፎች የከባድ መኪናና ሎኮሞቲቭ ማምረቻ ቢዝነስ ዩኒት፣ የኢንዱስትሪ ዕቃዎች ማምረቻ ቢዝነስ ዩኒት፣ የኢንዱስትሪ ኮንስትራክሽንና ተከላ ቢዝነስ ዩኒት፣ የአቶሞቲቭና የእርሻ መሣሪያዎች ማምረቻ ቢዝነስ ዩኒት መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

‹‹በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለንን ትልቅ ራዕይ ለማሳካት የኤምኤኤን ተሽከርካሪዎችን ገጣጥመን ማቅረባችን መስፍን ኢንጂነሪንግ ወደፊት መኪና ወደማምረት ደረጃ የሚደርስ መሆኑን ማሳያ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የኢፈርት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አዜብ መስፍን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአውሮፓም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ከሆነው የመኪና አምራች ኩባንያ ጋር በመስማማት ተሽከርካሪዎቹን ገጣጥሞ ለገበያ ማቅረቡ የመስፍን ኢንጂነሪንግ ዕድገትን ያመለክታል፡፡ ከኤምኤኤን ቀደም ብሎ ከሌሎች አገሮች ኩባንያዎች ጋር ድርድር ተደርጐ እንደነበር ያስታወሱት ወይዘሮ አዜብ መጨረሻ ላይ ኤምኤኤን የተሻለ በመሆኑ ችሏል፡፡  

አሁን የተጀመሩት ተጨማሪ ማስፋፊያዎች ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ የመስፍን ኢንጂነሪንግን አቅም ከ10 እጥፍ በላይ እንዲያድግ ያስችለዋል፡፡  

የእነዚህ ተሽከርካሪዎች በአገር ውስጥ መገጣጠም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው የገለጹት ሥራ አስኪያጁ በተለይ ያለቀላቸው ከባድ ተሽከርካሪዎችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ለመቀነስ ያስችላል ብለዋል፡፡

በኩባንያው የሚገጣጠመት ጀርመን ከባድ ተሽከርካሪዎች ለአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ መሆናቸውን አቶ ሀብተ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሚገጣጠሙት የመኪና አካላት ከውጭ የሚመጡ ቢሆንም እንደ ጐማ፣ የመኪና ባትሪና የተለያዩ የመኪና አካላትን በአገር ውስጥ ምርት በመጠቀም የውጭ ምንዛሪ ወጪውን የመቀነስ ዕድል እንዳለም ጠቁመዋል፡፡

በመጀመሪያው ዙር 150 ተሽከርካሪዎች የሚገጣጠሙ ሲሆን፣ በማስፋፊያ ሥራው የሚገነባው አዲስ መገጣጠሚያ ግን የመገጣጠም አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድግ ተናግረዋል፡፡ አሁን ባለው ደረጃ ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የወጣበት ሲሆን፣ ይህም የሆነው አሁን እየተገጣጠመ ያለው በፋብሪካው ነባር ይዞታ ላይ በመሆኑ ነው፡፡ የምርት አቅሙን ለማሳደግም በመቀሌ ከተማ በተረከበው ቦታ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቀው የመጀመሪያው የማስፋፊያ ሥራ በመከናወን ላይ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

በመቀሌ 100 ሔክታር ላይ የሚያርፍና ከ15 በላይ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን ያቅፋል የተባለው የመስፍን ኢንጂነሪንግ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ መንደር ግንባታ የመጀመሪያው ምዕራፍ በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡ በዚህ ኢንዱስትሪ ውስጥ የብረታ ብረት ማቅለጫ፣ የንፋስ ተርባይኖች፣ የክሬን፣ የአውቶብሶችና የባቡር ፉርጐች ማምረቻዎች የሚኖሩት ነው፡፡

የፋብሪካዎቹ መጠናቀቅም ከ10 ሺሕ በላይ ለሚቆጠሩ ዜጐች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ የገለጹት አቶ ሀብተ፣ የአውቶሞቲቭና የእርሻ መሣሪያ የማስፋፊያ ሥራው በውቅሮ ከተማ በ50 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ለመገንባት ታቅዷል ብለዋል፡፡ በዚህ ኢንዱስትሪ መንደር እንዲመረቱ የታቀዱት የቤት አውቶሞቡሎች፣ ሚኒባሶች፣ ፒካፕ ተሽከርካሪዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ግዙፍ ኢንዱስትሪዋችን የመስፍን ኢንዱስትሪን አቅም በማሳደግ ረገድ ጉልህ ሚና እንዳላቸው የጠቆሙት ወይዘሮ አዜብ በተለይ እንደ ኤምኤኤን ካሉ ኩባንያዎች ጋር በጋራ ለመሥራት የተደረገው ስምምነት በመገጣጠም የተጀመረውን ሥራ ሙሉ መኪና ወደማምረት እንደሚያሸጋግር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በቴክኖሎጂ ሽግግርና በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገዙ ተሽከርካሪዎችን እዚህ በመገጣጠም ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ መቀነስ የሚችል መሆኑን ያስታወሱት ወ/ሮ አዜብ፣ ከኤምኤኤን ጋር የተደረሰው ስምምነትም ወደዚያ የሚወስድ ነው ብለዋል፡፡ የመደራደር አቅማችን ከፍተኛ በመሆኑም ብዙ ሥራዎች ለመሥራት ያስችለናል ብለዋል፡፡  

ኩባንያው በተለይ በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪው መስክ ትኩረት ያደረገው የኢንዱስትሪዎች ሁሉ እናት በመባል የሚታወቅ በመሆኑ እንደሆነ የገለጹት በምረቃ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶ/ር አዲስ ዓለም ባሌማ፣ መስፍን ኢንጂነሪንግ የያዘውን ውጥን እንደሚያሳካ ገልጸዋል፡፡ 

በገቢ ምንጭና በሰው ኃይል ቅጥር ረገድም ዘርፉ ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ኩባንያው ሥራውን አጠናክሮ እንዲሠራ አሳስበዋል፡፡ ያደጉ አገሮችን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማሟጠጥ የሚታወቅ ዘርፍ በመሆኑ እዚህ ኢንዱስትሪ ላይ ትኩረት አድርጐ መሥራቱ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑም ተብራርቷል፡፡  

የኤምኤኤን የዓለም አቀፍ ገበያዎች ፕሬዚዳንት ሚስተር ጀረአን ላጋርዴ እንደገለጹት፣ ኩባንያቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ኤምኤኤን እንዲገጣጠም የወሰነበት ዋነኛ ምክንያት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የገበያ ዕድልና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን በመመልከት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በምረቃው ሥርዓት ላይ በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ሚስተር ሳሚስ ዴሽን፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ዓለሙ ስሜና ሌሎች እንግዶች ታድመው ነበር፡፡

ዘርፉ ለአገራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ቢሆንም ብዙ ትኩረት አልተሰጠውም ተብሏል፡፡

መስፍን ኢንጂነሪንግም ሆነ ሌሎች የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች የሚያካሂዱት እንቅስቃሴ በመንግሥት ካልተደገፈ፣ የታሰበው ደረጃ ለመድረስ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችልም ተጠቁሟል፡፡ አቶ ሀብተም የዘርፉ ጠቀሜታ ታይቶ በመንግሥት በኩል ልዩ ድጋፍ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡ አሁን እያቆጠቆጡ ያሉ የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካዎችን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ረዘም ያለ የታክስ እፎይታና የባንክ ብድር ሊመቻችላቸው ይገባል ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ መንግሥት ዘርፉን ለመደገፍ መተግበር አለበት ብለው የጠቀሱት ሌላው ነጥብ፣ ያገለገሉ አውቶሞቢሎች ወደ አገር እንዳይገቡ መገደብ ነው፡፡ ይህ ካልሆነም ያገልግሎት ዕድሜን መገደብና የመሳሰሉት የፖሊሲ ዕርምጃዎች ለዘርፉ ዕድገት መወሰድ የሚገባቸው ናቸው ተብሏል፡፡

መስፍን ኢንደስትሪያል ኢንጂነሪንግ በአሁኑ ወቅት እያመረታቸው ካሉት መካከል የደረቅና ፈሳሽ ጭነት ማጓጓዣ ተሳቢዎች፣ ሃይቤድ እና ሎውቤድ፣ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዲፓዎች፣ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች የሚያገለግሉ መሣሪያዎች፣ ለሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ አገልግሎት የሚውሉ ፔንስቶክና ኢንቴክ ላይነር የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በኤሌክትሮ መካኒካል ተከላ ሥራዎች፣ ለተለያዩ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች የሚያገለግሉ የማሽን ተከላ ሥራዎች፣ የሲቪል ሕንፃ ግንባታዎች፣ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ቁሳቁሶች፣ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ከጅምር እስከ ፍጻሜ (ተርንኪ) በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ኩባንያው ገልጿል፡፡

ከዚህም ሌላ የሙቀት ማቀዝቀዣ ሥርዓቶችን የመትከል ሥራዎች እንዲሠራ፣ ለኢንዱስትሪ አገልግሎቶች የሚውሉ ተገጣጣሚ ሕንፃ የብረታ ብረቶች መዋቅሮችን የማምረትና የተከላ ሥራዎችን፣ የመሣሪያ አስተዳደርና ጥገና ተግባራትን ማከናወን የሚያስችለው የብቃትና ጥራት ማረጋገጫ የISO 9001 – 2008 Quality Management System (QMS) ሰርተፊኬት ያለው መሆኑም ተገልጿል፡፡

በ2008 በጀት ዓመት ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ሽያጭ ለማከናወን ዕቅድ የያዘ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ያሉት የሠራተኞች ቁጥርም ከ2,300 በላይ መድረሱ ታውቋል፡፡

   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች