Saturday, March 2, 2024

​የማንነት ጥያቄ ስንክሳሮችና ፅኑ መሠረቶች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹በእኛ እምነት የማንነት ጥያቄ በአገራችን ከመጀመሪያው ተመልሶ ያደረ ነው፡፡ በሚገባ በሕገ መንግሥታችን አንድ በአንድ ተዘርዝሮ ተመልሷል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 39(5) መሥፈርት አስቀምጦ ጥያቄዎችን ይመልሳል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና በክልል የሚገኙ የብሔረሰቦች ምክር ቤቶች ከሕገ መንግሥቱ ውጪ ማንኛውንም የማንነት ጥያቄ ማስተናገድ እንደማይገባ ማስመር አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተመለሰ የማንነት ጥያቄ የለም፡፡ የማንነት ጥያቄ ተመልሶ አልቋል የሚል ምላሽ መሰጠት አለበት፡፡››

መጋቢት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የመንግሥታቸውን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ በማንነት ጥያቄ ላይ ለቀረበው ጥያቄ ማብራሪያ ሲሰጡ ነው ይህን የተናገሩት፡፡

ይህ የአቶ ኃይለ ማርያም ‹በቃን!› የሚመስል አስተያየት በተሰጠበት ወቅት፣ በሊቀ መንበርነት የሚመሩት ገዢው ከኢሕአዴግ አባላትና አጋር ፓርቲዎች በማንነትና ራስን በራስ ከመወሰን ጋር በተገናኙ ጥያቄዎች ተወጣጥረዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ዛይ፣ በአማራ ክልል ቅማንት፣ በትግራይ ክልል ራያና ወልቃይት፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልል ወለኔና ኮንሶን ጨምሮ በርካታ ጥያቄዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በርካታዎቹ የማንነት ጥያቄዎች የሚመጡበት የደቡብ ክልል የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድር በመሆን ለዓመታት በማገልገላቸው ስለማንነት ጥያቄ ፈታኝነት በቂ ግንዛቤ እንዳላቸው መገመት ይቻላል፡፡ በመሠረቱ ከማንነት ጋር ለተገናኙ ጉዳዮች እንደ መነሻነት የሚያገለግለው የስልጤ ጉዳይ በ1992 ዓ.ም. በደቡብ ክልል ውድቅ ሆኖ በይግባኝ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲወሰን ንቁ ተሳታፊ ነበሩ፡፡

የተለየ ማንነት ለመጠየቅ መሟላት ስላለባቸው መሥፈርቶች ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 39(5) ላይ የዘረዘረ ቢሆንም ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የመገንጠልና ክልል የመሆን መብታቸውን የትና እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው የተቀመጠው ዝርዝር አሠራር ለማንነት ጥያቄ አለማካተቱ በወቅቱ እንደ ትልቅ ተግዳሮት ተጠቅሶ ነበር፡፡ በስልጤ ጉዳይ ዝርዝር አሠራር ለመወሰን በጥልቀት ውይይት ተደርጎ ነበር፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም የማንነት ጥያቄን ለማስተናገድ በሕገ መንግሥቱ በግልጽ የተቀመጠ ነገር ስለሌለ ወደ ክልሉ ቢላክም፣ በተጨባጭ የሚሠራበት መንገድ ስለሌለው አካሄዱ በግልጽ እንዲቀመጥ ጠይቀው ነበር፡፡ ይህ ግልጽ አሠራርም የሕገ መንግሥቱ አካል እንዲሆን የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ይደረግ እስከማለት አድርሷቸው ነበር፡፡ ‹‹ምን ያህል ሕዝብ ሲጠየቅ ሪፈረንደም ሊደረግ እንደሚገባውና ሌሎች ዝርዝር አካሄዶች በግልጽ ቢቀመጡ የተሻለ ነው፡፡ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በርካታ ጥያቄዎች የሚያነሱበት ሁኔታ በመኖሩ ለጥያቄዎች መሠረታዊ መፍትሔ ለመስጠት የአሠራር ደንቡ በሕገ መንግሥቱ መቀመጥ አለበት፤›› ብለው ነበር፡፡

የማንነት ጥያቄ አሠራር ግልጽነት ሕገ መንግሥታዊ መሠረት እንዲኖረው በ1992 ዓ.ም. ጠይቀው የነበሩት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ከ16 ዓመታት በኋላ የአስፈጻሚው አካል መሪ ሆነው ያሳዩት ፍጹም የሆነ የአቋም ለውጥ በጉዳዩ ላይ ክልሎችና ፌዴራል መንግሥቱ ያላቸው ልዩነት ነፀብራቅ ይሁን ወይስ አገሪቱ የሄደችበት ጉዞ የደረሰበት ደረጃ ብዙም ግልጽ አይደለም፡፡

የሩሲያ መሪ የነበረው ጆሴፍ ስታሊን የማንነት ጥያቄን በተመለከተ ሁለት ጽንፍ የያዙ አቋሞችን በማንፀባረቅ ይታወቃል፡፡ መጀመሪያ አናሳ ሆኑም አልሆኑ ሁሉም ብሔሮች ግዛት እንዲኖራቸው ጥሯል፡፡ በኋላ ላይ ግን ከመቶ በላይ የተለያዩ ብሔሮች ሳይሆኑ አንድ ሩሲያዊ ሕዝብ እንዲኖር ሰበከ፡፡ ከቆይታ በኋላ በሩሲያ የብሔር ጥያቄ መፈታቱን አወጀ፡፡ የራስን ዕድል በራስ መወሰን ላይ ያተኮረውን ‹‹አንቀጽ 39›› የተሰኘ መጽሐፍ ያሳተሙት የሕገ መንግሥት ኤክስፐርቱ አቶ ውብሸት ሙላት በዚሁ ጉዳይ ላይ ሲጽፉ፣ ‹‹በየጊዜው እየተለዋወጠ መጥቶ ሰላሳ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሩሲያ የብሔሮች አገር መሆኗ ቀርቶ አንድ የሩሲያ ሕዝብ እንደተፈጠረ አወጀ፤›› ሲሉ ጽፈዋል፡፡

የስታሊን ውሳኔ ሩሲያ እንድትበታተን አድርጓታል ተብሎ የሚተች ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ግን፣ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አንድነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንክሯል፤›› ብለዋል፡

ከማንነት ጥያቄ ጋር የተያያዙ ግጭቶች የሚለው አገላለጽም እንዳልተስማማቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹የማንነት ጥያቄ በጭራሽ ግጭት የሚያስከትል ጉዳይ ሊሆን አይችልም፡፡ አይገባምም፡፡ ዋናው የግጭት መንስዔ የመልካም አስተዳደር ችግር ነው፡፡ አንደኛ ጆሮ ሰጥቶ ያለመስማት ችግር ነው፡፡ ሌላኛው በሰበብ አስባብ የማዘግየት ችግር ነው፤›› ብለዋል፡፡

እርግጥ ነው አቶ ኃይለ ማርያም በዕለቱ በፓርላማ ከነበራቸው ውሎ ለመረዳት እንደሚቻለው፣ መንግሥታቸው የማንነት ጥያቄን ለሌላ ዓላማ ማስፈጸሚያ በሚጠቀሙ አካላት ድርጊት ተማሯል፡፡

‹‹በደቡብ ክልል የማንነት ጉዳይ በተሳሳተ መንገድ የሚተረጉሙ አንዳንድ ሰዎች በአንድ ብሔር ሥር ያለ ጎሳ ሁሉ ተነጥሎ ራሱን ችሎ ብሔር ይሁን የሚል ጥያቄ ይዘው ይነሳሉ፤›› ያሉ ሲሆን፣ የማንነት ጥያቄ አንግበው ሕዝቡን ገንዘብ አዋጡ እያሉ የሚበዘብዙ ጥገኞችን ማሳረፍ አስፈላጊ መሆኑንም አስምረውበታል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሕዝቡን ባህላዊ ልብስ እያስለበሱ በየቦታው እየዞረ ሥራ እንዲፈታ የሚያደርጉ እንዳሉም አመልክተዋል፡፡

ከ21 ዓመታት በፊት ማንነት ላይ የተመሠረተ ፌዴራላዊ መዋቅር ይዞ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ብቅ ሲል አንዳንዶች ይህ ምርጫ በኢትዮጵያ ውጥረትና መከፋፈል እንዲፈጠር ያደርጋል፣ የፖለቲካ ልሂቃኑም ወደ ሥልጣን ለመምጣትና እዚያው ለመቆየት መሣሪያ ያደርጉታል ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይኼ ጉዳይ አሁንም እንደሚነሳ አስታውሰው፣ ‹‹ብዙኃነት ላይ ማተኮር ግዴታ ነበር፡፡ አንድነታችን ሊጠናከርና በፅኑ አለት ላይ ሊመሠረት የሚችለው በእኩልነት ላይ በመመሥረት ብዙኃነትን በአግባቡ ማስተናገድ ሲችል ነው፡፡ በእኩልነት፣ በመተሳሰብና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ገንብተናል፡፡ የማንነት ጥያቄ አንድነታችን ላይ ችግር ይፈጥራል የሚለው ስህተት ነው፡፡ ብዙኃነታችን ውበታችንና ጥንካሬያችን ነው፡፡ አንድነትን የሚያደናቅፈው ብዝኃነትን ማክበር ሳይሆን ጥገኛ አመለካከት፣ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች ናቸው፤›› ሲሉም አብራርተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከማንነት ጥያቄዎች መብዛት ጀርባ ሌላ አጀንዳ ያላቸው አካላት እንዳሉና ጥያቄዎቹ ‹‹በቃ!›› ሊባሉ እንደሚገባ በአንድ በኩል እየተከራከሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የማንነት ጥያቄዎችን መመለስ ለአገሪቱ አንድነት ቁልፍ መሆኑን ማስረዳታቸው አብሮ የሚሄድ አይመስልም፡፡ ይሁንና ከምርጫ 97 በኋላ ፓርቲያቸው ልዩነትን ከማወደስና ከማበረታታት ወደ አገራዊና የጋራ አጀንዳዎች መሸጋገሩን በመጥቀስ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ትርጉም ለመስጠት የሞከሩም አልታጡም፡፡

ለዚህ የኢሕአዴግ ሽግግር እንደ አንድ ማሳያ የ120ኛ ዓመት የአድዋ ድል የተከበረበትን መንገድ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በተቃዋሚዎቹና በተቺዎቹ ዘንድ በፀረ አንድነት የሚፈረጀው ኢሕአዴግ የዓድዋ ድልን በደማቅ ሁኔታ ከማክበርም በላይ፣ ለዘመናት በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ለዘለቀው የጋራ ዕጣ ፈንታ እንደ ምልክትም ቀርቧል፡፡

ኢሕአዴግ በ1983 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን መጥቶ የብሔር ብሐረሰቦችና ሕዝቦችን መብት ከማረጋገጡ በፊት የነበሩት ገዢዎች የፈጠሯት ኢትዮጵያ ‹የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እስር ቤት› እንደነበረች ያምናል፡፡ በተቃራኒ የአሁኗ ኢትዮጵያ በብሔሮች በጎ ፈቃድ ብቻ አንድነቷን የፈጠረች ናት ይላታል፡፡ በ1983 ዓ.ም. የወቅቱ ፕሬዚዳንት አቶ መለስ ዜናዊ የመንግሥታቸው ዓላማ፣ ‹‹በጭቆና ሳይሆን በፈቃደኝነት ላይ በተመሠረተ ኅብረት የኢትዮጵያን አንድነት መገንባት›› እንደሆነ ተናግረው ነበር፡፡

በተመሳሳይ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በቅርቡ በፋና ኤፍ ኤም ሬድዮ ‹ሞጋች› ፕሮግራም ላይ ቀርበው ስለኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት ስኬቶችና ተግዳሮቶች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ስለ ዓድዋ ድል ሲናገሩ፣ ‹‹ብዙኃነትን ይዘን ስለሄድን ነው የዓድዋ ጦርነትን ድል ማድረግ የቻልነው፡፡ ያኮረፈ ኦሮሞ፣ ወላይታና ብዙ ሕዝብ ለዚች የጋራ ፕሮጀክት ቅሬታዬን ትቼ እሳተፋለሁ በማለቱ የተገኘ ድል ነው፤›› ብለዋል፡፡

ጥናቶች እንደሚያሳዩት አገሪቱ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ባለመኖሩ ጉዳት እየደረሰባት ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ባለፉት ሥርዓቶች ስለደረሰው ጭቆና፣ መገለልና መድልኦ የተጻፉ የታሪክ ሰነዶች ላይ ስምምነት የለም፡፡ ኢሕአዴግ በበላይነት እንዲመሠረት ያደረገውን ማንነት ላይ ያተኮረ የፌዴራል ሥርዓት ለመከላከል እንዲመቸው፣ እነዚህን የበደል ታሪኮች አጋኖ ያቀርባል በሚልም ይተቻል፡፡ ነገር ግን፣ ተመሳሳይ የበደልና የመገለል ታሪክ በመጥቀስ አዲስ የማንነት ጥያቄዎች ሲቀርቡ ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ፍላጎት ማጣቱ ተቃርኖ ነው ሲሉም አጥኚዎች ያመላክታሉ፡፡ ይሁንና የመስተዳድሮች መዋቅር እንዲቀየርና አዲስ ማንነት እንዲሰጣቸው የሚጠይቁ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቁጥር ከመቀነስ ይልቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጨመረ ይገኛል፡፡ አንዳንዶቹ ጥያቄዎችም ለግጭት መነሻ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ ለእነዚህ ማንነትን መሠረት ላደረጉ ግጭቶች በሕግ ማዕቀፉ ላይ ያሉ ክፍተቶች የተወሰነ አስተዋጽኦ ያላቸው ቢሆኑም፣ በዋናነት የፖለቲካ ሥሌቶች ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው፡፡

ማንነት ላይ ያተኮረው የኢትዮጵያ የፌዴራል መዋቅር ለግጭት መነሻ ከመሆን በተቃራኒ ለግጭት መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ምንጮችን ማድረቁን፣ ገዢው ፓርቲና ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ይስማማሉ፡፡ የአገሪቱ ተቀዳሚ የፌዴራሊዝም ኤክስፐርት ዶ/ር አሰፋ ፍሰሐ፣ “Ethiopia’s Experiment in Accommodating Diversity: 20 years’ Balance Sheet” በሚለው ጥናታቸው፣ የኢትዮጵያ ብሔር ተኮር የፌዴራል ሥርዓት ከዚህ ቀደም ተገፍተው ለነበሩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የፖለቲካ ምኅዳር በመክፈት ቋንቋቸውን፣ ባህላቸውንና ታሪካቸውን ለማሳደግና ለማስፋፋት የተሻለ አቅም የሰጣቸውን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንዳጎናፀፋቸው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተቃራኒ ማንነት ላይ ያተኮረ የፌዴራል ሥርዓት የመገንጠል፣ አዲስ ክልል የማዋቀርና አዲስ የማንነት ጥያቄ፣ የአስተዳደራዊ መዋቅሮች ክለሳ ጥያቄዎችን በመጋበዝ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ማምጣቱንና ልማትንም እያደናቀፈ ነው በማለት የሚከራከሩም አሉ፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት መንግሥት የማንነት ጥያቄዎችን ችላ ማለት የጀመረውም እነዚህን አደጋዎች ከግምት ውስጥ አስገብቶ ነው በማለት ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ ከ1997 ዓ.ም. በኋላ መንግሥት ልዩነት ከማንቆለጳጰስ ይልቅ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ በአገሪቱ ለመፍጠር ደፋ ቀና የሚለውም በዚሁ ምክንያት ነው ሲሉ ይጠቅሳሉ፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብን የመሳሰሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን የአገር ተምሳሌት ማድረግ፣ የባንዲራ ቀን፣ የብሔረሰቦች ቀንና የከተሞች ቀን ክብረ በዓሎች የዚህ እሳቤ መገለጫዎች ተደርገው ይወስዳሉ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹በቃን!›› አባባልም ይህ እሳቤ የደረሰበትን ደረጃ አመላካች ተደርጎ ተወስዷል፡፡

የማንነት ጥያቄዎች የመጨመር አንድምታ

ለክልልና ለፌዴራል መንግሥታት የማንነት ጥያቄዎች ከአገሪቱ ከሁሉም አቅጣጫዎች እየጎረፉ ይገኛሉ፡፡ አንዳንዶቹ በክልል ደረጃ መፍትሔ ያላሟጠጡ ሲሆን፣ ሌሎች ግን በይግባኝ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርበዋል፡፡ ወለኔ፣ ዛይ፣ ኮንሶ፣ ራያና ወልቃይት በክልል ደረጃ የመጨረሻ ውሳኔ ገና ያላገኙ ናቸው፡፡ እንደ ቅማንት፣ መንጃና ኮንቶማ ያሉት ደግሞ በምክር ቤቱ በይግባኝ ከታዩት የሚካተቱ ናቸው፡፡ ለአንዳንድ ምሁራን በክልል ደረጃም ሆነ በፌዴራል መንግሥቱ ለማንነት ጥያቄዎች የሚሰጡት ምላሾች ወጥነት የሚጎላቸው ናቸው፡፡

አቶ ውብሸት፣ ‹‹በሽግግሩ መንግሥት ወቅት 63 ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለራሳቸው ዕውቅና ሰጥተው ነበር፡፡ ሕገ መንግሥቱ በ1987 ዓ.ም. ሲፀድቅ 67 ደርሰው ነበር፡፡ በወቅቱ በደቡብ ክልል የነበረው ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቁጥር 46 ነበር፡፡ አሁን 56 ደርሰዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ አዳዲስ ብሔሮች ማንነታቸውን እንዴት እንዳገኙ ዝርዝር መረጃ የለም፤›› ብለዋል፡፡

የማንነት ጥያቄዎች በአብዛኛው ለአዲስ ማንነት ዕውቅና በመጠየቅ፣ አዲስ አስተዳደር በመጠየቅ፣ ፍትሐዊ የሆነ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል በመጠየቅና በመሳሰለው ሊገለጽ ይችላል፡፡ አቶ ውብሸት የማንነት ጥያቄዎች በዋናነት የዕውቅና ጉዳይ እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡ ‹‹አንድ አካል ዕውቅና ሳይሰጠው መብት አይኖረውም፡፡ ዕውቅና ቅድመ ሁኔታ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብትን በተመለከተ የኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ እጅግ ቸር ሲሆን፣ ከዕውቅና የዘለሉ በርካታ መብቶችን ያጎናፅፋል፡፡ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 8 የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ በአንቀጽ 39 ላይ ደግሞ ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብና ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብቱ በማንኛውም መልኩ ያለገደብ የተጠበቀ እንደሆነ፣ በቋንቋው የመናገር፣ የመጻፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግና ባህሉን የመግለጽ፣ የማዳበርና የማስፋፋት እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት እንዳለው፣ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት እንዳለው፣ በሰፈረበት መልክዓ ምድር ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግሥታዊ ተቋማት የማቋቋም፣ እንዲሁም በክልልና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብት እንዳለው ተደንግጓል፡፡

ለዚህም ነው የማንነት ጥያቄ በአንቀጽ 39 ከተቀመጠው ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ጋር ተናቦ የሚተረጎመው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደበበ ባሩድ፣ በአገሪቱ የማንነት ጥያቄዎች እየተበራከቱ የመጡት ኅብረተሰቡ ስለሕገ መንግሥቱ በተለይም ራስን በራስ ስለማስተዳደር መብት ያለው አረዳድ እየጨመረ በመምጣቱ ነው ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 62(3) ላይ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብትን በተመለከተ በሚነሱ ጥያቄዎች ላይ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንደሚወስን ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ለማጠናከርና ሥልጣንና ተግባሩን ለመዘርዘር በወጣው አዋጅ ቁጥር 251/1993 እና በግንቦት ወር 1999 ዓ.ም. በወጣው የተሻሻለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የአሠራርና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ፣ ምክር ቤቱ ይህን ኃላፊነት የሚወጣባቸው ዝርዝር ሁኔታዎችን ያስቀምጣሉ፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከአባላቱ ጥንቅርና ከተሰጠው ሥልጣን አኳያ በማንነት ጉዳይ ላይ ውሳኔ መስጠቱ የሚጠበቅ ነው፡፡ ምክር ቤቱ በሥርዓቱ ዕውቅና የተሰጣቸው ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን በአባልነት ይይዛል፡፡ ምክር ቤቱ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ፍላጎትና ጥቅም እንደሚያስቀድም የሚገመት ቢሆንም፣ አንዳንድ ጥናቶች በምክር ቤቱ እንቅስቃሴ ላይ ክልሎች ብርቱ ተፅዕኖ እንደሚፈጥሩ ይጠቁማሉ፡፡ እርግጥ ነው ከ1997 ዓ.ም. በኋላ በክልል ያሉ ከፍተኛ አመራሮች ርዕሰ መስተዳድሮችን ጨምሮ በምክር ቤት አባልነት ብቅ ማለታቸው እውነት ነው፡፡ ለአቶ ደበበ ይህ ከተፅዕኖ ይልቅ የአፈጻጸም ቅልጥፍና የሚጨምር እሴት ነው፡፡

በማንነት ጥያቄ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያለው ሥልጣን ክልሎች ካላቸው ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ጋር ተነፃፅሮ በጥያቄው ላይ ቅድሚያ መወሰን ያለበት ማነው የሚል ጉዳይ መነሳቱ አልቀረም፡፡ በማንነት ጥያቄ ላይ እንደ መነሻ የሚያገለግለው የስልጤ ጉዳይ ማጠንጠኛ ካደረጋቸው ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ ይኼው ጥያቄ ነበር፡፡ ስልጤዎች ከጉራጌ የተለየ ማንነት ስላለን ተነጥለን ራሳችንን በራሳችን እንድናስተዳድር ይፈቀድልን ሲሉ ጥያቄያቸውን ለክልሉ አቀረቡ፡፡

የስልጤ ጉዳይ የተለየ ማንነት የሚሰጠው ለማን ነው? በማንነት ጥያቄ ዙሪያ የክልልና የፌዴራል መንግሥት ሚና ምንድነው? ጥያቄ ያቀረበ አካል ሊከተለው የሚገባው ሥነ ሥርዓትስ ምንድነው? የሚሉትን ወሳኝ ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክሯል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የስልጤን ጉዳይ በይግባኝ ያየው የደቡብ ክልል በቅድሚያ ጥያቄውን ውድቅ ካደረገው በኋላ ነው፡፡ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ በጥልቀት የመከረው ምክር ቤት የስልጤ ማኅበረሰብ በማንነቱ ላይ በመጋቢት ወር 1993 ዓ.ም. ሕዝበ ውሳኔ አድርጎ እንዲወስን አስቀምጧል፡፡ በሕዝበ ውሳኔው ውጤት ስልጤ ከጉራጌ ተለይቶ የራሱ ዞን ለማቋቋም በቅቷል፡፡

በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉምና ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወልዱ መርኔ፣ ምክር ቤቱ የስልጤን ጉዳይ ሲወስን ሕገ መንግሥቱን በመተርጎም ለሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮችም ተፈጻሚ እንዲሆን አድርጎ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ሁለት ዋና ጉዳዮች ተነስተው ነበር፡፡ አንደኛ መጀመሪያ ጥያቄው የት ነው የሚታየው የሚል ነው፡፡ ሁለተኛ ማንነትን የሚወስነው አካል ማነው የሚል ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከስልጤ ውሳኔ ለመረዳት እንደሚቻለው የማንነት ጥያቄ ለክልሎች ከተሰጠው ራስን በራስ የማስተዳደር ሥልጣን ጋር የተገናኘ ስለሆነ በቅድሚያ ጉዳዩ ለክልሎች መቅረብ አለበት፡፡ ማንነትን የሚወስነውን አካልም በተመለከተ በሕገ መንግሥቱ ለማንነት የተቀመጠውን መሥፈርት አሟልቻለሁ ብሎ ጥያቄ ያቀረበ አካል የራሱን ማንነት ራሱ ማረጋገጥ እንዳለበት ተወስኗል፡፡

እንደ ስልጤ ሁሉ ሌሎች የማንነት ጥያቄዎች በአብዛኛው የሚነሱት ከደቡብ ክልል ነው፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተመሳሳይ መሠረት ባይኖራቸውም፣ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች እየተነሱ ይገኛል፡፡

ከስልጤ በኋላ በአከራካሪ ሁኔታ የማንነት ጥያቄው የተመለሰለት ለቅማንት ነው፡፡ ቅማንት ለበርካታ ዓመታት ጉዳዩ በክልል ከቆየ በኋላ ከአማራ ብሔር የተለየ ማንነት የላችሁም ተብሎ በክልል ደረጃ ውድቅ ሆኖ ነበር፡፡ ጉዳዩ በይግባኝ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ከመጣ በኋላ ምክር ቤቱ የራሱን ጥናት በማድረግ ላይ እያለ ግን፣ ክልሉ ሐሳቡን ለውጦ ምላሽ ልስጥበት ብሎ እንደገና ያየዋል፡፡ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር በመመካከር ጥናት የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች የለየው የአማራ ክልል ምክር ቤት፣ መጋቢት 2 ቀን 2007 ዓ.ም. ለቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር ዕውቅና ሰጥቷል፡፡

ይሁንና በወገራ፣ ላይ አርማጭሆ፣ የጎንደር ከተማ የገጠር ቀበሌዎች፣ የጎንደር ዙሪያ ወረዳ፣ በደንቢያ ወረዳ፣ ጭልጋ ወረዳ፣ በመተማና ቋራ ወረዳዎች ኩታ ገጠም 126 ቀበሌዎች በአዲሱ አስተዳደር እንዲካተቱ ጥያቄ ቢቀርብም፣ የክልሉ ምክር ቤት ግን በጭልጋና በላይ አርማጭሆ ወረዳዎች የሚገኙ 42 ቀበሌዎች ብቻ እንደሚካተቱ ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ ቅር የተሰኙት ቅማንቶች ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በድጋሚ ይግባኝ ይላሉ፡፡ ምክር ቤቱም ሰኔ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ የክልሉ ምክር ቤት ዋናውን ጥያቄ ለመመለስ በሄደበት አግባብ ጥያቄውን እንዲፈታው ጠይቋል፡፡ የክልሉ ምክር ቤት ግን ሐምሌ 4 ቀን 2007 ዓ.ም. የቅማንት ልዩ ወረዳን ያቋቋመውን አዋጅ ሲያፀድቅ በድጋሚ 42 ቀበሌዎች ብቻ እንዲካተቱ ወስኗል፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁና በጉዳዩ ላይ ለሪፖርተር አስተያየት የሰጡ የቅማንት ተወላጆች፣ የክልሉ ምክር ቤት በአቋሙ በመፅናት ቅሬታቸውን አለማስተናገዱ በሰሜን ጎንደር ለተቀሰቀሰው ግጭት መነሻ ነው ብለዋል፡፡ በውሳኔው ላይ ቅሬታ በማቅረባቸው በቅማንት ሕዝብ ላይ ግድያ፣ ድብደባ፣ እስር፣ የአካል ጉዳትና ሌሎች የኃይል ዕርምጃዎች እየተወሰዱ ነው ብለዋል፡፡ ይኼ ሁሉ ችግር እየደረሰና የፌዴራል መንግሥት ከቅማንት ተወላጆች ጋር መጠነ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ፣ ተጨማሪ ሕይወትና ንብረት እንዳይወድም በአካባቢው በመከላከያና በፌዴራል ፖሊስ ጥበቃ ከማድረግ ውጪ ዘላቂ የእርምት ዕርምጃ አለመውሰዱ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የቅማንት ጥያቄን ለመመለስ መዘግየትና መጓተት እንዳልነበረበት ገልጸው፣ ክልሉ የእርምት ዕርምጃ ወስዷል ብለዋል፡፡ ‹‹ተጨማሪ ቀበሌዎች ይካተቱ የሚለው ጥያቄም ተገቢ በመሆኑ ክልሉ መልስ ሰጥቶበታል ብዬ አምናለሁ፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ስለዚህ በቂ ውሳኔ ተወስኗል ማለት ነው፡፡ አሁን ጥያቄው ስለተመለሰ ሥርዓት ባለው መልኩ መሄድ አለበት፡፡ ከዚህ በኋላ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሌላ ነው፡፡ የማንነት ጥያቄ አይሆንም፤›› ብለዋል፡፡

ጉዳዩ በይግባኝ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መቅረቡን በተመለከተ አቶ ወልዱ፣ ‹‹ምክር ቤቱ ይህን ያህል ቀበሌ ይገባችኋል በሚለው አይገባም፡፡ ይኼ የክልሎች ሥልጣን ነው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ውብሸት የቅማንት ጉዳይ ከሌሎች የማንነት ጥያቄዎች ሲነፃፀር ልዩ ባህሪያት እንዳሉት ያስገነዝባሉ፡፡ ‹‹የቅማንት ጉዳይ እንደ ስልጤ በሕዝብ ውሳኔ አላለቀም፡፡ የቅማንትን ጉዳይ የአማራ ክልል ዕውቅና ሊሰጥ ወደ ቅማንት ማኅበረሰብ ተመልሶ ሕዝበ ውሳኔ አልተደረገም፡፡ የቅማንት ሕዝብ የሚኖረው አንድ አካባቢ ብቻ አይደለም፡፡ የተለያዩ ወረዳዎች ላይ ይኖራል፡፡ ኩታ ገጠም ወይም በአንድ አካባቢ የሚለው እንደ አንድ ቦታ ብቻ እንደማይወሰድ መወሰኑ ለሌሎች ጉዳዮችም ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፡፡ የቅማንት ጉዳይ የተለየ ቋንቋ ኖሮ በዚያው ቋንቋ መግባባትም እንደ መሥፈርት የወሰደ አይመስልም፡፡ ቅማንቶች አስቀድሞ የተለየ ቅማንትነይ የሚል ቋንቋ የነበራቸው ቢሆኑም አሁን በዚህ ቋንቋ አይግባቡም፤›› በማለትም አስረድተዋል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከስልጤና ከቅማንት ጥያቄ ውጪ በቅርብ ዓመታት ለቀረቡለት ጥያቄዎች የሰጠው ምላሽ ከክልሎች ውሳኔ ጋር የተስማማ ነበር፡፡ ለአብነት ያህል መንጃና ኮንቶማ ያቀረቡት አዲስና የተለየ ማንነት ይሰጠን የሚል ጥያቄ በደቡብ ክልል ውድቅ ተደርጎ ነበር፡፡

አቶ ደበበ ምክር ቤቱ የማንነት ጥያቄዎች አይደሉም በማለት ውድቅ የሚያደርገው በሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ‹‹በአንድ በኩል ሌላ አጀንዳ ያላቸው አካላት ይኖራሉ፡፡ በሌላ በኩል የመልካም አስተዳደር ችግርን ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ የማንነት ጥያቄ አድርጎ የሚመጣ አለ፤›› ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ አቶ ወልዱ የመንጃ ጉዳይ የመልካም አስተዳደር ችግር እንደ ማንነት ጥያቄ ሆኖ ለመቅረቡ ምሳሌ እንደሚሆን ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹የማንነት ጥያቄዎች የክልል መፍትሔ አሟጠው በይግባኝ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲመጡ የምናያቸው ለሚመለከተው ኮሚቴ ተመርተው፣ የባለሙያዎች ቡድን አቋቁመን አልፎ አልፎም የመስክ ጥናት አድርገን ነው፡፡ መንጃ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን የማንነት መሥፈርት አያሟላም፡፡ አባላቱ ከሚኖሩበት ማኅበረሰብ አካባቢ ሕዝብ የተለየ ቋንቋ የላቸውም፣ ባህላቸው ተቀራራቢ ነው፡፡ ነገር ግን የተለያዩ ችግሮች ይደርስባቸዋል፡፡ የመገለልና የአጉል አስተሳሰብ ተጠቂ ናቸው፡፡ የማንነት ጥያቄአቸው ተቀባይነት የለውም ማለት ሌሎች ችግሮቻቸው ሊፈቱላቸው አይገባም ማለት አይደለም፡፡ ለዚህም ነው የክልሉ መንግሥት በዚህ ላይ እንዲሠራና መብቶቻቸውን እንዲያከብር ምክር ቤቱ አስገዳጅ ውሳኔ የሰጠው፤›› ብለዋል፡፡

እዚያው ደቡብ ክልል ኮንሶ ያነሳው ጥያቄ ሌላ ውጥረት አንግሷል፡፡ እስከ 2003 ዓ.ም. ልዩ ዞን ሆኖ የቆየው ኮንሶ ባለፉት አምስት ዓመታት የሰገን ዞን አንድ አካል ሆኖ ቆይቷል፡፡ የኮንሶ ብሔረሰብ አካላት ወደ ቀድሞው ልዩ ዞን ለመመለስ ያላቸውን ጥያቄ እንዲያስፈጽሙ 12 አባላት ያሉትን ኮሚቴ መርጠው እንቅስቃሴ ያደጉ ሲሆን፣ ከክልሉ ምላሽ ማግኘትና መፍሔውን አሟጠው ወደ ፌዴራል አካላት ለመምጣት እንዳልቻሉ የኮሚቴው አባላት አቶ ገመቹ ገንፌ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹ክልሉ እኔን ጨምሮ አምስት የኮሚቴው አባላትን ከዚህ በፊት አስሮ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የኮንሶ የባህል አባትና የኮሚቴው አባል ካላ ገዛኸኝ ወልደ ዳዊትን የካቲት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. አስሯል፡፡ የክልሉ ልዩ ኃይል፣ የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ የኮንሶ ብሔረሰብ አባላት የሆኑ አርሶ አደሮችና ነጋዴዎችን፣ ሠራተኞችንና ተማሪዎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እያደናቀፉ ነው፡፡ የታሰሩ፣ የተጎዱና የተለያዩ ዕርምጃዎች የሚወሰድባቸው አባላት በርካቶች ናቸው፤›› በማለት የአስተዳደር ለውጥ መጠየቃቸው ያመጣውን ጫና ዘርዝረዋል፡፡

አቶ ውብሸት፣ ‹‹የኮንሶ ጥያቄ በተወሰነ መልኩ የማንነት ገፅታ አለው፡፡ የራስህ መስተዳደር ሲኖርህ ማንነትህን የተሻለ ትጠብቃለህ፤›› ብለዋል፡፡ በሕገ መንግሥት አንቀጽ 50(4) እና 52(2) (ሀ) መሠረት ክልሎች የራሳቸውን የአስተዳደር መዋቅር የመፍጠር ነፃነት አላቸው፡፡

በትግራይ ክልል በራያና በወልቃይት የተነሳው ጥያቄ ሌላ አጀንዳ ባላቸው አካላት የተነሳና መላው ሕዝብን የማይወክል ነው በሚል በክልል ደረጃም መታየት እንዳልቻለ የተያዩ ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡ የአማራ ክልል ምክር ቤት በቅርቡ ባደረገው ስብሰባ በወልቃይትና ፀገዴ ጉዳይ ከትግራይ ክልል ጋር ውይይት እንደሚያደርግ መነጋገሩ ይታወሳል፡፡

ለተለያዩ የማንነት ጥያቄዎች የሚሰጠው ምላሽ አስቀድሞ በሚታወቁ መርሆዎች ላይ የተመሠረተ እንዳልሆነ በመጥቀስ አቶ ውብሸት ይተቻሉ፡፡ ‹‹መንግሥት ወጥ የሆነ አሠራር ወይም መርህ የለውም፡፡ አገሪቱ ያላትን ውስን በጀት በአግባቡ በሥራ ላይ ለማዋል፣ መመለስ በምትችልበት አቅም መመለስ ትችልም ዘንድ ወጥ የሆነ ሥርዓት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አልቀረፀም፡፡ ምክር ቤቱ ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን የተሰጠው አካል እንደመሆኑ በሌሎች አገሮች ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚሰጧቸው ውሳኔዎች ወጥ የሆኑና ለሁሉም ተቀባይ የሆነ አሠራር የሚያስተዋውቁ ከመሆኑ አንፃር በዚህ መልኩ መሄድ ነበረበት፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከ15 ዓመታት በኋላ ፓርቲያቸው ከባድ ችግር እንደገጠመው ለፓርላማው አምነዋል፡፡ ያኔ በተሃድሶ ከችግሩ እንደወጣ ሁሉ ከሕዝቡ ጋር በመሆን የአሁኑን ችግርም እንደሚወጣው ተማምነዋል፡፡ ይሁንና ብዝኃነትን ማክበር የህልውና ጉዳይ ነው እያሉ የብዝኃነትን ጥያቄ መልሰን ጨርሰናል በማለት መልሶ በመሰረዝ ከውጥረት መውጣት አይቻልም የሚሉ አሉ፡፡ ለማንነት ጥያቄዎች የሚሰጠው ምላሽ ከኃይል ዕርምጃ ፀድቶ ዴሞክራሲያዊ፣ ሕጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነታቸውን አስቀድመው ሊወጡ እንደሚገባ የሚያስገነዝቡ ብዙዎች ናቸው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -