Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜና​በኢትዮጵያ የአልቃይዳንና የአልሸባብን ተልዕኮ ለማስፈጸም ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ ተከሳሾች እስከ 19 ዓመት ጽኑ...

​በኢትዮጵያ የአልቃይዳንና የአልሸባብን ተልዕኮ ለማስፈጸም ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ ተከሳሾች እስከ 19 ዓመት ጽኑ እስራት ተፈረደባቸው

ቀን:

የአልቃይዳና አልሸባብ የሽብር ቡድኖችን የጋራ ዓላማና ተልዕኮ በመቀበል የወንጀል ተግባር በኢትዮጵያ ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል ተብለው የሽብር ተግባር ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው 28 ተከሳሾች፣ መጋቢት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሦስት እስከ 19 ዓመታት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተፈረደባቸው፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ሐምሌ 4 ቀን 2005 ዓ.ም. ጽፎ ያቀረበውን ክስ ሲመረምር የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት የጽኑ እስራቱን ፍርድ የሰጠው፣ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው የተከታተሉትን አማን አሰፋን በ13 ዓመታት ከአሥር ወራት፣ አንዋር አደም በ13 ዓመታት፣ ሙፍቲህ መሐመድ በአሥር ዓመታት ከአሥር ወራት፣ አብዱራዛቅ ሼክ አህመድ በ13 ዓመታት ነው፡፡ በተጨማሪም ኢብራሂም አብዱ፣ ኑረዲን መሐመድ፣ አህመድ ማሞ መሐመድ ኑር አብደታ እያንዳንዳቸው በሰባት ዓመታት ከሁለት ወራት፣ መሐመድ አብዱልቃድር በስድስት ዓመታት፣ ሰላህዲን ሰይድ በአራት ዓመታት ከአራት ወራት፣ ሁሴን ሮባ በስድስት ዓመታትና ጋዜጠኛ ሰለሞን ከበደ በሦስት ዓመታት ከ11 ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተፈርዶባቸዋል፡፡

በሌሉበት ሁሉም 19 ዓመታት ጽኑ እስራት የተፈረደባቸው ደግሞ መሐመድ አህመድ፣ ሼክ እድሪስ ዓሊይ፣ መሐመድ አህመድ፣ አንጋሱ ሁሴን፣ ኢብራሂም አህመድ፣ አብዱራህማን ቢላል፣ የዚድ ጀማል፣ ኢብራሂም የሱፍ፣ ጃፋር፣ ሼክ እድሪስ አህመድና ኑር አብዱ አሊይ ናቸው፡፡

- Advertisement -

ፍርደኞቹ የአልቃይዳና የአልሻባብ የጋራ ዓላማና ተልዕኮ በምሥራቅ አፍሪካ የሽብር ግንባር ማቋቋም፣ በአካባቢው ባሉ አገሮች ጦርነት ማድረግ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማፍረስ፣ በሸሪዓ የሚተዳደር እስላማዊ መንግሥት መመሥረት እንደነበር ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

ከ1995 ዓ.ም. ጀምሮ በተለይ በኢትዮጵያ የአልቃይዳና የአልሻባብ የሽብር ክንፍ ወታደራዊ አጠቃላይ መሪ መሆኑ የተጠቀሰው ፍርደኛ አማን አሰፋ የሽብር ቡድኑን ዓላማና ተልዕኮ በመቀበል፣ በህቡዕ በመደራጀት አባላትን ለመመልመል፣ የጦር መሣሪያ አጠቃቀም ሥልጠና ለመውሰድ ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሶማሊያ መሄዱንና ሥልጠና መውሰዱን ክሱ ያብራራል፡፡

በ2003 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በኢትዮጵያ ሊፈጸም የታቀደውን የሽብር ተልዕኮ ለማስፈጸም፣ የአልቃይዳ አልሸባብ የምሥራቅ አፍሪካ የሽብር መረብ ክንፍ ማቋቋሙንም ክሱ ያክላል፡፡ ከሌሎቹ ፍርደኞች ጋር የሥራ ክፍፍል በማድረግ አባላትን በመመልመል፣ የጦር ማሠልጠኛ ቦታዎችን በመምረጥና ሌሎች ለሽብር ተግባር የሚሆኑ ተግባራትን ሲያከናወኑ እንደነበር በክሱ ተተንትኗል፡፡ ለሽብር ቡድኑ መለያ ‹‹ሀረከቱል ሸባብል ሙጃህዲን ፊ ቢላደል ሂጀራይተን›› የሚል ስያሜ በመስጠት፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ከሚገኙ ግለሰቦችና የሽብር መዋቅሮች ጋር ትስስር ፈጥረው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር በዝርዝር በክሱ ተጠቅሷል፡፡ የእያንዳንዳቸውን የሥራ ድርሻና በሽብር ቡድኑ የተሰጠው ተልዕኮና ዓላማም ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስታውቋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ክስ ለተከሳሾቹ ተነቦላቸው የእምነት ክህደት ቃላቸውን፣ ‹‹ድርጊቱን አልፈጸምንም ወንጀለኞችም አይደለንም፤›› በማለት ሰጥተዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ እንደ ክሱ ያስረዱልኛል ያላቸውን ምስክሮች አሰምቶ እንዳበቃ ሁሉም ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል፡፡

ተከሳሾቹ በርካታ የሰነዶችና የሰዎች ምስክሮችና ማስረጃዎችን ያቀረቡና የተከላከሉ ቢሆንም የዓቃቤ ሕግን ክስ፣ የምስክሮች ቃልና የሰነድ ማስረጃዎች ማስተባበል እንዳልቻሉ ተገልጾ ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡

የቅጣት ማክበጃና ማቅለያ እንዲያቀርቡ ዓቃቤ ሕግና ተከሳሾቹ ተጠይቀው፣ ዓቃቤ ሕግ የወንጀሉ ደረጃ ከፍተኛና መካከለኛ እንዲባልለት፣ የቅጣት ደረጃው ግን ከፍተኛና ከባድ እንዲሆንለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

ተከሳሾቹ በጽሑፍ ባቀረቡት የቅጣት ማቅለያ ድርጊቱ ጅምር እንጂ አለመጸሙን፣ በሰውም ሆነ በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን፣ በአገሪቱ የተለያዩ ልማቶች ላይ ተሳታፊ መሆናቸውንና የወንጀል ሪከርድ የሌለባቸው መሆኑን በመግለጽ የወንጀል ደረጃው ዝቅተኛ እንዲባልላቸውና ቅጣቱም ቀሎ እንዲፈረድባቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ እንደገለጸው፣ ጥፋተኛ የተባሉበት የፀረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4 እና አንቀጽ 7(1) ነው፡፡ ይህም ከ15 ዓመታት እስከ ሞት ሊያስቀጣ እንደሚችል ጠቁሞ፣ ፍርድ ቤቱ ግን መነሻውን 15 ዓመታት ይዞ መድረሻውን ዕድሜ ልክ እስራት የሚለውን በመውሰድ የያዘላቸውን የቅጣት ማክበጃና ማቅለያ ተጠቅሞ፣ ከላይ የተጠቀሰውን የጽኑ እስራት ቅጣት ፈርዶባቸዋል፡፡ ከእስር ሲፈቱም ከማንኛውም ሕዝባዊ መብቶቻቸው ለሁለት ዓመታት መታገዳቸውን አስታውቋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...