Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊ​አራት ሰዎችን በመግደል የተጠረጠረው አሽከርካሪ እጁን ለፖሊስ ሰጠ

​አራት ሰዎችን በመግደል የተጠረጠረው አሽከርካሪ እጁን ለፖሊስ ሰጠ

ቀን:

  • በሚድሮክ የተገነባው መከለያ ግንብ ለጥንካሬ የሚያስፈልገው ብረት የለውም

በአዲስ አበባ ከተማ ሲኤምሲ አካባቢ ወደ ሰሚት ለስላሳ ፋብሪካ በሚያመራው መንገድ ላይ ሐሙስ መጋቢት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በዩሮትራከር ከባድ የጭነት ተሽከርካሪ አደጋ ያደረሰ ሾፌር፣ ሰሚት ፔፕሲ አደባባይ ሲደርስ ከየረር ጎሮ ወደ ሰሚት የተገነባ የመንገድ መከለያ ግንብ በመደርመስ በአራት ሰዎች ሕይወት ማጥፋት በመጠርጠሩ እጁን ለፖሊስ ሰጠ፡፡

አሽከርካሪው የመንገዱን ግንብ ሲገጭ ከየረር ጎሮ በኩል አራት ሰዎችን አሳፍሮ ወደ ሰሚት አደባባይ በመጓዝ ላይ በነበረ አንድ ባጃጅ ላይ በመገልጠቡ፣ የባጃጁ አሽከርካሪና ሦስት ተሳፋሪዎች ወዲያውኑ ሕይወታቸው ማለፉ እንደተረጋገጠ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ምክትል ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ ገልጸዋል፡፡

አሰቃቂው የትራፊክ አደጋ ሊደርስ የቻለው በተሽከርካሪው የቴክኒክ ችግር ይሁን ወይም በአሽከርካሪው ብቃት ማነስ ለማረጋገጥ ገና እየተሠራ መሆኑን የገለጹት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው፣ ከአደጋው አደራረስ ለመገመት እንደተቻለው ተሽከርካሪው ከፍተኛ ፍጥነት ላይ ሳይሆን እንዳልቀረ ግምት መወሰዱን አስረድተዋል፡፡ አደጋው በደረሰበት ወቅት የከባድ ተሽከርካሪው ሾፌር ለጊዜው ተሰውሮ የነበረ ቢሆንም፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ሄዶ እጁን መስጠቱን ምክትል ኢንስፔክተር አሰፋ ጠቁመዋል፡፡

- Advertisement -

በአካባቢው የነበሩ የዓይን እማኞች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በግምት ከቀኑ 9፡30 ሰዓት ሲሆን ከአያት መንገድ ወደ ቀኝ ታጥፎ በከባድ ፍጥነት ሲሽከረከር የነበረው ከባድ የጭነት ተሽከርካሪ ሾፌር ቀጥ ብሎ ነው አደባባዩ ላይ የወጣው፡፡ ሰሚት ፔፕሲ አደባባይ ሲደርስ ወደ ሰሚት ኮንዶሚኒየም፣ ወደ አያት፣ ወደ ተባበሩትና ወደ የረር ጎሮ የሚታጠፉ መንገዶች መኖራቸውን የጠቆሙት እማኞቹ፣ የጭነት ተሽከርካሪው ከላይ እየበረረ መጥቶ አራት አቅጣጫ ያለው መንገድ ላይ ሲደርስ ወደሚፈልገው መታጠፍ ባለመቻሉ፣ ከፊት ለፊቱ ያገኘውን የመንገድ መከለያ ግንብ ደርምሶ መገልበጡን አስረድተዋል፡፡ በወቅቱ ከየረር ጎሮ ወደ ሰሚት ፔፕሲ አደባባይ ለመታጠፍ የደረሰው ባጃጅ ግንቡ ሥር ደርሶ ስለነበር፣ ግንቡ እንደተደረመሰበት ተናግረዋል፡፡

ዩሮትራክተሩ ሲገጨው የተደረመሰው የመንገድ መከለያ ግንብ የተገነባው በሚድሮክ ኮንስትራክሽን ሲሆን፣ ግንባታው ረጅም ጊዜ ወስዶ በ2001 ዓ.ም. ተጠናቆ መመረቁ ይታወሳል፡፡

የመንገድ መከለያ ግንቡ ሲደረመስ ለጥንካሬ የሚረዳው ምንም ዓይነት ብረት እንዳልተካተተበት ለማየት ተችሏል፡፡ የመንገድ መከለያ ግንብ ከመከለያነት በተጨማሪ ጥንካሬ ኖሮት ግጭት መከላከል እንዳለበት ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ስለግንባታውና ስለሚጠቀሙት የግንባታ ማቴሪያል ሁኔታ ማብራሪያ እንዲሰጡ፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፍቃዱ ኃይሌን ለማነጋገር ሪፖርተር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

በኢትዮጵያ እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋን በሚመለከት መጋቢት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. የመንግሥትን የስድስት ወራት ሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ‹‹በዓለም ደረጃ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የአገራችን ሕዝቦች ሕይወት በመኪና አደጋ እየተቀጠፈ ነው፡፡ ይህንን እጅግ አሳሳቢ የሆነና ኢትዮጵያን ከዓለም ሕዝቦች የተለየች ሆና እንድትታይ ማድረጉንና ማንኛውም ወረርሽኝ በሽታ እንኳን የማይቀጥፈውን ሕዝብ እየቀጠፈ ያለ አደጋ ለመቀነስ መሥራት ይገባል፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...