የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አዲስ ባወጣውና ተግባር ላይ ባዋለው አዋጅ ቁጥር 859/2006 ‹‹ዕቃዎችንና ማጓጓዣዎችን ስለመውረስ›› በሚለው አንቀጽ 147 ላይ ያካተተውን ድንጋጌ እንደሚቃወሙ፣ የኢትዮጵያ የፈሳሽ ጭነት ማጓጓዣ ባለንብረቶች መጋቢት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. አስታወቁ፡፡
የኢትዮጵያ የፈሳሽ ጭነት ማጓጓዣ ባለንብረቶች ማኅበር ሐሙስ መጋቢት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በፌዴራል መንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን የመሰብሰቢያ አዳራሽ በጠራው የግማሽ ቀን አስቸኳይ ስብሰባ እንደገለጸው፣ ባለሥልጣኑ ማንኛውም የፈሳሽ ጭነት ተሽከርካሪ የኮንትሮባንድ ዕቃ ጭኖ ከተያዘ እንደሚወረስ በአዋጁ አካቷል፡፡ ‹‹የተሽከርካሪው ባለቤት በማያውቀውና ድርጊቱን ራሱ ባልፈጸመበት ሁኔታ እንዴት ንብረትን ያህል ነገር ይወረሳል ይባላል?›› በማለት ጠይቀዋል፡፡
የተሽከርካሪው ባለቤት የሚቀጥረው ኢትዮጵያዊና በኢትዮጵያ ሕግ የሚገዛ ዜጋ መሆኑን የጠቆሙት ባለንብረቶቹ፣ ሕገወጥ ተግባር ፈጽሞ ከተገኘ ቅጣቱ ሕጉን ተከትሎ በአሽከርካሪው ላይ መፈጸም ሲገባው፣ ‹‹ተሽከርካሪው ይወረሳል›› ማለት ‹‹ሥራውን አትሥሩ ማለት ነው›› በማለት ድንጋጌውን ተቃውመዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በርካታ የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ተይዘው በክርክር ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ባለንብረቶቹ፣ የ18 ሺሕ ብር ኮንትሮባንድ ጨርቃ ጨርቅ በመያዙ በሚሊዮኖች ብር የተገዛ ተሽከርካሪን ለመውረስ ደብዳቤ መጻፍ አሳዛኝና እንደ አገር አሳፋሪ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
አንድ ባለሀብት ከአሥር በላይ የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ሊኖሩት እንደሚችል የተናገሩት ባለንብረቶቹ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ጂቡቲ በሚደረገው ጉዞ በሚገኙ መዳረሻ ከተሞች ላይ አሽከርካሪው ተመሳጥሮ ወይም በራሱ ኃላፊነት ሻግ ‹‹ዕቃ መደበቂያ›› አሠርቶ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ጭኖ ቢያዝ፣ ባለንብረቱ የሚያውቅበትና የሚከታተልበት ሁኔታ ሊኖር እንደማይችል ተናግረዋል፡፡ ባለሥልጣኑ ግምት ወስዶ የዕርምጃ አቅጣጫውን ሊያስተካክል እንደሚገባና ቅጣቱንም በአሽከርካሪው ላይ ብቻ ሊያደርግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ አሽከርካሪው ነዳጅ ሊያመጣ ወደሚሄድበት አገር ሲጓዝ ሻግ አሠርቶ ወደ አዲስ አበባ ሲመለስ ሊያስነሳው ስለሚችልና ባለንብረቱ ሊያውቅ እንደማይችል ጠቁመው፣ ባለሥልጣኑ ከመነሻው እስከ ጂቡቲና ሱዳን ድረስ ያሉ መዳረሻ ቦታዎችን የሚቆጣጠርበት ሥልት ቢዘረጋ እነሱም ተባባሪ እንደሚሆኑ አክለዋል፡፡
በትራንስፖርት ኢንዱስትሪው ውስጥ ኢንቨስት አድርገው የሥራ ዕድል ከመፍጠራቸውም በተጨማሪ፣ ለመንግሥትም ገቢ እያስገቡ የሚገኙ ልማታዊ ባለሀብት መሆናቸውን ጠቁመው፣ ጥፋት እንኳን ቢገኝ ቅጣቱ በአስተዳደር በኩል ሆኖ ነገሮች የሚስተካከሉበትን ሁኔታ መንግሥት ማመቻቸት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
አንድ አውሮፕላን አደንዛዥ ዕፅ ጭኖ ቢያዝ የሚወረሰው የተያዘው አደንዛዥ ዕፅ ሲሆን፣ ቅጣት የሚጣልበት ከተያዘ የጫነው አካል እንጂ አብራሪው እንደማይቀጣ ወይም አውሮፕላኑ እንደማይወረስ አስረድተው፣ የእነሱም ነዳጅ ማመላለሻ ቦቴዎች በዚያ መልኩ እንዲታዩ ጠይቀዋል፡፡
ኮንትሮባንድ ጭኖ የተገኘ ተሽከርካሪ መወረስ እንዳለበት በሕግ ደረጃ ድንጋጌ እንዲወጣ ያደረገው አካል አርቆ ሳያስብ ወይም ግብታዊ ሆኖ ካልሆነ በስተቀር፣ እንደዚህ ዓይነት ድንጋጌ ባለንብረቱን ሳያወያይና የሐሳብ ፍጭት ተደርጐበት ስምምነት ላይ ሳይደረስ ሊሆን እንደማይችል ተናግረው፣ በአዋጁ ውስጥ የተካተተችውን አንቀጽ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሚመለከታቸው አካላት ተመልክተው መፍትሔ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል፡፡ መንግሥት ሁኔታውን ተመልክቶ ያላግባብ ተይዘው በፍርድ ቤትና በተለያዩ ቦታዎች በክርክር ላይ የሚገኙ ባለንብረቶች፣ ንብረታቸው እንዲለቀቅላቸውና ወደ ሥራቸው እንዲገቡ እንዲያደርግም አሳስበዋል፡፡ አዋጁ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ግን፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለአገሪቱ ሕዝብ ችግራቸውን አሳውቀው ሥራ ለማቆም እንደሚገደዱ፣ በሕዝብ ገንዘብ ከባንክ ተበድረው የገዟቸውን ፈሳሽ የጭነት ማመላለሻ ቦቴዎቻቸውንም ከሥራ እንደሚያስወጡ ተናግረዋል፡፡
ባለንብረቶቹ ያነሱትን ቅሬታ አስመልክቶ ምላሽ ለሪፖርተር ምላሽ የሰጠው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ አዋጅ ቁጥር 859/2006 ተግባር ላይ የዋለው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተወያይተውበትና ተስማምተውበት መሆኑን ገልጿል፡፡ የባለሥልጣኑ የትምህርትና ኮሙዩኒኬሽን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ፋሲካ በላይ እንደገለጹት፣ አዋጁ ሥራ ላይ ከዋለ ሁለት ዓመታት አልፎታል፡፡ በሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተወያይተውበታል፡፡ ስምምነት ላይም ተደርሷል፡፡ ችግር ካለ መነሳት የነበረበት አዋጁ ከመፅደቁ በፊት ነበር፡፡ አሁን የሚናገሩት የግል ጥቅማቸው ተነክቶባቸው እንጂ አዋጁ ጐድቷቸው እንዳልሆነ አቶ ፋሲካ አስረድተዋል፡፡
አንድ ተሽከርካሪ ትርፍ አካል (ሻግ) የሚሠራለት በአራትና በአምስት ቀናት ውስጥ ሳይሆን ጊዜ ወስዶ በመሆኑ፣ ባለንብረቱ የመቆጣጠር ኃላፊነት እንዳለበት የገለጹት ምክትል ዳይሬክተሩ፣ ባለሥልጣኑ ባለንብረቶቹ ሳያውቁ ሊሠራ ይችላል የሚል እምነት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡ አዲሱ አዋጅ ከነባሩ አዋጅ የተሻለ እንጂ የባሰ አለመሆኑን የገለጹት አቶ ፋሲካ፣ በነዳጅ ማጓጓዣ ላይ ሻግ (ዕቃ መደበቂያ) ተሠርቶ ሲገኝ ባለቤቶቹ ዕርምጃ መውሰድ ካልቻሉ፣ ቅጣቱ ተግባራዊ የሚሆነው በእነሱ ላይ መሆኑንና ተገቢ አሠራር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሻግ በማሠራት የሚገኘውን ጥቅም ስለሚያውቁትና ታክስ ላለመክፈል የሚያደርጉት ሕገወጥ ተግባር እንጂ፣ አሽከርካሪዎችን መቆጣጠር ከባለሥልጣኑ ይልቅ ለባለንብረቱ ቀላል መሆኑን ገልጸው፣ አዋጁ ለባለሥልጣኑ ሳይሆን ለባለንብረቶቹ ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሌላው የነዳጅ ጭነት ማጓጓዣ ባለንብረቶቹ እየገጠማቸው የሚገኘው ችግር ጂቡቲና ሱዳን ለመጫን በሚያደርጉት ጉዞ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይ ጂቡቲ ውስጥ ከፍተኛ ችግር እየገጠማቸው መሆኑን የሚናገሩት ባለንብረቶቹ፣ ከጂቡቲ ጭነው ወደ ኢትዮጵያ እስከሚመለሱ ድረስ በቆሙበት የአገሩ ተሽከርካሪ ቢገጫቸው፣ ክፍያ የሚፈጽሙት እነሱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹እናንተ ባትመጡ አንገጭም ነበር፤›› በማለት እስከ ሩብ ሚሊዮን ብር ክፍያ እንደሚጠየቁ፣ ተሽከርካሪያቸው በማንኛውም አጋጣሚ ቢገለበጥ ያለፈቃዳቸው በማንሳትና በማጓጓዝ ከ180 ሺሕ እስከ 200 ሺሕ ብር ክፍያ እንደሚጠየቁና ሌሎች በደሎች እንደሚፈጸምባቸው ገልጸዋል፡፡ ሁለቱ አገሮች በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ፣ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መፍትሔ እንዲፈለግላቸው ጠይቀዋል፡፡ ችግሩ የሚደርስባቸው በአገሪቱ መንግሥት ሳይሆን በተለያዩ የሥልጣን እርከን ላይ ባሉ ሹማምንት በመሆኑ፣ ተመጣጣኝ ሥልጣን ያላቸው የኢትዮጵያ የትራንስፖርት ባለሥልጣናት አነጋግረው መፍትሔ እንዲሰጧቸውም ጠይቀዋል፡፡