- የጣሊያን የፋይናንስ ተቋም የብድር ዋስትና ሰጠ
የጣሊያን ግዙፉ ኩባንያ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን፣ ጊቤ አራት ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት እንዲሰጠው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ሲያካሄድ የቆየው ድርድር ተጠናቀቀ፡፡ ሳሊኒ በቅርብ ቀናት ውስጥ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ስምምነት ይፈራረማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ያካሄደ በመሆኑ የቴክኒክ ጉዳይ አሳሳቢ እንዳልነበረ ያስታወሱት የሪፖርተር ምንጮች፣ የድርድሩ ማጠንጠኛ ሆኖ የቆየው የፋይናንስ ግኝት ጉዳይ እንደነበር አመልክተዋል፡፡
ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ለዚህ ፕሮጀክት የሚያስፈልገውን በጀት (1.5 ቢሊዮን ዩሮ) የጣሊያን ብድር ዋስትና አገልግሎት ሰጪ ተቋም (SACE) ዋስትና እንደሚሰጥ መተማመኛ በማቅረቡ፣ በጥር ወር 2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀና የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የሕግ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ዋሲሁን አባተ የተገኙበት ልዑካን ቡድን ጣሊያን ሮም በመጓዝ ውይይት አድርጎ ተመልሷል፡፡
ምንጮች እንደገለጹት፣ የልዑካን ቡድኑ ከጣሊያን ብድር ዋስትና አገልግሎት ሰጪ ተቋም ጋር ባደረገው ውይይት ለፕሮጀክቱ ፋይናንስ አቅራቢ ተቋም ዋስትና ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ በዚሁ ምክንያት የፋይናንስ ጉዳይ መቋጫ አግኝቷል ተብሏል፡፡ በዚህ ሳቢያ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው የኤሌክትሪክ ቦርድ በዚህ ሳምንት መጀመርያ ፕሮጀክቱን ያፀድቀዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እስካሁን ማረጋገጫ ባይገኝም በዚህ ሳምንት ኢትዮጵያን የሚጎበኙት የጣሊያኑ ፕሬዚዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ በተገኙበት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና በሳሊኒ ኮንስትራክሽን መካከል የግንባታ ውል እንደሚፈረም ተገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን የመንግሥታቸውን የግማሽ ዓመት ሪፖርት ለሕዝብ ተወዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ሰነድ፣ 2,200 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ፕሮጀክት ግንባታ ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት እንደተጠናቀቀ ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በጥቂት ወራት ውስጥ በይፋ እንደሚጀምር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢገልጹም ፕሮጀክቱ የቱ እንደሆነ ግን ምንም ሳይሉ አልፈዋል፡፡
የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት ጊቤ አራት ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክትን በሚመለከት ነው፡፡
ከማምረት አቅሙ ሲሶ ያህል (540 ሜጋ ዋት) ማምረት የጀመረው ጊቤ ሦስት ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ጣቢያ ቀጣይ ክፍል የሆነው ጊቤ አራት፣ በደቡብ ክልል በቱርካና ሐይቅ አቅራቢያ የሚገኝ ፕሮጀክት ነው፡፡
ቀድሞ በተካሄደ ጥናት ይህ ፕሮጀክት 1,450 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ይኖረዋል ቢባልም፣ በተደረገው የዲዛይን ክለሳ የማምረት አቅሙ ወደ 2,200 ሜጋ ዋት ከፍ ማለቱ ታውቋል፡፡
ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ በሐምሌ ወር 2007 ዓ.ም. ይኼንን ፕሮጀክት ለማጥናት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የመግቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ ነገር ግን በዚሁ ስምምነት ብቻ የግንባታ ውል ሳይፈጸም የአፈር ቆረጣ ሥራዎችን በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ መዘገባችን ይታወሳል፡፡