Sunday, September 24, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

​የሕዝቡን ቀልብ የሳበው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በተግባር ካልተደገፈ ፍሬ አልባ ይሆናል!

ሕዝብና መንግሥትን ሆድና ጀርባ ያደረጉ አጠቃላይ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሰሞኑን እየተነገረ ያለው በቅጡ ሊደመጥ ይገባል፡፡ በመላ አገሪቱ በመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በፍትሕ መዛባትና በሙስና ምክንያት ሕዝብና መንግሥት ተቃቅረዋል፡፡ ይህንን መቃቃር ከልቡ ለመቀበል የማይፈልገው መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መጠነኛ ለውጥ ቢያሳይም፣ አሁን ግን በጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበት ችግሮችን ወደ ውጭ ከመግፋት ይልቅ ወደ ራሱ ማየት እንደሚሻለው አምኗል፡፡ በእርግጥም ተጨባጩን ሀቅ ከማመን የተሻለ አማራጭ የለም፡፡ ችግሮችን ወደ ውጭ እየገፉ ሌሎችን ለማሳቀል ከመሯሯጥ ይልቅ፣ ወደ ራስ መመልከት ይጠቅማል፡፡ በውስጡ ብቃት አልባዎችን፣ ሙሰኞችን፣ ፍትሕ የሚያዛቡትን፣ ሰብዓዊ መብት የሚረግጡትንና የዴሞክራሲውን ባቡር ሐዲድ የሚያስቱትን፣ ወዘተ ታቅፎ አገሪቱንና ሕዝቡን ከማሰቃየት እነሱን አራግፎ መገላገል ይሻለዋል፡፡ አገር የምትበለፅገውና ሕዝብ በነፃነት በአገሩ መኖር የሚችለው ሰላም፣ የሕግ የበላይነት፣ ዴሞክራሲ፣ ነፃነትና እኩልነት ሲኖሩ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሕዝቡ መንግሥትን ወጥሮ መያዝ አለበት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሐሙስ መጋቢት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ፣ በመላ አገሪቱ የሚሰሙት ምሬቶች ከጫፍ እስከ ጫፍ ተመሳሳይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ መንግሥትም በዚህ ምክንያት በሕዝቡ ከመንገዱ ላይ ዘወር በል እየተባለ መሆኑን፣ በዚህም  የተነሳ መልካም አስተዳደርን ማስፈን አገራዊ ህልውናን የማረጋገጥ ጉዳይ እንደሆነ አውስተዋል፡፡ በመልካም አስተዳደር ችግር ምክንያት የተከሰቱት አለመረጋጋቶች ማሳያ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ መንግሥትም ጣቱን ወደ ሌሎች መቀሰር ትቶ ችግሮቹ የራሱ መሆናቸውን በማመን ይቅርታ እንደሚጠይቅ አክለዋል፡፡ ይህ የሕዝቡን ቀልብ የሚስብ ንግግር በተግባር ሲደገፍ ደግሞ ከግርድ ይልቅ ፍሬ ያፈራል፡፡ መንግሥትና ሕዝብን የሚያግባባው ከመናገር በላይ መንግሥት ማሳየት ሲችል ብቻ ነው፡፡

ችግሮችን ሁሉ ወደ ውጭ ከመግፋት ይልቅ፣ መንግሥት የራሱ ድርሻ እንዳለበት አምኖ ለለውጥ ሲነሳና ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህንን በአደባባይ ሲያምኑ መስማት ተቀባይነት ያለው ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ከትግራይ ጫፍ እስከ ደቡብ ጫፍ ድረስ የሕዝቡ ምሬት አንድ መሆኑ በመንግሥት ከታመነበት፣ ለመፍትሔው ደግሞ ተግባራዊ የሆነ ርብርብ ማድረግ የግድ ነው፡፡ በሕዝብ መቶ በመቶ ተቀባይነት አግኝቼ ተመርጫለሁ ያለ መንግሥት በጥቂት ወራት ውስጥ ከፍተኛ ሕዝባዊ ምሬት ሲቀሰቀስበት፣ ከዚያም አልፎ ተርፎ ሕይወት የሚያስከፍል ብጥብጥና አመፅ ሲነሳበት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ወደ ራስ ከመመልከት ውጪ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ ወደ ራስ መመልከት ብቻ ሳይሆን፣ ምልዓተ ሕዝቡን ተሳታፊ ያደረገ በተግባር የሚታገዝ ወሳኝና ቆራጥ ዕርምጃ ያስፈልጋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት መንግሥት በመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ በፍትሕ ማዛባትና በሙስና ተወጥሮ ሕዝቡ ዘወር በል እያለው ነው ብለው መናገራቸው በእጅጉ የሚደገፍ ነው፡፡ ወደ ሌሎች ኃይሎች ሲተላለፍ የነበረው ሰበብ ሁሉ ጋብ እንዲል ተደርጎ፣ መንግሥት ወደ ራሱ እንዲመለከትና የሚታዩበትን መጠነ ሰፊ ችግሮች እንዲፈታ ከተፈለገ ተግባራዊ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ከፍተኛ የመንግሥትና የፓርቲ አመራሮች፣ በየደረጃው የሚገኙ ሹማምንት፣ በመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞችና ሕዝቡ ጭምር ለተግባራዊ ዕርምጃዎች ስኬት መሳተፍ አለባቸው፡፡ በየተገኘው መድረክ እየተደሰኮረ በየኔትወርኩ ውስጥ በመጠለል አገር ማጥፋት መቆም አለበት፡፡ ሕዝብ ከንግግር በላይ የናፈቀው ተግባር ብቻ ነው፡፡

በመላ አገሪቱ የሚስተዋሉ ችግሮች ተመሳሳይ መሆናቸው ከታመነ መፍትሔውም ተጨባጭ ሁኔታውን የሚመጥን ይሆናል፡፡ አገሪቱ አሁን የገጠማት ችግር ለህልውናዋ ጭምር ያሰጋታል ሲባል ከንግግር የበለጠ ተግባር ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር በአንክሮ ሰምቶ በፍጥነት ወደ ተግባር ካልተገባ ሕዝባዊ አመፅ ይጠራል፡፡ ምሬቱ ከመጠን በላይ የሆነበት ሕዝብ በንግግር ብቻ  ተደልሎ እንደማይቆም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከታዩ እንቅስቃሴዎች መረዳት ይቻላል፡፡ ሕዝብን እያስቆጡና ምላሽ ሳይሰጡ መኖር የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን ማመን ያስፈልጋል፡፡ ሕዝቡ ውስጥ የሚታዩ መሠረታዊ ችግሮች ፍንትው ብለው ስለሚታወቁ፣ ያለው አማራጭ አንድ ነው፡፡ ተግባር፡፡

ሁከቶችና አለመረጋጋቶች ከመከሰታቸው በፊት መንግሥት ለሕዝቡ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠትና ብልሹ አሠራሮችን ነቅሶ ማውጣት ላይ እንደሚያተኩር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡ በእርግጥ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ ክልሎች ከሕዝቡ ጋር ውይይት በማድረግ በተለያዩ ዘርፎች የችግሮችን ምንጮች ለማወቅ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የተዘጋጁት መድረኮች ሕዝቡ በትክክል ተወክሎባቸው ከሆነ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ሕዝብን እንወክላለን ከሚሉና በሕዝቡ ውስጥ መልካም ስምና ግብር ከሌላቸው ወገኖች ጋር የሚደረጉ የማስመሰያ ውይይቶች፣ አሁንም ለሌላ ዙር ሁከትና ብጥብጥ ምክንያት እንዳይሆኑ ማረጋገጫ ሊሰጥ ይገባል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ያለ ሕዝብ ሁለንተናዊ ተሳትፎ መፍታት አይቻልም ሲባል፣ በሕዝብ ስም የሚሠሩ ሸፍጦችን መታገል ይገባል ማለት ነው፡፡ ከእውነተኛ የሕዝብ ሁለንተናዊ ተሳትፎ የሚገኝ ግብዓት ወሳኝ በመሆኑ፣ መንግሥት ለአገሪቱ ህልውናም ሆነ ለራሱ ሲል ይህንን አማራጭ ቢከተል ይሻለዋል፡፡

በቅርቡ በአዲስ አበባም ሆነ በተለያዩ ክልሎች በፍትሕ አካላት፣ በመሬት አስተዳደርና በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ላይ በሚገኙ የሙስና ተጠርጣሪዎች ላይ እስር፣ ክስና ከሥራ የማሰናበት መጠነኛ ዕርምጃዎች እየታዩ ነው፡፡ በእርግጥ ካለው ችግር ውስብስብነት አንፃር የሚቀሩ በርካታ ተግባራት ቢኖሩም፣ የሚወሰዱት ዕርምጃዎች ከበቀልና ከአድልኦ ነፃ የሆኑ፣ መፈራራት የሌለባቸው፣ የሕጋዊነትን ሚዛን ያልሳቱ፣ በጥናት ላይ የተመሠረቱና የሕዝብን ይሁንታ ያገኙ መሆን አለባቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አርሶ አደሮችን ከይዞታቸው የሚያፈናቅሉ፣ ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶችን አገር ውስጥ በማስገባት በሸማቹና በመንግሥት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ፣ የፍትሕ ሥርዓቱን የሚያዛቡና በአጠቃላይ ሕዝቡን ለምሬት የሚዳርጉ አመራሮችንና ፈጻሚዎችን የማጥራቱን ሥራ መንግሥት በጥልቀት ይገፋበታል ብለዋል፡፡ በመሬት አስተዳደርና በንግዱ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን በገቢዎችና ጉምሩክ፣ በመንግሥት ግዢና በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና ሙስናን መፋለምም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ ይህ በእጅጉ የሚደገፍና ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ሐሳብ ነው፡፡ አሁንም ተግባር ይቅደም፡፡ ከአስመሳዮችና ከአድርባዮች ወሬ ይልቅ ሕዝቡ ይደመጥ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተስፋ የሚሰጥ ንግግር ከቃለ ነቢብ አልፎ ወደ ተግባር ይሸጋገር ዘንድ የሕዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡፡ መንግሥት ከአመራሩ ጀምሮ እስከ ታችኛው እርከን ድረስ ራሱን በመመርመር ሕዝብን የሚያረካ አስተዳደር ለመፍጠር የሚችለው ግን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስቀመጡት መሠረት ለመንቀሳቀስ የሚችል ቁርጠኛ አመራርና ተከታይ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ በየመድረኩ ለታይታ የሚደረጉ ማስመሰሎች ቆመው ለሕዝብ ጥያቄዎች በትክክል ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል መንግሥታዊ ቁመና ያስፈልጋል፡፡ ሙስና ውስጥ የተዘፈቁና ካለሱ መኖር የማይችሉ ከንቱዎችን አዝሎ የትም መድረስ አይቻልም፡፡ ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና እሴቶቹ፣ ስለሰብዓዊ መብት ክብር፣ ስለፍትሐዊ እኩልነትና የሀብት ክፍፍል፣ ስለሕግ የበላይነት፣ ስለሕዝብ ክብር፣ ስለአገር ፍቅር፣ ወዘተ ክብር የሌላቸው ራስ ወዳዶችና በቡድንተኝነት ናላቸው የዞረ ይህንን የተቀደሰ ሐሳብ ያደናቅፋሉ፡፡ ለእነሱ አገር ማለት ምንም አይደለም፡፡ ሕዝብ ማለት ምንም አይደለም፡፡ ከእንዲህ ዓይነቶቹ ጋር ሁሉ ታግሎ አሸናፊ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ተግባር ይቅደም፡፡

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱት ሁከቶችና አመፆች ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕይወት ጠፍቷል፡፡ ከፍተኛ የሆነ የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ንብረት ወድሟል፡፡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ተስተጓጉሏል፡፡ ትምህርት ቆሟል፡፡ የእርሻና የንግድ ሥራዎች ቆመዋል፡፡ ከፍተኛ የሆነ የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሷል፡፡ ሰላማዊው ድባብ ወደ አለመረጋጋት ተቀይሯል፡፡ ብዙዎች ለከፍተኛ ሐዘንና የልብ ስብራት ተዳርገዋል፡፡ ሕዝብ በሰላማዊ መንገድ መንግሥትን ወጥሮ ጥያቄ የሚያቀርብበት ሥነ ምኅዳር በመበላሸቱ ምክንያት፣ ሰላማዊ ጥያቄዎች ወደ ብጥብጥ ተቀይረው ደም ፈሷል፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን የሕዝብ ጥያቄን ለመፍታት ባለመቻሉ ምክንያት የደረሰው ሰቆቃ ያሳዝናል፡፡ ካሁን በኋላ እንዲህ ዓይነት አሳዛኝ መከራ እንዳያጋጥም ከተፈለገ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፅንኦት ያቀረቡት ሐሳብ በሁሉም ወገን ይደመጥ፡፡ ይደገፍ፡፡ በተግባር ይተርጎም፡፡ መንግሥት ለሕዝቡ ከመንገር በላይ በተግባር ያሳይ፡፡ የሕዝቡን ቀልብ የሳበው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በተግባር ካልተደገፈ ግን ፍሬ አልባ ይሆናል!      

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...

የመጀመርያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላው እንደገና ሊከናወን መሆኑ ተሰማ

እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ዕድሳቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...