- ‹‹ከትግራይ እስከ ደቡብ ጫፍ ሕዝቡ ተመሳሳይ ቅራኔ ፈጥሯል
- በአንዳንድ አካባቢ በእጁ ዞር በሉ ብሎናል
- ችግሩን በመፍታት ከሕዝቡ መታረቅ አለብን››
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ
በግንቦት ወር 2007 ዓ.ም. በተካሄደው አምስተኛ ጠቅላላ ምርጫ መቶ በመቶ ያሸነፈው ኢሕአዴግ በመስከረም ወር 2008 ዓ.ም. የመሠረተው መንግሥት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ በአገሪቱ በርካታ ሥፍራዎች የተከሰቱ ግጭቶችንና ተቃውሞዎችን በመዳሰስ በዋናነት ራሱንና ገዥውን ፓርቲ ተጠያቂ አድርጓል፡፡
ኢሕአዴግና አጋሮቹ በግንቦቱ ምርጫ መቶ በመቶ ከማሸነፋቸው ውጪ ድምፅ ከሰጠው መራጭ ሕዝብ 90 በመቶውን ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡
ይህንኑ ተከትሎ በ2008 ዓ.ም. መስከረም ወር መጨረሻ ላይ የተሰበሰበው ፓርላማ የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትርና ካቢኔያቸውን በመሰየም፣ መንግሥት መመሥረቱ ይታወሳል፡፡
በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የራሳቸውን የምርጫ ዘመን አንድ ብለው ጀምረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የሥልጣን ዘመናቸው የመጀመሪያ መንፈቅ አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ አገሪቱ ላለፉት 50 ዓመታት አይታው በማታውቀው ድርቅ ምክንያት ችግር ውስጥ የገቡ ከአሥር ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያንን መታደግ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በኦሮሚያ በርካታ አካባቢዎች ከአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ የተቀናጀ ማስተር ፕላንን በመቃወም የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ፣ በአማራ ክልል የቅማንት ማኅበረሰብ የማንነት ጥያቄ ተከትሎ የተቀሰቀሰ በጦር መሣሪያ የታጀበ ግጭት፣ በኦሮሚያ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ለመመለስ የክልሉ መንግሥትና ፓርቲ የጋራ ማስተር ፕላኑ እንዲታጠፍ መደረጉን ቢገልጹም፣ ተቃውሞው መልኩን ቀይሮ በሌሎች አካባቢዎች የመቀጠል አዝማሚያ አሳይቷል፡፡
መንግሥት ባያረጋግጥም በኦሮሚያ ከሁለት መቶ በላይ ዜጐች ሕይወታቸውን ሲያጡ በርካታ የመንግሥትና የባለሀብቶች ንብረት መውደሙ፣ በጋምቤላ ክልል በሁለት ግለሰቦች ግጭት የተነሳ የብሔረሰቦች ግጭት መቀስቀሱና በዚህ ግጭት ውስጥም የክልሉ የፀጥታ ኃይል መሳተፍና ሌላው የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት ጉልህ ፈተናዎች የሚባሉት ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ2008 ዓ.ም. በጀት ዓመት የስድስት ወራት ወይም የአምስት ዓመት የሥልጣን ዘመናቸው የመጀመሪያ መንፈቅ ሪፖርትን ባለፈው ሐሙስ መጋቢት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ባቀረቡበት ወቅትም፣ መንግሥታቸው የገጠመውን ፈተና ግልጽ አድርገው አስቀምጠዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ አካባቢዎች ለተከሰቱ ግጭቶችና ተቃውሞዎች ተጠያቂ መሆን ያለበት፣ የሚመሩት መንግሥትና የሚመሩት ፓርቲ ኢሕአዴግ ከነአጋር ፓርቲዎቹ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
‹‹ሌላ አካል ላይ ጣት ከመቀሰር ይልቅ ችግሩ የራሳችን እንደሆነ አስምረን መሄድ አለብን፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ላለፉት 12 ዓመታት የአገሪቱ አርሶ አደሮችና የከተማ ነዋሪዎች ይህ አገር ተስፋ ያለው እንደሆነ አምነው መንቀሳቀሳቸውን ጠቁመዋል፡፡
‹‹በእኛ ውስጥ ባለ መበላሸት ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ የሕዝቡን ጥያቄዎች ፈጥኖ ምላሽ ባለመስጠት፣ ከሕዝቡ ጋር ቅራኔ ውስጥ እየገባን መጥተናል፤›› ብለዋል፡፡
ኦሮሚያ ውስጥ ግጭት ስላለ ቅራኔው ኦሮሚያ ውስጥ ብቻ ነው ማለት እንደማይቻል የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ከትግራይ አንስቶ እስከ ደቡብ ጫፍ ድረስ ይኸው ችግር ያውና ተመሳሳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡
በማከልም፣ ‹‹ስለዚህ ግጭቱ ባልተፈጠረበት አካባቢ ችግሩን ቶሎ ፈተን ከሕዝቡ ጋር መታረቅ፣ ግጭት በተፈጠረበት አካባቢ ደግሞ ግጭቱን ቶሎ አብርደን በተመሳሳይ ከሕዝቡ ጋር መታረቅ አለብን፤›› ብለዋል፡፡
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተፈጠረው ቅራኔ መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ሊገነዘበው የሚገባ ነገር አርሶ አደሩም ሆነ የከተማው ነዋሪ የነቃ በመሆኑ፣ ‹‹በትከሻው ላይ ተጣብቀንበት›› መኖር አይቻልም ብለዋል፡፡
‹‹ችግሩ የራሳችን በመሆኑ ማስተካከል አለብን፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሌሎች ፀረ ሰላም ኃይሎች ሚና በዚህ ውስጥ የሚያስጨንቅ አይደለም ብለዋል፡፡
መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ያለባቸውን ችግር በመፍታት ሕዝቡን መምራት ከቻሉ ሌሎች አካላት መክሰማቸው አይቀርም ሲሉ አክለዋል፡፡
‹‹እነዚህ ፀረ ሰላም አካላት መፋፋት የቻሉት በእኛ ችግር ላይ እየተመገቡ ነው፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ዋናው ቁምነገር ችግሩ የመንግሥትና የፓርቲው መሆኑን ማመን ነው፡፡ ሌላ ምክንያት መፍጠር ማለት ግን፣ ቀዳሚው የውድቀት መንገድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ኢሕአዴግ ከዚህ የባሰ ፈተና ከ15 ዓመታት በፊት እንደገጠመው በመጠቆም ከፈተና መውጣት እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ከ12 ዓመታት በፊት የገጠመን ፈተና ፈቶ ትክክለኛ መፍትሔ በማስቀመጡ አገሪቱ ፈጣን ዕድገት ማስመዝገቧን፣ ሕዝቡም ይህንን ሲያጣጥም መቆየቱን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ይህ ጥቅም እንዲቀጥልለት ፍላጐት እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ሕዝቡ በሚሄደው ፍጥነት መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ሳይንቀሳቀስ ሲቀር ወይም ደንቃራ ሲሆን ‹‹ዞር በሉ ብሎ መግፋቱ›› አይቀርም ብለዋል፡፡
‹‹ዞር በሉ ሲል አንዳንዴ በአንደበቱ ይላል፣ አንዳንዴ በእጁ ይላል፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ አሁን በእጁ ነው ዞር በሉ ያለው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ችግሩን አውቀናል፣ መንገዱን አውቀናል፣ ይኼንን አጠናክሮ መቀጠል ነው፤›› ብለዋል፡፡
በአገሪቱ ከተነሱት ግጭቶች የተወሰኑት ከማንነት ጋር የተያያዘ መነሻ ምክንያት እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ በአማራ ክልል ለተነሳው ግጭት የቅማንት ማኅበረሰብ የማንነት ጥያቄ መነሻ ምክንያት ሲሆን፣ በትግራይ በአሁኑ ወቅት እየተደመጠ ያለ የወልቃይት ጥያቄ እንዲሁም በሶማሌ ክልል የሲቲ ዞን ራስን የማስተዳደር ጥያቄ ማሳያዎች ናቸው፡፡
ከማንነት ጥያቄ የሚመነጩ ግጭቶችን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹የማንነት ጥያቄ እንዴት የግጭት መንስዔ ሊሆን ይችላል?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹በእኛ እምነት የማንነት ጥያቄ ከጅምሩ ያለቀ ነው፡፡ አንዳንድ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችን በየዓመቱ ስንሠራ መጥተናል፤›› ብለዋል፡፡
በመሆኑም አሁን መደረግ ያለበት ነገር ቢኖር የማንነት ጥያቄ ኢትዮጵያ ውስጥ ተመልሶ አልቋል የሚል ምላሽ መስጠት እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
የቅማንት ጥያቄ መመለሱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከዚህ በኋላ ከቅማንት ጋር ተያይዞ የሚነሳ የማንነት ጥያቄ ሳይሆን ሌላ ነው የሚሆነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በመጀመሪያ ዓመት የሥልጣን ዘመናቸው መንግሥታቸው አጋማሽ የገጠመው ሌላው ፈተና በአገሪቱ የተከሰተው ድርቅ ነው፡፡
በድርቁ ምክንያት በዘር የተሸፈነው መሬት ዝቅተኛ መሆኑን፣ በተወሰኑ አካባቢዎች የተዘራው ዘር እርጥበት ባለማግኘቱ አለመብቀሉ፣ የበቀለውም የመጠውለግና የመድረቅ ሁኔታ እንደታየበት ገልጸዋል፡፡
በዚህም ምክንያት የተጐጂዎች ቁጥር መበርከት፣ እንዲሁም የእንስሳት መኖና የውኃ እጥረት ከፍተኛ ፈተና እንደነበር ገልጸዋል፡፡
የእንስሳት ሞትና የአርብቶ አደሩ ውኃና ግጦሽ ፍለጋ ከቀየው እንዲፈናቀል ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ድርቁ ያደረሰውን አገራዊ ጫና በመቋቋም ደረጃ የፌዴራል መንግሥት የመሪነት ሚና በመውሰድ፣ እስከ የካቲት ወር ድረስ ስምንት ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉንም ጠቅሰዋል፡፡
የድርቁን አደጋ መሻገር እስኪቻል ድረስ በፌዴራልና በክልል መዋቅሮች የተቋቋሙ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚቴዎች ተናበው መሥራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡ በአጠቃላይ ድርቅና ሌሎች ምክንያቶች የአገሪቱ ኢኮኖሚ በታቀደው መሠረት በ11 በመቶ እንዳያድግ ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡