Wednesday, October 4, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

እንደማመጥ!

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ውስጥ ትልቁ ችግር አለመደማመጥ ነው፡፡ ባለመደማመጥ ምክንያት የደረሱት ችግሮች ምን ያህል ከባድ እንደሆኑም ይታወቃል፡፡ የፖለቲካው የጥበብ መጀመርያ መደማመጥ መሆን ሲገባው፣ መደማመጥ ባለመኖሩ ብቻ አገሪቱና ሕዝብ በርካታ መከራዎችን ዓይተዋል፡፡ የመጠማመድና የመጠላላት አዙሪት በመብዛቱም ኢትዮጵያዊያን ለሞት፣ ለእስራት፣ ለሥቃይና ለስደት ተዳርገዋል፡፡ ፖለቲካው ሁሌም ደም ስለሚሸተው ሰከን ብሎ ለመነጋገር ዕድል ሳይሰጥ ቆይቷል፡፡ አሁን ግን ከእዚህ ዓይነቱ የቂምና የመመራረዝ በሽታ እንላቀቅ እየተባለ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. በፓርላማ በሰጡት ማብራሪያ፣ አንዱ አፅንኦት የሰጡበት ጉዳይ የጥላቻና የቂም በቀል አስተሳሰብ መወገድ እንደሚገባው ነው፡፡ በይቅር ባይነት መንፈስ ውስጥ ሆኖ ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረገ የፖለቲካ ምኅዳር መኖር እንዳለበት አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ አንዱ ሌላውን ገድሎ ሥልጣን ላይ መውጣት፣ አንዱ ሌላውን እያሰቃየ ሥልጣን ላይ መቆየት እንደሌለበትም አሳስበዋል፡፡ ይህ እውነት ከቤተሰብ እስከ መንግሥት ሥልጣን ድረስ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ከእልህና ከቂም በቀል ትርክት ውስጥ በመውጣት ሐሳብን በነፃነት እያንሸራሸሩ መደማመጥ የሥልጣኔ ምልክት ነው፡፡ እየተናቆሩ መኖር ግን ኋላቀርነት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ፋሽኑ አልፎበታል፡፡

ዘወትር እንደምንለው አስተዋዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ የመነጋገር ባህሉ ጥልቅና ሰፊ ነው፡፡ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ አገር ባለ ጉዳይ በመሰለው መነገድ ይነጋገራል፡፡ ብሔር፣ ሃይማኖት፣ እምነት ወይም ሌላ ልዩነት ሳይገድበው እየተነጋገረና እየተደማመጠ ዘመናትን አብሮ ዘልቋል፡፡ አሁንም ቢሆን ሕዝቡ ውስጥ ሰላም፣ ፍቅርና አብሮነት በስፋት አሉ፡፡ ለመነጋገርም ሆነ ለመደማመጥ ምንም ዓይነት እንቅፋት የለም፡፡ ነገር ግን በሕዝብ ስም የሚነግዱ ፖለቲከኛ ነን ባዮች በሚፈጥሩት ግርግር የንፁኃን ደም ይፈሳል፣ የአገር አንጡራ ሀብት ይወድማል፡፡ አገርንና ሕዝብን ሳይሆን የራሳቸውንና የቡድናቸውን ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ በሚሯሯጡ እኩዮች ምክንያት ሰላም ይደፈርሳል፡፡ በሴራ ፖለቲካ የተካኑ፣ ነገር ግን ለአገርና ለሕዝብ ደንታ የሌላቸው ከንቱዎች ሊበቃቸው ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአገሩ የበለጠ የሚያስቀድመው አንዳችም ነገር የለም፡፡ ይኼንን የተከበረና አስተዋይ ሕዝብ ወደ ጎን እየገፉ መቀጠል እንደማይቻል ሊታወቅ ይገባል፡፡ በቀኝም ሆነ በግራ የተሠለፉ ኃይሎች በሙሉ ከኪሳራ ፖለቲካ ራሳቸውን በማላቀቅ ለሕዝብ ፍላጎት ይገዙ፡፡

በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ፖለቲከኞች መጀመርያ ከግብታዊነትና ከስሜታዊነት መፅዳት አለባቸው፡፡ አርቆ ማሰብና ማመዛዘን የከዳው ግንፍልተኝነት ውስጥ ሆኖ መፎከር፣ ወይም በወቅታዊ ሁኔታዎች በመነዳት የቂም በቀል ሒሳብ ለማወራረድ መሞከር፣ የለውጡን ግስጋሴ ከመጉዳት በስተቀር ፋይዳ እንደሌለው መረዳት ይገባቸዋል፡፡ ፖለቲካ የብልሆች መሣሪያ እንጂ የዋሆች ወይም ተላሎች የሚሰማሩበት መስክ አይደለም፡፡ ተፎካካሪን አጥፍቶ ራስን ብቻ ለማንገሥ ይደረግ የነበረው አካሄድ ፉርሽ እንደሆነው ሁሉ፣ እከሌን ዓይኑን አያሳየኝ ብሎ የፉከራ ሐተታ ማሰማት ለዘመኑ አይመጥንም፡፡ ትናንት ተገፍተናል የሚሉ ወገኖች በብዛት አሉ፡፡ የትናንቱን መገፋት በሥልጣኔ መንገድ ትክክል አለመሆኑን ለማሳየት ሲቻል፣ የቂም በትር ይዞ መነሳት በራሱ ከትናንቱ አለመሻል ነው፡፡ ‹‹የጥላቻና የቂም በቀል አስተሳሰብ ይሰረዝ›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕዝብ ከልብ የመነጨ ድጋፉን የገለጸው፣ የእልህና የአጉል ፉክክር ፖለቲካ ለኢትዮጵያ እንደማይጠቅማት በሚገባ ስለሚገነዘብ ነው፡፡ ከአንዳንድ ጮርቃ ፖለቲከኞች የሚሰማው አጉል ድንፋታም መስከን አለበት የሚባለው ሕዝብ ስለማይቀበለው ነው፡፡ ለፖለቲከኛ ደግሞ ሕዝብን መምሰል የመሰለ ነገር የለም፡፡ ሕዝብን ማዳመጥ ይበጃል፡፡

‹‹ብልሆች ከሌሎች ስህተት ይማራሉ፣ ሞኞች ግን ከራሳቸውም አይማሩም›› የሚባል አባባል አለ፡፡ ትናንት የተሄደበት መንገድ ኢትዮጵያና ሕዝቧን የት እንዳደረሰ ታይቷል፡፡ ይኼንን የሰለቸና የጠነዛ ነገር ትቶ በዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ለመመራት፣ የሐሳብ ነፃነትን ማክበር ተገቢ ነው፡፡ የሐሳብ ነፃነትን ማክበር ያለበት መንግሥት ብቻ አይደለም፡፡ ከግለሰብ ጀምሮ በየትኛውም የሥራ መስክ ሆነ ኃላፊነት ላይ ያሉትን በሙሉ ይመለከታል፡፡ በተለይ በፖለቲካው ጎራ ውስጥ ያሉ ወገኖች ተቃራኒን አምርረው ከመጥላት አልፈው፣ መሀል ሰፋሪን እንደ ጠላት የሚያዩበት ነውር መታረም አለበት፡፡ ጠላት ሲያፈላልጉ የሚውሉ የሚመስሉ ፖለቲከኞች፣ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ሚዲያ ድረስ በመፈረጅ አገሪቱን ያኮማትራሉ፡፡ በአንድ በኩል መንግሥት የሚባለው ተቋም ያደረሰው ጥፋት አልበቃ ብሎ፣ እነሱ ሲያክሉበት ደግሞ የበለጠ ይጎመዝዛል፡፡ ትናንት ታስሮ ሥቃይ የደረሰበት ወገን ሳይቀር እንዲህ ዓይነቱ ፍረጃ ሲደርስበት ያሳፍራል፡፡ ይህ ዓይነቱ አስፈሪና ኋላቀር ድርጊት ከኢትዮጵያ ምድር መሰረዝ አለበት፡፡ ለማንም አይጠቅምም፡፡ የሚበጀው መደማመጥ ብቻ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለሁሉም ልጆቿ የሚበቃ የተፈጥሮ ሀብት ያላት አገር ናት፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን ልጆቿ አሁንም ይሰደዳሉ፡፡ በፖለቲካ ምክንያት ሳይወዱ በግድ ተሰደው በባዕድ አገር የሚኖሩ ልጆቿን፣ አስተማማኝ ዋስትና ሰጥቶ ወደ አገር ቤት መመለስ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ በድህነትና በተስፋ መቁረጥ ወደ ዓረብ አገሮች የሚሰደዱትን መታደግም እንዲሁ፡፡ የአገሪቱ ፖለቲካ ምኅዳር እንዲሰፋና ዜጎችም ከልማቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚ የሚሆኑበት አዲስ ተስፋ ሲሰማ፣ ይህ ተስፋ የበለጠ እንዲጎመራና ኢትዮጵያዊያን ከዳር እስከ ዳር ለጋራ ጉዳይ እንዲሠለፉ በአንድነት መነሳት የሁሉም ወገኖች ድርሻ መሆን አለበት፡፡ አንድ እንሁን ሲባል የሚያፈነግጥ፣ የአገር ሀብት አትዘርፍም ሲባል አፍንጫውን የሚነፋ፣ በሕዝብ ስም አትነግድ ሲባል ሕዝብ ውስጥ ትርምስ የሚፈጥር፣ ወዘተ ለኢትዮጵያ አይጠቅማትም፡፡ የክልሎችን አስተዳደራዊ ወሰን ምክንያት እያደረጉ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩና የብሔር ልዩነትን እያጦዙ የአገር ህልውናን የሚያናጉም ተቀባይነት የላቸውም፡፡ ከዚህ በፊት የደረሱትን ጥፋቶች ብቻ እያራገበ ትውልድን ዕዳ ከፋይ የማድረግ ኋላቀር አስተሳሰብም ፋይዳ የለውም፡፡ አሁን ትልቁ የሚፈለገው ጉዳይ ኢትዮጵያዊያንን በአንድነት የሚያቆም የጋራ ብሔራዊ አጀንዳ ነው፡፡ ልዩነትን አክብሮ ለአገር የጋራ ጉዳይ ተቀምጦ መነጋገርና መደማመጥ ባህል ይሁን፡፡

ኢትዮጵያዊያን የሚያምርባቸው በአንድነት፣ በፍቅርና በመተሳሰብ መኖር ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ኢትዮጵያዊያን አንድ ሆነው ሲቆሙ ይከበራሉ፣ እርስ በርስ ሲጣሉ ደግሞ ይናቃሉ፡፡ አንድ መሆን ማለት ልዩነት የለም ማለት አይደለም፡፡ ልዩነቱን ይዞ በመከባበር መንፈስ መነጋገር ሥልጣኔ ነው፡ ከዚህ ዓይነቱ ሥልጣኔ ሲራራቁ የሚከተለው ጉልበት ነው፡፡ ጉልበት ደግሞ ያስራል፣ ያሰቃያል፣ ያሰድዳል፣ ይገድላል፡፡ ዴሞክራሲ ሥርዓት ሆኖ መቆም የሚችለው መነጋገርና መደማመጥ በሚችል አገር ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ይህ ሲሳካ ደግሞ የሐሳብ ብዝኃነት ያለ ገደብ ይስተናገዳል፡፡ መራጩ ሕዝብ የፈለገውን ይወስዳል፣ የማይፈልገውን ይተዋል፡፡ ዴሞክራሲ የሐሳብ ገበያ ስለሆነ ለመነጋገገርና ለመደማመጥ ዕድል መሰጠት አለበት፡፡ ከእኔ በላይ ላሳር ማለት የኋላቀርነት መገለጫ ብቻ ሳይሆን፣ የሰውነት ባህሪን የሚያሳጣ አውሬነት ነው፡፡ የማናምንበት ሐሳብ እንኳን ቢሆን እየመረረንም ማዳመጥ ይኖርብናል፡፡ ተናጋሪዎችን በተናጠልና በጅምላ እየፈረጁ ማስደንበር ለዘመኑ አይመጥንም፡፡ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያው ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ ያላቸው ወገኖች ሐሳቦች ከሚደፈጠጡ ይልቅ፣ እየተደመጡ በሕዝብ የህሊና ፍርድ እንዲዳኙ ዕገዛ ቢያደርጉ ለአገር ይጠቅማል፡፡ ሐሳብ ሲገደብ ነው አገርና ሕዝብ ሥቃይ የሚገጥማቸው፡፡ ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያዊያን እንደማመጥ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የባለሥልጣናትና የባለሀብቶች ግንኙነት ሥርዓት ይኑረው!

በሕዝብ ድምፅ ሥልጣን የያዘ ፓርቲ የሚመሠርተው መንግሥት ከምንም ነገር በፊት ለሕግና ለሥርዓት መከበር ኃላፊነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንን ኃላፊነት በሚገባ ሊወጣ የሚችለው ሥራውን በግልጽነትና በተጠያቂነት...

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...