Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹እምንለብሰውና እምንበላው አፈር ነው››

ዶ/ር ተክሉ ኤርኮሳ፣ የአፈር ሳይንቲስትና በጂአይዜድ የአፈርና ተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም አማካሪ

ዶ/ር ተክሉ ኤርኮሳ የአፈር ሳይንስ ተመራማሪ ናቸው፡፡ አስመራ ዩኒቨርሲቲ በአፈርና ውኃ እቅበት (ሶይል ኤንድ ዋተር ኮንሰርቬሽን) የመጀመርያ ዲግሪ፣ ወደ ሆላንድ አቅንተው ሸክንንገን ዩኒቨርሲቲ በአፈርና ውኃ አያያዝ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በጀርመን ስቱትጋርት ከሚገኘው ሆሄን አይም ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲና በኢንተርናሽናል ወተር ማኔጅመንት ተቋም በተመራማሪነት ሠርተዋል፡፡ ሶማሌላንድ ለሚገኘ አንድ ዩኒቨርሲቲ አማካሪ ሆነው ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የጂአይዜድ በአፈርና በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ዙሪያ አማካሪ ናቸው፡፡ በአፈርና ውኃ አጠቃቀም ዙሪያ ዶ/ር ተክሉን ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት የአፈር ዓይነት ምን ምን ናቸው?

ዶ/ር ተክሉ፡- እምንበላውና እምንለብሰው አፈር ነው፡፡ ከአጠቃላይ የተፈጥሮ ሀብት ሁሉ አፈር ለሰው ልጅ ትልቅ ሀብት ነው፡፡ ይህንን ሀብት ያወቁት በአግባቡ ሲጠቀሙበት፣ የማያውቁት ደግሞ እየተጠቀሙበት እየመሰላቸው ሲያበላሹትና ሲያጎሳቁሉት ይስተዋላል፡፡ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሩዝቬልት ‹‹አፈርን የሚያጎሳቁል ሕዝብ ራሱን እያጎሳቆለ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለው ይኼው ነው፡፡ ወይም የምናየው ይኼንኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ጠቃሚ የሆኑ ብዙ ዓይነት የተለያዩ አፈር ዓይነቶች አሉ፡፡ በዓለም ውስጥ ያለው የአፈር ዓይነት በአብዛኛው ኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛል፡፡ ይህም ፀጋ ነው፡፡ አንድ ዓይነት የአፈር፣ የአየር ንብረትና ሜዳማ መሬት ያላቸው አንድ ዓይነት ሰብል ይዘራሉ፡፡ አንድ ዓይነት የአስተራረስ ዘዴ ይጠቀማሉ፡፡ የኢትዮጵያ ግን በቆላውና በወይና ደጋው፡፡ በደጋው እንዲሁም በተዳፋትነት በሜዳ፣ በስምጥ ሸለቆ ያለው አፈር የተለያዩ ባህሪ አላቸው፡፡ ለዚህም የየራሳቸው የሆነ አያያዝና የአጠቃቀም ዘዴ ይፈልጋሉ፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ያስፈልጋል፡፡ በእነዚህም ዕጦት የተነሳ ፀጋውን አላየነውም፡፡ ምን ልንጠቀም እንደምንችልም አናውቀውም፡፡

ሪፖርተር፡- ወንዝና ምንጭ ከአፈር ጋር ያላቸው ቁርኝት ምን ይመስላል?

ዶ/ር ተክሉ፡- ወንዝም ሆነ ምንጭ ያለ አፈር አይታሰቡም፡፡፡ ዝናብ ቢዘንብም አፈር ከሌለ ጎርፍ ይሆናል፡፡ አፈር ካለ ግን የሚጠጣውን የዝናብ ወኃ ከሥሩ ቀስ እያለ አጠራቅሞና አፅድቶ ሲለቀው ምንጭ ይሆናል፡፡ ምንጮች ሲገናኙ ደግሞ ወንዝ ይሆናሉ፡፡ ምንጮች ብዙውን ጊዜ የሚገኙት ከተራራ ሥር ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ተራራዎች ብዙ ጊዜ ሰው አይደርስባቸውም ወይም ከሰው ንኪኪ ነፃ ናቸው፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ደን አላቸው፡፡ ደኑም አፈሩን ይጠብቃል፡፡ በዚህም ውኃው ተራራ ውስጥ ይቆይና ቀስ እያለ ከተራራው ሥር ይመነጭና ወንዝ ይሆናል፡፡ አሁን ግን ተራራዎች እየተመነጠረ ነው፡፡ ደንና አፈር የላቸውም፡፡ ይህ ምንጭም ሆነ ወንዝ እንድናጣ ያደርገናል፡፡ አፈርና ውኃ ከሌለ ደግሞ የሕይወት መኖር አጠራጣሪ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ለእርሻ ተስማሚ የሆነው የትኛው ዓይነት አፈር ነው?

ዶ/ር ተክሉ፡- አርሶ አደሩ የአፈሩን ባህርይ በልምድ ለማወቅ ይሞክራል፡፡ ይህም ሆኖ ግን በልምድና በሳይንስ የሚታወቀው አንድ ዓይነት አይደለም፡፡ አፈር ውስጥ ያለው የሳይንስ ዓይነቶች ብዙ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት የአፈር ኬሚስትሪ፣ ፊዚክስ፣ ባዮሎጂ፣ ባዮኬሚስትሪ፣ ኢንጂነሪንግ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ይህን ሁሉ አንድ ላይ አምጥቶ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ አያያዝና አጠቃቀም ሊኖር ግድ ይላል፡፡ አጠቃቀሙም ሕጋዊና ተቋማዊ መሆን አለበት፡፡ ለእርሻ የሚሆነው ጥቁር ወይም የኮትቻ አፈር ነው፡፡ ምክንያቱም ውኃ ሲያገኝ ያብጣል፡፡ ሲደርቅ ደግሞ ይሟሽሻል፡፡ የዚህ ዓይነቱ አፈር ላይ ሕንፃ ግንባታ ሳይሆን ለእርሻ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ሕንፃ ለመገንባት ከተፈለገ መሠረቱን ለመትከል ወይም ለማውጣት ቢያንስ አሥር ሜትር መቆፈር አለበት፡፡ ከዚህ አኳያ ለግንባታ እንደማይጠቅም ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ለእርሻ ግን ምርጥ አፈር ነው፡፡ ማዳበሪያ ሳይሰጠው ለረዥም ዘመን ያለማቋረጥ ለያበቅል ይችላል፡፡   

ሪፖርተር፡- ከአዲስ አበባ እስከ ቢሾፍቱ ጥቁር ወይም ኮትቻ አፈር ነው፡፡ በዚህ ዓይነት አፈር ላይ የሚታየው እርሻ ሳይሆን የሕንፃ ግንባታና ኢንዱስትሪ ዞን እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህንን እንዴት ያዩታል?

ዶ/ር ተክሉ፡- ከአዲስ አበባ እስከ ቦሾፍቱ ያለው አካባቢ ለጥ ያለ ሜዳ ከመሆኑም ባሻገር ኮትቻ ወይም ጥቁር አፈር ያለበት ነው፡፡ አካባቢው ለኢንዱስትሪና ለከተማ ሠፈራ እየሆነ ነው፡፡ አፈሩ ግን ለዚህ አይሆንም፡፡ ነገር ግን በግድ ለግንባታ እንዲውል እየተደረገ ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ በኩል ቀይ አፈር ያለባቸው አካባቢዎች አሉ፡፡ በዚህም አፈር ሸክላ ይሠራበታል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት አፈሩ ውኃ ሲያገኝ አያብጥም፡፡ ሲያጣም አይሟሽሽም፡፡ ስለዚህ በማቃጠል ሸክላ ይሠሩበታል፡፡ የመሬት አቀማጡ ወጣ ገባ ያለ ስለሆነ ለመኖሪያ ቤትና ለኢንዱስትሪ ግንባታ ወይም ከእርሻ ውጪ ለሆነ ለሌላ ነገር እንዲውል ቢደረግ መልካም ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- በአፈር ላይ ያተኮሩ ምርምሮች በኢትዮጵያ በምን ያህል መጠን ይሠራሉ?

ዶ/ር ተክሉ፡- አፈርን አስመልክቶ በዓለም ላይ የተሠሩ ጥናቶች እንዳሉ ሁሉ በኢትዮጵያም ተሠርቷል፡፡ ግን የተበጣጠሱ ናቸው፡፡ ይኼን መሰል ጥናት በተወሰነ ደረጃ እየሠሩ ያሉትም የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ ዩኒቨርሲቲዎችና በክልል የተቋቋሙ የምርምር ተቋማት ናቸው፡፡ ምርምሩ ግን በቂ አይደለም፡፡ ብዙዎቹ ምርምሮች የሚሠሩት ይኼ ሰብል በዚህ አፈር ላይ ምን ያህል ማዳበሪያ ይፈልጋል? ማዳበሪያ መቼና እንዴት ይጨመር? አፈሩ ቢሸረሸር ምን እናድርግ? የሚሉ ትንንሽ ነገሮች ላይ ነው፡፡ ዓለም እየሠራበት ያለው አሠራር ግን አፈሩን በጥልቀት አጥንቶ የአፈር ካርታ ማዘጋጀት ላይ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የአፈር ካርታን ምንነት ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ተክሉ፡- የዓለም የእርሻና ምግብ ድርጅት (ፋኦ) በ1980ዎቹ ያወጣው የኢትዮጵያ አፈር ካርታ አለ፡፡ ይህም ከአፍሪካ የአፈር ካርታ ተቆርጦ የወጣ ነው፡፡ ይህ ካርታ በጣም በግርድፉ የተሠራ ነው፡፡ አፈር ደግሞ በየአሥር ሜትሩ፣ በየአንድ ሜትር ወረድ ሲልም በየግማሽ ሜትር ልዩነት አለው፡፡፡ ልዩነቱን አቻችሎ አንድ ላይ ለመጠቀም ዝርዘር ካርታ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ዝርዝር ካርታ ከተዘጋጀ በኋላ የአፈር አጠቃቀም ካርታ መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ ይህ ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ማውጣት ግድ ይላል፡፡ ፖሊሲው አፈሩን ለምን ዓይነት ጥቅም እንደሚውል ያመላክታል፡፡ የፖሊሲው ማስፈጸሚያ መመርያም ይኖረዋል፡፡ ይኼን ዓይነቱን አጠቃቀም የጣሰ ሰው እንደሚቀጣ ፖሊሲው ያመለክታል፡፡ አንድ ኢንቬስተር የዱከምን መሬት የሸክላ ፋብሪካ አቋቁማለሁ ብሎ ቢጠይቅ ካርታው ታይቶ ነው የሚወሰነው፡፡ የዱከም አፈር ምርጥ የጤፍ መሬት ነው፡፡ ከሥሩ ደግሞ የከርሰ ምድር ውኃ አለ፡፡ ውኃውን ለመጠበቅ ከላይ ያለው ምርታማነቱ ደግሞ ለሌላ ነገር ከማዋል ይልቅ ለዚህ እርሻ ማዋል ጠቃሚ እንደሆነ ካርታው የሚናገር ከሆነ ሸክላ ፋብሪካ ማቋቋም እንደማይቻል ልንነግረው ይገባል፡፡     

ሪፖርተር፡- ተራራ አካባቢዎች ምን ያህል ለእርሻ የተመቹ ናቸው?

ዶ/ር ተክሉ፡- ተራሮች በደን ይሸፈናሉ፡፡ ተዳፋትነት ያላቸው ደግሞ በዛፍ ነው የሚሸፈኑት፡፡ ሜዳዎች ብዙ ጊዜ በሳር ነው የሚሸፈኑት፡፡ ስለዚህ እርሻ ተራራ ላይ መታረስ የለበትም፡፡ ሜዳ ላይ ነው መታረስ ያለበት፡፡ ሜዳ ላይ ሲታረስ ደግሞ ራሱን የቻለ አሠራር አለው፡፡ ለምሳሌ ያህል የአዳኣ ወረዳ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ሽምብራና ምስር አምራች ነው፡፡ በመሬት ጥበት የተነሳ ኤረር ጋራ ላይ ወጥቶ የተጠቀሱትን ወይም የለመደውን ሰብሎች ለማምረት ከተንቀሳቀሰ፣ ለአንድ ወይም ለሁለት ዓመት ሊገለገልበት ይችል ይሆናል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን አፈሩ ታጥቦ ድንጋይ ብቻ ይቀራል፡፡ ቀደም ሲል የነበረውም ደን አይኖርም፡፡ በድጋሚ ደን ለማልማትም ቢሞከር ትልቅ ስፋት ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ ተራራው ላይ ወጥቶ ማረስ ከፈለገ ከጤፍ ይልቅ ለተራራው ተስማሚ የሆነውን ቋሚ ሰብል ማልማት ነው ያለበት፡፡ እንዴ ከተከለ ከዚያ በኋላ ምርት መሰብስብ እንጂ ደጋግሞ ማረስ አይታሰብም፡፡

ሪፖርተር፡- የአፈርን ለምነት ለማጥናት ምን እየተደረገ ነው?

ዶ/ር ተክሉ፡- የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የሚባል ተቋም በቅርብ ተቋቁሟል፡፡ ኤጀንሲው የኢትዮጵያን አፈር ለምነት ላይ ያተኮረ ጥናት (ሶይል ፈርቲሊቲ ስተዲስ) ያካሂዳል፡፡ ለምነቱንም የሚያጠናው ምን ምን ንጥረ ነገሮን ይዟል የሚል ካርታ እያዘጋጀ ነው፡፡ እስካሁንም የተወሰኑ ካርታዎች ወጥተዋል፡፡ ጥናቱ በአፍሪካን ሶይል ኢንፎርሜሽን ሲስተም ሥር የሚገኝ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የመሬት አሲዳማነት መንስዔው ምንድነው ይላሉ? አሲዳማነት ድሮም ያለ ነው ወይስ ከጊዜ በኋላ የመጣ ነው?

ዶ/ር ተክሉ፡- አሲዳማነት ድሮም ነበር፣ አሁን ግን እየባሰበት የመጣው ነው፡፡ የአገሪቱ ምዕራብ ክፍል ማለትም ከደቡብ ኦሞ ጀምሮ እስከ ጎንደርና መተማ ድረስ አፈሩ አሲድ ሆኗል፡፡ በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ የሚገኙ ቦታዎች አብዛኛዎቹ አሲዳማነት ያጠቃቸው ናቸው፡፡ አፈሩ ወደ አሲድነት ሊለወጥ የቻለው ዋናውና አንደኛው ምክንያት ዝናብ ስለሚበዛ ነው፡፡ በእርግጥ ድንጋያማነት ወደ አሲድነት ሊያመራ እንደሚቻል መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ዝናቡ አሲዳማነትን የሚከላከሉ ንጥረ ነገሮችን ከአፈሩ ውስጥ አጥቦ አውጥቷል፡፡ ወይም በጎርፍ ጠርጎ ወስዷል፡፡ የታጠበው አፈር ደግሞ በሦስትና አራት ሜትር ከምድር በታች ዝቅ ብሎ ተከማችቷል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ቦታ ላይ እስከ ሦስት ወይም አራት ሜትር ድረስ ሥሩ የሚገባ ሰብል ማምረት ብቻ ነው አማራጩ፡፡

ሪፖርተር፡- የመስኖ ልማትን እንዴት ይገመግሙታል? የጠብታ መስኖ ተግባራዊነትንስ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ተክሉ፡- መስኖ ብዙ ዓይነት አሠራር አለው፡፡ አንዱና በአገራችን በስፋት ሥራ ላይ የዋለው የጎርፍ መስኖ (ፍለድ ኢሪጌሽን) ነው፡፡ ውኃው ዝም ብሎ ተለቆ ወደ ፈለገበት ቦታ ይሄዳል፡፡ ብዙ ጊዜ አርሶ አደሩ በአካፋ ወይም በገሶ ይመራዋል፡፡ አንዳንዴም ከደከመ ይተወዋል፡፡ ይኼ ዓይነት መስኖ በጣም አደገኛ ነው፡፡ አንደኛ ውኃው በጣም ይባክናል፡፡ ሰብሉ ምን ያህል ውኃ ይፈልጋል? አፈሩ ምን ያህል ውኃ ይይዛል? የሚለውም አይታይም፡፡ ሁለተኛ ጎርፍ ያስከትላል፡፡ ሦስተኛ ጨዋማነትን ያስከትላል፡፡ አፈሩ አንዴ ጨዋማ ከሆነ ጨውን መልሶ ማውጣት ከባድ ነው፡፡ እርግጥ የማጠቢያ መንገድ አለው፡፡ ግን እኛ የምንችለው አይደለም፡፡ አፈር ውስጥ ያለው የአየርና የውኃ መጠን ሚዛናዊ አልሆነም፡፡ ውኃ በዝቶ ሰብሉን ሊያፍነው ይችላል፡፡ ጥሩ አፈር የሚባለው 50 ከመቶ ያህሉ ውስጡ ክፍት ነው፣ የቀረው 50 በመቶ ደግሞ ደረቅ ነው፡፡ ክፍት የሆነውን አፈር ወደ 25 በመቶው ውኃ ቢሆን የቀረው 25 በመቶ ደግሞ አየር ቢሆን ለሰብሉ ይመቸዋል፡፡ ውኃ ከበዛበት ግን ሰብሉ ይታፈናል፡፡ አየርም ቦታ አይኖረውም፡፡ ትንሽ የተሻሻለው የመስኖ አጠቃቀም ዘዴ መሬቱን ሰንጥቆ ሰብሉን በመስመር መዝራትና ቦይ እንዲሠራለት አድርጎ በቦይ ማውጣት ነው፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ ግን ገና አልደረስንም፡፡ ወይም በመስኖ ተክሎ ወይም ዘርቶ በቦይ ማጠጣት ላይ ገና አልደረስንበትም፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ዓለም በቦይ ማጠጣቱን ትቶ መርጨትን እየተጠቀመ ነው፡፡ የጠብታ መስኖ ላይም ገና አልደረስንም፡፡ ይህም ሆኖ ግን በሙከራ ደረጃ በትንንሽ ቦታዎች ላይ ሲተገበር ይስተዋላል፡፡ በአጠቃላይ የጠብታ መስኖ በቅርቡ የሚሆን አይደለም፡፡ ምክንያቱም ጠብታ መስኖ የሚውለው በየጊዜው መታረስ ለማይፈልግ ሚ ሰብል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የተጠቀሱትን ችግሮች ለመፍታት ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

ዶ/ር ተክሉ፡- እስካሁን የአፈር ጉዳይ ባለቤት አልነበረውም፡፡ ባለቤት የሌለውን ደግሞ ማንም እንደፈለገው ያደርገዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ የአፈር ሀብት ተቋም (ኢትዮጵያን ሶይል ሪሶርስ ኢንስቲትዩት) ባለፈው ኅዳር በአዋጅ ተቋቁሟል፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን መሬት ላይ አልወረደም፡፡ ይህ ተቋም የተመሠረተው ከፍ ብሎ የተጠቀሰውን ጥናት ማካሄድ፣ በተቆራረጠ መልክ የሚከናወኑትን ሥራዎች አንድ ላይ ለማምጣት፣ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ለመሥራት ነው፡፡ ይህም ማለት ዩኒርሲቲዎች ብዙ ሥራ እንደሚሠሩ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በዩኒቨርሲቲዎች ላይ ያለው ዕውቀት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ አርሶ አደሩን የሚደግፉ ሰዎች ዕውቀቱ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ አሁን ያለንበት ዘመን የኮምፒውተር ዘመን እንደመሆኑ መጠን ለአርሶ አደሩ ማሳ ምንድነው የሚያስፈልገው የሚለውን በሞባይል ስልኩ ላይ እንዲያገኝ የሚደረግበት ጊዜ ላይ ደረሰናል፡፡ ለዚህም የሚያስፈልገውን ቴክኖሎጂ ለማቅረብ ከባድ አይደለም፡፡ ሳተላይት አለ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ብዙ መረጃ ከሳተይላት ነው የሚወርደው፡፡ የአፈር መረጃንም ጭምር ማለት ነው፡፡ አፈሩን እዚያው መርምሮ የጎደለውን እዚያው ማሳወቅ የሚችል ተንቀሳቃሽ ቤተ ሙከራ ሊኖር ይገባል፡፡ ተቋሙ ይህን ሁሉ ተግባር ያከናውናል፡፡  ምርምሮችንም ያስተባብራል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...