Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምአቅጣጫውን እየቀየረ ያለው የዓለም አመራር

አቅጣጫውን እየቀየረ ያለው የዓለም አመራር

ቀን:

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው አስቀድሞ ለረዥም ዓመታት ሲያራምዱት ከነበረው ‹‹ቅድሚያ ለአሜሪካ›› ከሚለው አቋማቸው ጋር በእኩል ሲያራምዱት የነበረው፣ አሜሪካ የዓለም ፖሊስነትን ማቆም አለባት የሚለው አቋማቸው ነው፡፡ ዶናልድ ትራምፕ በፕሬዚዳንትነት ከተመረጡ በኋላም ሲወስዷቸው የነበሩ የንግድና የደኅንነት ዕርምጃዎች ሙሉ በሙሉ በዚህ እሳቤ የተቃኙ ናቸው፡፡

ፕሬዚዳንቱ ለአሜሪካ ጥቅም የማይሰጡ ናቸው ካሏቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ያለምንም ማመንታት ሲወጡ፣ በኋላም በትዊተር ገጻቸው ይኼንን ዕርምጃቸውን ሲያውጁ ቆይተዋል፡፡ ከፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥና ከኢራን የኑክሌር ስምምነቶች መውጣት በተጨማሪ፣ በአጋር አገሮች ላይ የጣሉትን የገቢ ዕቃዎች ቀረጥ እንደ ማሳያ ማንሳት ይቻላል፡፡

ይኼንንም ተከትሎ አሜሪካ በዓለም ላይ የነበራት የመሪነት ሥፍራ ክፍተት በመፈጠሩ፣ ሌሎች አገሮች ይኼንን ክፍተት የመሙላት ኃላፊነት እንዲረከቡ ግድ ሆነባቸው፡፡ ይኼንንም ኃላፊነት ለመውሰድ የሚንቀሳቀሱት ከምዕራቡ ዓለም ጀርመን በጉልህነት ስትጠቀስ፣ ከምሥራቁ ደግሞ ቻይናንና ሩሲያን ያቀፈው ቡድን ይጠቀሳል፡፡ ጀርመን ነባራዊውን የዓለም አመራር ለማስቀጠል ጥረት ስታደርግ፣ በአሜሪካ ላይ ያላት እምነት እንደተሸረሸረና ያለ አሜሪካ ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ መግደርደር መቅረት አለበት ስትል፣ ቻይናና አጋሮቿ ደግሞ በዚያኛው ጥግ የራሳቸውን አዲስ የዓለም አመራር ቡድን በማቋቋምና በማጠናከር ተጠምደዋል፡፡

አቅጣጫውን እየቀየረ ያለው የዓለም አመራር

 

ከፓሪሱ ስምምነት በኋላ ዶናልድ ትራምፕ ከቡድን ሰባት አባል አገሮች ጋር በካናዳ ኩቤክ ያደረጉት ስብሰባ ውጤትና የእሳቸው የትዊተር መግለጫ፣ የቆየውን የዓለም አመራር ጥሰት የሚያሳይ እንደሆነ የሚናገሩ በርካቶች ናቸው፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በምንም ዓይነት ወዳጅነት ላይ የሚገኝ አገር ቢሆን እንኳን፣ ከአሜሪካ ጋር የሚደረገው የንግድና ሌላ ስምምነት አሜሪካን በማይጠቅም መንገድ ነው ካሉ፣ ስምምነቱን ከመሰረዝና ዕርምጃዎችን ከመውሰድ የማይመለሱ መሆናቸውንም ያሳዩበት ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ በአገሮቹ ላይ የጣሉትን የገቢ ዕቃ ቀረጥ በምንም ሁኔታ ሊያጥፉ ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው፣ ስብሰባው ሲካሄድባት የነበረችው ካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ የመንግሥታቸውን የመልስ ምት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሲንጋፖር ለማቅናት በወጡ በሰዓት ውስጥ ያስታውቃሉ፡፡ በዚህም የተበሳጩት ዶናልድ ትራምፕ የስብሰባውን መግለጫ እንደማይቀበሉና ያኖሩትን ፊርማም እንደሰረዙ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስታወቁ፡፡

ይህም በቡድን ሰባት አባል አገሮች መካከል እየተፈጠረ ያለውን ክፍተት የሚያሳይ እንደሆነ እየተጠቆመ ነው፡፡

የምዕራቡ ዓለም እየተከፋፈለ ባለበት በዚህ ወቅት ግን የምሥራቁ ዓለም እየጠነከረና ብቁ ተቋማትን እየገነባ የዓለም አመራርን ጉልህ ሥፍራን ለመያዝ የሚያስችሉትን ውጥኖች እያዘጋጀ ነው፡፡ ይኼንንም ግብ ለማሳካት ከተቋቋሙ ተቋማት አንዱ የሻንጋይ ትብብር ድርጅት ይባላል፡፡

በሩሲያና በቻይና ጠንሳሽነት በይፋ የዛሬ አሥር ዓመት የተቋቋመው ይህ የሻንጋይ የትብብር ድርጅት፣ የቡድን ሰባት አባል አገሮች በካናዳ ስብሰባ ባደረጉበት ሳምንት ስብሰባውን በቻይና ሻንጋይ ከተማ በድምቀት ሲያካሂድ ነበር፡፡

ይሁንና ከስብሰባዎቹ በኋላ የወጡት ፎቶዎችና የውይይቶቹ ውጤቶች የሚሳዩት በአሜሪካ የሚመራው የዓለም አስተዳደር እየተፍረከረከና ሌላ ጠንካራ የምሥራቁ ዓለም የዓለም አስተዳደር እያደገ እንደመጣ ማሳያ ናቸው ሲሉ ዕይታቸውን ያጋሩ ነበሩ፡፡

አቅጣጫውን እየቀየረ ያለው የዓለም አመራር

 

ይህ ስምንት አባል ድርጅቶች ያሉት የሻንጋይ የትብብር ድርጅት የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ይቀናቀናል የተባለለት ነው፡፡ በደኅንነት፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ነው፡፡ በዋናነት ሩሲያን፣ ቻይናን፣ ህንድን፣ ካዛኪስታንን ያቀፈ ሲሆን፣ በርካታ አገሮችንም በታዛቢነት የያዘ ነው፡፡

ይህ ድርጅት በተለይ በአባል አገሮቹ መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን፣ በየዓመቱ በሚቀያየሩ የአባል ድርጅቶቹ መሪዎች ሊቀመንበርነት የሚመራ ተቋም ነው፡፡ በዓመት አንዴ በወቅቱ ሊቀመንበር አገር ስብሰባውን ያደርጋል፡፡ በእነዚህ ስብሰባዎች ሚናዎቹን እያሳደገ የሚመጣ ድርጅት ሆኗል፡፡

በመጀመርያ አካባቢ በአገሮቹ መካከል ወዳጅነትን ለማጠንከር በማለት የተቋቋመው ድርጅት፣ አሁን ወደ ደኅንነትና ወደ ንግድ አድጎ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል፡፡ በተለይም ለሽብርተኝነት ዋነኛ የገቢ ምንጭ የሆነውን የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር በመከላከል ላይ በትኩረት ይሠራል ተብሏል፡፡

የአሜሪካ የግምጃ ቤት ሰነድን በመግዛት ቀዳሚ የሆነችውና 1.18 ትሪሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሰነድ የያዘችው ቻይና የምትመራው ድርጅት በመሆኑ፣ ሩሲያም የአሜሪካን የግምጃ ቤት ሰነድ በመግዛት 25ኛ ሥፍራ ያላት በመሆኗ በዚህ አቅማቸው አገሮቹ የዓለምን አመራር አቅጣጫ የማስቀየር ዕድል ሊኖራቸው ይችላል ይባልላቸዋል፡፡

የአሜሪካ ከኢራን የኑክሌር ስምምነት መውጣቷና የአውሮፓ አገሮች ከኢራን ጋር በሚያደርጉት የነዳጅ ግዥ ስምምነት ዶላርን እየተው መምጣታቸው፣ ይባስ ብሎም ሩሲያ ካላት የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሰነድ ግማሽ ያህሉን ዋጋ የሚይዘውን ሰነድ በመሸጧ አገሮች በሚያደርጉት የንግድ ልውውጥ ዶላርን ወደ ጎን እያሉት ነው፡፡ ይህም የተባለውን ለውጥ በዓመታት ውስጥ ካልሆነ ከአሠርት ዓመታት ባልዘለለ ጊዜ ውስጥ ሊያመጣ ይችላል የሚል መላምት እንዲሰጥ አድርጓል፡፡

ከዚህ በተቃራኒ የቻይና ፕሬዚዳንት ለዓለም አገሮች አንድነትና መቀራረብን ሲሰብኩ በሌላ ወገን ዶናልድ ትራምፕ ስለዓለም ምን አገባኝ እያሉ መሆናቸው፣ የሌላው አገር ፖለቲካ ውስጥ አልገባም ስትል የነበረችው ቻይና ወደ ዓለም አመራር ሥፍራ እንዴት እየመጣች እንዳለች ማሳያ አድርገውም የሚያቀርቡ አሉ፡፡

ግሎባል ታይምስ የተባለውና በቻይና የሚታተመው መጽሔት ርዕሰ አንቀጽ ሁከት ከበዛበት የቡድን ሰባት አባል አገሮች ስብሰባ ይልቅ፣ የሻንጋይ ትብብር ድርጅት ውጤታማና ትኩረት ሳቢ መሆን ችሏል ብሏል፡፡

በአሜሪካ ላይ የተመሠረተው አሃዳዊ የዓለም አመራር እንዳበቃለትና ብዝኃዊ የዓለም አስተዳደር እየመጣ እንዳለም ማሳያ ነው ይላል ይህ ርዕሰ አንቀጽ፡፡ አሃዳዊ ሥርዓት ከላዩ ሲታይ ጠንካራ ቢመስልም፣ በዕውን ቀጣይነት የሌለው ነው ሲል ይደመድማል፡፡

በማዕከላዊነት በአገር መሪዎች ምክር ቤት የሚመራው የሻንጋይ ትብብር ድርጅት እንደ ህንድ ያሉ አገሮችን እያቀፈ መምጣቱም ጥንካሬ እንደሚሰጠው ይነገራል፡፡ የዚህ ድርጅት ጥንካሬም በዓለም ጉዳዮች ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ሌላ ጠንካራ ኃይልን ሊፈጥር ይችላል እየተባለም ነው፡፡

አቅጣጫውን እየቀየረ ያለው የዓለም አመራር

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...