Thursday, May 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርሁለቱ የኢሕአዴግ ውሳኔዎች

ሁለቱ የኢሕአዴግ ውሳኔዎች

ቀን:

በሰለሞን መለሰ

ከታሪካዊው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ የ17 ቀናት ስብሰባ ወዲህ አገራችን ኢትዮጵያ ዳግም ወደ ለውጥ ጎዳና የምትጓዝበት ጎዳና መጠረጉን፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳንሆን ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ሳይገባው አልቀረም፡፡ የምድራችንን የዕለት ተዕለት ልብ ምት የሚከታተሉትና በፍጥነትም ለታዳሚዎቻቸው በማቅረብ አቻ የማይገኝላቸው ታላላቆቹ የምድራችን የመገናኛ ብዙኃን ሳይቀሩ ትኩረት ከሚሰጧቸው ሰሞንኛ ክስተቶች ውስጥ፣ በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘው የፖለቲካ እንቅስቅሴ አንዱ መሆን ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

      ከቡድን ሰባት አገራት ትርምስና ከታላቁ የትራምፕና የኪም ስብሰባ ቀጥሎ ከቻይናው የሻንጋይ ትብብር አገሮች ስብሰባም በኋላ፣ ከላቲን አሜሪካ አገሮች የእሳተ ገሞራ ውጣ ውረድና ከትልቁ የዓለም ዋንጫ ዘገባዎች ጋር ተያይዞ፣ የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳትና “አዲሱ” የኢሕአዴግ መንግሥት እየወሰዳቸው የሚገኙት ዕርምጃዎች የእነዚህኑ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን ለማግኘት ከቻሉ፣ በእርግጥም ታላቅ የሚባል የለውጥ እንቅስቃሴ በአገራችን እየተካሄደ ለመሆኑ ምንም ጥረጣሬን ሊያሳድር አይገባም፡፡

- Advertisement -

      በዚህ መንገድ ዓለም አቀፋዊ ትኩረትን የሳበውን ወቅታዊው የአገራችን ሁኔታ በእኛ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ደግሞ ቀዳሚና አንገብጋቢ ጉዳያችን ቢሆን ማንንም ሊያስደንቅ አይገባውም፡፡ እንዲያውም እኔ የአገራችን መገናኛ ብዙኃን (በተለይ ሬዲዮዎች ቴሌቪዥኖች) ከዕለት ተዕለት የዜና ዘገባ ብዙም ያልዘለለ ትኩረት እንደሰጡት ነው የሚሰማኝ፡፡ በተለይም ያለፉት ሁለት ሳምንታት ታላላቅ ክስተቶች መደበኛ ፕሮግራሞች ታጥፈውም ቢሆን እጅግ ጥልቅና ተከታታይ ውይይትን ሊያስተናግዱ የሚችሉበትን አጋጣሚ ቢፈጥርም፣ ከአገር ውስጥ የኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት ይልቅ፣ የሻይና የቡና ጨዋታ ወደመሆን ያዘነበለ ይመስላል፡፡ በውጭ አገሮች የሚገኙ የኢትዮጵያውያን የቴሌቪዥንና የድረ ገጽ ሚዲያዎች ግን በአገር ውስጥ ካሉት አቻዎቻቸው የተሻለ ትኩረት ሲሰጡት ይታያል፡፡ ምናልባትም ይህንን የለውጥ እንቅስቃሴ እዚህ ለማድረስ ከማኅበራዊ ሚዲያው ባልተናነሰ የወሰዱትን ኃላፊነት ከግብ ለማድረስ ተግተው መሥራታቸው ሊሆን ይችላል፡፡

      በዚህ ጽሑፍ ትኩረት ልሰጣቸው የፈለግኳቸው ጉዳዮችም፣ ከዚሁ ያሳለፍነው ሳምንት ታላላቅ የአገራችን ክስተቶች መካከል አንዱን መሠረት በማድረግ ይሆናል፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቅርቡ ያሳለፋቸው ሁለት ታላላቅ ውሳኔዎች (እጅግ ታላላቅ ከመሆናቸውም በላይ የዚህችን አገር ታሪክ ሊቀይሩ እንደሚችሉ እገምታለሁ) ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከአገር ውስጥ እስከ ዳያስፖራ፣ ከምሁራን እስከ ነጋዴዎች፣ ወዘተ ባሉት ኢትዮጵያውያን ዘንድ ዳግም የመነጋገሪያ አጀንዳ መክፈቱ የሚጠበቅ ነው ሆኗልም፡፡ እነዚህ ሁለት ውሳኔዎች በአልጀርሱ የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪዎች ስምምነት መሠረት የተቋቋመው ዘ ሔግ ፍርድ ቤት የወሰነውን ይግባኝ የሌለውን የፍርድ ውሳኔ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መቀበልና (ቀደም ሲል ኤርትራ ውሳኔውን ሙሉ በሙሉ ስትቀበል ኢትዮጵያ ግን “በመሠረተ ሐሳቡ” ተስማምታ ነገር ግን ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጧ ምክንያት ትልቅ የውዝግብ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል) መንግሥት ባለፉት ዓመታት ከመሬት ቀጥሎ የህልውናው መሠረት አድርጓቸው የሰነበተውን የንግድ ተቋማት ድርሻ ወደ ግል ለማዘዋወር የወሰነባቸው ናቸው፡፡ እንደ ሚጠበቀውም በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ የሆነ የውይይት አጀንዳ ሆነው እስከ ዛሬም ድረስ ቀጥለዋል፡፡

      ሁለቱንም የኢሐዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔዎች በከፍተኛ ደረጃ ትኩረትን እንዲስቡ ካደረጋቸው ምክንያቶች ውስጥ አንደኛው ድንገተኛነታቸው ነው፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በዓለ ሲመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰበሰበው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ይነጋገርባቸዋል ተብለው ቀድመው የወጡት አጀንዳዎችና የጊዜ ገደቡም (ስብሰባው በሁለት ቀናት ይጠናቀቃል መባሉን ስሰማ በበኩሌ እስከ አሥር ቀን ድረስ ሊራዘም እንደሚችል ከቀደሙት ልምዶች በመነሳት ግምት ወስጄ ነበር ጭምር ባልተጠበቀ ሁኔታ መለዋወጣቸው፣ የአራዳ ልጆች እንደሚሉት ‘ሰርፕራይዝ’ አድርጎናል፡፡ ውሳኔዎቹን ያገዘፋቸው ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ አሁንም ፈጽሞ ያልተጠበቁ የኢሕአዴግ የአቋም የመስመር ለውጦች በመሆናቸው ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከአብዮታዊው ዴሞክራሲ መስመሩ ወደ ልማታዊ መንግሥትነት ለመሸጋገር ከወሰደበት ጊዜ እጅግ ባነሰ ፍጥነት፣ ለዚያውም ውስጠ ዴሞክራሲውን ለማረጋጋት በሚታትርበት በዚህ አስጨናቂ ሰዓት፣ እንዲህ በብርሃን ቅፅበት ወደ ‘ኒዮ ሊበራሊስትነት’ ይለወጣል ብሎ ማንም የጠበቀ አልነበረም፡፡  

      አሁንም ቢሆን በትክክል የዚህ ሐሳብ ጠንሳሽ ጎልቶ ባለመውጣቱ የሁለቱንም ውሳኔዎች መድረሻ ለማወቅ አስቸጋሪ ቢያደርገውም፣ የመንግሥቱን ሥልጣን በያዘው የገዥው ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ ይሁንታን አግኝቷልና ሌላ ‘ሰርፕራይዝ’ ካልመጣ በስተቀር፣ የሚጠበቀው የአፈጻጸም መመርያ ወጥቶለት ወደ ሥራ መገባቱ ይመስለኛል፡፡ ቢቻል የውሳኔ ሐሳቡን አመንጪ ማወቁ በርካታ ጠቀሜታዎች ነበሩት፡፡ በዋነኛነት የውሳኔ ሐሳቡን ምክንያት (Motive) ለማወቅ እንድንረዳ ስለሚያስችለን ነው፡፡ በቀላሉ ለማብራራት እንበልና ከአራቱ የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች መካከል በሕወሓት የቀረበ ሐሳብ ከሆነ፣ በኤርትራ በኩል ያለውን ሰፊውን የትግራይ ወሰን ችግር ለመፍታት የፈለገበትን መንገድ በቀላሉ ለመረዳት ያስችለናል፡፡ ኢኮኖሚውን አስመልክቶም በማቆጥቆጥ ላይ ያሉት ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶችና ከፍተኛ የመዋዕለ ንዋይ ክምችት ያላቸው ግዙፍ ድርጅቶች ታላላቆቹን የአገሪቷን የኢኮኖሚ አውታሮች ሊረከቡ የተዘጋጁበትን መንገድ ያመላክተናል ብዬ አስባለሁ፡፡ በአንፃሩም የሐሳቡ አመንጪዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩና በዙሪያቸው ያሉት አጋሮቻቸው ከሆኑ ወቅታዊው የአገሪቷ የብድር ግሽበት፣ የበጀት ጉድለትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመንግሥቱ መረጋጋት ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ በመረዳት መውጫ ያሉትን አማራጭ በመፈለግ ላይ መሆናቸውን ለመረዳት ያስችለናል፡፡

      ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ሁላችንም ኢትዮጵያውያን በእነዚህ ሁለት ውሳኔዎች መደነቃችን እንዳለ ሆኖ፣ ሁለት የተለያዩ አቋማት መንፀባረቃቸው ግን በትክክል የሚጠበቅና ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ በግልጽ እንደ ሚታየው እየተሰሙ ያሉት ሁለቱ ድምፆች የድጋፍና የተቃውሞ ድምፆች ናቸው፡፡ እስካሁን ድረስ “ድምፀ ተዓቅቦ” ያደረገ ወይንም ‘ምን አገባኝ’ ያለ ግለሰብ አልገጠመኝም፡፡ ከሚሰሙት የተቃውሞ ድምፆችም ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት፣ የአልጀርሱን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የተቋቋመው የዘ ሔግ ፍርድ ቤት ውሳኔ መቀበላችንን ከአገር የሉዓላዊነት ጥያቄ አንስቶ፣ ውሳኔው በኤርትራ የሚገኘው የአቶ ኢሳያስን አስተዳደር አቋም የሚያስለውጥ ባለመሆኑ ምንም ፋይዳ እንደሌለው የሚቀርቡ ትንተናዎች ናቸው፡፡ በተጨማሪም የፍርድ ውሳኔው ሳይወዱ በግድ ዜግነታቸውን የሚያስለውጣቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችም የሚያቀርቡት የማንነት ጥያቄም ችላ የሚባል አይደለም የሚሉት ናቸው፡፡ እንዲያውም ለእኔ ይኼኛው ጥያቄ ከሌሎቹ በተሻለ ውኃ የሚያነሳ (ሌሎቹን አቋሞችን ማቃለሌ አይደለም) ሆኖ ይሰማኛል፡፡

      በኢሕአዴግ ምክር ቤት የፕራይቬታይዜሽን ውሳኔ ላይ የሚቀርቡት ተቃውሞዎች፣ ከተቃውሞነታቸው ይልቅ ሥጋትነታቸው ጎልቶ የወጣባቸው ይመስላሉ፡፡ መንግሥት ትልልቆቹን የንግድ ተቋማት በከፊል ወደ ግል ይዞታ ለመቀየር ያቀረባቸው የተለያዩ ምክንያቶች ያልተዋጡላቸውና እነዚህንም ዓላማዎች ከግብ ለማድረስ የፕራይቬታይዜሽኑ መፍትሔ እንደማይሆን የሚገልጹ ትንታኔዎችም ይሰማሉ፡፡  እነዚህም ሥጋቶች በቀላሉ ለባዕዳን የኢኮኖሚ ተፅዕኖ ሊያጋልጡን ይችላሉ ከሚል ቀና አስተሳሰብ የመነጩ ይመስላሉ፡፡ አንዳንዶቹም ተከራካሪዎች በትርፍ የሚያንበሸብሹንን የንግድ ተቋማት አንዴት ሲባል ለመሸጥ እናስባለን? በማለት ዕንቁላል የምትጥለውን ዶሮ ከማረድ ጋር በማመሳሰል ሊገልጹት ይሞክራሉ፡፡ ተደጋግሞ የሚሰማው ቅሬታ የኢትዮጵያ አየር መንገድን የኩራታችን ምንጭ አድርጎ ማቅረብና የቴሌንም ከፍተኛ አትራፊነትና ለመንግሥት ፈሰስ የሚያደርገውንም ከፍተኛ ገንዘብ መንግሥት እንዴት ችላ እንዳለው ያልገባቸው ዜጎች ንግግር ነው፡፡

      ከላይ ጠቅሼው እንዳለፍኩት ትክክለኛውን የእነዚህ ሐሳቦችን አመንጪ ምክንያቶች ብንደርስበት፣ የተሻለ ይሆን የነበረውን የመፍትሔ ሐሳብ ለማቅረብ ይረዳን የነበረ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ነገር ግን ሐሳቡ ከየትም ይምጣ ከየት በእርግጥ የዚህን ያህል የሥጋት ምንጭ ሊሆን ይችል እንደሆነ በበኩሌ ያለኝን ሐሳብ አቅርቤ ጽሑፌን ወደ ማጠቃለሉ እሄዳለሁ፡፡ እንደሚታወቀው የአልጀርሱ የሰላም ስምምነት ከ16 ዓመታት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀ በመሆኑ፣ ትልልቆቹን የመንግሥት ተቋማት ወደ ግል ለማዞር የሚያግድ ምንም ዓይነት የሕግ ክልከላ ባለመኖሩ፣ መንግሥት ሁለቱንም የፓርቲውን ውሳኔዎች ከመተግበር ሊያግዱት የሚችሉ ሕጋዊ መሰናክሎች የሉበትም፡፡ በዚህም መሠረት ከዛሬ ጀምሮ በማንኛውም ቀን የኢትዮ ቴሌኮምንም ሆነ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ከፊል ድርሻ ወደ ግል ለማዘዋወር የሚወጣ የጨረታ ማስታወቂያ መጠበቅ እንችላለን፡፡

      በኤርትራም በኩል ስላለው የድንበር ወሰን በሔግ የፍርድ ውሳኔ መሠረት ሁለቱም አገሮች ያለምንም ይግባኝ (ማንገራገር) ተስማምተው፣ በቀጣይ ግን እርስ በእርስ ግንኙነቶቻቸው ተወያይተው ሊያሻሽሉት እስካልፈቀዱ ድረስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተሰጠ ውሳኔ በመሆኑ፣ ባድመንም ሆነ ሌሎቹን የኤርትራን ግዛቶች ለማስረከብና የኢትዮጵያ ናቸው የተባሉትንም ቦታዎች ለመቀበል መዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡ በዚህ ሐሳብ ላይ በእጅጉ ካስገረሙኝ ጉዳዮች አንዱ የሕግ የበላይነትን ጠንቅቀው የሚያውቁ የሚባሉ ሰዎች ይህንን አግባብ ባለው ፍርድ ቤት የተወሰነን ውሳኔ ለመቀበል ሲቸገሩ ማየቴ ነው፡፡ በግልጽ የተወሰነንና ይግባኝ የሌለውን የፍርድ ውሳኔ ለመቀበል የሚቸግረውን ሰብዓዊ ፍጥረት እንዴት እውነታን ሊያስረዱት ይቻላል?

      አንዳንድ ወገኖች ገዥው ፓርቲም ሆነ መንግሥት በኢትዮጵያ የድንበር ጉዳይ ላይ የመወሰን መብት ስለሌለው ሕዝበ ውሳኔ መካሄድ አለበት ብለው ሐሳብ ሲያነሱ አስተውያለሁ፣ እውነታው ግን የድንበሩን ጉዳይ የወሰነው መንግሥት ወይም ገዥው ፓርቲ ሳይሆን ይግባኝ የማይጠየቅበት ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ይኼንን ውሳኔ ደግሞ ከመቀበል ውጪ ሌላ ምንም ዓይነት አማራጭ የለም፡፡ ጉዳዩን የኤርትራ መንግሥት ለጊዜው ችላ ቢለውም፣ ከ20 ወይም ከ50 ዓመታት በኋላም ቢሆን ባድመ የእኛ ናት የሚል ኤርትራዊ መንግሥት ወይንም ትውልድ ቢመጣ ምንም ዓይነት መከላከያ ማቅረብ አይቻልምና፡፡ ጉዳዩን በማያስፈልግ ሁኔታ ለሌላ ቀጣይ ትውልድ መናቆሪያነት ከማቆየት፣ በጊዜ አጀንዳውን ዘግቶ በሌሎች የጋራ ጥቅሞቻቸው ላይ የሁለቱ መንግሥታት መደራደር ብቸኛው አማራጭ ነው፡፡ ማን ያውቃል በድርድሩ ሁለቱም መንግሥታትና ቀድሞም አንድ የነበሩት ሕዝቦች የተሻለ ጥቅምን የሚያስገኙ ስምምነቶች ላይ ሊደርሱ ይችሉ ይሆናል፡፡

በድንበሩ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችን በተመለከተም ውሳኔው ግለሰቦቹን ብቻ የሚመለከት ነው የሚሆነው፡፡ ወደ ኤርትራ መጠቃለል እንፈልጋለን ካሉ ከእነ መሬታቸው ዜግነታቸውን ቀይረው ኤርትራውያን የሚሆኑ ሲሆን፣ የምንፈልገው በኢትዮጵያዊነታችን ፀንተን መቆየት ነው ካሉም የኢትዮጵያ መንግሥት የሚሠፍሩበትን ቦታ ሊያቀርብላቸው ይችላል፡፡ ከ27 ዓመታት በፊት ኤርትራ ነፃነቷን ስትቀዳጅም እኮ ይህንን ዓይነት ጉዳይ ተከስቷል፡፡ አገራችንን እንወዳለን ያሉ ኤርትራውያን ጓዛቸውን ጠቅልለው ሲሄዱ፣ ኢትዮጵያ ነች አገራችን ያሉት ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን መርጠው ዜግነታቸውን ይዘው ቀጥለዋል፡፡ ዛሬም ድረስ በመካከላችን ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ የጋራችን፣ ኤርትራ የግላችን ብለው ለነፃነታቸው ድምፅ ከሰጡ በኋላ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ተቀማጥለው ለመኖር ያሰቡት ብቻ ናቸው ‘እባብ የልቡን ዓይቶ. . . ’ የተባለው ተረት የደረሰባቸው፡፡

      ወደ ግል ይዞታነት ይቀየሩ ስለተባሉት መንግሥታዊ የንግድ ተቋማት በበኩሌ ያሉኝ ሁለት አስተያየቶች ናቸው፡፡ አንደኛው ውሳኔው ከመዘግየቱ በስተቀር ትክክለኛ መሆኑና መንግሥት ሊይዘው የሚገባው ድርሻም አነስተኛውን መጠን ሆኖ፣ እርሱም ድርጅቶቹ በማንኛውም ጊዜ ለመክሰር ቢቃረቡ (ቢከስሩ) መንግሥት ሊያደርግላቸው የሚችለውን ድጎማ (Bailout) መጠን ባያልፍ እላለሁ፡፡ የሚቻል ቢሆን እንደ ንግድ ባንክን የመሳሰሉትንም ድርጅቶች ጨምሮ ወደ ግል ይዞታ ካዘዋወረ በኋላ መንግሥት ‹ንግድ› ከሚባል ከጨዋታ ራሱን ሙሉ በሙሉ ቢያገል ተመራጭ ነው የሚሆነው፡፡ እነዚህ መንግሥታዊ ድርጅቶች ዛሬ አትራፊ መሆናቸውን ብቻ አይደለም መመልከት ያለብን፣ በየትኛውም አገርና በብዙ የንግድ ድርጅቶች ላይ ደርሶ እንዳየነው ነገ የመክሰር ዕጣ ፈንታ ሊደርስባቸው ይችላል፡፡ ያን ጊዜ ዛሬ ያላቸውን ዋጋ ሊያወጡ አይደለም፡፡ እንታደጋቸው ብንል እንኳ ለማትረፍ የሚከፈለው ዋጋ ቀላል አይሆንም፡፡

      ከዚህ ይልቅ መንግሥት የንግድ ድርጅቶችን በሙሉ ወደ ግል ካዘዋወረ በኋላ ከድርጅቶቹ የሚሰበስበው ግብር፣ ምናልባትም ዛሬ እነዚሁ ድርጅቶች በትርፍነት ከሚሰበስቡትም የበለጠ ሊሆን ይችላልና፡፡ ዛሬም ቢሆን ከመርፈዱ በፊት በፍጥነት ቢሸጣቸው ይሻላል ባይ ነኝ፡፡ ጊዜው ለቀልድ ብዙም የተመቸ ባይሆንም አንድ ቀደም ባለው ጊዜ የተነገረ ቀልድ ላንሳና ጽሑፌን ላብቃ፡፡ ሰውዬው ከአገራችን ብሔረሰቦች መካከል በንግድ ሥራቸው ከሚታወቁት መካከል ነው አሉ፡፡ በቀደመው ጊዜ “ኤርትራ ከእናት አገሯ አትገነጠልም፣ ለዓረብ ቅጥረኞች አትሸጥም” እያሉ መፈክር ሲያሰሙ ‘ካተረፈች ምናለበት ብትሸጥ?’ ብሎ ሐሳቡን ሲያቀርብ ሁሉም ሳቁበት አሉ (አለመታሰሩም ትረፍ ቢለው ነው)፡፡ ታዲያ በግንቦት 1983 ዓ.ም. ኤርትራ በራሷ ጊዜ ሄደች፡፡ ያም ምስኪን ምን ቢል ጥሩ ነው? ‘ይኸው ትሸጥ ስላችሁ እምቢ ብላችሁ ዛሬ በኪሳራ ሄደችላችሁ’ ብሎ ቁጭ አለ ይባላል፡፡ እንግዲህ ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው  [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...