Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርሕወሓትና ኢሕአዴግ ምንና ምን ናቸው?

ሕወሓትና ኢሕአዴግ ምንና ምን ናቸው?

ቀን:

በመርሃጽድቅ መኰንን ዓባይነህ

በአዲስ አበባ በቅርቡ የተጠራው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና እሱን ተከትሎ መቀሌ ላይ ያስቻለው የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በሁለት ተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ አቋሞችን እንዳራመዱ፣ ከየከተሙባቸው ሥፍራዎች ባወጧቸው መግለጫዎች ነግረውናል፡፡

ኢሕአዴግ በኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ላይ ከ18 ዓመታት በፊት የተደረሰውን የአልጀርስ ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን አሳሪ ውሳኔ ካሁን በኋላ ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ ለመቀበል ወስኛለሁ ባለ ማግሥት ይህ እውነት ቢሆንም፣ ሕዝቡ ሳይወያይበትና በቂ መተማመን ላይ ሳይደርስበት በሚዲያ መገለጽና ባፋጣኝ ይፋ መደረግ አልነበረበትም ሲል ሕወሓት ሥነ ሥርዓታዊ ሙግት ማቅረቡን ሰማን፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በሌላ በኩል ደግሞ ኢሕአዴግ የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ለማሻሻል ያመች ዘንድ በመንግሥት ሞኖፖሊ ተይዘው የቆዩት ግዙፍ የልማት ድርጅቶች ለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ክፍት እንዲሆኑ ተደርጓል ባለ ማግሥት፣ ሕወሓት በበኩሉ በችግሩ ላይ ሳይሆን በውጤቱ ላይ አተኩሮ በችኮላ የተወሰደ አቋም ነበር ሲል የራሱ አባላት ሳይቀሩ የተሳተፉበትን የግንባሩን ውሳኔ ያለ ይሉኝታ ተችቷል፡፡

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ከዚህ አልፎ ለዘመናት ፀንቶ የቆየው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመራችን በአዲሱ የኢሕአዴግ አመራር እየተሸረሸረ ነው፣ አመራሩ የግንባሩን ሕግና ደንብ ያላከበረ የሥራ ኃላፊዎች ሹመትና ምደባ እያካሄደ ነውና ሊታረም ይገባል፣ በዴሞክራሲና በጥገኝነት መካከል መሪር ትግል ገና በመካሄድ ላይ ነው፣ የወሰንና የማንነት ጉዳይ በሕገ መንግሥቱ የተመለሰና የተዘጋ አጀንዳ በመሆኑ እንደገና እያንሰራራ ነው ያለው፡፡ ፀረ ሕወሓትና ፀረ ትግራይ አፍራሽ እንቅስቃሴ ረብሾናልና መቆም ይኖርበታል፣ ወዘተ በማለት ምሬቱን ባልተለመደ ሁኔታ ካስደመጠን በኋላ፣ እነዚህን ቅሬታዎች እንደገና ለመመርመርና ለመዳኘት የግንባሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴም ሆነ የምክር ቤቱ አስቸኳይ ስብሰባዎች እንዲጠሩለት ተማፅኗል፡፡

ለመሆኑ ሕወሓትና ኢሕአዴግ ምንና ምን ናቸው? ሕወሓት የኢሕአዴግ ይግባኝ ሰሚ ነውን? ይህስ ከሆነ በእርግጥ የይግባኝ ማመልከቻውን ያቀረበለት ማን ሊሆን ይችላል? እንዲያው ለነገሩ ሕወሓት ከራሱ የውስጥ ጉዳይ አልፎ በአገርና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በብቸኝነት ለመምከርና የተናጠል ውሳኔዎችን ለማሳለፍ የሚችልበትን ሕጋዊ ሥልጣን ያገኘው ከየት ይሆን? አግራሞትን ከሚጭሩት ከእነዚህ ተነባባሪ ጥያቄዎች መካከል ይሳካልኝ እንደሆነ፣ እስኪ የመጀመርያውን አንስቼ ለመተንተን ልሞክር፡፡

ኢሕአዴግ ማንንም ጣልቃ ሳያስገባ መንግሥታዊ የፖለቲካ ሥልጣን በምርጫ ለመያዝ አልሞ በሚከተለው ርዕዮተ ዓለማዊ ፍልስፍና የተጣመረ የብሔራዊ (ክልላዊ) ፓርቲዎች ግንባር እንጂ፣ በዜግነት ፖለቲካ ላይ የተመሠረተ ወጥ አገራዊ ድርጅት አይደለም፡፡ እስካሁን እንደምንታዘበው አባል ድርጅቶቹ ሰፋ ያለውን የአገሪቱን ክፍል በየሚወክሏቸው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ስም ያስተዳድራሉ፡፡ በዚህ ድልድል መሠረት ታዲያ የሕወሓት ድርሻ የትግራይ ክልል መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

በግንባሩ ውስጥ በሚኖረው ውክልና ብቻ አገሪቱን ከሌሎች እህት ድርጅቶች ጋር በተጣማሪነት የመግዛት መብቱ እንደሚጠበቅለት ዕሙን ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በብቸኝነት የሚመክርበትና ውሳኔ የሚያሳልፍበት አገራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ጉዳይ ሊኖረው ከቶ አይችልም፡፡ ቢያንስ የሕገ መንግሥቱ አቀራረፅ ይኸው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

በሕገ መንግሥቱ መሠረት የፌዴራል መንግሥቱ ሥልጣን በሆኑ በማናቸውም ጉዳዮች ላይ ሊመክርና ውሳኔ ሊሰጥ የሚችለው ኢሕአዴግ እንጂ ሕወሓት ሊሆን አይችልም፡፡ እንደ ሌሎች የግንባሩ አባል ድርጅቶች ሁሉ የሕወሓት ሥልጣን ክልላዊ ጠባይ ባላቸው ጉዳዮች ብቻ የተወሰነ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ በመሠረቱ የሁለት ተጎራባች አገሮች ጉዳይ ነው፡፡ ዝነኛዋ የባድመ ከተማም ሆነች ሌላ አቻ አካባቢ በትግራይ ውስጥ ተካልለው የመገኘታቸው አጋጣሚ ብቻ ጉዳዩን የአንድ ክልል ጉዳይ አያደርገውም፡፡ ከዚህ የተነሳ ሕወሓት የተናጠል ውሳኔ ቢሰጥ ወይም የኢሕአዴግን ውሳኔ ለማጣጣል ቢሞክር በሕግም ሆነ በፖለቲካ ረገድ ያን ያህል አትራፊ አይሆንም፡፡ ወረራውን በብቸኝነት እንዳልመከተ ሁሉ፣ በሰላም ፍለጋው ረገድ ከቀሪ አባል ድርጅቶችና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖች የላቀ ተቆርቋሪነት አሳያለሁ ቢል ፍጹም ግብዝነት እንዳይሆንበት ቆም ብሎ ማሰብ ይኖርበታል፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ በጊዜው አንዳች የልዩነት አቋም እስካልተመዘገበበት ድረስ አዲስ አበባ ላይ የተላለፈው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ የሕወሓትም ውሳኔ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ የልዩነት አቋም የተመዘገበበት ቢሆን እንኳ በአብላጫ ድምፅ ሳይቀር ለተሰጠ ወይም ለሚሰጥ የትኛውም የኮሚቴው ውሳኔ አባል ድርጅቶች ያለማወላወል ታምኖ መገኘትና መገዛት ያለባቸውና የሚገባቸው ስለመሆኑ፣ የዴሞክራሲን ሀ-ሁ የቆጠረ ሁሉ ይስተዋል ተብሎ አይገመትም፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ከፍተኛ መቆራቆስ እንዳለ የሚነግረን ሌላ ሳይሆን ራሱ ኢሕአዴግ ነው፡፡ ያም ሆኖ አውራነቱ ቀርቶብኛል ካላለ በስተቀር ሕወሓት ዛሬም ቢሆን የማይናቅና ወሳኝ ድርሻ ያለው የኢሕአዴግ አባል ድርጅት እንደሆነ የሚጠራጠር ወገን የለም፡፡

ስለዚህ በአዲስ አበባና በመቀሌ መካከል የቦታ ርቀት ቢኖርም ሕወሓት ለኢሕአዴግ ምኑም አይደለም ለማለት የምንችልበት ምክንያት ገና አላገኘንም፡፡ ይህ እውነት ከሆነ ታዲያ የጋራ ርዕዮተ ዓለማዊ ቃል ኪዳን ተጣማሪዎቼ ናቸው ከሚላቸው የግንባሩ አባል ድርጅቶች ጋር አብሮ አዲስ አበባ ላይ የተባበረ ውሳኔ ያሳለፈበትን የራሱን ጉዳይ ወደ ግል መዲናው ሲመለስ በራሱ ጊዜ ለመከለስ ምን አነሳሳው?

ሕወሓት የኢሕአዴግ አንድ ክፋይ እንጂ ብቻውን ሙሉ ኢሕአዴግ እንዳልሆነ ራሱም ቢሆን አይጠፋውም፡፡ እንደሚመስለኝ በዘጠኝ አባላቱ የተወከለበትንና ራሱ አካል የሆነበትን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ ወደመገዳደሩ ፅንፍ የተገፋበት ዓብይ ምክንያት፣ የሚያስተዳድረው አካባቢ ሕዝብ በውሳኔው የወደፊት አተገባበር ላይ በተከታታይ እያሰማው ያለውን ተቃውሞ በመጠኑም ቢሆን ለማርገብ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሆኖም ይህ የተናጠል ዕርምጃው በጥብቅ እመራበታለሁ የሚለውን ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መጣስ ይሆንበታል፡፡ ከግንባሩ ጋር ያለውን ግንኙነት ያለጥርጥር ያሻክርበታል፡፡ ጊዜያዊ ትኩሳቱን ከማናር ባለፈ ለአካባቢው ሕዝብ የሚሰጠው የተስፋ ቃል ቢኖር ብቻውን ተፈጻሚ ሊያደርገው አይችልም፡፡

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ቅር ተሰኝቼበታለሁ የሚለው ሌላው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ እንደ ቴሌኮምና አየር መንገድ ያሉ ግዙፍ መንግሥታዊ የልማት ድርጅቶች ለግል ባለአክሲዮኖች ተሳትፎ ክፍት የሚደረጉበትን ዕርምጃ የሚመለከተው ነው፡፡ በአንድ በኩል ይኼንን የፖሊሲ ዕርምጃ ሕወሓት ራሱ ለዘመናት ሲያቀነቅንለት እንደኖረና ከያዘው ልማታዊ መስመር ጋር ያን ያህል ተፃራሪ እንዳልሆነ ለማስታመም ይሞክራል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይህም ቢሆን ከሕዝብ ጋር በቂ ምክክር ሳይደረግበት የተላለፈ ውሳኔ ነው ሲል በተቃራኒው ያማርራል፡፡

እንግዲህ ግንባሩ አገራዊ ፋይዳ ባላቸው በሁለቱም ዓበይት ጉዳዮች ላይ መክሮ ውሳኔዎችን ሲያሳልፍ፣ ከሌሎች ብሔራዊ ድርጅቶች ጋር እኩል ተዋፅኦና የድምፅ ውክልና የነበረው ሕወሓት እነዚህኑ ዘግይቶ የሚያሰማቸውን ቅሬታዎች አስቀድሞ የማንሳትና የመከራከር ዕድል ነበረው፡፡ ይኼንን ሳያደርግ ቀርቶ ከዋናው የስብሰባ አዳራሽ ከወጡ ከበርካታ ቀናት በኋላ አዳዲስ ህፀፆችን እያፈላለጉ ከማዕከላዊነት የማፈንገጡ ሙከራ በጊዜው ካልታረመ፣ ግንባሩን ወደ ማፍረስ ያልታሰበ አደጋ ሊያንደረድር ይችላል፡፡

ከመግለጫው እንደምንመለከተው የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በሰሞኑ አስቸኳይ ስብሰባው አግራሞትን የሚጭሩ ሌሎች ተጓዳኝ ጉዳዮችንም አንስቷል፡፡

ከመካከላቸውም በግንባሩ አመራር እየተካሄደ ያለው ሹመትና ምደባ የግንባሩን መተዳደሪያ ሕግና ተቋማዊ አሠራር ያልተከተለ ስለሆነ እንዲታረም፣ በክልሎች ውስጥ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች አይነሱብኝ፣ ፀረ ሕወሓትና ፀረ ትግራይ ሕዝብ እንቅስቃሴዎች ይቁሙ፣ ለነባር የድርጅቱ አባላት የተለየ ዕውቅና እንዲሰጥ፣ ወዘተ የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች ሲካሄዱ የቆዩትን ሕዝባዊ መነሳሳቶችና ደም አፋሳሽ ግጭቶች ተከትሎ ሥር ነቀል ነው ባይባልም፣ ኢሕአዴግ በለውጥ ማዕበል ውስጥ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይኸው ምክንያት ሆኖ ራሱን እንደገና በማደራጀትና አመራሩን በማስተካከል ላይ መሆኑም የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ታዲያ ኢሕአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ አካሂጃለሁ በማለት የግንባሩን ሊቀመንበር እንደለወጠ፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ይኸው ሊቀመንበር የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቀርቦ ቃለ መሐላ እንደፈጸመ እናስታውሳለን፡፡

እንግዲህ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሥራውን ከመጀመሩ በፊት ካቢኔውን እሱ በሚፈልገው መንገድ ማዋቀሩ ነውር አይደለም፡፡ በሌሎች የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቦታዎች ላይ ሳይቀር ብቁ ናቸው ብሎ ያመነባቸውን ዜጎች መሾምና መሻሩም ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣኑ ስለሆነ የሚነቀፍበት ምክንያት የለም፡፡ በሲቪል ሹማምንትም ሆነ በወታደራዊ አዛዦች ሹመትና ምደባ ወቅት እስከተቻለ ድረስ የፆታ ጥንቅርና የብሔር ብሔረሰቦችን ተዋፅኦ መጠበቅ ይኖርበት ይሆናል፡፡ ለዚህ እንዲረዳው የብሔራዊና የአጋር ድርጅቶችን ምክርና አስተያየት መጠየቁ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የመጨረሻ ውሳኔ ግን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 74 መሠረት የራሱና የራሱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡

ስለሆነም ሕወሓት በኢሕአዴግ አመራር ወይም በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ ያሰማው ወቀሳ ውኃ የሚቋጥር አይደለም፡፡ እንዲህ ያለውን ነቀፌታ በዘፈቀደ የመሰንዘር መብትም በፖለቲካ ድርጅቱ ባህል እንደሆነ ነው እንጂ በሕግ እንዳልተሰጠው ማወቅ በተገባው ነበር፡፡

ሕወሓት በማዕከላዊ ኮሚቴው አማካይነት አሁን በሥራ ላይ ያለውና ከፌዴሬሽኑ ይፋዊ እወጃ በፊትም ሆነ በኋላ የአገሪቱ ክልሎች አወቃቀር የተመሠረተበት የመልክዓ ምድራዊ ወሰን፣ የሕዝብ አሰፋፈርና የማንነት ጥያቄ እንዳይነሳበት መወራጨቱና ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት ማስተላለፉ ደግሞ በይበልጥ ግር የሚያሰኝ ጉዳይ ሆኗል፡፡ እንደ ብሔራዊ ድርጅቱ የተዛባ አመለካከት ከሆነ እንዲህ ያለው ጥያቄ በተለይ የትግራይን ሕዝብ ሰላም ስለሚያደፈርስና አንድነቱን ስለሚያናጋ በአፋጣኝ መቆም አለበት፡፡ ምንትስ ያለበት ዝላይ አይችልም ነው ነገሩ፡፡

በብሔር ብሔረሰቦች መብት ንግሥናና ጥበቃ ስም አገሪቱ ያለበቂ ጥናትና ምርምር ቀድሞውኑ የተከለለችው በአፍ መፍቻ ቋንቋና በሕዝብ አሰፋፈር ላይ መሆኑ እየታወቀ፣ ትግራይ ላይ ሲደርስ ብቻ የወሰንና የማንነት ጥያቄ ዝግ ነውና እንዳይነሳ አጥብቆ መከላከሉና ማስፈራራቱ ከምን የመጣ ሀኬት ነው?

ከስያሜው ለመረዳት እንደሚቻለው ሕወሓት ማኅበራዊ መሠረቱም ሆነ ቀዳሚ የትግል መንደርደሪያው በእርግጥ ትግራይ መሆኑ አይካድም፡፡ ይሁን እንጂ የዴሞክራሲ ጥያቄ ከዚህ ወይም ከዚያ በመለስ ተብሎ በደምሳሳው የሚገደብና ዳር ድንበር የሚበጅለት አይደለም፡፡ ስለሆነም በሕግ አግባብ ሊስተናገድ የሚችል ሆኖ እስከተገኘ ድረስ የትግራይ ክልልን ጨምሮ በየትኛውም አካባቢ የሚነሳ የመብት ጥያቄ፣ በተለይ የትግራይን ሕዝብ የሚረብሽበት አንዳች ምክንያት አይኖርም፡፡

በአገሪቱ ውስጥ በየትኛውም ሥፍራ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚቀርቡ የማንነት ጥያቄዎችን ሲያደፋፍር እንደኖረ ጠንቅቀን የምናውቀው ብሔራዊ ድርጅት፣ በዚህኛው የማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫው ትግራይ ክልል ላይ ብቻ ስላተኮረ በስም ደፍሮ አይጥቀሰው እንጂ የወልቃይትን ጥያቄ አታንሱብኝ ማለቱ እንደሆነ አነጋገሩ ብቻ ቀድሞ ያሳብቅበታል፡፡ ይህ ዓይነቱ ገዳቢ አቋም ግን በያዙት መስመር ጥራት አዘውትረው ለሚመፃደቁት አብዮታዊ ዴሞክራት ጓዶቻችን ምን ተጨማሪ ትርፍ እንደሚያስገኝላቸው በውል መረዳት አዳጋች ይሆናል፡፡

በመጨረሻም የትግራይ ሕዝብ ከሕወሓት በላይ መሆኑን ለአንዳፍታም ቢሆን አለመዘንጋት ተገቢ ነው፡፡ ይህ የማያጠራጥር እውነታ ከሆነ ደግሞ ምንጊዜም ቢሆን ሕወሓትን የሚገዳደርና የፖለቲካ ፍልስፍናውን የሚቃወም ሁሉ የትግራይ ሕዝብ ጠላት እየተደረገ በቁንፅሉ የሚቀርበው አጃቢ ትንተና ራሱ ከመስመር የወጣና ፍፁም ኃላፊነት የጎደለው እንዳይሆን እሠጋለሁ፡፡ የትግራይ ወገኖቻችንን ጨምሮ መላው ሕዝባችን መንግሥታዊ ሥልጣንን የጨበጡ የፖለቲካ ቡድኖች ከየራሳቸው ጠባብ ፍላጎት እየተነሱ በየጊዜው ያሰመሩለትን መልክዓ ምድራዊ የግዛት ወሰን በመከተልና በእሱ ብቻ ታጥሮ እንደሚኖር አድርጎ ማሰቡ ብዙ ርቀት ሊወስደን እንደማይችል ነባርና አዳዲስ መሪዎቻችን ልብ ሊሉ ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...