በተያዘው በጀት ዓመት የሻይና ቅመማ ቅመም ምርቶችን ጨምሮ ከቡና ወጪ ንግድ የ746 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በ11 ወራት ውስጥ ማስገኘቱ ታወቀ፡፡ በዚህ ወቅት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ይጠበቅ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ቅመማ ቅመም ልማትና ግብይት ባለሥልጣን ባወጣው ስታቲስቲካዊ መረጃ መሠረት፣ በ11 ወራት ውስጥ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ211 ሺሕ ቶን በላይ ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ የመነጨ ነው፡፡ ይሁንና የቡናው ገቢም ሆነ የተላከው መጠን ባለፈው ዓመት ከተገኘው ብቻም ሳይሆን፣ በዚህ ዓመት ይገኛል ተብሎ ከታቀደውም መጠን ያነሰ ሆኗል፡፡
በዚህ በጀት ዓመት ማለትም ከሐምሌ እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ ይገኛል ተብሎ የታቀደው ገቢ አንድ ቢሊዮን 35 ሚሊዮን ዶላር ቢሆንም፣ በአፈጻጸሙ ግን 746.23 ሚሊዮን ዶላር ላይ ተገቷል፡፡
ከባለሥልጣኑ የተገኘው መረጃ፣ ‹‹ከሐምሌ እስከ ግንቦት 2010 በጀት ዓመት የኤክስፖርት ቡና ክንውን በመጠን 211,383.29 ቶን ጥሬ ቡና ወደ ውጭ ተልኮ 746.23 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡ ይህ አፈጻጸም ከዕቅዱ ጋር ሲነፃፀር በመጠን የ90.05 በመቶና በገቢ የ74.36 በመቶ አፈጻጸም በመሆን ተመዝግቧል፤›› በማለት ይጠቅሳል፡፡ በመሆኑም ይህ አፈጻጸም በ2009 ዓ.ም. ከሐምሌ እስከ ግንቦት ወር ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በመጠን 14,977.94 ቶን ወይም የ7.63 በመቶ እንዲሁም በገቢ ረገድ የ25.42 ሚሊዮን ዶላር (-3.29 በመቶ) ቅናሽ ማሳየቱን ባለሥልጣኑ ጠቁሟል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን የግንቦት ወር አፈጻጸምን ባመላከተበት መረጃው፣ ለዓለም ገበያ ከቀረበው የኢትዮጵያ ቡና 95 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡ በግንቦት ወር የነበረው የቡና የወጪ ንግድ ክንዉን በመጠን ሲታይ የ26,142.14 ቶን ጥሬ ቡና ወደ ውጭ መላኩን ይጠቁማል፡፡ በዚህ መሠረትም 94.51 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቅሷል፡፡ ይህ አፈጻጸም ከዕቅዱ ጋር ሲነፃፀር በመጠን የ72.29 በመቶ እንዲሁም በገቢ ረገድ የ60.71 በመቶ አፈጻጸም ማሳየቱ ተመልክቷል፡፡ ይሁንና የዚህ ዓመት የግንቦት ወር አፈጻጸም ከ2009 ግንቦት ወር ጋር ሲነፃፀር በመጠን 4,299.13 ቶን (-14.12 በመቶ) እንዲሁም በገቢ ረገድ የ27.65 ሚሊዮን ዶላር (-22.63 በመቶ) ቅናሽ አሳይቷል፡፡
ባለፈው ዓመት እስከ ሰኔ ወር በነበረው የቡና የወጪ ንግድ አፈጻጸም 226 ሺሕ ቶን ከሚጠጋ የቡና የወጪ ንግድ ከ881 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱ ይታወሳል፡፡ በዓምናው የቡና የወጪ ንግድ ዕቅድ መሠረት 241 ሺሕ ቶን ሊላክ እንደሚችልና 941 ሚሊዮን ዶላር እንደሚገኝ ቢታቀድም፣ የተገኘው የ881 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከቡና ከተገኘው ገቢ አኳያ ከፍተኛው እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ከሰባት ዓመታት በፊት ወደ ውጭ ከተላከው 200 ሺሕ ቶን ከሚጠጋ ቡና 842 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ በትልቅነቱ ከሚጠቀሱ የቅርብ ጊዜ የቡና ንግድ ውጤታማ አፈጻጸሞች የሚካተት ነው፡፡
ከቡና ባሻገር በሻይና ቅመማ ቅመም የወጪ ንግድም የሚጠበቀውን ያህል ባይሆንም መጠነኛ ገቢ እየተገኘ ስለመሆኑ የባለሥልጣኑ መረጃ ይጠቁማል፡፡ በዚህ ዓመት 11 ወራት 21 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ተመዝግቧል፡፡ ባለፈው ዓመት ከሻይና ቅመማ ቅመም ዘርፍ ከ20 ሚሊዮን ዶላር ያልበለጠ ገቢ መገኘቱ ይታወሳል፡፡