Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያ በንግድ ጦርነት ጦስ ሊጠቁ ከሚችሉ ቀዳሚ አገሮች ተርታ ተመደበች

ተዛማጅ ፅሁፎች

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና የልማት ጉባዔ (UNCATD) በዓለም ላይ እየታየ ያለውን የንግድና የታሪፍ ከለላ ዕርምጃ በተመለከተ በድረ ገጹ ባስነበበው ጽሑፍ፣ በወጪ ንግዳቸው ላይ ከፍተኛ ታሪፍ ሊጋጥማቸው ይችላሉ ካላቸው ከ30 በላይ አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያን በሦስተኛ ደረጃ አስቀምጧል፡፡ አሁን እየታየ ባለው የታሪፍ ከለላ ሳቢያ በዓለም ላይ የ32 በመቶ አማካይ የታሪፍ ዋጋ ጭማሪ ሊኖር እንደሚችል ሲገመት፣ ኢትዮጵያ እስከ 50 በመቶ ጭማሪ ሊያጋጥማት እንደሚችል ተገምቷል፡፡

የተመድ ድረ ገጽ ያሰፈረው ጽሑፍ መነሻውን ያደረገው አሌክሳንድሮ ኒሺዳ በተባሉ የድርጅቱ የኢኮኖሚ ባለሙያ የቀረበውን ትንታኔ ሲሆን፣ አሜሪካ በቅርቡ ተግባራዊ ያደረገችውን የታሪፍ ዋጋና እርሱንም ተከትሎ የተንሰራፋውን የንግድ ጦርነት ሥጋት ያስቃኛል፡፡

አሜሪካ በመጋቢት ወር ይፋ ያደረገችው የታሪፍ ከለላ ዕርምጃ ምንም እንኳ ወደ አገሪቱ በሚገቡ ሁሉም ሸቀጦች ላይ ተግባራዊ ሊደረግ የታቀደ ቢሆንም፣ በርካታ የአሜሪካ ወዳጅ አገሮች ከታሪፍ ከለላው መጠነኛ ዕፎይታ እንዲያገኙ ወይም በልዩነት እንዲስተናገዱ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ማሻሻያ አድርጓል፡፡ መጋቢት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው የአሜሪካ የታሪፍ ዕርምጃ የ50 ቢሊዮን ዶላር ግምት ያላቸውን የቻይና ምርቶች እስከ 25 በመቶ ታሪፍ እንዲጣልባቸው ሲያደርግ፣ መጋቢት 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ቻይና በሰጠችው የአፀፋ ምላሽ የ100 ቢሊዮን ዶላር የታሪፍ ጭማሪ ሊኖር እንደሚችል ይፋ አድርጋለች፡፡ ይኸው የማጥቃትና መልሶ ማጥቃት ዘመቻ በሁለቱ አገሮች ሲፋፋም፣ በተናጠል ኩባንያዎችን የሚመለከት ዕርምጃ ውስጥ በመግባቱ የሁለቱ አገሮች የተካረረ የታሪፍ እሰጣ አገባ ወደ ንግድ ጦርነት ሊያመራ ይችላል የሚሉ ሥጋቶችን አስከትሏል፡፡

ልዕለ ኃያላኑ አገሮች በሚያደርጉት የንግድ ፉክክር ምክንያት ወደ ንግድ ጦርነት አለያም አንዱ በሌላው ምርት ላይ ከፍተኛ የታሪፍ ጭማሪ በማድረግ በሚያደርጉት ትንቅንቅ ሳቢያ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ውስጥ ምርት ወደ ውጭ በመላክ የተሠማሩ ላኪዎች ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቃቸው አካሄድ እየመጣ በመሆኑ፣ የወጪ ንግድ አዋጪ ከመሆን ይልቅ አክሳሪ እንዲሆን ሊያደርገው የሚችል አኳኋን መታየት ጀምሯል፡፡

የአገሮችን የንግድ ጦርነት ለማስቀረት ዓይነተኛው መንገድ እንደ የዓለም ንግድ ድርጅት የሚመራበት የባለብዙ ባለድርሻዎች ትብብር ስለመሆኑ ተመድ ይገልጻል፡፡ አገሮች ወደ ንግድ ጦርነት ሊገቡ የሚችሉት ያልተገባ የንግድ ውድድር ውስጥ በመግባት፣ በውስጣቸው ያሉ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች የሌሎች አገሮችን ሸቀጦችና ምርቶች በገበያ መወዳደር ሲሳናቸው፣ ደካማ የንግድ ዘርፋቸውን ከውጭ ውድድር ለመከላከል ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ የንግድ ከለላ ወይም ማገጃ ዘዴዎችን ይተገብራሉ፡፡ በዚህ ረገድ ታሪፍ የንግድ ከለላ ዋናው ዕርምጃ ዘዴ ሲሆን፣ ከታሪፍ ውጭ በርካታ ቀጥተኛ ያልሆኑ ከለላዎችም በስፋት ሲተገበሩ ይታያል፡፡ አብዛኞቹ ያላደጉ አገሮች የኢኮኖሚያቸውን እንቅስቃሴ በውጭ ኩባንያዎች ጫና ውስጥ ላለመጣል ሲሉ በርካታ ኢኮኖሚ አውታሮችን ከንግድ ውድድር እንዲከለሉ ያደርጋሉ፡፡ ለአብነት ኢትዮጵያ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ ክፍት ያደረገቻቸው የንግድ ዘርፎች ማለትም የፋይናንስ፣ የትራንስፖርት፣ የቴሌኮምና መሰል ዘርፎች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

ያደጉ አገሮች በተለይም የዓለም ንግድ ድርጅት አባላት በፊናቸው ቀጥተኛ ወይም መደበኛ ያልሆኑ የታሪፍ ከለላዎችን በማድረግ ኢኮሚያቸውንና የንግድ ዘርፋቸውን ከሌሎች አገሮች ውድድር ሲከላከሉና ከለላ ሲሰጡ ይታያሉ፡፡ ከፍተኛ የጥራትና የምርት መስፈርቶችንና ደረጃዎችን በማውጣት አነስተኛ አቅም ያላቸው አገሮች ባላቸው የንግድ ብልጫ ሳቢያ እንዳይወዳደሯቸው ይከላከላሉ፡፡

ለምሳሌ ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብቷ የቱንም ያህል የላቀ አቅም ቢኖራት፣ በወጪ ንግድ ረገድ የሚገባውን ያህል የሥጋና መሰል የወጪ ንግድ ላይ ተሳትፎ እንዳታደርግ ከሚጫኗት ተፅዕኖዎች መካከል ታሪፍ ነክ ያልሆኑ ክልከላዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከፍተኛ የጤና ደረጃዎችን ማሟላት ግዴታም ቢሆን፣ ከዚህ ያለፉና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ መስርቶችና ስታንዳርዶች አገሪቱን በሥጋ ኤክስፖርት ረገድ ተወዳዳሪ ሊያደርጓት አልቻሉም፡፡ ይህ ሲባል ግን አገሪቱ ያላት የቄራዎች አቅምና ብቃት ደካማ መሆን ድርሻ የለውም ማለት እንዳልሆነም የዘርፉ ተንታኞች ይጠቅሱታል፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከሚላክ ይልቅ በአገር ውስጥ ለሚገኙ የቆዳ ፋብሪካዎች እሴት ለመጨመር ይረዳል በማለት ቀድሞ ወደ ውጭ ሲላክ በነበረው የጥሬ ቆዳ ላይ የ300 በመቶ ታሪፍ መጣሏም በታሪፍ ክልከላ የተወሰደ የንግድ ውድድርን የሚገድብ ዕርምጃ ተደርጎ ሊጠቀስ እንደሚችል፣ ከዚህ ቀደም ሲደረጉ የነበሩና ንግድን ለውድድር ነፃ የማድረግና የታሪፍ ዕምርጃዎችን የተመለከቱ ክርክሮች ከሚያነሷቸው ጉዳዮች ውስጥ ሲጠቀስ የነበረ ዕርምጃ መሆኑም ይታወሳል፡፡ 

ይህ እንዳለ ይሁንና ወደ ተነሳንበት ነገረ ጉዳይ ስንመለስ በትልልቆቹ አገሮች የተፈጠረው የንግድ ከለላን መነሻ ያደረገው እሰጥ አገባ፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ላይ ዳፋውን እያሳረፈ ጦሱ ሊተርፋቸው የሚችልባቸውን አኃዛዊ መረጃዎች ተመድ አስፍሯል፡፡ በዓለም ላይ ትልቁን የንግድና ኢኮኖሚ ልዕልናን የተቆጣጠሩት አሜሪካ፣ ቻይና፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ ብራዚል፣ ህንድና ጃፓን የንግድ ከለላ ዕርምጃዎችን ተግባራዊ ቢያደርጉ፣ የሚገመተው የታሪፍ ጭማሪ 60 በመቶ ሊሆን እንደሚችል የተመድ ባለሙያዎች ይገምታሉ፡፡

አሜሪካ በምትወስደው የንግድ ከለላ ሳቢያ ሊታይ የሚችለው አማካይ የታሪፍ ጭማሪ ወደ 14 በመቶ እንደሚሆን ሲገመት፣ በአውሮፓ ኅብረት በኩል ሊታይ የሚችለው የታሪፍ ጭማሪም ወደ 25 በመቶ ሊያድግ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ይህም ሆኖ እነዚህ አገሮች አቅሙና ብቃቱ ስላላቸው የታሪፍ ጭማሪውን ሊቋቋሙት እንደሚችሉ ይታመናል፡፡ በአንፃሩ እንደ ኢትዮጵያ ያሉት አገሮች ግን የአሜሪካን ወይም የአውሮፓ ኅብረትን ያህል ታሪፍ ጭማሪ እናድርግ ቢሉ ምንም ዓይነት ምርት ወደ ውጭ መላክ ወደማያስችላቸው ደረጃ ሊደርሱ እንደሚችሉ ተንታኞቹ ለማመላከት ሞክረዋል፡፡ የታሪፍ ለውጥ ያድርጉ ቢባል እንኳ እንደ ቡርኪና ፋሶ፣ ጉያና ያሉ እጅግ አነስተኛ የገበያ ኃይል ያላቸው አገሮች ከአንድ በመቶ ያነሰ ጭማሪ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተገምቷል፡፡

ዓለም ሙሉ ለሙሉ ሊባል ወደሚችል የንግድ ጦርነት ብታመራ፣ የአሜሪካ ላኪዎች ከሦስት እስከ 30 በመቶ አማካይ የታሪፍ ጭማሪ ያጋጥማቸዋል፡፡ ይህም አሁን ካለው የአሥር በመቶ እጥፍ ጭማሪ እንደሚሆን ሲገመት፣ ቻይናውያን ላኪዎች በበኩላቸው የ36 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ይህ በተዘዋዋሪ አሜሪካ ከቻይናና ከአውሮፓ ኅብረት ጋር እስከ 100 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የንግድ ሽርክና ያላቸውን አገሮች ሊጎዳ እንደሚችልም ታሳቢ ተደርጓል፡፡ በዚህ መሠረትም ሜክሲኮና ሆንዱራንስ እስከ 60 በመቶ አማካይ የታሪፍ ጭማሪ ሊገጥማቸው እንደሚችል ሲገመት፣ ኢትዮጵያና ኮስታሪካ እስከ 50 በመቶ የዋጋ ጭማሪ በወጪ ሸቀጦቻቸው ላይ የታሪፍ ጭማሪ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል የባለሙያዎቹ ትንበያ አሳይቷል፡፡

አሁን ባለው የታሪፍ ሁኔታ ኢትዮጵያ ከታሪፍና ከኮታ ነፃ ተጠቃሚ ከሆኑ አገሮች ተርታ ትመደባለች፡፡ ይኸውም አሜሪካ ለአፍሪካ አገሮች በሰጠችውና (አፍሪካን ግሮውዝ ኤንድ ኦፖርቹኒቲ አክት) አጎዋ በተሰኘው ነፃ የታሪፍና የኮታ ሕግ መሠረት ተጠቃሚ ከሆኑ አገሮች ተርታ ኢትዮጵያ ብትመደብም፣ በንግድ ከለላውና የታሪፍ ክለሳው ሳቢያ ተጎጂ ስለመሆን አለመሆኗ በይፋ ሲነገር አልተደመጠም፡፡ አጎዋ ከካቻምና ወዲህ ለአሥር ዓመታት እንዲራዘም መደረጉ ይታወሳል፡፡ ከአጎዋ በተጨማሪም በአውሮፓ ኅብረት አማካይነት ከጦር መሣሪያዎች በስተቀር (ኤቭርቲንግ በት አርምስ) በሚለው ማዕቀፍ መሠረት ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ታዳጊ አገሮች የወጪ ንግድ ገበያ እንዲያገኙ የሚያግዙ ዕርምጃዎች ቢወሰዱም፣ በተግባር ግን ከእንዲህ ያሉ ማበረታቻዎች ብዙም ተጠቃሚ ሳይሆኑ ቆይተዋል፡፡

ላለፉት 15 ዓመታት በአጎዋ እንደሚገባቸው መጠቀም ያልቻሉት የአፍሪካ አገሮች አዲሱ የታሪፍ ለውጥ ምን ያህል ከጨዋታው ውጪ ሊያደርጋቸው እንደሚችል የሚቀርቡ ትንታኔዎች ባይታዩም፣ ኃያላኑ አገሮች ወደ ሁሉ አቀፍ የንግድ ጦርነት ቢገቡ ግን እንዲህ ያለው የታሪፍና የኮታ ነፃ ገበያ የመጠቀም ዕድላቸው በተዘዋዋሪ መንገድ ሊቀር እንደሚችል አመላካች ሥጋቶች እየታዩ ነው፡፡ አጎዋ በአሜሪካ ሕግ መወሰኛው ምክር ቤት መፅደቁ የሚታወስ ነው፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች