በካዳና በሚዘጋጀው የሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ጨዋታ ለመዳኘት ኢትዮጵያዊቷ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ታጨች፡፡ 22 ዋና ዳኛዎች ሰባት ዕረዳት ዳኞችና 44 ምክትል ዳኞች ከተለያዩ የዓለም አገሮች መመረጣቸውን የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር ፊፋ በድረ ገጹ አስታውቋል፡፡
በዚህ 24 አገሮች በሚሳተፉበት የሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ጨዋታ ዳኞች የተመረጡት የዳኝነትን የጨዋታ አግባብ በመረዳት፣ የግል ችሎታቸውን በመመልከትና በጨዋታዎች ላይ የሚያደርጉት እንቅስቃሴን ባገናዘበ መልኩ እንደሆነም ዘገባው አመልክቷል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ዛምብያ፣ ካሜሮን፣ ቶጎ፣ ማላዊ፣ ሞሮኮና ማዳጋስካር ለዚህ ጨዋታ ዳኞችን ካስመረጡት ይገኙበታል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም የተመረጡት ዳኞች እ.ኤ.አ. ሚያዝያ ወር ላይ ውድድሩ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ሁለት የዳኝነት ሥልጠና እንደሚሰጣቸው ታውቋል፡፡ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር ፊፋ በበኩሉ ለተመረጡት ሴት ዳኞች ከፍተኛ ድጋፍ ለማድረግ እንደተዘጋጀም ገልጿል፡፡ በውድድሩ ለመጀመርያ ጊዜ የጎል ላይን ቴክኖሎጂ እንደሚገጠምለት ለሚጠበቀው የዘንድሮው የሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ከአፍሪካ ኮትዲቯር፣ ካሜሮንና ናይጄሪያ ተካፋይ ይሆናሉ፡፡