Tuesday, November 28, 2023

በኦሮሚያ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ለመቆጣጠር መንግሥት ከመጠን ያለፈ ኃይል መጠቀሙን ሰመጉ አስታወቀ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተካሄደውና እየተካሄደ ባለው ሕዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ለተቃውሞ በወጡ ዜጎች ላይ በወሰዱት ከመጠን ያለፈ የኃይል ዕርምጃ 103 ሰዎች መሞታቸውን፣ 59 ሰዎች መቁሰላቸውን፣ 22 ሰዎች ድብደባና ስቃይ እንደተፈጸመባቸው፣ 226 ሰዎች ከሕግ ውጪ መታሰራቸውን፣ 12 ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁን፣ 800 ሰዎች መፈናቀላቸውንና 892 መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) ባወጣው ሪፖርት ይፋ አደረገ፡፡

ሰመጉ ሰኞ መጋቢት 5 ቀን 2008 ዓ.ም. በዋና ጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት፣ በሪፖርቱ የሰፈረው በክልሉ ከሚገኙ 342 ወረዳዎች ውስጥ በ33 ወረዳዎች ከኅዳር 2 እስከ የካቲት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ውስጥ ባካሄደው የመስክ ምርመራ አማካይነት የተገኘ ውጤት መሆኑን አስታውቋል፡፡

በዚህም መሠረት በምዕራብ ሸዋ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ በፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን፣ በምዕራብና በምሥራቅ ወለጋ፣ በሆሮ ጉድሩ፣ በምዕራብና በምሥራቅ ሐረርጌ፣ በባሌ፣ በአርሲ ዞኖች የሚገኙ 33 ወረዳዎች ውስጥ የመስክ ምርመራ መካሄዱ ተገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ የተለያዩ የመንግሥትና የሕዝብ ንብረት መውደሙ የተገለጸ ሲሆን፣ ‹‹ከክልሉ መስተዳድር አካላት ባገኘነው መረጃ መሠረት በርካታ የገበሬ ማኅበር ጽሕፈት ቤቶች፣ ንዑስ ፖሊስ ጣቢያዎች፣ የገበሬዎች ማሠልጠኛ አዳራሾችና ንብረትነታቸው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ የሆኑ ከአሥር በላይ መኪናዎች ተቃጥለዋል፡፡ አንድ ሚሊዮን ሰባት መቶ ሺሕ ብር የሚገመት አንድ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስም ተቃጥሏል፤›› በማለት የሰመጉ ሪፖርት የጉዳቱን መጠን ይጠቁማል፡፡

‹‹የመንግሥት ታጣቂ ኃይሎች በአምቦ፣ በጀልዱና በግንደበረት አስገድዶ መድፈር መፈጸማቸውን ከነዋሪዎች ለማወቅ ችለናል፤›› የሚለው የሰመጉ ሪፖርት በተጨማሪም በአንዳንድ ቦታዎች የመንግሥት ታጣቂዎች ሕገወጥ የቤት ለቤት አሰሳ ሌሊት ላይ ማድረጋቸውን፣ በፍተሻ ወቅት የሚያገኙትን ንብረት መውሰዳቸውን፣ በዜጎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ድብደባ መፈጸማቸውንና ዛቻ፣ ማስፈራሪያና ስድብ መሰንዘራቸውን ያትታል፡፡ በተቃውሞ እንቅስቃሴው የተነሳ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አመያ ወረዳ ኩኖ ቁሊታ (ቀረሳ ቁሊት)፣ ወረወገሪ (በሬዳ) እንዲሁም አብሌ መድኃኔዓለም በተባሉ ቀበሌዎች ከ30 ዓመታት በላይ በአካባቢው የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች መኖሪያ ቤት ከነሙሉ ንብረቱ ማስተር ፕላኑን በመቃወም ሰልፍ በወጡ ጥቂቶች አማካይነት ታኅሳስ 2 ቀን 2008 ዓ.ም. መቃጠሉም በሪፖርቱ ሰፍሯል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በቤት ውስጥ የነበረ ለሽያጭ የተዘጋጀ በርበሬና የተለያዩ የእህል ዓይነቶች ምርት መውደሙን፣ ማሳ ላይ የነበረ እህል መቃጠሉንና በዚህም ምክንያት ቁጥራቸው ከ500 የማያንስ ተፈናቃዮች በድንኳን ውስጥ መጠለላቸውን የሰመጉ ባለሙያዎች ማረጋገጣቸውን ሪፖርቱ ያብራራል፡፡

በዚህ የንብረት ውድመትና መፈናቀል የተነሳ በኩኖ ቁሊቲ ቀበሌ የአማራ ተወላጆች በወሰዱት የአፀፋ ዕርምጃ ቁጥራቸው 96 የሚሆን የኦሮሞ ተወላጆች ቤት መቃጠሉንም የሰመጉ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ ‹‹ይህ ሕዝብን በሕዝብ ላይ የማነሳሳት ድርጊት የሚፈጸመው በዋነኛነት በጥቂት የራሳቸው ያልሆነውን መሬትና ሀብት በመንጠቅና ያለአግባብ ለመክበር በሚፈልጉ የአካባቢው ሀብታሞች አነሳሽነትና መሪነት፣ እንዲሁም በመሰል ጥቅም ፈላጊ ባለሥልጣናት አይዞህ ባይነት›› መሆኑን ከተጎጂዎቹ መረዳቱን ሰመጉ ገልጿል፡፡

መንግሥት በክልሉ አሸባሪዎችና የታጠቁ አካላት የሕዝቡን ጥያቄ ተገን አድርገው በአገር ንብረትና በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት እያደረሱ ነው የሚል ወቀሳ የሚሰነዝር ሲሆን፣ የሰመጉ ሪፖርት ግን ምርመራ ባካሄደባቸው አካባቢዎች እንዲህ ያለ ነገር አለመመልከቱን አስታውቋል፡፡

‹‹ማጣራት ባደረግንበት ሥፍራና ጊዜ ውስጥ በዓለም አቀፍ ብያኔ መሠረት አሸባሪዎች የምንላቸው ክፍሎች የአሸባሪነት ጥቃት ማድረሳቸውን አላየንም፡፡ እንዲሁም የታጠቁ ኃይሎች ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር ተኩስ ሲያደርጉ አላስተዋልንም፤›› በማለት የሰመጉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ብፅአተ ተረፈ አስረድተዋል፡፡

በክልሉ የተለያዩ ሥፍራዎች እየተካሄዱ ያሉ ተቃውሞዎች አሁንም በመካሄድ ላይ ያሉ በመሆናቸው በተቃውሞው የተገደሉ፣ የተጎዱ፣ የታሰሩና የወደሙ ንብረቶች ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ሰመጉ አስገንዝቧል፡፡

በዚህም የተነሳ ተቃውሞው በተካሄደበት ወቅት በምዕራብ አርሲ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት ማለትም የኦርቶዶክስ፣ የፕሮቴስታንትና የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸው በሪፖርቱ ከተካተቱ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡

ሰመጉ ከዚህ ቀደም በዚህ ጉዳይ ላይ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ከተቃውሞ እንቅስቃሴው ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መንግሥት በገለልተኛ አካል እንዲያጣራ፣ ለጥሰቱ ተጠያቂ የሆኑ አካላትን ለፍርድ እንዲያቀርብ፣ በግጭቱ ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ተገቢው ካሳ እንዲከፈል፣ እንዲሁም ቤቶቻቸው ለተቃጠሉባቸው፣ ንብረት ለወደመባቸውና ከኑሮአቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች መልሶ የማቋቋም ሥራ እንዲከናወን ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

አሁንም ጥሪውን አጠናክሮ በመቀጠል በተማሪዎችና በሕዝቡ ለቀረበው ጥያቄ በመንግሥት የተሰጠው መልስ በምንም መልኩና በማንኛውም መለኪያ በሰመጉ ተቀባይነት እንደሌለው፣ በተማሪዎችና በሕዝቡ በተቀሰቀሰው ሰላማዊ የተቃውሞ ሠልፍ ሰበብ የሕይወት፣ የአካልና የንብረት ጉዳት ያደረሱትና ጉዳቱ እንዲደርስ ያዘዙት ኃላፊዎች በአስቸኳይ ለሕግ እንዲቀርቡ፣ በተማሪዎችና በሕዝብ ሰላማዊ ሠልፍ ምክንያት የታሰሩት እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣ ግድያና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ግለሰቦችና ቤተሰቦች ተገቢው ካሳ እንዲከፈል በማለት በድጋሚ ጥያቄውን አቅርቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -