Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየመላ ኢትዮጵያ ጨዋታ ለዛ በሐዋሳ

የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታ ለዛ በሐዋሳ

ቀን:

የደቡብ ክልል መናገሻዋ ሐዋሳ ካደላት የተፈጥሮ መስህቧ ላይ ሰው ሠራሽ መስህብ እየጨመረች ትገኛለች፡፡ በተለይ ከሰሞኑ አምስተኛውን የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ውድድር የምታስተናግድበት ዘመናዊ ስታዲየም ለውበቷ ተጨማሪ መስህብ ሆኗታል፡፡ ይህ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘውና ማራኪው ስታዲየም ከዚህ ቀደም የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) የእግር ኳስ ሻምፒዮና በማስተናገድ ማሟሸቷ ይታወሳል፡፡ አሁን ደግሞ የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ከሚያካትታቸው የኳስና ሌሎችንም ስፖርታዊ ውድድሮች እያስተናገደ ይገኛል፡፡

ከአራት ሺሕ በላይ ስፖርተኞች ከመላ አገሪቱ የተሳተፉበት የዘንድሮው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች፣ ከዚህ ቀድሞ ከታዩት በተሻለ የኦሊምፒክ ጣዕምና ለዛ ያላቸው ስፖርት፣ ስፖርት የሚሸቱ አቀራረቦች የተንፀባረቁት ሆኖ ተጀምሯል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበባት ኮሌጅ ከአዲስ አበባ፣ ከደቡብ ዞኖችና ከራሱ ከሐዋሳ በተውጣጡ ወጣቶች አማካይነት ያዘጋጀው የድራማዊ ኮንሰርት መክፈቻ ይህንኑ ያረጋገጠ ነበር፡፡

እሑድ መጋቢት 4 ቀን 2008 ዓ.ም. በሐዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም የተጀመረው አምስተኛው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ለስፖርታዊ ውድድሮቹ ልዩ ድምቀት የሰጠው ‹‹አገር፣ ሰውና ስፖርት›› በሚል በመክፈቻው የቀረበው ድራማዊ ኮንሰርት፣ የመላ አገሪቱን ብሎም የክልሉን ሕዝቦችን በሦስት ክፍል ማለትም ልጅነት፣ ወጣትነትና አዋቂነት በሚልም ከፋፍሎ ያቀረበበት መንገድ የተሳታፊዎችን ቀልብ የሳበ ነበር፡፡

 ድራማዊ ኮንሰርቱን ያዘጋጀው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበባት ኮሌጅ መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር አቶ ነብዩ ባዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በድራማዊ ኮንሰርቱ በመጀመርያው ማለትም ልጅነት በሚለው ክፍል የቀረበው ሀ ሁ … የክልሉን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴና የአኗኗር ዘይቤን የተላበሰ ነበር፡፡ በሁለተኛውና ወጣትነት በሚለው ደግሞ በሰው ልጆች የዕድገት ደረጃ ወጣትነት ሁሉን አቀፍ በመሆኑ ይህን የጊዜ ዑደት በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስፈልግ የቀረበበት አግባብም መሳጭና ሳቢም ነበር፡፡ አዋቂነት በሚለው የመጨረሻ ክፍል የቀረበውም በተለይ አገሪቱ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አገር እንደመሆኗ ስፖርት ደግሞ ከዘር፣ ከሃይማኖት፣ ከጾታና ከመሳሰሉት የፀዳ በዚያው መጠን ለሰው ልጆች የሚሰጠውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ ፋይዳ ትልቅ የሆነበት ዘመን ላይ መድረሱን ያመላከተ እንደነበር ረዳት ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡

በዘመናዊና በክልሉ በሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ታጅቦ በቀረበው በዚህ ድራማዊ ኮንሰርት፣ ተሳትፎ ያደረጉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ከሐዋሳና ከክልሉ የተለያዩ ዞኖች በተውጣጡ ወጣቶች መሆኑን ያስረዱት ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ፣ ኮንሰርቱ የተዘጋጀው በሁለት ደራሲዎች፣ በሁለት አዘጋጆችና ሙዚቃ አቀናባሪዎች እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በመክፈቻው በቀረበው ድራማዊ ኮንሰርት ከተላለፉት መልዕክቶች በአገሪቱ ባለው እግር ኳሳዊ እንቅስቃሴን በሚመለከት በአሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው የቀረበው ይጠቀሳል፡፡ አቶ ሰውነት በመድረኩ ያስተላለፉት መልዕክት በተለይ ወጣቱ ‹‹ከጠባቂነት›› አስተሳሰብ መላቀቅ ይችል ዘንድ ጥረት ማድረግ እንዳለበት የሚያመላክት መሆኑ እንደተጠበቀ፣ ነገር ግን በዚህ የሰው ልጆች የሕይወት ዑደትና ስኬትን በሚያመላክተው ኮንሰርት ላይ ከእግር ኳሱ ይልቅ አትሌቲክሱን መነሻ ማድረግ ነበረበት የሚሉ አስተያየቶች ተደምጠዋል፡፡

ለቀረቡት አስተያየቶች ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ፣ ‹‹አስተያየቱ እውነትነት ያለው ብቻ ሳይሆን እኔም የማምንበት ነው፡፡ ነገር ግን አስተናጋጁ የደቡብ ክልል በዋናነት የሚታወቀው ከአትሌቲክሱ ይልቅ በእግር ኳሱ መሆኑ፣ ይህንኑ ለሚመለከተው ለክልሉ አንዳንድ አካላትና ተጨዋቾችም አቅርበን የተስማሙበት በመሆኑ ነው የቀረበው፤›› ብለዋል፡፡ ለድራማዊ ኮንሰርቱ የወጣውን ወጪ በተመለከተ ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ በመክፈቻው የቀረበው ዝግጅት እስከ መዝጊያው የሚቀጥል ስለሚሆን ትክክለኛውን አኃዝ አሁን ላይ መናገር እንደማይቻልም ተናግረዋል፡፡

በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ መለሰ ዓለሙ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኔ ኪዳነማርያም ሌሎችም ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡ በዕለቱ በተላለፈው መልዕክትም በየዓመቱ የሚከናወነው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች መንግሥት ለወጣቱና ለስፖርቱ ከሰጠው ትኩረት ጎን ለጎን በአገሪቱ በተደጋጋሚ ሲነገር ለቆየው የማዘውተሪያ እጦት መልስ በመስጠትም ዓይነተኛ ድርሻውን በመወጣት ላይ መገኘቱ ተመልክቷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...