በ2.5 ሚሊዮን ብር እየተደረገ የነበረው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ማስፋፊያ ተጠናቀቀ፡፡ ማስፋፊያ የተደረገው ለድንገተኛ የአዋቂዎች ሕክምና ክፍል ሲሆን በቦታ ጥበት ታካሚዎች ላይ ይደርሱ የነበሩትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በተወሰነ መልኩ ይፈታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል፡፡ በ340 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው የተንጣለለው ቤት የሕሙማን መቆያ ቦታ፣ የምርመራ ክፍል፣ የሕሙማን ደረጃ መለያ ክፍል፣ አልትራሳውንድ፣ ቀላል ምርመራ፣ ሕሙማን ተለይተወ የሚታከሙበት ክልፍ ሌሎችም ደጋፊ ክፍሎችን አካትቷል፡፡ በራሱ ወጪ ሕንፃውን ያስገነባው ተክለ ብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ድርጅት ሲሆን፣ ማክሰኞ መጋቢት 6 ቀን 2008 ዓ.ም. በቅጥር ግቢው የርክክብ ሥነ ሥርዓት ተፈጽሟል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የድንገተኛ ሕክምና ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር አክሊሉ አዛዥ እንደሚናገሩት ሆስፒታሉ ሲገነባ የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎትን ከግምት ውስጥ ያስገባ አልነበረም፡፡ በቂ የሕክምና ክፍልም አልተሰጠውም፡፡ በመሆኑም በርካታ ሰዎች በጠባብ ክፍል ውስጥ በተጨናነቀ መልኩ እንዲታከሙ፣ የተለያዩ ምርመራዎች የሚሰጡት የታካሚዎችን ግለኝነትን በሚጋፋና ምቾት በሚነሳ መልኩ ነበር፡፡
ግንባታው ያለውን ችግር እስከ 50 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል ከሰኞ መጋቢት 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮም አስፈላጊው የሕክምና ቁሳቁስ እየገባ እንደሚገኝ እና ሥራ መጀመሩንም አክለዋል፡፡
የግንባታ ተቋራጩ እዚያው ሆስፒታሉ ውስጥ ተጨማሪ የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት መስጫ ሕንፃ በ220 ሚሊዮን ብር እያስገነባ ይገኛል፡፡ ግንባታውም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የታፍ ኮርፖሬት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፉ አምባዬ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሕንፃውን መገንባት የጀመርነው በሆስፒታሉ ያለውን የድንገተኛ ሕክምና ክፍል እጥረት ተመልክን ነው፤›› የሚሉት ሥራ አስፈጻሚው ይህ ተቋሙ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አኳያ የሠራው ሥራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
‹‹ችግሩን እኔ ራሴ ዓይቼው ቢሆን የተደረገውን የግንባታ ሥራ በእጥፍ አሳድገው ነበር፤›› ያሉት የታፍ ኮርፖሬት ግሩፕ ፕሬዚዳንት አቶ ተክለብርሃን አምባዬ ድርጅቱ ተጨማሪ ድጋፎችን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የድንገተኛ ህመም ሕክምና የአገሪቱ የጤና አገልግሎት ዘርፍ ትልቅ ራስ ምታት ሆኖ ለዓመታት ዘልቋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ይህን ችግር ለመፍታት የተለያዩ ጥናቶች ተደርገዋል፡፡ ጥረቶቹ ያስገኙት ለውጥ ቢኖርም ችግሩ ግን ችግር ሆኖ መቀጠሉ ይታያል፡፡ የድንገተኛ ሕክምና አሰጣጥ አገልግሎቶችን ማሻሻል ከሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መካከል ነው፡፡ ሁሉም የጤና ተቋማትም የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡ የባለሀብቶችና የተለያዩ ተቋማት እገዛም ክፍተቶች ለመሙላትና የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የኢመርጀንሲ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ህሊና ኃይሉ ተናግረዋል፡፡
ከአምስት አሠርታት በፊት በሕዝብ መዋጮ በ22 ሚሊዮን ብር የተገነባው ሆስፒታሉ በአገሪቱ ብቸኛ ሪፈራል ሆስፒታል ሆኖ ለዓመታት አገልግሏል፡፡ ዛሬም ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከባድ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች ወደ ሆስፒታሉ ይመጣሉ፡፡ ሁኔታው ለሆስፒታሉ ከባድ ጫና ሆኗል፡፡ በዚህም ከሚያጋጥሙት ችግሮች መካከል የመታከሚያ ክፍሎችና የአልጋ እጥረት ዋነኞቹ ናቸው፡፡ እንዳደረገው ልክ ታፍ ኮርፖሬት የተለያዩ ተቋማትና ባለሀብቶች እገዛ ቢያደርጉ አሁን ያለውን የአልጋ ቁጥር በ1/3 መጨመርና ሕክምናውን ተደራሽ ማድረግ እንደሚቻል በጤና ሳይንስ ኮሌጅና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ዋና ኃላፊ ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃን ገልጸዋል፡፡