Friday, September 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልከሩሲያ ኢትዮጵያ የዘለቀው ‹‹የሌሊት ተኩላዎች›› የሰላም ጉዞ

ከሩሲያ ኢትዮጵያ የዘለቀው ‹‹የሌሊት ተኩላዎች›› የሰላም ጉዞ

ቀን:

ዩሪ ቮልኮቭ እና ኢሊያ ዳቢኒየን ሩሲያውያን ሲሆኑ፣ ናይት ውልቭስ (የሌሊት ተኩላዎች) የተሰኘ የሞተር ብስክሌት ክለብ አባላት ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1989 የተመሠረተው ክለባቸው ከ5,000 በላይ አባሎች አሉት፡፡ የክለቡ አባላት ባጠቃላይ ወንዶች ሲሆኑ፣ ወደተለያዩ አገሮች በመሄድ ስለ ሰላምና ፍቅር፣ መቻቻልና አንድነት መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡ ከአንድ አገር ወደ ሌላ ሲዘዋወሩ አብዛኛው ጉዟቸው በሌሊት ስለሚካሄድ የሌሊት ተኩላዎች የሚለውን ስያሜ ለራሳቸው ሰጥተዋል፡፡ ተኩላ በሩሲያ የጥንካሬ ተምሳሌት ከሆኑ እንስሳት አንዱ ነው፡፡ እነሱም ክለባቸው የጥንካሬ ተምሳሌት እንደሆነ ያምናሉ፡፡

ባለፈው ኅዳር ወር ዩሪ እና ኢሊያ መላው አፍሪካን በሞተር ብስክሌት ለመዞር ጉዟቸውን ከሩሲያ ጀመሩ፡፡ ወደ አምስት ወራት በወሰደው ጉዟቸው 33 የአፍሪካ አገሮችን አቆራርጠው ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ ደርሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ እንደደረሱ በቅድሚያ ያመሩት ወደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነበር፡፡ ከሩሲያ ሲነሱ ካነገቡት ዓላማ አንዱ ለቤተ ክርስቲያኗ ምስል (አይቀን) ማበርከት ነበር፡፡

መጀመሪያ ወደ ሁለት ቤተ ክርስቲያኖች አመሩ፡፡ ከዛም ወደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ሄደው ሉሲን ጎበኙ፡፡ በአሌክሳንደር ፑሽኪን ሐውልት ስርም እቅፍ አበባ አኑረዋል፡፡ ምስሉ የቅዱስ ሰርጌስ ሲሆን፣ የተረከቧቸው ብፁዕ ዶ/ር አቡነ ጢሞቴዎስ ከዓመታት በፊት በሩሲያ ተምረዋል፡፡ ዘንድሮ በሩሲያ 700ኛው ዓመት የሚከበርለት ቅዱስ ሰርጌስ ከኢትዮጵያው ቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ጋር የሚነጻጸር ነው፡፡ ምስሉን ለኢትዮጵያ እንዲያስረክቡ የጠየቃቸው በሩሲያ ዘጎርስክ ከተማ የሚገኝ ገዳም ሲሆን፣ የገዳሙ አባቶች መርቀዋቸው አይቀኑን ለኢትዮጵያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡

‹‹በሩሲያና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ወዳጅነት የተንፀባረቀበት ርክክብ ነበር፤›› ይላል ኢሊያ፡፡ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ወደ ደቡብ አፍሪካና ዑጋንዳ የተላኩ የቤተ ክርስቲያን መገልገያዎችም ነበሩ፡፡ ደቡብ አፍሪካ ለሚገኝ አንድ የሩሲያ ቤተ ክርስቲያን ምስል ሰጥተዋል፡፡ ዑጋንዳ በቪክቶሪያ ሐይቅ የሚገኝ አንድ ቤተ ክርስቲያን በችግር ላይ ስላለ ከሩሲያ ቤተ ክርስቲያን መስቀሎችና ሌሎችም መገልገያዎች ተልኮም አስረክበዋል፡፡

ዩሪ እና ኢሊያ የአፍሪካ ጉዟቸው ብዙ ተልዕኮዎች እንደያዘ ይናገራሉ፡፡ በሃይማኖት ረገድ በኢትዮጵያና ሩሲያ መካከል ጥብቅ ትስስር እንዳለ ይገልጻሉ፡፡ በሁለቱ አገሮች ዜጎች መካከል ያለው የማኅበራዊ እሴቶች መመሳሰል በሥነ ጽሑፍ ሥራዎችም ይንፀባረቃል፡፡ ዩሪ ‹‹ኢትዮጵያ ስንደርስ ልዩ ስሜት የተሰማን በሁለቱ አገሮች ያለው ትስስር የጠበቀ በመሆኑ ነው፤›› ይላል፡፡

ሩሲያ ውስጥ ጤናማ ስለሆነ የአኗኗር ዘይቤ በማኅበረሰቡ ዘንድ ግንዛቤ ለመፍጠር ከቦታ ቦታ በመዘዋወር ነዋሪዎችን ያነቃቃሉ፡፡ ወደ አፍሪካ የመጡትም ተመሳሳይ ዓላማ አንግበው ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የሞተር ብስክሌት ክለቡ አባላት ወደ ተለያዩ አኅጉሮች ተጉዘዋል፡፡ ተራ የደረሳቸው ዩሪ እና ኢሊያ ወደአፍሪካ ሲመጡ የመጀመሪያቸው ነው፡፡

በአፍሪካ አገሮች ሲዘዋወሩ ከባህል፣ ከኪነ ጥበብ፣ ከስፖርት፣ ከሳይንስና ከሌሎችም ተቋሞች ጋር ተገናኝተዋል፡፡ በሚያልፉባቸው አገሮች በአጋጣሚ ከሚያገኗቸው ሰዎች ጋርም አጠር ያለ ቆይታ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡ ኢሊያ በተለይም ወጣቶች ቀና፣ ጤናማና ሰላማዊ ሕይወት እንዲመሩ ማነሳሳት ከክለቡ ዓላማዎች አንዱ ነው ይላል፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ሲዘዋወሩ በተለይ በገጠራማ አካባቢዎች ካሉ ነዋሪዎች ጋር የነበራቸው ቆይታ አስደሳች እንደነበር ያክላል፡፡

ሞተር ብስክሌት ጥንካሬን፣ ክብርን፣ ወጣትነትና ወዳጅነትን እንደሚወክልና ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር ምቹ በመሆኑም እንደመረጡት ይገልጻል፡፡ በተለያዩ አገሮች የሞተር ብስክሌት ክለቦች አሉ፡፡ እነዚህ ክለቦች በአብዛኛው ከአመፅ፣ ከአደገኛነትና ከማኅበረሰቡ መገንጠል ጋር ሲያያዙ ይስተዋላል፡፡ የሌሊት ቀበሮዎች ከዚህ በተቃራኒው እንደሆኑ ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡

ወደ አፍሪካ ያደረጉት ጉዞ መነሻውን ያደረገው ሩሲያዊው ጠፈርተኛ ዩሪ ጋጋሪ ወደ ህዋ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጠቀበትን 55ኛ ዓመት ማክበርን ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ በህዋ ሳይንስ ዙሪያ ከሚሠሩ ወጣቶች ጋር ተገናኝተዋል፡፡ የፊታችን ሚያዝያ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ለሚከበረውን የዩሪ ጋጋሪ ክብረ በዓል በየአገሩ ያለውን ዝግጅት አይተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም በህዋ ሳይንስ ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ ወጣቶች ካሉበት ስፔስ ጄኔሬሽን አድቫይዘሪ ካውንስል ጋር ተገናኝተዋል፡፡

በዓሉን ለማክበር ሽር ጉድ ከሚለው ከዚህ ድርጅት በተጨማሪ የሩሲያ የባህልና የሳይንስ ማዕከል (ፑሽኪን) በየዓመቱ የዩሪ ምሽት ያከብራል፡፡ ዩሪ እና ኢሊያንም ያገኘናቸው በፑሽኪን ማዕከል ውስጥ ነበር፡፡ ዓርብ መጋቢት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በማዕከሉ ካነጋገርናቸው በኋላ ከአዲስ አበባ ባህር ዳር ከተማ ከዛም ወደ ሌሎች አገሮች ለመሸጋገር እየተዘጋጁ ነበር፡፡ የዩሪን በዓል በሩሲያ ለማክበር እንዳቀዱ ይናገራሉ፡፡

የሌሊት ተኩላዎች የሞተር ብስክሌት ክለብ የሚመራው አሌክሳንደር ሒሩክ በተባለ ሩሲያዊ ነው፡፡ ክለቡ በሩሲያ ታዋቂ ሲሆን፣ በአገሪቱ ካሉ የሞተር ብስክለት ክለቦች ትልቁ ከመሆኑ ባሻገር በተለያዩ አገሮች ተመሳሳይ ተልዕኮ ካላቸው ክለቦች ጋር በቅርበት ይሠራሉ፡፡ በአውሮፓ፣ በእስያና በኢንዶኔዥያ ደግሞ ተመሳሳይ ክለቦች መሥርተዋል፡፡ ዩሪ ‹‹በየአገሩ ስንዞር ወጣቶችን ስለጠንካራ የሕይወት አመራር እናነቃቃለን፡፡ የሰላምና የአገር ወዳድነት መልዕክትም እናስተላልፋለን፤›› በማለት ስለክለባቸው ይገልጻል፡፡

ክለባቸው በሩሲያ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በሚያደርገው ተሳትፎ ይታወቃል፡፡ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ያላቸው ወዳጅነት የብዙዎችን ትኩረት ይስባል፡፡ ከፑቲን ጋር ወዳጅ ቢሆኑም እንደ ጀርመንና ፖላንድ ያሉ አገሮች ደግሞ ወደ አገራቸው እንዳይገቡ ከልክለዋቸዋል፡፡

በተጓዦቹ እምነት፣ ስለ አፍሪካ ቁንጽል አንዳንዴም የተሳሳተ ምልከታ ያላቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ኢሊያ ስለ አፍሪካ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሁኔታ የሰማውና በዕውን ያስተዋለው እንደሚለያይ ይገልጻል፡፡ ‹‹በየአገሩ የተሰማኝ ስሜት ልዩ ነበር፡፡ ብዙ አዳዲስ ነገሮች አይተናል፡፡ ከቴሌቪዥን መርሐ ግብሮች ባለፈ ስለ አፍሪካ ለመረዳት ችያለሁ፤›› ይላል፡፡

ዩሪም በመገናኛ ብዙኃን ከሚያውቀው አፍሪካ የተለየ እውነታ እንደተመለከተ ይናገራል፡፡ ‹‹ስለአፍሪካውያን ሲነገር ደን ውስጥ የሚኖሩ ሥልጣኔ ያልገባቸው እንደሆኑ ዓይነት ይደረጋል፡፡ እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው፤›› ይላል፡፡ በየአገሩ ዜጎች የተደረገላቸውን መልካም አቀባበልም ያነሳል፡፡ የተዛባ አመለካከት ያለው ስለ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን ስለ ሩሲያ ጭምርም እንደሆነ ይናገራል፡፡ ‹‹ሩሲያ ከበረዶና ከእንስሳት ውጪ ያለ የማይመስላቸው አሉ፡፡ የሩሲያ ስም ሲነሳ ዘወትር ከኒውክሊየር ቦምብ ጋር አያይዘው የሚናገሩ ሰዎች ገጥመውናል፤›› ይላል፡፡

በተቃራኒው በጉዟቸው በተለያዩ አገሮች ለሩሲያ ልዩ ፍቅር ያላቸው ሰዎችም ገጥመዋቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያገኙት አንድ ሾፌር የሩሲያ ሙዚቃ አዘውትሮ ይሰማል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ የሞተር ስፖርት ክለብ አባላት አግኝተው ነበር፡፡ በክለቡ ቀደምት የሩሲያ ሞተር ብስክሌት መለዋወጫዎች ያሉት ሰው ገጥሟቸዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካና በሌሎችም አገሮች የድሮ የሩሲያ የውጊያ መኪናዎች እንዲሁም የሩሲያ ባህል መገለጫ የሆኑ ቁሳቁሶች የሚያሰባስቡ ግለሰቦች ተመልክተው ለአገራቸው ባላቸው ፍቅር ተገርመዋል፡፡

ጉዞው ግን አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ የከፋ መሰናክል ባይገጥማቸውም አንዳንድ ችግሮች ነበሩ፡፡ እንደ ደቡብ ሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ያሉ አገሮችን ማለፍ ቀላል አልነበረም፡፡ ኢሊያ ‹‹አብዛኞቹ ጉዞዎቻችን በፈተና የተሞሉ ስለሆኑ ችግርን ተላምደናል፤›› ይላል፡፡ ከጊኒ ወደ አይቮሪኮስት ለመሻገር ድንበር ላይ ችግር ገጥሟቸው ነበር፡፡ በሌሎች አገሮችም ከድንበር ድንበር ማለፍ፣ የመልክዓ ምድር ውጣ ውረድና፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት ቢገጥማቸውም ተጋፍጠውታል፡፡

ዩሪ አስቸጋሪ ነገሮች ሲገጥሟቸው አስከትሎ የሚመጣውን አስደሳች ነገር በማሰብ እንደሚፅናኑ ይናገራል፡፡ ‹‹ለምሳሌ በታንዛኒያ ስናልፍ በኪሊማንጃሮ ተራራ በኩል ነበር፡፡ የተራራውን ግርማ ሞገስ ስናየው አልፈነው መሄድ አልቻልንም፡፡ ተራራውን ወጣን፤›› ይላል የተሰማቸው ሐሴት ፊቱ ላይ እየተነበበ፡፡

ሁለቱም ባለትዳርና የልጆች አባት ናቸው፡፡ በአንድ አህጉር ውስጥ ለረዥም ወራት ሲጓዙ የመጀመሪያቸው ነው፡፡ ኢሊያ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች ማምረቻ ፋብሪካ አለው፡፡ ዩሪ ደግሞ የሬስቶራንት ባለቤት ነው፡፡ ለጉዟቸው ቢዝነሳቸውን ገታ ቢያደርጉትም ደስተኛ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ ዩሪ ‹‹ቤተሰቦቻችንና አገራችን ቢናፍቁንም የጉዞው አስደሳችነት አፅናንቶናል፤›› ይላል፡፡ በተለያየ አኅጉር ባሉ አገሮች ዜጎች መካከል ያለው አመለካከት፣ ዝንባሌና አኗኗር ተመሳሳይነት የሰው ልጆችን ትስስር እንደሚያሳይ ሁለቱም ይናገራሉ፡፡

በጉዟቸው የተነሱለትን ዓላማ እንዳሳኩ ያምናሉ፡፡ በተለያዩ አገሮች ከየማኅበረሰቡ ጋር በነበራቸው ቆይታ መልዕክታቸውን እንዳስተላለፉ ይናገራሉ፡፡ 33ኛው የጉዞ መዳረሻቸው ኢትዮጵያን አልፈው ጉዟቸውን ወደ ሱዳን ቀጥለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...