Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየአሜሪካን የምርጫ ፖለቲካ ትርምስ ውስጥ የከተቱት ዶናልድ ትራምፕ

የአሜሪካን የምርጫ ፖለቲካ ትርምስ ውስጥ የከተቱት ዶናልድ ትራምፕ

ቀን:

በአሜሪካ እ.ኤ.አ. በ2016 ለሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዕጩ ለመሆን የሪፐብሊካን ፓርቲን ለመወከል ዘመቻ ላይ የሚገኙት አወዛጋቢው ዶናልድ ትራምፕ፣ የአሜሪካን የምርጫ ባህል በስድብና ባልተገቡ ቃላት በመመረዝና ቢመረጡ የነገዋን አሜሪካ ምን እንደሚያደርጓት መነጋገሪያ ሆነዋል፡፡ በአፍሪካውያን፣ በላቲኖች፣ በሙስሊሞችና በሌሎች ላይ ከሚሰነዘሩት መረን የለቀቀ ንግግር በተጨማሪ አብረዋቸው የሚወዳደሩትን በማንጓጠጥና ያልተገባ ባህሪ በማሳየት የሚታወቁት ትራምፕ በአሜሪካ በርካታ ደጋፊዎችን ማፍራታቸው አስገራሚ ሲሆን፣ በዓለም ዙሪያ ግን በጥላቻ ስማቸው እየነሳ ነው፡፡ በሪፐብሊካን ፓርቲ ውስጥም ክፍፍል እየፈጠሩ ነው፡፡

ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በሪፐብሊካን ፓርቲ የፕሬዚዳንታዊ ዕጩዎች ፉክክር የታዩ ለውጦች አሉ፡፡ ትራምፕ ቀንቷቸው የሪፐብሊካን ዕጩ ተወዳዳሪ ቢሆኑ አይደግፏቸውም የሚባሉ ተፎካካሪዎች የፓርቲ መሪዎች አሉ፡፡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ባለፈው ሳምንት የሪፐብሊካን ዕጩ ተወዳዳሪዎች በመጨረሻ የፓርቲው ተወዳዳሪ የሚሆነውን ሰው ለመደገፍ ተስማምተው የነበረ ቢሆንም፣ ይህ ስምምነታቸው ከጥቂት ሰዓታት በላይ መዝለቅ አልቻለም፡፡

ላለፉት ጥቂት ቀናት በሪፐብሊካን ፓርቲ ውስጥ የታየው ለውጥ ምናልባትም ጉልህ ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ትልቅ ተፅዕኖ እንደሚኖረው እየተገለጸ ነው፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ሳምንት ዓርብ ትራምፕ በቺካጎ ትልቅ የምረጡኝ ቅስቀሳ ፕሮግራም አዘጋጅተው ነበር፡፡ ፕሮግራሙ ላይ ለመገኘት በርካታ ሰዎች የተሠለፉት ማልደው ነበር፡፡ ከእነዚህ ሰዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቢሆኑም፣ እዚያ ቦታ የተገኙት ዶናልድ ትራምፕን ለመደገፍ ሳይሆን፣ የሪፐብሊካን ፓርቲ ፊታውራሪ ሆነው በዘንድሮው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ መወዳደራቸውን ለመቃወም ነበር፡፡ እነዚህ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች እዚያ ቦታ ላይ በመገኘት እንዲታዩ ድምፃቸውም በደንብ እንዲሰማ አድርገዋል፡፡ በመጨረሻ ሁኔታው በግልጽ የገባቸው የትራምፕ የምረጡኝ ቅስቀሳ አስተባባሪዎች ፕሮግራሙን ለመሰረዝ ሲገደዱ፣ የትራምፕ ደጋፊዎችና የትራምፕ ዕጩ መሆንን ለመቃወም የተገኙ ፕሮግራሙ ሊካሄድበት የነበረውን አዳራሽ ለቅቀው ሲወጡ ፍጥጫ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ ፍጥጫውና የቃላት ጦርነቱ አይሎ እነዚህ ሁለት ወገኖች ድብድብ ውስጥ ገብተውም ነበር፡፡ ፖሊስ ሁኔታውን ለመቆጣጠር ቢሞክርም አምቧጓሮው ጎዳና ላይ መውጣቱ አልቀረም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አንድ የአሜሪካ ቴሌቪዥን ሁኔታውን ለአመፅ ጥቂት የቀረው ቢለውም፣ ብዙዎች ግን ከፍተኛ ቁጣ የተሰማበት ትንሽ ግጭት ብለውታል፡፡ የተፈጠረውን ችግር በማስመልከት የትራምፕ ተቀናቃኝ የሆኑት የቴክሳሱ ሴናተር ቴድ ክሩዝ ድርጊቱ በአገሪቱ ትልቅ ቦታ ያለውንና የዜጎችን ነፃነት የሚያረጋግጠውን ‹ፈርስት አመንድመንት› መፃረር ነው ብለዋል፡፡ ቢሆንም ግን ትራምፕንም ነቅፈዋል፡፡ ለተፈጠረው ነገር ትራምፕም በሚገባ አስተዋጽኦ አድርገዋል በማለት ድምፅ ሰጪዎችን የማያከብርና በስውር አመፅን የሚያበረታታ የምረጡኝ ቅስቀሳ መከተል ውጤቱ የታየው ዓይነት መሆኑን ተናግረዋል ቴድ ክሩዝ፡፡ ክሩዝ ትራምፕ ለመገናኛ ብዙኃን ያልተመቹ መሆናችውንም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የሪፐብሊካን ዕጩዎች የመጨረሻ ክርክር ዕጩዎች ምንም ይሁን ምን በመጨረሻ ፓርቲውን የሚወክለውን ተወዳዳሪ ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ሲጠየቁ መልሳቸው አንድ ዓይነት ነበር፡፡ ስምምነታቸውንም ገልጸው ነበር፡፡ ከ48 ሰዓት በኋላ ግን በዕጩዎቹ የአቋም ለውጥ መታየት ጀመረ፡፡ ማርኮ ሩቢዮ የተባሉት ዕጩ ተወዳዳሪ ዶናልድ ትራምፕ የሪፐብሊካን ዕጩ ለመሆን ቢያሸንፉ ሊደግፏቸው መቻላቸውን እንደሚጠራጠሩ ለመገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል፡፡ ዕለት በዕለት የዶናልድ ትራምፕ ነገር እየከበዳቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት በዚህኛው የሪፐብሊካን ፓርቲ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩዎች ፉክክር አካሄድ የሚስተዋሉት ችግሮች ፓርቲው በተለየ አቅጣጫ እየሄደ ነው? የሚል ጥያቄ ለማንሳት የግድ የሚል ነው፡፡ ፓርቲው የተለየ ሐሳብ የማንፀባረቅና የተለየ አማራጭ የማቅረብ አቅሙንስ ይዞ እየተጓዘ ነው ወይ? የሚል ጥያቄም በብዙዎች እየተነሳ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ስለዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወይም ስለሪፐብሊካን ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ስለአሜሪካ ፖለቲካ ብዙ የሚለው እንዳለ እየተነገረ ነው፡፡

የኦሀዮው ገዥ ጆን ኬሲክ የምረጡኝ ቅስቀሳ የተረጋጋና ፀጥ ያለ ነው፡፡ እሳቸውም ትራምፕ የሚያሸንፍ ከሆነ የሪፐብሊካንን ጉዞ እስከ መጨረሻው መደገፍ ከባድ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ ባደረጉት አንድ ቃለ ምልልስ ሚሊየነሩ የቢዝነስ ሰው ትራምፕ ለፕሬዚዳንትነት ብቁ ናቸው ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል በሪፐብሊካን ፓርቲ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያላቸው ሁለት ፖለቲከኞች ፓርቲውን እስከ መጨረሻው ስለመደገፍ ተጠይቀው በሰጡት መልስ፣ የትራምፕ ወደ ላይ መምጣት በፓርቲው ውሰጥ ያለመመቸት ስሜት መፍጠሩን ነው የተናገሩት፡፡ ይህ ጉደይ ትልቁን ፓርቲ ሊከፍለው እንደሚችልም ብዙዎች አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው፡፡ ቀደም ሲልም የትራምፕ የምረጡኝ ቅስቀሳ ዘዬ አቀራረባቸውም ጭምር በአሜሪካ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ፖለቲካ ገጽታ ላይ አሉታዊ ለውጦችን ማምጣቱን የሚጠቅሱም አሉ፡፡

የሪፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊዎችና የፓርቲው መሪዎች ማንም ያሸንፍ ማንም ፓርቲውን የሚወክለውን ሰው መደገፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል አሸናፊ የሚሆነው ዕጩ ፓርቲውን ለመወከል የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለመሆንም ምርጥ የሚባለው መሆን አለበት፡፡ የዕጩዎች ፉክክር ግማሽ መንገድ በደረሰበት በአሁኑ ወቅት ግን፣ የፓርቲው ደጋፊዎችና መሪዎች መስቀለኛ መንገድ ላይ መሆናቸው እየተነገረ ነው፡፡ በፓርቲው ትኬት ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር ደግሞ ከሦስቱ ተፎካካሪዎቻቸው ትራምፕ በተሻለ አቋም ላይ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ከዚህ ወዲህ ያለው ቀሪ መንገድ ለትራምፕ ከባድ እንደሚሆን እየተጠቆመ ነው፡፡ ሪፐብሊካን ፓርቲ ከትራምፕ ይልቅ በሌላ ዕጩ እንዲወከል የሚፈልጉ ያላቸው ጊዜ አጭር ቢሆንም፣ ዋናውን ምርጫ የማሸነፍ የተሻለ ዕድል ያለው ለአገሪቱም ጥሩ መሪ ይሆናል የሚሉት ሰው ወደ ላይ እንዲመጣ የቻሉትን ከማድረግ የሚቆጠቡ እንደማይመስሉ እየተገለጸ ነው፡፡ የትራምፕ ደጋፊዎች ትራምፕን ለመደገፍ እየታገሉ እንዳሉት ሁሉ ትራምፕን ለመጣል የሚደረገው የእነዚህ ወገኖች ትግልም ምንም ችግር እንደሌለበት፣ ይልቁንም የሚጠበቅ መሆኑን አስረግጠው የሚናገሩ አሉ፡፡

ሪፐብሊካን ፓርቲን በመደገፍና ዶናልድ ትራምፕን በመደገፍ መካከል እየታየ ያለው ሁኔታ በአሜሪካ ፖለቲካ የተለመደ የሚባል አይደለም፡፡ ዶናልድ ትራምፕ አሁን እየሄዱ ባለበት መንገድ ቀጥለው በሪፐብሊካን ትኬት ፕሬዚዳንታዊ ተፎካካሪ የሚሆኑ ከሆነ ደግሞ፣ በአገሪቱ ፖለቲካ የማይጠበቁ ብዙ ነገሮች መምጣታቸው የማይቀር ይሆናል፡፡ ፓርቲውን በመደገፍና ትራምፕን በመደገፍ መካከል ያለው ልዩነት እንዴት ይታረቃል? የሚለው ዋናው ጥያቄ ይሆናል፡፡ የትራምፕ ዕጩ ተወዳዳሪ መሆን እርግጥ ሲሆን፣ የፓርቲው መሪዎች ምን ያደርጋሉ? እ.ኤ.አ. በ1980 ለማይወዷቸውና ለፓርቲው እንግዳ አድርገው ይመለከቷቸው ለነበሩት በመጨረሻ ግን የፓርቲው ጀግና ለሆኑት ሮናልድ ሬገን ድጋፍ እንደሰጡት ለትራምፕም እንዲሁ ያደርጋሉ? ወይስ እ.ኤ.አ. በ1964 ፀረ ጎልድዋተር የሪፐብሊካን ፓርቲ መሪዎች ለፓርቲው ሽንፈት ይሠራሉ? የሚሉ ዓይነት ጥያቄዎች እየተነሱ ነው፡፡

ሪፐብሊካን እንዴት ዶናልድ ትራምፕ ፊታውራሪያቸው እንዲሆኑ ይመርጣሉ? በማለት ጠንካራ ትችትና ትንታኔ የሚሰጡ ጥቂት አይደሉም፡፡ ብዙዎቹ ከሚያነሱት ነጥብ ተመሳሳይ የሆነ አንድ ነገር አለ፡፡ ፓርቲው ከኮሚዩኒዝም እስከ ሽብርተኝነት ጉዳይ በያዘው አቋም ከደጋፊዎቹና ከመሪዎቹም የልብ ትርታ ውጪ ሆኖ እንደማያውቅ፣ የዶናልድ ትራምፕ የፓርቲው ዕጩ ሆኖ በፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ተወዳዳሪ የመሆን ነገር ግን በየትኛውም መንገድ ለመቀበል የሚቸግር እንደሆነ በግልጽ ያስቀምጣሉ፡፡ ትራምፕ ሁሉንም ነገር፣ ሁሉንም የፓርቲውን ፖለቲካዊ አመለካከት ትክክል ነው ተብሎ በፓርቲው የሚታመንበትን ባህሪ ጭምር መለወጣቸውንም ይገልጻሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...