Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ያልታጣጣመው የሕንፃ ግንባታና የከተማ ገፅታ

የኮንስትራክሽን ዘርፍ በአጭር ጊዜ ካሳየው ለውጥና ወደፊትም እንዲያስመዘግብ ከተቀመጠለት አገራዊ ግብ አንፃር ከዲዛይን ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከግንባታ መሣሪያዎች፣ ግብአት አጠቃቀም፣ ከከተማ ውበትና ተስማሚነት አንፃር የተሻለ እንዲሆን ልዩ ልዩ የደረጃ መሥፈርቶችና መመርያዎች እየወጡ ነው፡፡ የተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትም ለዘርፉ ዕድገት የበኩላቸውን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የአካባቢ፣ የዲዛይን፣ የከተማ ፕላንና የኮንስትራክሽን የማብቃት ማዕከል አንዱ ነው፡፡ ድርጅቱ ከተቋቋመ ሦስት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ የተለያዩ ሥራዎችንም ሲሠራ ቆይቷል፡፡ አጠቃላይ የድርጅቱን እንቅስቃሴና በኮንስትራክሽን ዘርፉ ስለሚስተዋሉ አንዳንድ ጉዳዮች የተቋሙን ሥራ አስኪያጅ አቶ መንገሻ ኃይለ መለኮትን ሻሂዳ ሁሴን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ የተቋቋመበት ዓላማ ምንድነው?

አቶ መንገሻ፡- የዚህ ማዕከል ዓላማ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ልህቀት ለመገንባት የሥልጠና፣ የምርምርና የልማት ማዕከል ሆኖ ማገልገል ሲሆን በአካባቢ ጥበቃ፣ በዲዛይን፣ በከተማ ፕላንና በኮንስትራክሽን ላይ ያተኮሩ አጫጭር ሥልጠናዎች ለፌዴራል፣ ለክልል ከተሞች ለተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች ይሰጣል፡፡ እስካሁን 20 የሚሆኑ የተለያዩ ሥልጠናዎችና ሴሚናሮችም የተዘጋጁ ሲሆን፣ 1,000 የሚሆኑ ዜጐች ሥልጠናውን ማግኘት ችለዋል፡፡ ከአገር ውጪና ከአገር ውስጥ የትምህርትና የምርምር ተቋማት ጋር በመተባበርም የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የትምህርትና የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በነፃ ይሰጣል፡፡ በአካባቢ፣ በዲዛይን፣ በከተማ ፕላንና በኮንስትራክሽን ዙሪያም የተለያዩ የምርምር ሥራዎች ይሠራል፡፡ በግንባታ ዙሪያ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ልዩ ልዩ መረጃዎችን የተለያዩ የመገናኛ አውታሮችን በመጠቀም ለማኅበረሰቡ ያደርሳል፡፡ የማማከር ሥራም ይሠራል፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ከፍተኛ የትምህርት፣ የምርምር ተቋማትና የሙያ ማኅበራትን በማቀራረብ የግንኙነት መረብ ይፈጥራል፡፡ በዚህም የልምድና የዕውቀት ልውውጥ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሌሎች ተቋማት ጋር ያላችሁ ትብብር ምን ይመስላል?

አቶ መንገሻ፡- በተለያዩ ጉዳዮች እንደመሥራታችን ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር አብረን እንሠራለን፡፡ ለምሳሌ ከተለያዩ የግንባታ ቢሮዎች፣ ከከተማ ልማት መሥሪያ ቤቶች፣ በአካባቢ ጥበቃ ላይ ከሚሠሩ ድርጅቶች፣ ከማዘጋጃ ቤቶች እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከሙያ ማኅበራት ከኢትዮጵያ ሕንፃ ተቋራጭ ማኅበር፣ ከኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኅበርና ከመሳሰሉት የሙያ ማኅበራት ጋር እንደየአግባቡ አብረን እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከአዲስ አበባ ውጪ በሌሎች ከተሞች ላይ በቅርቡ የሠራችሁ ሥራ አለ?

አቶ መንገሻ፡- በቅርቡ የኮንስትራክሽን ኮንትራት አድሚኒስትሬሽን በሚል ለድሬዳዋ ከተማ ሥልጠና አዘጋጅተናል፡፡ በሥልጠናው ከማዘጋጃ ቤት፣ ከውኃና ፍሳሽ ቢሮ፣ ከተለያዩ የመንገድ ሥራ ተቋራጮች የተገኙ ባለሙያዎች ተካተዋል፡፡ በሌላ በኩልም በከተሞች በሚካሄዱ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ዙሪያ ከክልሎች በሚቀርብልን ጥያቄ መሠረት አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ሙያዊ እገዛ የምንሰጥበት አሠራር አለ፡፡ በዚህ መሠረትም በድሬዳዋ እየተገነባ ላለው ዘመናዊ ስታዲየም ለመሥሪያ ቤታችን በቀረበው ጥያቄ መሠረት ከተለያዩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ለተውጣጡ 45 ሰዎች በአስተዳደር ጉዳዮች ላይ ሥልጠና መስጠት ተችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- ሥልጠናዎችን ከመስጠታችሁ አስቀድሞ የምታደርጉት ዳሰሳ አለ?

አቶ መንገሻ፡- የምንሰጠው ሥልጠና ፍላጐትን አልያም ክፍተትን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ወደ ሥልጠናው ከመግባታችን በፊት በተለያዩ ዘርፎች የሚታዩ ችግሮችን ለይተን አውጥተናል፡፡ ለችግሮቹ መፍትሔ የሚሆኑ እስከ 40 የሚደርሱ የሥልጠና ዓይነቶችን አዘጋጅተናል፡፡ በሌላ በኩልም የከተማዎች ገጽታ ምቹ ይሆን ዘንድ፣ በዲዛይን፣ በኮንስትራክሽን፣ በከተማ ፕላን፣ በአካባቢ ጥበቃ ጋር የተዋሃደ አሠራር እንዲኖር የዲዛይን ባለሙያዎችን የማገዝ ሥራ ይሠራል፡፡ ማንኛውም ሕንፃ አልያም ሆስፒታል ሲገነባ ተገልጋይም ሆነ ሠራተኛ በጨረራ እንዳይጎዳ ዲዛይን ሲሠራ ምን መካተት እንዳለበት ጭምር ሥልጠና ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት እየተገነቡ ያሉ ሕንፃዎች ምን ያህል በጥናት የተደገፉ ናቸው፡፡ ከአካባቢ ጋርስ ያላቸው መስተጋብርስ የተጠና ይመስላል?

አቶ መንገሻ፡- አዲስ አበባ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገች ያለች ከተማ ነች፡፡ ከተማዋ የኮንስትራክሽን ሳይት እስክትመስል በርካታ ግንባታዎች እየተካሄዱባት ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ ግንባታዎቹ የአካባቢውን የአየር ንብረት ያላገናዘቡ፣ በጥናት ያልተደገፉና ከውጭ አገሮች የተኮረጁ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ዱባይ በጣም ሞቃታማ ነው፡፡ ለዚህም ሙቀቱን ለማቀዝቀዝ ብዙ ዓይነት ቴክኖሎጂዎች ሥራ ላይ ይውላሉ፡፡ በተቃራኒው አላስካ ቀዝቃዛ በመሆኑ አየሩን ለማሞቅ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ይገደዳሉ፡፡ የሚሠሩ ሕንፃዎችም ይህንን ያናዘቡ ናቸው፡፡ ነገር ግን አዲስ አበባ ያለው አየር ሚዛናዊ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እየተገነቡ ያሉት ሕንፃዎች የከተማዋን የአየር ፀባይና ፕላን ያላገናዘቡ በዘፈቀደ ከባህር ማዶ የሚኮረጁ በአልሙኒየም የተሸፈኑ የሕንፃ ዲዛይኖች ናቸው፡፡ ሁኔታው ለዓለም ሥጋት ለሆነው የሙቀት መጠን መጨመር አስተዋጽኦ እያደረገም ይገኛል፡፡ በሌላ በኩልም ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙት መስታወቶች ከጥራት በታች በመሆናቸው ያልተመጠነ ሙቀት ወደ ከባቢ እንዲለቁና ማኅበረሰቡ በጨረራ እንዲቸገር ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል የካርቦን ልቀትን በተመለከተ የተለያዩ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ ተሽከርካሪዎችን በብስክሌቶች በመተካት ወደ ከባቢ አየር የሚገባውን የተቃጠለ አየር ለመቀነስ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም በሐዋሳና ባህርዳር ከተሞች ብስክሌት ቀዳሚው የትራንስፖርት አውታር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከከተማ ዕድገት ጋር ተያይዞ ብስክሌት በባጃጅና በታክሲ ተተክቷል፡፡ ይህም የካርቦን ልቀት የሚጨምር ነው፡፡ በመሆኑም ድርጅቱ በከተሞቹ እንደ ቀድሞ ብስክሌት ጥቅም ላይ እንዲውል የሚጠቀሙበት ልዩ መስመር እንዲሰጣቸውም የተለያዩ ሥራዎች እየሠራ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣውን የሕዝብ ቁጥርና አረንጓዴ የሕዝብ መናፈሻ ቦታዎች ፍላጐት ምን ያህል ማስማማት ይቻላል?

አቶ መንገሻ፡- ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ በቂ የሆነ የሕዝብ መገልገያ ቦታዎች ነበሯት፡፡ ጥሩ ማኅበራዊ ሕይወትም የሚታይባት ነበረች፡፡ ዛሬ ነገሮች መልካቸውን ቀይረዋል፡፡ ከተማዋ እያደገች ስትመጣ የሕዝብ መገልገያ ቦታዎች እንደዚህ ያሉ በዲዛይን ውስጥ  ሳይካተቱ ይቀራሉ፡፡ ኮንክሪት ጃንግል (የሕንፃ ጫካ) የሚባል ሁኔታ ውስጥ እየገባን እንገኛለን፡፡ ለለቅሶና ለሰርግ የሚሆን የድንኳን መትከያ፣ የልጆች መጫወቻ ቦታ እያጣን ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ መንግሥትም ባለሙያዎችም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ ክፍት ቦታዎችን ለሕዝብ መናፈሻነት ማስቀረት በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ከመጣው የሕዝብ ቁጥር አንፃር አስቸጋሪ ቢመስልም የተለያዩ የውጭ ተሞክሮዎችን መጠቀም የግድ ይላል፡፡ ብዙዎቹ ተመሳሳይ ችግር የሚታይባቸው የውጭ ከተሞች በአረንጓዴ የተሸፈነ ሕንፃ ይገነባሉ፡፡ ይህም እኛ አገር ተግባራዊ ቢደረግ በሕዝብ መናፈሻ ቦታዎች በኩል የሚታየውን ችግር መቅረፍ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ከግንባታ ሳይቶች የሚወጡ ቆሻሻዎች በአካባቢ ፅዳት ላይ ምን ያህል ተጽእኖ እያሳደሩ ነው?

አቶ መንገሻ፡- የግንባታ ሳይቶች ላይ ከፍተኛ ብክነት ይታያል፡፡ ከግንባታ የቀሩ ተረፈ ምርቶች እንደ ሲሚንቶ፣ ኖራ፣ የቀለም ፕላስቲኮችም በሳይቶች ላይ ተከምረው ይቀራሉ፡፡ በአግባቡ ስለማይወገዱም ረዘም ላሉ ጊዜያት ይቆያሉ፡፡ አጋጣሚው የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች እንዲዘጉ በማድረግ የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓቱ እንዲዛባ፣ የቀለም ፕላስቲኮችም አፈር በኬሚካል እንዲጠቃ ምክንያት ይሆናሉ፡፡ በአካባቢ ፅዳት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ በመሆኑም የግንባታ ግብአቶችን ለብክነት እንዳይዳረጉና ተረፈ ምርቶችም በአግባቡ ተመልሰው ጥቅም መስጠት እንዲችሉ ተቋሙ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ይሠራል፡፡

ሪፖርተር፡- በሥራችሁ ምን ዓይነት ችግሮች ያጋጥሟችኋል?

አቶ መንገሻ፡- ድርጅቱ ከተለያዩ ክልሎች ጋር ይሠራል፡፡ ይህም በክልሎች ጥያቄና ፍላጐት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ነገር ግን በአንዴ በሁሉም ክልሎች መሥራት አንችልም፡፡ የአቅም ውስንነት አለ፡፡ የድርጅቱ ገቢ በጣም ውስን ነው፡፡ አገር በቀል ድርጅት እንደመሆኑ ከውጭ አገሮች ድጋፍ አያሰባስብም፡፡ የገቢ ምንጮቹ ውስን ናቸው፡፡ በዚህም ሁሉን ክልል በአንዴ ለመሸፈን አስቸጋሪ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ የምንሠራቸው ሥራዎችም ወጪዎችን በመጋራት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በግንባታ ሒደት ውስጥ አማካሪ ድርጅቶችን የማሳተፍ ባህሉ ምን ያህል የዳበረ ነው?

አቶ መንገሻ፡- አብዛኛዎቹ ባለሀብቶች ገንዘብ ለመቆጠብ ሲሉ አማካሪ ድርጅቶችን የማሳተፍ ፍላጐት የላቸውም፡፡ ነገር ግን ይህ ፈጽሞ የተሳሳተ ነው፡፡ ገንዘብ ለማትረፍ የሚደረገው ሩጫ ሌላ ኪሳራ ሲያመጣ ይስተዋላል፡፡ ብዙዎቹ ጥናት ሳይደረግባቸው የሚገነቡ ሕንፃዎች የተለያዩ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል፡፡ የግንባታ ግብአቶች ብክነትና ግንባታው በተባለበት ጊዜ አለመጠናቀቅ ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች ይጠቀሳሉ፡፡ ይህም ያላግባብ ወጪ እንዲወጣ ከማድረጉም ባሻገር አልፎ አልፎ የተገነባው ሕንፃ እንዲፈርስ የሚደረግበት አጋጣሚም አለ፡፡

ሪፖርተር፡- በሕንፃዎች ላይ የግንባታ ጥራት ጉድለት በስፋት ይታያል፡፡ ይህ ከምን አኳያ የሚፈጠር ነው?

አቶ መንገሻ፡- የግንባታ ጥራት ችግር በሁለት ምክንያቶች ይፈጠራል፡፡ በባለሙያ ብቃት ማነስ የሚፈጠረው የጥራት ችግር የመጀመሪያው ሲሆን በግብአት ጥራት ጉድለት የሚፈጠረው ሌላው ነው፡፡ አብዛኛዎቹ በአገሪቱ የሚገኙት የግንባታ ሙያተኞች በልምድ የሚሠሩ ናቸው፡፡ የተማሩ ሙያተኞች ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩት በቅርብ ነው፡፡ ከግብአት ጋር በተያያዘም ከደረጃ በታች የሆኑ ግብአቶች ሲገቡና ሥራ ላይ ሲውሉ ይታያል፡፡ ይህም ለሕንፃዎቹ ከጥራት በታች መሆን ትልቁን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ችግሩ ከሙስና ጋርም ተያያዥነት እንዳለውም ግልጽ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በከተማዋ የሚገኙ ሕንፃዎች በሕንፃ አዋጅ የተደነገጉትን ሕጐች ምን ያህል ያሟላሉ?

አቶ መንገሻ፡- በአዋጁ ሕንፃዎች ደረጃውን የጠበቀ የአደጋ ጊዜ መውጫ፣ ለአካል ጉዳተኞችና ልዩ ፍላጐት ላላቸው የማኅበረሰቡ ክፍሎች ተደራሽ እንዲሆኑ የራምፕና የሊፍት አገልግሎት እንዲኖራቸው ግድ ይላል፡፡ ደንቡ ከወጣ ዓመታት ቢቆጠሩም በአግባቡ እየተፈጸመ አይደለም፡፡ በዚህም ራምፕን ጋር ተያይዘው የሚታዩት ችግሮችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በከተማው ከሚገኙ ጥቂት ሕንፃዎች በስተቀር አብዛኞቹ ደረጃውን የጠበቀ መወጣጫ ራምፕ የላቸውም፡፡ አልፎ አልፎ ራምፕ ያላቸው ሕንፃዎች ቢያጋጥሙም ለሻንጣ መንሸራተቻነት የታሰቡ እንጂ አካል ጉዳተኛውን ታሳቢ ያደረጉ አይደሉም፡፡ መወጣጫ ደረጃዎችም ከተገቢው ከፍታ በላይ ሲገነቡ ይስተዋላል፡፡ የአደጋ መወጣጫ በሮችም ቢሆኑ አስተማማኝ ሆነው አይገነቡም፡፡   

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...