እነሆ መንገድ። ከሳር ቤት ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። እሳት እንደያዘው ክምር ፍልጥ፣ የጀንበር ፋና ብርሃን ንዳድ አናት እየበሳ ወጪ ወራጁን ያስመርረዋል። ዝግባ መሀል ቢዋጡ፣ እንደ ቁጥቋጦ አንሰው እልፍ ዋርካ መሀል ቢጠፉ፣ ወበቁ እንደ እንፋሎት እያተነነ ሥጋን ከማላላት አልመለስ ብሏል። “ሄሎ ጋይስ’ ይኼ የ‘ግሎባል ዋርሚንግ ኢሹ’ በጣም ሊታሰብበት ይገባል፤” ይላል አንድ ቀውላላ ፍንዳታ። ታክሲ ጥበቃ የተኮለኮለው ሠልፈኛ ወጣቱን ባሳሰበው ጉዳይ፣ በቋንቋ አጠቃቀሙ ወይም ጉልበቱ ላይ በታጠቀው ዘልዛላ ሱሪው መሀል አንዳች አማካይ ሥፍራ ጠፍቶት እንደ ትንግርት ያየዋል። “እኔስ ከአየር ንብረት ለውጡ የባሰብኝ መብረቁ ነው፤” ትለዋለች ከኋላው። “መብረቅ? ‘ሚድ ዴይ’ እኮ ነው!” ይላታል። “የለም! ወገብና ቀበቶን ያጣላ ሌላ መብረቅ አለ፤” አለችው አፏን አሞጥሙጣ ሱሪ አስተጣጠቁን እየጠቆመች።
ወጣቱ ሳይሸበር ወይም ሳያፍርና ሳይኮራ “ፋሽን ማለትሽ ነው? ለነገሩ የፈለግሽውን ብትይው አይከፋኝም። ‘ኢት ኢዝ ዩር ራይት፤’ ‘አፍተር ኦል’ ዘመኑ የዴሞክራሲ ነው። 21ኛው ‘ሴንቸሪ’ እ?” ደስ የማይል ሳቅ ሳቀ። “እውነት ብለሃል። ዘመኑ የዴሞክራሲ ነው እያሉን ትተነው ነው እንጂ ጅራፍ ይዘን በዞርን ነበር፤” አለችው። “ከመብረቅ በአንዴ ወደ ጅራፍ?” ወጣቱ ነገር ማዋዛቱን ችሎበታል። “ምን እናድርግ ብለህ ነው? ይኼው እያየኸው? በአንዴ ከክብር ወደ ውርደት ዘመንና ሰው እየተገለባበጠ? እኛስ ምን ይለናል? የሚይዝ ባይዘን ማለቴ ነው፤” ስትለው በዙሪያቸው ያለነው ፈገግ አልን። እውነትም የሚይዝ ይዞን እንጂ በአክራሪና በለዘብተኛው መሀል የሚጮኸው ጅራፍ ያስኖረን ኑሯል ዘንድሮ? የነገር ጅራፉ ሳይረሳ ነው ታዲያ!
ጉዟችን ጀምሯል። “ዋ ስንቱ አለፈ እንደ ዋዛ…፤” ይላል ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየመ ጎልማሳ። ከፊት ለፊቱ ‘ከታገሱት ሁሉም እንደሚያልፍ’ ትዕግሥት በሚያስጨርስ ውስብስብ ጠማማ አጻጻፍ ተጽፎ የሚነበብ ጥቅስ ይታያል። “ዋናው ጤና ነው ወንድሜ?” ይለዋል አጠገቡ የተሰየመ ወጣት። “የኢንተርናሲዮናል መዝሙር ዘምረን፣ ዓለም በተባበሩ የሠራተኞች ክንድ ፍፁም ፍትሐዊ ትሆናለች እያልን ፎክረን፣ ገድለን ተጋድለን የተረፍነው ይኼው ካልጠፋ ነገር በሙቀት ታፍነን ስንሞት እያየህ ምን ጤና አለ?” ብሎ ጎልማሳው የሚያደርገውን አሳጣው። ወጣቱ ‘ኢንተርናሲዮናል’ ምን እንደሆነ የገባው አይመስልም። ሲፈራ ሲቸር ቆይቶ ጠየቀው። ጎልማሳው እንደወበራ በሬ በግንባሩ ዓይን እያየው፣ “ኢንተርናሲዮናልን ሳታውቅ ነው የኢምፔሪያሊስቶችን ግሎባላይዜሽን የምታራግበው? ማርክስ እንኳም ይኼን አልሰማ… ትሮትስኪ እንኳን ይኼን አላየ…” እያለ ተወራጨ።
“ኧረ አረጋጉት ሰውዬውን። ላለፈ ክረምት ቤት አይሠራም አትሉትም እንዴ? ነው ተረት የመተረት መብት እንደ ኮንዶሚኒየም መኖሪያ ቤቶች በዕጣ ካልታደላችሁ የባለቤትነት መብት የላችሁም ተብሏል?” እያለች ሦስተኛው ረድፍ አጠገቤ የተቀመጠችው ወይዘሮ ታያይዛለች። “ቤት ያጣነው አንሶ፣ ያለውም እንዳለ አልታወቅ ብሎ እየተቆጠረ ጭራሽ ያሳደገንን ተረት እንነጠቅ? ነው ወይስ እንደ መሬት ላራሹ ተረት ለተራቹ ባይ አብዮተኞች አሸንፈውናል? ዘንድሮ በህቡም በግላጭም ያላሸነፈን የለም፤” ይላል መጨረሻ ወንበር ዝምታ ከሚያበዙ አዛውንት ጎን የተቀመጠ ተሳፋሪ። “እውነት ነው! ሐበሻ ራሱን እንጂ ማሸነፍ የማይችለው ከተነሳበት የማይረታው የለም፤” ትለዋለች መስኮቱን ታካ ንፋስ የአንግት ልብሷን እንደ ድል ባንዲራ የሚያርገበግብባት ለግላጋ። ይኼኔ ጎልማሳው ሰምቶ፣ “ሳንሸነፍ ተሸንፈን በጥቂት አላዋቂዎች ግባችን ተጨናግፎ እንጂ ያኔ ‘ኢንተርናሲዮናል’ የዘመርን እኛ፣ እንኳን ለአገራችን ለዓለማችን ሕዝብ ተድላና ሰላም ታይቶን ነበር፤” ብሎ ወጣቱ ላይ አፈጠጠበት። “እያፈጠጡ ተድላ ከማስፈንስ እንኳንም ቀረብን፤” ብሎ ተሳፈሪው ያጉረመርማል።
ይኼ ጨዋታ አበቃለት ስንል ቀጥሏል፡፡ “እኔ ምለው ፍቅር የሌለው፣ በአንድ ፓርቲ በአንድ መደባዊ ሥርዓት ላይ የሚገነባ ሥርዓት ቀርቶ ሁሉን አቻችለን ሁሉን አስማምተን በሚሉን ርዕዮተ ዓለሞች ያላየነው ተድላና ሰላም እንዴት ሊሳካ ኖሯል? እኔ እኮ ከኬሚስትሪ ቀጥሎ የማይገባኝ ይኼ የግራ ዘመሞች አስተሳሰብ ነው፤” ብሎ ቀጠለ። “አቦ ‘ሁ ኬርስ?’ ‘ካም ኦን ጋይስ’ ይልቅ ቦክስ ኦፊስን ስለሚመራው ‘ሙቪ’ ትንተና እንስማበት ዝም በሉ…” ብሎ ገሃድና ምናብ ተደባልቀውበት መንፈስና ሥጋው የተለያዩበት ወጣት አንባረቀ። “ወይኔ ‘አንበሳ ሲያረጅ የዝንብ መጫወቻ ይሆናል’ አለ ነፍሱን ይማረውና ያ የሠራተኞች ፓርቲ አባል ወዳጄ። ‘ኮሙዩኒስት ሲያረጅ የተንበርካኪዎችን ተረት ያዳምጣል’ ማለቱ እንደነበር ዛሬ እንጂ ያኔ መቼ ገባኝ?” ብሎ ጎልማሳው ከጣራ በላይ የሽንፈት ሳቅ ሳቀ።
“ኧረ በፈጠራችሁ እናንተ ሰዎች። አሁን የእኛ ችግር ሌላ ነው። የኑሮ ውድነት፣ የቤት ኪራይ፣ ሥራ አጥነት፣ የውኃና የመብራት እጥረት ነው እንጂ የርዕዮተ ዓለም ውዥንበር ነው? ምናለበት የሚበላንን ብናክ?” አለች ወይዘሮዋ። መሀል የዘመንና የባህል ውዥንብር ያጣበቀው ወጣት “ወይኔ አስመለጣችሁኝ፤” ብሎ ይጮሃል። “ቦክስ ኦፊስ ብርቁ ነው እንዴ ፍሬንድ? ይኼኔ በትምህርት ቤት ዘመኑ ስሙ በቀይ እስክሪብቶ ሲጻፍ እኮ እንዲህ አልተበሳጨ ይሆናል፤” እያሉ ጋቢና የተሰየሙት ሲያሙት እሱም ይሰማል። የሐሳብ፣ የአድማስ፣ የርዕዮትና የራዕይ ልዩነቶች እንዲህ በግልጽ ከየተጓዡ አፍ ሲደመጡ የጥናት ዘገባ የምንከታተል እንጂ የዕለት ጉርሳችንን ለማግኘት ታክሲ ላይ ያለን አይመስልም። ወይ ታክሲና እንጀራ!
ጉዟችን ቀጥሏል። ወያላው ወደ መቀመጫችን እየመጣ ሒሳብ ሲቀበል ሳለ ሳይታሰብ የታክሲው ሞተር ጠፋ። ወደፊት ወደኋላ ተንገጫግጫ ስትቆም ደግሞ ወያላው ሳያስበው ለግላጋዋ ጭን ላይ በፊቱ ተደፋ። “በጣም ይቅርታ መብራት ጠፍቶ ነው፤” አላት ደንግጦ ራሱን እያረጋጋ። “ታዲያ መብራት ቢጠፋ ይጨልማል እንጂ ያሰግዳል እንዴ?” አለችው ንፋሱ አሸንፏት የከፈተችውን መስኮት እየዘጋች። “እሱ እንኳን በፍቅር ከሆነ መብራትም መጥፋትም አያስፈልግም ነበር። ዋናው የሚፋቀሩ መገናኘታቸው ላይ ነው፤” ብሎ ሲክሳት ከሁላችን ቀድሞ 20መልስ ሰጣት። “አሁን እውነት ተናገርክ። ለነገሩ እስካሁን ቆጠራ ላይ ስለነበርክ አልተናገርክም። ግን ፍትሕ ከሌለ ፍቅር እንዴት ይኖራል? በየመንገዱ የሻይና የቡና ሸጉጡልን የሚሉ ከምድረ ገጽ ሳይጠፉና መተማመን ሳይኖር እንዴት የሚፋቀር ይኖራል?” እያለ ጎልማሳው ከዘመኑ ህልም የተረፈ ዲስኩሩን አንበለበለው።
ይኼን ጊዜ ደግሞ ሆነ ብሎ ይመስላል ከአዛውንቱ በስተግራ የተቀመጠው ወጣት፣ “ግን መብራት የሚጠፋው ለምድነው?” ብሎ ደንቃራ ሆነ። “የመብራቱን ጥቅም እስክታውቀው ታስቦ መሰለኝ፤” ብላ ከፍንዳታው አጠገብ የተሰየመች ተሽኮርማሚ ሸፋፋ የምፀት ፈገግታ ልታሳየው ዞረች። ወይ! ውይ! በትራንስፎርመሮቻችን ፈንታ እንዳንቺ ያሉ ፀዳል ጥርሶችን ቢገጠሙልን እኮ ግድብ መገደብ ባላስፈለገን ነበር፤” አላት። “ሄይ ሄይ! ራስህን ችለህ ተላከፍ። ምንድነው እንደ አፍሪካ አምባገነን መንግሥታት ዓይንህን በጨው አጥበህ ሳትወከል እንደ ተወካይ የሚሠራራህ?” ብሎ እዚያው ተርታ ያለ ወጣት አሾፈ። አዛውንቱ ቀልድ መሆኑን ሳይገነዘቡ ይመስላል፣ “ተው እንጂ ለፀብ በስማችን ተነግዶ አይደለም ወይ? ምናለበት በፍቅሩ ንግድ ብንካተት?” ብለው ግራ ቀኝ ሲያዩ ሳይሸመገሉ ተግባብተው የታረቁትን ወጣቶች አዩና ዝም አሉ። አሁን ይኼን ሰምቶ ደግሞ በፍቅር ስም ንግድ ፈቃድ ካልተሰጠኝ የሚለውን ማሰበው ነው እንግዲህ። ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣ! ታክሲያችንም ሞተሯ ተነሳ!
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። አዛውንቱ በፆም የዛለ ሰውነታቸውን እያፍታቱ በለሆሳስ ያጉተመትማሉ። “ምን አሉ አባት?” ብሎ ወጣቱ ያስጨንቃቸዋል። “ኧረ እኔስ ወዲህ ነው ያወጋሁት፤” አሉት። “እኛ እያለን? ብቸኝነት በአዳም ዘመን እኮ አብቅቷል፤” ብሎ በራሱ መንገድ የማይገናኘውን ማገናኘት ሲጀምር፣ “ካልክስ በአዳም ዘመን ሊጀመር ይገባው የነበረ ጉዳይ ተረስቷል፤” አሉት። ሊያብራሩ ጉሮሮአቸውን ጠራረጉ። “እሱም ምን መሰለህ? ንስሐ ነው። የሰው ልጅ ማጥፋቱ ሳያንሰው ጥፋቱን ማመኑ ላይ እጅግ እየዘገየ በሥጋም በነፍስም ዋጋ ይከፍላል፤” ሲሉት አቋርጦ፣ “እሱንማ አልሰሙም እንዴ? ኢሕአዴግ እኮ ንስሐ ገባ፤” ብሎ ተንቀለቀለ። “ምንድነው የሚያወራው ሰውዬው?” እያለ ተሳፋሪው ዓይን ለዓይን ተፋጠጠ። “ምን አገናኘው?” አሉት አዛውንቱ ግራ ገብቷቸው ዓይናቸውን አጨንቁረው እያስተዋሉት።
“እንዴት አይገናኝም ጋሼ? እኛ እኮ ይኼን ሁሉ ዘመን ያጣነው የበላዮቻችንን፣ የአባቶቻችንን፣ የመሪዎቻችን ጥፋትን አምኖ መቀበል ነበር። ከዚ መማር ነበር። አይደለም እንዴ? አግዙኝ እንጂ። ይኼው ዘንድሮ መንግሥታችን ባሳለፋቸው የሥልጣን ጊዜያቱ ከማንነትና ከአስተዳደር ችግሮች ጋር ተያይዘው የተነሱ ግጭቶችና መዘዞቻቸው የእኔ የራሴ የውስጥ ዝርክርክነት ያመጣቸው ናቸው። ሌላው ላይ ጣት መቀሰር የውድቀት መጀመሪያ ነው ብሎ ንስሐ ገባ። ይኼን ከዚህ ቀደም አይተናል? አላየንም። ሰምተናል? አልሰማንም!” ሲል አዛውንቱ አቋረጡት። “የተናጠል ንስሐ ለተናጠል ድህነትና ወድቆ መነሳት ካልሆነ በቀር ብቻውን ምን ዋጋ አለው ልጄ? አንዱ ጥፋቱን ሲያምን ሌላው እንደ ሽንፈት ከቆጠረበት፣ አንዱ ሸክሙን ሲሸከም ሌላው ዳር ቆሞ በባርነት ከፈረጀበትና ከተጠቋቆመበት ፋይዳ ቢስ አይሆንም?” እያሉት ሳለ ወያላው “መጨረሻ” ብሎ ጮኸ። ወራጆች ከመውረዳችን በፊት ከደጅ አሰፍስፈው የሚጠብቁ ተሳፋሪዎች በሩን አንቀው ያዙ፡፡ “አገር የጋራ ናት። እርማቱንም የጋራ፣ ንስሐውንም የጋራ፣ ሸክሙንም የጋራ ያድርግልን በሉ!” እያሉ አዛውንቱ ቀድመው ሲወርዱ በሩን ገጥግጦ ይዞት የነበረ ችኩል በአክብሮት ሸሸ። እኛም ፋታውን ተከትለን ዱብ። ‘ለጋራ አገር የጋራ ንስሐ’ አሉ አዛውንቱ። ጣት መቀሳሰር አይበቃም? መልካም ጉዞ!