Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየኤርትራ መንግሥት አተራማሽነት መቆም አለበት

የኤርትራ መንግሥት አተራማሽነት መቆም አለበት

ቀን:

በዘመኑ ተናኘ

ሲያትል ውስጥ በሚገኘው ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርት የሆኑት ሬይሞንድ ጆናስ ‹‹The Battle of Adawa African Victory in the Age of Empire›› በሚለው መጽሐፋቸው ላይ እንደጠቀሱት፣ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት ዮሐንስ አራተኛ የግብፅን ጦር በጉራ የጦር ሜዳ ላይ ድል ካደረጉ በኋላ የኢትዮጵያን ግዛት በማስከበር ኤርትራን ጠቅልላ ፖለቲካዊ ድንበሯን የቀይ ባህር አደረጉ፡፡

ይህ ፖለቲካዊ ድንበር እስከ ዛሬ ድረስ የተለያዩ ግለሰቦችና ምሁራን የተለያየ አመለካከት እንዲኖራቸው ያስቻለ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያና የኤርትራን የቆየ በአንድ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ መኖር ያረጋገጠ ጉዳይ እንደነበረ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በእርግጥ ሬይሞንድ ጆናስ በዚሁ መጽሐፋቸው ሲገልጹ፣ የኤርትራ አዲስ ስያሜና አዲስ አገርነት የሚመነጨው ከጣሊያን ወረራ በኋላ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ የጀርመኑ ቢስማርክ የአውሮፓ ኃያላን አገሮችን ሰብስቦ የአፍሪካ ቅርምት (The Scramble of Africa) ብሎ በሰየመው የስብሰባ አጀንዳ ከተሳተፉት አገሮች መካከል አንዷ ጣሊያን ነች፡፡

ጣሊያን በዚህ ስብሰባ ተሳታፊ ከሆነች በኋላ ግዛቷን ለማስፋፋትና በርካሽ የሚገኘውንና ያልተነካውን የአፍሪካ ሀብት ለመዝረፍ ጦሯን ሰብቃ ወደ አፍሪካ ምድር አቀናች፡፡ በሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ ካሉ ለም አካባቢያዎች አንዱ የኢትዮጵያ ምድር እንደሆነ የተረዳችው ጣሊያን፣ በቀይ ባህር በኩል አድርጋ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ገሰገሰች፡፡ መንገዱ አልጋ በአልጋ ሆነላትና ያለምንም የተኩስ ድምፅ የኤርትራን ምድር በቁጥጥሯ ሥር አዋለች፡፡ ምድሩን በቁጥጥሯ ሥር ባዋለች ማግሥት ለቦታው የራሷን ስያሜ ሰጠች፡፡ ‹‹ኤሪትሮስ›› የሚለውን የግሪክ ቃል በመውሰድ ግዛቱን ‹‹ኤርትራ›› በማለት ሰየመች፡፡ የቃሉ ትርጉምም ‹‹ቀይ›› ማለት ሲሆን ቀይ ባህርን የሚወክል ነው፡፡ ቃሉ የመካከለኛው ዘመን የሮማውያንን ኃያልነት የሚያስታውስ ሲሆን፣ አዲሲቷ ቅኝ ግዛት ኤርትራም የሮማውያን መነሳትና ህዳሴ ማሳያ ሆነች፡፡

እንግዲህ የኤርትራ አፈጣጠርና ራሷን የቻለች አገር ሆና እንድትቆም ካደረጉት አንዱ ክስተት ይህ እንደነበር ብዙዎቹ ይስማማሉ፡፡ በተለያዩ ዘመናትና የአስተዳደር ሥርዓቶች አልፋ ዛሬ ሉዓላዊት አገር የሆነችው ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ሁለት ገጽታ ነበረው፡፡

በተወሰነ ዘመንና ሥርዓት እጅና ጓንት ሲሆኑ፣ በተወሰነ ዘመንና ሥርዓት ደግሞ ዓይንና ናጫ ሆነዋል፡፡ እነዚህ ሁለት ገጽታ ያላቸው ግንኙነቶች የተፈጠሩት በየዘመናቱ በነበረው የአስተዳደር ሥርዓት ልዩነት የተነሳ ቢሆንም፣ በአሉታዊ ገጽታው ከሚጠቀሱት ግንኙነቶች መካከል አንዱና ዋነኛው ጉዳይ የአፄ ምንሊክ ጦር ጣሊያንን ከኢትዮጵያ ምድር ሙሉ በሙሉ ጠራርጐ አስወጥቶ፣ በኤርትራ ጠረፍ ብቻ ከቁጥር የማይገቡ የጣሊያን ምሽጐች ሲቀሩት ዓድዋን ለቆ ወደ ሸዋ መመለሱ እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡

 ንጉሠ ነገሥቱ በወቅቱ ያገኙትን ድል ሙሉ በሙሉ ሳይጠቀሙና ዮሐንስ አራተኛ የግብፅን ጦር ጉራዕ ላይ ድባቅ መትቶ የኢትዮጵያን ድንበር ቀይ ባህር ድረስ እንደነበረ ያወጀውን እሳቸው ሳያሳኩ መቅረታቸው፣ እስከ ዛሬ ድረስ በብዙዎች ዘንድ ይወቀሳሉ፡፡ ይህንን ድል በወቅቱ ባለመጠቀማቸው ብዙ አከራካሪ አስተያየቶች እስከዛሬ ድረስ እየተሰጡ ቢሆንም፣ ይህ ጉዳይ ግን የኤርትራን ሕዝብ ቅር ሊያሰኝ እንደሚችልና የሌላ አገር ዜግነት ስሜት እንዲሰማቸው የሚያስችል የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ እንዳለፈ ግን መረዳት ይቻላል፡፡ ጣሊያንም ይህንን ነፃ መሬት (ኤርትራ) ለብዙ ዓመታት በቁጥጥሯ ሥር አውላ በራሷ የፖለቲካ ርዕዮት ስትዘውረው ኑራለች፡፡

የጣሊያን የአካባቢው ገዥነት የተወገደው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ነበር፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ኢትዮጵያ ያገኘችው ታላቁ የውጭ ፖሊሲ ድል የባህር በሯን መልሳ እጅ ማድረግ መቻሏ (ኤርትራ እንደገና የኢትዮጵያ መንግሥት አካል መሆኗ) ነው፡፡ ይህ ለአገሪቱ አቻ የሌለው ክስተት ነበር፡፡ በአንድርዜይ ባርትኒስኪና ዮአና ማንቴል ኒየችኮ ተጽፎ በዓለማየሁ አበበ የተተረጐመው ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከመጀመርያው እስካሁን ዘመን›› በሚለው መጽሐፍ ውስጥ እንደተጠቀሰው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ባደረገው ብርቱ ጥረት አምስተኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ስብሰባ ታኅሳስ 2 ቀን 1950 ዓ.ም. ኤርትራ የውስጣዊ አስተዳደር ነፃነት ያለው ጠቅላይ ግዛት ሆና ከኢትዮጵያ ጋር እንድትዋሀድና የራሷ መንግሥትና ፖለቲካ እንዲኖራት የሚል ውሳኔ አሳለፈ፡፡ በመጨረሻ በኅዳር 1962 ዓ.ም. የኤርትራ ፓርላማ ከኢትዮጵያ ጋር ሙሉ በሙሉ የመዋሀድን ውሳኔ አሳለፈ፡፡ የፌዴራሲያኑ አቋም ተሽሮ ኤርትራ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ግዛት ሆና ተዋሀደች፡፡        

በዚህ አኳኋን ብዙ ታላላቅ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የቀይ ባህርን በር ለማስመለስ ያደረጉት ጥረት ዕውን ሆነ፡፡  የንጉሠ ነገሥቱ ዘመን አክትሞ የአምባገነኑ የደርግ መንግሥት የፖለቲካ መዘውሩ ላይ ሲወጣ ሌላ ታሪክ ተፈጠረ፡፡ ደርግ ገና ወደ ሥልጣን በወጣ ማግሥት ጀምሮ ይከተለው የነበረው የአስተዳደር ሥርዓት ለኢትዮጵያም ሆነ ለኤርትራ ሕዝብ ረብ የሌለው ሆኖ ተገኘ፡፡ በዚህም የተነሳ የኤርትራና የኢትዮጵያ ጥቂት ወጣቶች የአምባገነኑን መንግሥት በነፍጥ ገርስሶ ለመጣል ወደ ጫካ ገቡ፡፡ እነዚህ ሁለቱ ኃይሎች ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ የነበራቸው ግንኙነት መሠረቱ የፖለቲካ አጀንዳ እንዳልነበር ብርጋዴር ጄኔራል አከለ አሳዩ ‹‹ያልተንበረከኩት የኢሕአዴግ/ብአዴን የትግልና የድል ጉዞ ቁጥር ሁለት›› በሚለው መጽሐፋቸው ገልጸዋል፡፡ ሁለቱም ኃይሎች የየራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳ የሚያራምዱና ግባቸውም ለየቅል እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ የኢትዮጵያውያን ኃይሎች ዓላማ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ማረጋገጥ (መደባዊ ይዘት ነበረው) ሲሆን፣ የኤርትራ ኃይሎች ደግሞ የነፃነት ጥያቄ ብቻ ነበር፡፡ ቢሆንም ግን እነዚህ ሁለቱ ኃይሎች ደርግን ለመጣል ልዩነታቸውን ወደ ኋላ ብለው አብረው ተሠልፈዋል፡፡ ይህ ውህደትም ደርግን ለመገርሰስ አስችሏቸዋል፡፡

ከትጥቅ ትግሉ በኋላም በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢሕአዴግ) እና በሕዝባዊ ግንባር ኤርትራ (ሕግደፍ) መካከል ታሪካዊ የሚባል ግንኙነት ነበር፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ ሻዕቢያ ኤርትራን ነፃ ለማውጣት የታገለና መስዕዋትነት የከፈለ መሆኑን ሙሉ ዕውቅና በመስጠት፣ የኤርትራ ሕዝብ ሪፈረንደም እንዲያካሂድና ፍላጐቱን እንዲመርጥ የነበረው ገለልተኛና ቀናኢ አስተሳሰብ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያና ኤርትራ ወዳጅነት ከድል ማግሥት ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ እየሻከረ መጣ፡፡ የሻቢያ መንግሥት በነበረው ድብቅ ፍላጐት የተነሳ ሁለቱ ወዳጅ ሕዝቦች የነበራቸው ግንኙነት ተቋርጧል፡፡ የሻዕቢያ የጠብ አጫሪነት ስሜት ሁለቱ አገሮች ወደ ጦርነት ገቡ፡፡ ብርጋዴር ጄኔራል አከለ አሳየ በመጻሐፋቸው እንደጠቀሱት ኢትዮጵያ ተገዳ ወደ ጦርነቱ ገባች፡፡

የኤርትራ መንግሥት ግንቦት 28 ቀን 1990 ዓ.ም. በአይደር ትምህርት ቤትና በተቋማት ላይ የአውሮፕላን ድብደባ በማካሄድ ምንም መከላከያ በሌላቸው ሰላማዊ ሕፃናትና አዛውንቶች ላይ አደጋ በማድረስ የ47 ንፁኃን ዜጐችን ሕይወት ሲቀጥፍ፣ በ136 ሰዎች ላይ ደግሞ የመቁሰል አደጋ ያስከተለ ድብደባ ፈጽሟል፡፡ በዚህ የተነሳ የኢትዮጵያ መንግሥት ሳይወድ በግድ ወረራውን ለማስቆምና ሉዓላዊነቱን ለማስከበር ወደ ጦርነቱ ገባ፡፡

ለሁለት ዓመት የቆየው የኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት የማታ ማታ በኢትዮጵያውያን አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ በኤርትራ ተይዞ የነበረው የኢትዮጵያ መሬትም ሙሉ በሙሉ ከጠላት ነፃ ሆነ፡፡ ይህ ጦርነት በሁለቱም ወገኖች በኩል ከፍተኛ የሆነ ቀውስ ያስከተለ ነበር፡፡ አገሮቹ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሊውል የሚችል በጀት ከማውደም ባለፈ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጐች ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ሁለቱ ወዳጅ ሕዝቦችም የነበራቸው ግንኙነት ተቋርጧል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአምባገነኑ መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ የምትመራው ኤርትራ ዜጐቿ የባዕድ አገር አላሚዎች እንዲሆኑ ተዳርገዋል፡፡ በዓለም የሚዲያዎች መነጋገሪያ አርዕስት በሆነው ስደት ሰለባ ሆነዋል፡፡ ዜጐቿ መንግሥት ከሚያደርስባቸው ማኅበራዊ ቀውስ ባሻገር ወጣቱ ትውልድ ተምሮ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ራሱን ብሎም አገሩን እንዲጠቅም ከማድረግ ይልቅ፣ የውትድርና ትምህርት ተከታትሎ ኢትዮጵያንና አካባቢውን የማተራመስ ሥራ እንዲሠራ ይገደዳል፡፡ በዚህም የተነሳ ባሁኑ ወቅት በየዕለቱ በመቶ የሚቆጠሩ ኤርትራዊያን አገራቸውን ለቀው ወደ ኢትዮጵያና ሌሎች ጎረቤት አገሮች እንደሚሰደዱ መረጃዎች ያጠቁማሉ፡፡ ኢትዮጵያንና ሌሎች ጎረቤት አገሮችን የሽብርተኞች መናኸሪያ ለማድረግ እንቅልፍ የማይወስደው የአምባገነኑ ኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት በአሁኑ ወቅት ወደ ለየለት እብደት እየገባ ይመስላል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት አሸባሪ ብሎ ለፈረጃቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች ወታደራዊ ሥልጠና ከመስጠት አንስቶ አስፈላጊ ሎጂስቲኮችን ማሟላት ድረስ የሚሠራው የኤርትራ መንግሥት፣ አካባቢውን ለማተራመስ ደፋ ቀና ማለት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

በተለይ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን ኃያልነት ለመግታትና እየፈጠረች ያለችውን ተሰሚነት ጥላሸት ለመቀባት ተኝቶ እንደማያድር ‹አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው› ጉዳይ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡

ከ1990ው ጦርነት ሊማር ያልቻለው ኤርትራ መንግሥት አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያን ለመውረር ዕቅድ እንደሌለው ማሰቡ ሞኝነት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሰሞኑን በወርቅ ፍለጋ ላይ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን አፍኖ የወሰደበትንና መልሶ የለቀቀበትን ሁኔታ ማየቱ በቂ ነው፡፡አሁንም ያለው የጠብ አጫሪነት ስሜት እንዳለ የምንረዳበት ሌላኛው ግልጽ ደብዳቤ ነው፡፡

የአንድን አገር ሉዓላዊነት መድፈር የሚጀምረው ከዚህ ነው፡፡ ድንበሯን ከመድፈር አንስቶ ዜጎቿን አፍኖ እስከ መውሰድ ይደርሳል፡፡ በአጭሩ ለ30 ዓመታት ለኤርትራ ሕዝብ ታግያለሁ ያለው የኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት ዛሬ በኤርትራ ሕዝብ ላይ ጠብ የሚል ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም፡፡ ኢትዮጵያንና ሌሎች ጎረቤት አገሮችን ለማተራመስ ከሚጽፍ ከሚደልዝ የሽብር ፖሊሲው ውጪ፡፡

ከላይ ከኢትዮጵያ የቀይ ባህር ድንበር አንስቶ ኤርትራ የምትባል አገር አፈጣጠር፣ በአፄ ምንሊክ ዘመነ መንግሥት ከነበረው የኢትዮ ኢጣሊያ ጦርነት እስከ ኤርትራ ዕጣ ፈንታ፣ እንዲሁም ኤርትራ ከኢትዮጵያ መገንጠል አንስቶ እስከ መዋሀድ ወዘተ. ስላለው ታሪካዊ ዳራ ሰፋ ያለ ዳሰሳ ለማቅረብ ሞክሬያለሁ፡፡

እንደ ማጠቃለያ ኤርትራ ራሷን ችላ መቆም ከጀመረች ወዲህ ጥፋቷ እንጂ ልማቷ ስለማይታይ የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩን በአንክሮ ሊከታተለው ይገባል፡፡ ከ1990ው ወረራ ተምረን ራሳችንን ዝግጁ ማድረግና ጊዜው የሚጠይቀውን ሁኔታ በሙሉ አሟልተን መገኘት አለብን፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ ያለንን ተሰሚነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት ተጠቅመን ኤርትራ ላይ ተፅዕኖ መፍጠር አለብን፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለን ተሳትፎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከዚህ በፊት ወስዶት የነበረውን ማዕቀብ እንዲያጠናክርና ወዳጅ አገሮቹ ሳዑዲ ዓረቢያን ጨምሮ የማዕቀቡ ታሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ አለብን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡  

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...