[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት]
- እየተከታተልክ ነው ለመሆኑ?
- ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
- ቴሌቪዥን ነዋ፡፡
- በሚገባ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን አሰብክ ታዲያ?
- በጣም አስፈሪ ነገር ነው፡፡
- ምኑ ነው የሚያስፈራው?
- ትራምፕ ነዋ፡፡
- ትራኩ ነው ያልከኝ?
- የአሜሪካኑ ትራምፕ ነው ያስጨነቀኝ ስልዎት፡፡
- እኔ ደግሞ የዩሮ ትራኩ ጉዳይ ነው የሚያስጨንቀኝ፡፡
- እኔ እኮ ወሬ ብቻ ይመስለኝ ነበር፡፡
- ምኑ?
- ክቡር ሚኒስትሩ ዩሮ ትራከር አላቸው ሲባል፡፡
- ቢኖረኝ ምን ችግር አለው?
- ያው ከየት ያመጡታል ብዬ ነው?
- ከብዙ ቦታ ላመጣው እችላለሁ፡፡
- ለነገሩ እርስዎ ብዙ ቦታ እንዳለዎት አውቃለሁ፡፡
- ምን አልክ አንተ?
- ማለቴ ሊያመጡበት የሚችሉበት ብዙ አቅም አለዎት ብዬ ነው፡፡
- ዛሬ የፈለኩህ እንዴት አየኸው ልልህ ነው?
- ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
- የሰሞኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር፡፡
- በቴሌቪዥን ነዋ፡፡
- ቀልዱን ተውና ቁምነገሩን አስቀድም፡፡
- ሰው በጣም ተገርሟል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በምኑ ነው የተገረመው?
- ኢሕአዴግ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋቱን በማመኑ ነዋ፡፡
- ይኼ ምኑ ነው የሚያስገርመው?
- ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋቱን ማመኑ ነዋ፡፡
- እስከዛሬ አምኖ አያውቅም?
- አዎና ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምን አምኖ እንደማያውቅ ታውቃለህ?
- አላውቅም፡፡
- አጥፍቶ ስለማያውቅ ነዋ፡፡
- ምን አሉኝ?
- አጥፍቶ አያውቅም፡፡
- ለነገሩ አጥፍቶ የሚያውቀው ሌላ ነገር ነው፡፡
- ምን?
- መብራት፡፡
- እ…
- ውኃ፡፡
- እ…
- ኔትወርክ፡፡
- ሌላስ?
- አንዳንዴም የሰው ሕይወት፡፡
- በል በል ሌላ ፖለቲካ ውስጥ አትግባ፡፡
- ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለማንኛውም አሠራራችንን መለወጥ አለብን፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ሁሉን ነገር በአዲስ መልኩ መጀመር አለብን፡፡
- በአዲስ ሲሉ?
- ሕዝቡ በጣም ተማሮብናል፡፡
- እርሱማ ግልጽ ነው፡፡
- ስለዚህ ሕዝቡን ማስደሰት አለብን፡፡
- እኮ በምን እናስደስተው?
- አዲስ ሕንፃ ውስጥ መግባት አለብን፡፡
- ለምን ሲባል?
- ሕዝቡ በደል በደል በሚሸት ሕንፃ ውስጥ ከዚህ በኋላ መገልገል የለበትም፡፡
- እና ምን ይደረግ?
- አዲስ ሕንፃ ውስጥ መግባት አለብን ስልህ፡፡
- የትኛው ሕንፃ ውስጥ ነው የምንገባው?
- የምንገባበትን ሕንፃ እኔ እጨርሰዋለሁ፡፡
- የመንግሥት ሕንፃ ነው?
- የግል ነው እንጂ፡፡
- በኪራይ ክቡር ሚኒስትር?
- አዎና የግል ሴክተሩን እኮ ማበረታታት አለብን፡፡
- እና ከመንግሥት ሕንፃ ወጥተን ወደ ኪራይ እንግባ እያሉ ነው?
- ለሕዝቡ ሲባል የማይደረግ ምንም ነገር የለም፡፡
- ለማን አሉኝ?
- ለሕዝቡ፡፡
- ለእርስዎ ማለትዎ ነው?
[ክቡር ሚኒስትሩ ለምሳ ቤታቸው ሲሄዱ ሚስታቸውን አገኟቸው]
- ምነው ደስ ያለህ ትመስላለህ?
- እንዴት አልደሰት?
- እኮ ምን ተገኘ?
- ያው አፉን ከፍቶ የነበረው ሕንፃችን ተከራይ ተገኘለት፡፡
- ማን ሊከራየው ነው?
- እኛ ነና፡፡
- እናንተ ማን ናችሁ?
- የእኛ መሥሪያ ቤት፡፡
- ምን?
- አዎን ሁሉን ነገር ጨርሼዋለሁ፡፡
- ለምንድን ነው ቢሮ የምትቀይሩት?
- በአዲስ መንፈስ ሥራ መጀመር አለብና፡፡
- ያላችሁበት የመንግሥት ሕንፃ አይደል እንዴ?
- ቢሆንስ?
- ታዲያ ከዛ ወጥታችሁ ወደ ግለሰብ ሕንፃ ልትገቡ?
- ምን አለበት?
- ለነገሩ ከመንግሥት ሕንፃ ወደ መንግሥት ባለሥልጣን ሕንፃ ነው የገባችሁት፡፡
- አመጣሽው ጨዋታውን፡፡
- ያን ያህል ልዩነት ያለው አይመስለኝም፡፡
- ያው ነው ስልሽ፡፡
- የእኔ ሥራ ብቻ ተቀዛቅዟል፡፡
- የትኛው ሥራሽ?
- የፈርኒቸሩ ሥራ ነዋ፡፡
- ለእሱም ቢዝነስ ሥራ አግቼልሻለሁ፡፡
- ምን ተገኘ?
- አዲሱ ሕንፃ ውስጥ ስንገባ አዲስ ፈርኒቸር ያስፈልገናል፡፡
- የድሮዎቹ ምን ሆኑ?
- ወንበሮቹ ራሳቸው ግፍ ግፍ ይሸታሉ፡፡
- ታዲያ ወንበሮቹ ሳይሆኑ ወንበሮቹ ላይ የተቀመጡት እኮ ናቸው ግፈኞቹ፡፡
- ቢሆንም ሕዝቡ በእነዚህ ግፈኛ ወንበሮች ከዚህ በኋላ መገልገል የለበትም፡፡
- እኔማ ደስ ነው የሚለኝ፤ ቢዝነስ አገኘሁ፡፡
- ስለዚህ ተዘጋጂ፡፡
- ስለእሱ አታስብ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ሲገቡ አማካሪያቸውን አስጠሩት]
- አቤት ክቡር ሚኒስትት፡፡
- አንድ ሐሳብ መጥቶልኝ ነው፡፡
- የምን ሐሳብ?
- አዲሱ ቢሮ ስንገባ አዲስ ፈርኒቸር መግዛት አለብን፡፡
- ምን?
- ሁሉን ነገር በአዲስ መንፈስ መጀመር አለብን ስልህ፡፡
- ፈርኒቸሮቹ ከተገዙ እኮ ስድስት ወራቸው ነው፡፡
- ስማ ቢሆኑም ሕዝቡ በእነዚህ ግፈኛ ወንበሮች መገልገል የለበትም፤ መቀየር አለባቸው፡፡
- መቀየርማ ያለባቸው ሰዎቹ ናቸው፡፡
- ሰዎቹን መቀየር ከባድ ስለሆነ ወንበሮቹን ብንቀይራቸው ይሻላል፡፡
- ሕዝቡ እኮ የተማረረው በወንበሮቹ ሳይሆን በሰዎቹ ነው፡፡
- አየህ በወንበሮቹ ጀምረን በሰዎቹ እንቀጥላለን፡፡
- ለማንኛውም የሰዎቹን ቅያሬ ስንጠብቅ ቀኑ እንዳይደርስብን፡፡
- የምኑ ቀን?
- የምፅዓት ቀን!
[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ ቢሯቸው ገባች]
- ጠዋት የት ሄደሽ ነው?
- አንድ ጉዳይ ገጥሞኝ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ አታስፈቅጂም እንዴ?
- ስልክዎትን ብለው ብለው አልሠራ አለኝ፡፡
- ሞክረሽልኝ ነበር?
- በጣም ብዙ ጊዜ ነው የሞከርኩት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አየሽ ሌላም ሰው ቢፈልገኝ አልገኝም ማለት ነው፡፡
- ለእኔ አልሠራልኝም ነበር፡፡
- ሕዝቡ የሚማረረው እኮ እንደዚህ እየሆነ ነው፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ስልኬ በአዲስ መቀየር እንዳለበት ገብቶኛል፡፡
- እ…
- አዲስ አይፎን ያስፈልገኛል፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ የአይቲ ክፍል ኃላፊውን አስጠሩት]
- አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሕዝቡ ምን ያህል እየተማረረ እንደሆነ ታውቃለህ አይደል?
- በጣም ተማሯል፡፡
- ሕዝቡን እኔን ሊያገኘኝ አልቻለም፡፡
- ቢሮ መቼ ተቀምጠው ያውቃሉ?
- ቢሮ ባልቀመጥም ቢያንስ በስልክ ሊያገኘኝ ይገባል፡፡
- ስልክዎትን የሚያውቀውማ ይደውልልዎታል፡፡
- የማያውቀውም ቢሆን ቢያንስ በኢሜይል ሊያገኘኝ ይገባል፡፡
- ታዲያ ለምን አያገኝዎትም?
- አየህ ኮምፒዩተሮቻችን አሮጌ ናቸው፡፡
- እ…
- አሁን አዲስ ሕንፃ ውስጥ ስለምንገባ ሁሉንም በአዲስ ኮምፒዩተር መተካት አለብን፡፡
- ክቡር ሚኒስትር አሁን ያሉት ኮምፒውተሮች እኮ ከተገዙ ገና ስድስት ወራቸው ነው፡፡
- ስማ ቴክኖሎጂው እኮ በየጊዜው ነው የሚቀያየረው፡፡
- እ…
- ስልኮቻችንም በአዲስ መቀየር አለባቸው፡፡
- ጨረታ ይውጣ?
- ቢሮክራሲ አያስፈልግም፡፡
- ምን?
- እኔ እጨርሰዋለሁ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ የኮምፒዩተር ቢዝነስ የሚሠራው ወንድማቸው ጋ ደወሉ]
- አቤት ጋሼ፡፡
- የት ነው ያለኸው?
- ካርታ እየተጫወትኩ ነው፡፡
- አንተ ልጅ ይኼ ካርታ ሱስ ሆነብህ አይደል?
- ያው በዘር እኮ ነው ሱስ የሆነብን ጋሼ፡፡
- እኔ የት ነው ካርታ ስጫወት ያየኸው?
- ያው አንተ በመሬት ካርታ ነዋ የምትጫወተው፡፡
- ለማንኛውም አሁን ሥራ አግኝቼልሃለሁ፡፡
- የምን ሥራ ጋሼ?
- ለቢሯችን ሙሉ ኮምፒዩተር እንድታቀርብ፡፡
- እየቀለድክ ነው ጋሼ?
- የምን ቀልድ ነው? እውነቴን ነው፡፡
- ከስድስት ወር በፊት ነው እኮ ለሙሉ ቢሮው ኮምፒዩተር ያቀረብኩት፡፡
- እና ይኼኛውን አትፈልገውም?
- ኧረ እንደሱ ማለቴ አይደለም፤ በጣም ደስ ብሎኝ ነው፡፡
- ምኑ ነው ደስ ያለህ?
- በቃ በዚህ ሥራ ሕንፃዬን እጨርሰዋለሁ ብዬ ነዋ፡፡
- ሕንፃህንም ተጨማሪ ቦታ ስለሚያስፈልገን መከራየታችን አይቀርም፡፡
- አንጀት አርስ ነህ ጋሼ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ስብሰባ ተጠርተው ሄዱ፤ ሳያስቡት መገምገም ጀመሩ]
- ክቡር ሚኒስትር ከብልሹ አሠራርዎት ሊታቀቡ አልቻሉም፡፡
- እናንተ ከእኔ ውጪ ሰው አይታያችሁም እንዴ?
- ይኸው ባለፈው ተገምግመው አሁንም ያው ነዎት፡፡
- ምን አደረግኩ?
- ይኸው አዲስ ሕንፃ ውስጥ ካልገባን እያሉ ነው፡፡
- በአዲስ መልክ ሥራ መጀመር ስላለብን ነዋ፡፡
- ደግሞ ሕንፃው የእርስዎ ነው አሉ?
- በተመጣጣኝ ዋጋ እስካከራየሁት ድረስ ምን ችግር አለው?
- እ…
- ፈርኒቸሮቹንም ቢሆን በአገር ዋጋ ነው የምናቀርበው፡፡
- ሌላስ?
- ኮምፒዩተሮቹም ቢሆኑ ሌተስት የሆኑት እኛ ጋ ስላሉ ነው፡፡
- ወይ ቅሌት፡፡
- ይህንንም ያደረግነው ሥራችንን በአዲስ መንፈስ ለመጀመር ነው፡፡
- እርስዎም በአዲስ መልክ ጀምረውልኛላ፡፡
- ምኑን?
- ሌብነቱን!