አቶ ፈይሳ አራርሳ፣ የአዳማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት
ንግድ ምክር ቤቶች በአዲስ አደረጃጀት እንዲዋቀሩ የወጣው አዋጅ ቁጥር 34/95 ሲተገበር ከመጀመሪያዎቹ የንግድ ምክር ቤቶች አመራሮች መካከል አንዱ አቶ ፈይሳ አራርሳ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት የአዳማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፣ የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የቦርድ አባል ሆነው ያገለግላሉ፡፡ በንግድ ምክር ቤቶች የአመራር መዋቅር ውስጥ ከ10 ዓመታት በላይ ተሳትፎ ያደረጉት አቶ ፈይሳ፣ በትምህርት ረገድ የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ሲሆኑ፣ በቢዝነሱ መስክ በይበልጥ የሚታወቁት በትምህርት ዘርፍ ነው፡፡ በአዳማ ከኬጂ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ባለው ደረጃ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በአዳማ ከተማ ካማራ በሚል መጠሪያ የሚታወቅ ትምህርት ቤትና የሐራምቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ባለቤትም ናቸው፡፡ ከኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በዲፕሎማ ተመርቀው በመምህርነት ሥራ የጀመሩት አቶ ፈይሳ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በንግድ ሥራ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ሲያገኙ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በቢዝነስ አድሚኒስቴሬሽን ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ ተቀብለዋል፡፡ ለትምህርት ኢንቨስትመንት ልዩ ቦታ አለኝ የሚሉት አቶ ፈይሳ፣ ከቋንቋ ትምህርት ቤት ጀምሮ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባለቤት እስከመሆን ዘልቀዋል፡፡ ለመምህርነት ሙያ ልዩ ከበሬታ እንዳላቸውም ይገልጻሉ፡፡ በትምህርት ዘርፍ እያደረጉ ስላለው እንቅስቃሴ፣ በተለይ ከንግድ ምክር ቤቶች እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ከጅምሩ መምህር ነበሩ፡፡ ከዚያም ብዙውን ጊዜ በማስተማርና የትምህርት ተቋማትን በማደራጀት አሳልፈዋል፡፡ የትምህርት ዘርፍን በምን ምክንያት መረጡ?
አቶ ፈይሳ፡- ከመጀመሪያውኑ ወደ ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ መምህር ለመሆን በማሰብ በምርጫዬ ነበር የገባሁት፡፡ ይህ የራሱ ተፅዕኖ አለው፡፡ በምኖርበት አካባቢ ከኅብረተሰቡ ውስጥ ታዋቂ፣ ነጭ ሸሚዝ የሚለብስ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መምህር ነበር፡፡ ለመምህርነት የሚሰጠው ግምት መምህር እንድሆን ገፋፍቶኛል፡፡ ገባሁበት፡፡ በሙያው ውጤታማ ሆኜበታለሁ ማለት እችላለሁ፡፡ አሁንም ማስተማርን እወዳለሁ፡፡ በኮተቤ አንደኛ ምርጫዬ ነበር፡፡ በሌሎች ትምህርት ክፍሎች መግባት እችል ነበር፡፡ ነገር ግን መምህርነትን አስቀድሜያለሁ፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስገባም በምሠራቸው ሥራዎች ላይ ከትምህርትና ከሥልጠና ተለይቼ አላውቅም፡፡ የትምህርት ሥራ ከደሜ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከገንዘብ ወይም ከንግድ ጋር አያይዤው ሳይሆን ሙያዬ ብዬ የምሠራበት ስለሆነ ነው፡፡
ሳስተምር ደስተኛ ሆኜ ነው፡፡ ፍቅሩ አለኝ፡፡ ሰው የሚወደውን ከሠራ ውጤታማ ይሆናል፡፡ ብዙ ሰው የንግድ ሥራ ውስጥ ሲገባ በአብዛኛው የሚወስዳቸው መለኪያዎች አሉት፡፡ ትርፍ ያስገኛል ወይ? ወደ ሀብት ይወስዳል ወይ? ብሎ ሊነሳ ይችላል፡፡ ለእኔ ግን የመጀመሪያው መመዘኛዬ ይህንን ሥራ እወደዋለሁ ወይ? የሚለው ነው፡፡ ሰው የሚወደውን ሥራ የሚሠራ ከሆነ ደስተኛ ነው፡፡ እኔ በምመራው ተቋም ብዙ ሰዎች ለሙያው ፍቅር እንዲኖራቸው አድርጌያለሁ፡፡
በግል ወደ ማስተማር ሥራ የገባሁት በቋንቋ ትምህርት ቤት ነው፡፡ በ1993 ዓ.ም. የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ቤት አቋቁሜ አስተምሬያለሁ፡፡ ከዚያም ሐራምቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅን አቋቁሜ እየሠራሁ ነው፡፡ ኮሌጃችን የተለያዩ ዲግሪ ፕሮግራሞችን ይሰጣል፡፡ የድኅረ ምረቃ ፕሮግራም ለመክፈት ቅድመ ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ ከ2500 በላይ ተማሪዎች አሉን፡፡
ሪፖርተር፡- በኮሌጅ ደረጃ ማስተማር ጀምራችኋል፡፡ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ካቋቋማችሁ በኋላ እንደገና ከታች ከኬጂ ጀምሮ በማስተማር ትምህርት የሚሰጥበት ሌላ ትምህርት ቤት ማቋቋሙ ለምን አስፈለገ?
አቶ ፈይሳ፡- ይህ የተደረገበት የራሱ ምክንያት አለው፡፡ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመንግሥት የትምህርት ተቋማት የተረፉትን ነው የምንወስደው፡፡ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚያሠለጥኑት በነፃ ስለሆነ ጠንካራ የሚባሉት የሚገቡት ወደዚያ ነው፡፡ እንደ ሥራ የጀመርኩት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ቢሆንም በኋላ ላይ ነው ወደ መጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጣሁት፡፡ ወደዚህ ያመጣኝ ዋነኛ ምክንያት ወደ ግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመደበኛም ሆነ በተከታታይ ትምህርት የሚመጡት ተማሪዎች ከታች ቢያንስ 10 እስከ 12 ዓመት በትምህርት ሒደት ውስጥ ያለፉ ናቸው፡፡ በመሆኑም የመምህራን ማሠልጠኛ ጀመርን፡፡ በዲፕሎማ ፕሮግራም አካውንቲንግ፣ ሒውማን ሪሶርስ፣ ክሊኒካል ነርሲንግ፣ አይሲቲ የሚባሉት ትምህርት ክፍሎች ነበሩን፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላም የዲግሪ ፕሮግራም ጀመርን፡፡ ግን ጥሩ አፈጻጸም ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ ይህንን ክፍተት መድፈን የምትችለው ከሥር ሄደህ ስትጀምር ነው፡፡ ለዚህም ነው ከሥር የጀመርኩት፡፡ እኔ 12 ዓመት ሌላ ቦታ ተምሮ የመጣ፣ የአመለካከትና የሥነ ምግባር ጉድለት ያለበትን ከመቀበል ይልቅ ከሥር ያለውን ከጀማሪ (ሦስት ዓመት ሕፃን) ጀምሮ በመቀበል እስከ ኮሌጅ ድረስ እንዲጓዝ የሚያደርግ አሠራር ዘርግተን እየሠራን ነው፡፡
ትኩረት ሰጥተህ ካስተማርካቸው፣ ከሥር እየለወጥካቸው ከመጣህ፣ ምርጥ ልጆች ማግኘት ትችላለህ፡፡ እንደ ሐርቫርድ ወዳሉት ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች መፍጠር ትችላለህ፡፡ ስለዚህ መሠረቱ ላይ መሠራት አለበት ከሚል እምነት የተጀመረ ሥራ ነው፡፡ ከሥር ባለው ላይ መሠራት አለበት፡፡ የትምህርት ዕድል ብቻ አይደለም፡፡ ጥራት የሚጀመረው ከዚያ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ስለግል ትምህርት ተቋማት ስናወራ የትምህርት ጥራት ደረጃ መነሳት አለበት፡፡ የግሉ ዘርፍ ለትምህርት ጥራት ምን ሠርቷል ማለት ይቻላል? እናንተስ ምን እያደረግን ነው ትላላችሁ?
አቶ ፈይሳ፡- ይህ ጥናትና ትንታኔ ይፈልጋል፡፡ ጥራት እንደየግለሰቡ የሚታይ ነው፡፡ ጥራትን ደረጃ ስትጠይቅ የኢትዮጵያን የትምህርት ጥራት ደረጃ ከምን ጋር አወዳድረህ ነው? የመንግሥትን ከግሉ ጋር አወዳድረህ ነው? የአሁኑን ከቀድሞ ጋር ስታወዳድር ነው? ከኬንያ ጋር ስትወዳደር ነው? ወይስ አሁን ያለው የትምህርት ጥራት ከጃፓን ጋር ስትወዳደር ነው? ስለዚህ ይህንን ለመመለስ ወይም ትምህርቱ ጥራት አለው የለውም ለማለት የሆነ መስፈርት ማበጀት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ አገር በአንደኛ ደረጃ ትምህርት የግል ዘርፉ ያመጣው ነገር አለ፡፡ ተማሪዎቹ ዓለም የሚጠቀምበትን ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ ለማድረግ የግል ዘርፉ ቅርበት አለው፡፡
መንግሥት ደሃ ሀብታም ሳይል ትምህርትን ማዳረስ ስላለበት የበኩሉን ይሠራል፡፡ ትምህርትን ያዳርሳል፤ የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅም የመንግሥት ነው፡፡ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ግን የግሉ ዘርፍ ኃላፊነት ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ በመንግሥት ብቻ የሚሠራ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- እንደ አንድ የግል የትምህርት ተቋም ባለቤት የትምህርት ጥራት ማስጠበቅ ላይ በአግባቡ ኃላፊነታችንን እየተወጣን ነው ብላችሁ ታስባላችሁ? የግል የትምህርት ተቋማት የምትሠሩት ቢዝነስ ቢሆንም ለአገልግሎታችሁ የምትጠይቁት ዋጋ ከፍተኛ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ይህ ጉዳይ በእጅጉ የሚያነጋግር ነው፡፡ በከተማችሁና በእርስዎ የትምህርት ተቋማት ለአገልግሎታችሁ የምትጠይቁት ክፍያ ምን ያህል ነው?
አቶ ፈይሳ፡- እኛ ከአዲስ አበባ ውጭ ስላለን በዋጋ ትመና ረገድ ሐሜቱም ችግሩም የለብንም፡፡ ምክንያቱም ከፍተኛ የሚባል ክፍያ የሚጠይቁ የሉም፡፡ የመንግሥት ሠራተኛው ሊከፍል የሚችለውን ያህል ነው ትምህርት ቤቶቻችን የሚጠይቁት፡፡ ስለዚህ አዲስ አበባ አለ ያልከው ወቀሳ እዚህ የለም፡፡ ነገር ግን አዲስ አበባ ብዙ ጊዜ ይህ ችግር የሚነሳው ከፍተኛ አቅም ያለውም፤ የሌለውም ስላለ ነው፡፡ ከፋይ አለ፡፡ የሚከፍል ስላለ ደግሞ የማስከፈል ዕድሉ ሊኖር ይችላል፡፡ ትምህርትን ንግድ አደረጉትም አላደረጉት እንደሁኔታው የሚታይ ሊሆን ይችላል፡፡ የትምህርት ባለሙያዎች የሆኑ ለትምህርትና ለኅብረተሰቡ የሚያስቡ ተቋማት እንዳሉ ሁሉ፤ በሌላ በኩል ገንዘቡን ብቻ አይተው የሚሠሩ አይኖርም ሊባል አይችልም፡፡ ስለዚህ በትምህርት ጥራት ላይ ለውጥ ለማምጣት የግል ከፍተኛ ተቋማት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ የበኩላቸውን አስተዋጽኦም እያበረከቱ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ካቋቋሙ በኋላ እንደገና ወደታች ተመልሰው ከኬጂ ጀምሮ ትምህርት የሚሰጥ ተቋም አቋቁመዋል፡፡ ወደዚህ የገቡት ደግሞ በምክንያት ነው ብለዋል፡፡ ይህንን በማድረግዎ የሚፈልጉትን አግኝተውበታል? ያሰብኩትን እያሳካሁ ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ ፈይሳ፡- መንግሥት ያወጣው ሥርዓተ ትምህርት አለ፡፡ በእኔ የተለየ ጥረትና እገዛ ጥራት ያለው ትምህርት ከታች ጀምሮ መስጠት ከተቻለ እኮ ነገ ለእኔ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ግብዓት የሚሆኑ ተማሪዎችን ማፍራት ይቻላል፡፡ ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በቂ ተማሪዎችን ለማግኘት ከሥር ጀምረህ መታገል አለብህ፡፡ ለዚህም ነው ወደታች ወርጄ መሥራት የጀመርኩት፡፡ ሁለቱን ማስተሳሰሬ ደግሞ ወደምፈልገው ግብ ይወስደኛል፡፡
ሪፖርተር፡- በንግድ ምክር ቤቶች ውስጥ የግል ዘርፉን ወክለው ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ እርስዎ ከግል ዘርፉ በተለይም ከትምህርት ተቋማት የተወከሉ እንደመሆንዋ ጥያቄዎች በሚነሱበት በትምህርት ተቋማት ኢንቨስትመንትና መሰል ጉዳዮች ላይ ንግድ ምክር ቤቶች እንዲመክሩበት ያደረጉት አስተዋጽኦ አለ?
አቶ ፈይሳ፡- በንግድ ምክር ቤቶች ሳይሆን በትምህርት ተቋማት ማኅበር በኩል ነው፡፡ በክልል ደረጃ የኦሮሚያ የግል ኮሌጆች ማኅበር አለን፡፡ በዚህ ማኅበር በፕሬዚዳንትነት ሠርቻለሁ፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃም ማኅበር አለን፡፡ በእነዚህ ማኅበራት የትምህርት ደረጃችን ምን ይመስላል ብለን እንመክራለን፡፡ የትምህርት ጥራት ብዙ ጊዜ ይነሳል፡፡ ነገር ግን ይህ ጥያቄ ብዙ ጥናት ይፈልጋል፡፡ የግል ከፍተኛ ተቋማት ሚና ምን መሆን ይገባዋል በሚለው ላይ ብዙ መክረናል፡፡
ሪፖርተር፡- ወደ ንግድ ምክር ቤቶች ተሳትፎዎ ልግባ፡፡ በአዳማ፣ በኦሮሚያ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤቶች ውስጥ በአመራር ደረጃ ቆይተዋል፡፡ የንግድ ምክር ቤቶች እንደ አዲስ እንዲደራጁ ሲወሰን እርስዎም ነበሩና ሒደቱ ምን ይመስላል?
አቶ ፈይሳ፡- መደራጀት አስፈላጊ ነው፡፡ የግለሰቦችን ጉዳይ የምታይበት ዘመን ላይ አይደለንም፡፡ ማደራጀት ብዙ ነገሮች ላይ ተፅዕኖ እንደሚያደርግ አውቃለሁ፡፡ የወጡ መመርያዎች የግል ዘርፉን እንዳይጐዱና የግል ዘርፉ እንዲጠናከር በመንግሥትና በንግድ ኅብረተሰቡ መሀል ድልድይ አለ፡፡ ይህ ደግሞ ንግድ ምክር ቤት ነው፡፡ እኔ ወደ ንግድ ምክር ቤት የመጣሁት በ1995 ዓ.ም. ነው፡፡ ይህም ጊዜ በደርግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 148/70 ተሽሮ፤ አዋጅ ቁጥር 345/95 ሥራ ላይ የዋለበት ነበር፡፡ በዚህ ወቅት የአዳማ ምክር ቤት አባል ነበርኩ፡፡ አዲሱ አዋጅ ሥራ ላይ ሲውል የአዳማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሆኜ ተመረጥኩ፡፡ አዋጁም እኔም ለቻምበር ሥርዓት አዲስ ነበርን፡፡ በአዲሱ አዋጅ ንግድ ለብቻ፤ ዘርፍ ለብቻ በሚል ተከፋፍሎ የተቀመጠ አሠራር ስላለውና አደረጃጀቱም ውስብስብ ስለነበር ብዙ አባል ለማፍራትም ከባድ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበሩት የአዳማ ንግድ ምክር ቤት አባላት በቁጥር አንድ ሺሕ አይሞላም ነበር፡፡ አዲሱ አዋጁ ከፌዴራል እስከ ከተማ የሚደርስ መዋቅር እንዲኖረው ተደርጐ የተቀረፀ ነው፡፡
አዲሱ የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ተግባራዊ ሲሆን፣ የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ነበርኩና ከዚህ አንፃር የአዳማንም ሆነ የኦሮሚያን ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችን የመጀመሪያ ማህተሞች ማስቀረፅ ቻልኩ፡፡ ይህንን ሳደርግ ግን ብዙ ተግዳሮቶች ነበሩ፡፡ ተግዳሮቶቹ ከግንዛቤ ማነስ የመጡ ተግዳሮቶች ነበሩ፡፡ በወቅቱ የንግዱ ኅብረተሰብ በንግድ ምክር ቤቶች አባል መሆን ያለው ጥቅም ምን ያህል እንደሆነ ብዙ ግንዛቤ አልነበረም፡፡ በመንግሥት ኃላፊዎች ዘንድም ቢሆን ሙሉ ግንዛቤ አልነበረም፡፡ ያኔ የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በአዲሱ አዋጅ ቀድሞ ቢመሠረትም የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ስላልተቋቋመ፤ አሮጌው አዋጅ ቀርቶ አዲሱ አዋጅ ሥራ ላይ እንዲውል ወይም የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ይባል የነበረውን ወደ ኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በሚል ለመለወጥ በተቋቋመው ግብረ ኃይል ውስጥ አራት ሆነን ለስድስት ወር በምንሠራበት ወቅት ችግር የሆነው ሁሉንም ነገር በአዲስ አደረጃጀት የማዋቀር ሥራ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በዚህ ግብረ ኃይል ውስጥ ከእርስዎ ጋር እነማን ነበሩ?
አቶ ፈይሳ፡- በወቅቱ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ፣ የትግራይ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋ ገብረ ሥላሴ፣ የደቡብ ንግድ ምክር ቤት አቶ ወልደአማኑኤልና ከኦሮሚያ ደግሞ እኔ ነበርን፡፡ በአዲሱ አዋጅ እንደ አገርም የመጀመሪያዎቹ አመራሮች ነበርን፡፡ ብዙ ሥራዎችም አዲስ ናቸው፡፡ አዲስ መመርያ፣ አዲስ አሠራር፣ አዲስ መዋቅር፣ አዲስ ሠራተኛ መቅጠር ትልቅ ተግዳሮት ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ሁለት ዓመት ሠራን፡፡ በሦስቱም ንግድ ምክር ቤቶች የነበረኝን ሥራ ጨርሼ ወደ ሥራዬ ተመለስኩ፡፡ በወቅቱ የተገነዘብኩት ነገር የቻምበር ሥርዓት ብዙ ችግሮች ያሉበት መሆኑን ነው፡፡ ለአንድ አገር የንግድ ምክር ቤቶች እንቅስቃሴ ወሳኝ የመሆኑን ያህል ብዙ ያለተራመደ መሆኑን ተገነዘብኩ፡፡ ከሌሎች አገሮች ልምድ ጋር ስታነጻጽረውም እልህ የሚያስገባ ነው፡፡ እንደሌሎች አገሮች ንግድ ምክር ቤቶች ጠንካራ መሆን ይገባናል የሚለው እምነቴ ግን አሁንም አለ፡፡ በንግድ ምክር ቤቶች ዙሪያ ያለው ችግር መስተካከል አለበት የሚለው እምነቴ በድጋሚ ወደ ዩኒቨርሲቲ ስገባ የመመረቂያ ጽሑፌን በቻምበር ሥርዓት ላይ እንድሠራ ጭምር ገፋፍቶኛል፡፡ ምናልባት በቻምበር ላይ በማስተርስ ደረጃ መመረቂያ ጽሑፌን የሠራሁት እኔ ብቻ ሳልሆን አልቀርም፡፡ ምክንያቱም በመመረቂያ ጽሑፍ ደረጃ ማጣቀሻዎች አልነበሩም፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ቻምበር ሥርዓት ውስጥ ብዙ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ያሳይሃል፡፡
ሪፖርተር፡- መመረቂያ ጽሑፍዎች በንግድ ምክር ቤቶች አደረጃጀት ላይ ከሠሩ ጽሑፉን ለማዘጋጀት ያደረጉት ጥናት ያመላከትዎ ምንድነው?
አቶ ፈይሳ፡- መመረቂያ ጽሑፌን በንግድ ምክር ቤቶች ላይ እንዳደርግ የገፋፉኝ የንግድ ምክር ቤቶች ሥርዓት መጠናከር አለበት የሚለው እምነቴ ነው፡፡ ሥራውም ዕውቀት ላይ የተመረኮዘ መሆን አለበት የሚለውን እምነቴን አጠናክሮታል፡፡ እንዴት ነው መጠናከር ያለበት? ምንድነው ችግሩ? የሚለውንም እንዳይ ዕድል ሰጥቶኛል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለውጦች እየመጡ ቢሆንም አሁንም ችግሮች አሉ፡፡ ተቋሙ ጠንካራ አመራሮችን ይሻል፡፡ ጠንካራ አደረጃጀት ይፈልጋል፡፡ ይህ ካለ መንግሥትም ያዳምጠሃል፡፡ አብሮ መሥራትንም ያመጣል፡፡ የንግድ ኅብረተሰቡን የሚመለከቱ መመርያዎች ከመውጣታቸው በፊት መነጋገር ያስችላል፡፡ ከወጣ በኋላም ጠንካራ ባለድርሻ ለመሆን የሚቻለው ጠንካራ አመራር፣ ጠንካራ ጽሕፈት ቤት፣ ጠንካራ አደረጃጀት ሲኖር ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ደግሞ የሚያምንበት ተቋም መሆን አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን ያሉት ንግድ ምክር ቤቶች የንግድ ኅብረተሰቡ በሚፈልገው ጥንካሬ ደረጃ ላይ ደርሰዋል? በእርግጥ የሚጠበቅባቸውን ሥራ እየሠሩ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ፈይሳ፡- የንግድ ምክር ቤቶች ኃላፊነት ከፍተኛ ነው፡፡ ንግድ ምክር ቤቶች በሁሉም ደረጃዎች የሚፈለገውን ያህል ሠርተዋል ብሎ ደፍሮ መናገር አይቻልም፡፡
ሪፖርተር፡- ለዚህ ምክንያቱ ምንድነው?
አቶ ፈይሳ፡- አንዱ የግንዛቤ ችግር ነው፡፡ የአብዛኛው የንግድ ኅብረተሰብ ቢዝነስ መደበኛ አይደለም፡፡ የንግዱ ኅብረተሰብ ተምሮ ነጋዴ የሆነ ሳይሆን፣ መደበኛ ካልሆነ መስክ በልምድ የመጣ ነው፡፡ ወደ ውስጥ ጠልቀህ ካየህም አንዱ ሌላኛውን ጠልፎ የወጣ ነጋዴ ነው፡፡ ተገቢ ባልሆነ ውድድር አድገው የመጡም አሉ፡፡ ተደራጅቶ፣ ቡድን ፈጥሮ በቡድን መንፈስ የመጣ አይደለም፡፡ ስለዚህ መደራጀቱን የማይፈልጉ አሉ፡፡ በዚህ በተደራጀ ተቋም በኩል መንግሥትን ማነጋገር ሳይሆን፣ በግል መነጋገርን የሚመርጡ አሉ፡፡ አሁን ባለው ሥርዓት ለምሳሌ የግል ዘርፉን የተመለከቱ ጉዳዮች በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ተካተዋል፡፡ ይህም ማለት ጠንካራ የተደራጀ የንግድ ኅብረተሰቡን የሚወክል ያስፈልጋል፡፡ ጠንካራ ንግድ ምክር ቤት ካለ የንግድ ኅብረተሰቡን አመኔታ ያገኛል፡፡ ካልተጠናከረ ግን በልምምጥ ብቻ አባል ማድረግ አትችልም፡፡
ሪፖርተር፡- በተለያየ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ የንግድ ምክር ቤቶች ዓበይት ችግሮች ከሆኑት አንዱ ጠንካራ ተቋም ያለመፍጠር ነው፡፡ በተለይ የአባላት ድርቅ መቷቸዋል፡፡ በንግድ ምክር ቤቶች ውስጥ በአመራር ደረጃ ከሚሳተፉ ጠንካራ ተቋም በመፍጠርና አባላትን በማበራከቱ ረገድ ምን ሠርታችኋል?
አቶ ፈይሳ፡- ለዚህ የምሰጥህ አስተያየት ሌሎች ንግድ ምክር ቤቶችን አይወክልም፡፡ እንደ አዳማ ንግድ ምክር ቤት ግን በተለየ መንገድ የአባላትን ቁጥር ለማሳደግ ችለናል፡፡ ጥቂት የነበሩትን አባላት ከ10 ሺሕ በላይ አድርሰናል፡፡
ሪፖርተር፡- ከሦስት አራት ዓመታት በፊት አባሎቻችሁ ከሦስት ሺሕ አይበልጡም ነበር፡፡ በእርግጥ ከ10 ሺሕ በላይ ደርሰናል ካላችሁ ይህ እንዴት ሆነ?
አቶ ፈይሳ፡- የአባላትን ቁጥር በዚህ ደረጃ ማሳደግ የተቻለው በእኛ ጥረት ብቻ አይደለም፡፡ ከከተማው አስተዳደር ጋር በመሥራታችን ጭምር ነው፡፡ አንደኛው አዳማ ውስጥ ሰባትዮሽ የሚባል ቡድን አለ፡፡ ይህ ቡድን የንግዱን ኅብረተሰብ ችግር የምንፈታበት ነው፡፡ በዚህ ቡድን ውስጥ ከሁለቱ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች፣ ከፌዴራል፣ ከዞንና ከአዳማ ከተማ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ተወካዮች፣ የከተማውና የዞኑ የንግድና ገበያ ኤጀንሲ ተወካዮች ያሉበት ቡድን ነው፡፡ ይህ ቡድን በመቋቋሙ በከተማው የሚነሱ የንግድ ኅብረተሰቡ ችግሮችን ለመፍታት ረድቶናል፡፡ ሁለተኛው መዋቅራችን በቢሮ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በከተማ ውስጥ ባሉት ቀበሌዎችና የከተማው ንግድና ገበያ ኤጀንሲ አደረጃጀት ውስጥ ሁሉ የእኛ ሠራተኞች አሉ፡፡ ከዚያ በፊት ግን የንግድ ምክር ቤቱ ጥረት ብቻ ነበር፡፡ የመንግሥት እገዛ አልነበረም፡፡ መተጋገዙ በመኖሩ የአባላት ቁጥር ሊጨምር ችሏል፡፡ ይህ ሞዴል ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በንግድ ምክር ቤት ትልቁ ችግር የአባልነት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤቶች አባልነት በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በሌሎች አገሮች ግን የንግድ ምክር ቤት አባልነት በግዴታ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤቶች ውስጥ የአባላት ቁጥር እጅግ አነስተኛ ነው ሲባል የሚሰጠው መልስ አባልነት በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ነው ይባላል፡፡ 300 ሺሕ ነጋዴ ባለበት ከተማ የንግድ ምክር ቤት አባል የሚሆነው 10 እና 15 ሺሕ ብቻ ነው፡፡ በአባላት ማበራከት ላይ ያለው መሠረታዊ ችግር ምንድነው?
አቶ ፈይሳ፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁለት ዓይነት የማኅበራት አወቃቀር አለ፡፡ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተና በፈቃደኝነት ላይ ያልተመሠረተ ማለት ነው፡፡ የእኛ ንግድ ምክር ቤቶች አደረጃጀት በመንግሥት አዋጅ የተመሠረተ ማኅበር ነው፡፡ ለምሳሌ የኬሚስትሪ፣ የኢኮኖሚክስ፣ የመሳሰሉት ባለሙያዎች ማኅበራት አሉ፡፡ እነዚህ ነፃ ማኅበር ናቸው፡፡ መመሥረቻ ጽሑፋቸውን ራሳቸው ሠርተው ውልና ማስረጃ ሄደው የሚመዘገቡ ናቸው፡፡ ከመንግሥት አሠራር ጋር በተያያዘ (ፐብሊክ ሎው) የሚቋቋሙ ማኅበራት ይዘት ግን ይለያል፡፡ ዓለም አቀፋዊ ልምዱ እንደሚያሳየውም በዚህ ሕግ የሚቋቋሙ እንደ ንግድ ምክር ቤት ያሉ ተቋማት ከመንግሥት ድጋፍ ማግኘት አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያን ልምድ በምሳሌነት ልንገርህ፡፡ በንጉሡ ጊዜ ቻርተር ነበር፡፡ በመንግሥት ሕግ ለተቋቋመ ቻምበር ድጋፍ ይሰጣል ስንል፤ ለምሳሌ ሜክሲኮ አደባባይ የሚገኘው የኢትዮጵያ የንግድ ምክር ቤት ባለሰባት ወለል ሕንፃ የተገነባው በወቅቱ የነበሩ 400 አባል ነጋዴዎች ባዋጡት ገንዘብ አይደለም፡፡ በመንግሥት የቀረጥ ቴምብር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር በንጉሡ ተፈቅዶ የተሠራ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ንግድ ምክር ቤቱ በመንግሥት አዋጅ የተቋቋመ በመሆኑ ድጋፍ መደረግ ስላለበት ነው፡፡
የፈረንሳይ ንግድ ምክር ቤት በፐብሊክ ሎው የተቋቋመ በመሆኑ ከወደብ የሚገኝ ገቢ ለንግድ ምክር ቤቱ ፈሰስ ይደረጋል፡፡ መንግሥት ከሚሠራው ሥራ ገቢ ይሰጣል፡፡ ሌሎች አገሮች አዳዲስ የንግድ ፈቃዶችን ከሚያወጡ ነጋዴዎች ከሚከፈለው ገንዘብ የተወሰነውን ለንግድ ምክር ቤቶች ማጠናከሪያ ያውላሉ፡፡ ይህ የሆነው በፐብሊክ ሎው የተቋቋሙ በመሆናቸው ነው፡፡ በፐብሊክ ሎው ከተመሠረተና አባልነት ግን በግል ፍላጐት ላይ የተመሠረተ ከሆነ መንግሥት የሚያደርገውን ድጋፍ የሚስብ አድርገው ስለሚወስዱት አባል መሆን ያለባቸው ሰዎች አባል እንዲሆኑ ይገፋፏዋቸዋል፡፡ የእኛ ግን በፐብሊክ ሎው የተቋቋመ ቢሆንም እንደሌላው አገር አይደለም፡፡ ከመንግሥት የሚፈለገው ድጋፍ ተገኝቷል ማለት አይቻልም፡፡
እነዚህ ማኅበራት ልክ እንደ ነፃ ማኅበራቱ ከኖርክ ኑር ካልኖርክ የራስ ጉዳይ የተባሉ ናቸው፡፡ እንደ አዳማ ቻምበር ግን እኛ የዕድሉ ተጠቃሚዎች ሆነናል፡፡ ከመንግሥት ምን ይጠበቃል በሚለው ጉዳይ ላይ በከተማ ደረጃ ግንዛቤ ፈጥረናል፡፡ ለምሳሌ ፈቃድ በሚታደስበት ቦታ የመንግሥት አካላት የንግድ ምክር ቤት አባል መሆን አለባችሁ ብለው ራሳቸው ግንዛቤ መስጠታቸውና መቀስቀሳቸው የንግድ ምክር ቤቱን አባላት ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ አድርጓል፡፡ የመንግሥት ተሳትፎ መጨመሩ ለአባላት ቁጥር ዕድገት አስተዋጽኦ በማድረጉ የተገኘ ውጤት ነው፡፡
አሁንም ከላይ ጀምሮ በአንድ ዓመት ውስጥ ዕድሉን ይጠቀምበት አይጠቀምበት አላውቅም፡፡ ዕድሉ ግን ነበር፡፡ እኛ ማኅበራቱን በምናደራጅበት ጊዜ ሠራተኛና ባለሙያ ተመድቦ፣ አባል የመሆን አስፈላጊነቱ በመንግሥት አካል ተጠቅሶ መደራጀት አስፈላጊ መሆኑ ለየአንዳንዱ ነጋዴ የሚነገርበት መዋቅር ተዘርግቷል፡፡ እኛ ይህንን ዕድል ተጠቅመናል፡፡ ሌሎቹ ይህንን ዕድል ስለመጠቀማቸው አላውቅም፡፡
ሪፖርተር፡- መደራጀት እንዲታመንበት ተደርጓል፡፡ የዛሬ አሥር ዓመት ግን ይህ አመለካከት አልነበረም፡፡ ባበራከታችኋቸው አባላት ልክ አገልግሎት እየሰጣችሁ ነው?
አቶ ፈይሳ፡- ለንግዱ ኅብረተሰብ የሚፈለገው አገልግሎት ምንድነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት ያሻል፡፡ የንግድ ምክር ቤቶች የመንግሥትን ሚና መጫወት የለባቸውም፡፡ መንግሥት የተደራጀ በመሆኑ በራሱ የሚሠራውን ሥራ ይሠራል፡፡ የተደራጀን፣ ነባር ንግድ ምክር ቤት በመሆናችን ለምሳሌ በቁርጥ ግብር ትመና የእኛ ተሳትፎ አለ፡፡ አብሮ መተመን ማለት ነው፡፡ ቅሬታዎች ሲኖሩ አብሮ የማየት ልምድ አለ፡፡ በታክስ ጉዳይና በመሳሰሉት ላይ ሥልጠና የመስጠት ልምድም አዳብረናል፡፡ እኛ ባለሙያ ስላለን፣ አማካሪ ስላለንና የመንግሥት ድጋፍ ስላለን ጭምር ውጤታማ ሆነናል ማለት ይቻላል፡፡ ዱሮ የፈለግነውን ያህል ብንንቀሳቀስ አባል እሆናለሁ ብሎ የሚመጣ የለም፡፡ አሁን ግን ሥልጠናውን በሰጠህ ቁጥር ችግሮቹንም እየፈታህለት ስትሄድ አባል ለመሆን ይመጣል፡፡ ከአሁን በኋላም አዲሱ ትውልድ በአደረጃጀቱ እያመነ ይመጣል፡፡ በመንግሥት መልካም አስተዳደር ውስጥ ያሉ ጉድለቶችን የሚለይ፣ ለግል ዘርፉ የሚቆረቆር የጋራ አገር ለመመሥረት በሚደረግ ጥረት ውስጥ የራሱን አሻራ ለማሳረፍ የሚጥር ሁሉ በመጣ ቁጥር ለውጥ ይመጣል፡፡ ይህ ሲሆን ችግሮቹና ያለው ክፍተት እየጠበበ ልክ ሌሎች አገሮች እንደሚያደርጉት ነጋዴውን ታክስ ለምን አልከፈልክም ሳይሆን ታክስ ለምን አልተቀበልከኝም ብሎ የሚሞግት ዜጋ ልታገኝበት ትችላለህ፡፡
ሪፖርተር፡- አባሎቻችን የተጣለባቸው ግብር አግባብ አይደለም ብላችሁ እንደምትከራከሩት ሁሉ አባሎቻችሁ በአግባቡ ግብር እንዲከፍሉ ያደረጋችሁት ጥረት ምንድነው?
አቶ ፈይሳ፡- በዚህ በኩል የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን እንሰጣለን ከማለት ውጭ የተለየ ሚና ተጫውተናል ማለት አይቻልም፡፡ አንዳንዴ እኛ የምናስበውና እየሆነ ያለው ነገር እርስ በርስ ይጣረሳል፡፡ ሥልጠና እንሰጣለን ብንልም ብዙው የንግድ ኅብረተሰብ ሥልጠናውን አይፈልግም፡፡ አንዳንዴ ለሥልጠና የምንጋብዛቸው የሥራ ኃላፊዎችን ሊሆን ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- ሥልጠናዎች አይወደዱም የሚባለው ከሥልጠናው ጠቀሜታ ጋር ይያያዛል፡፡ ለንግዱ ኅብረተሰብ በትክክል ጠቃሚ የሆነና በልካቸው የተዘጋጀ ሥልጠና ካለመስጠት ጋር አይገናኝም?
አቶ ፈይሳ፡- ግልጽ እኮ ነው፡፡ በአብዛኛው የሚሰጡት ሥልጠናዎች አካዴሚክ አይደሉም፡፡ ከመመርያና ደንብ ጋር የተያያዙ በተግባር የንግዱ ኅብረተሰብ የሚጠቀምባቸው ናቸው፡፡ ሥልጠናዎቻችን ለምንድነው ግብ የማይመቱት ስንል ግን ሰዎች ለሥልጠና ካላቸው የግንዛቤ ማነስ ነው፡፡ ምክንያቱም ወደ ንግዱ የገባው አብዛኛው ኢመደበኛ በሆነ የአካዴሚ ዕውቀት ኖሮት አይደለም፡፡ በሥልጠና ሥራቸውን ሊያሳድጉ እንደሚችሉ ብዙዎች ቢገነዘቡም፣ አሁንም ገና ነው፡፡ ነባር የምትላቸው ትላልቅ ኩባንያዎች ሥልጠና እንደሚጠቅም እየተረዱ ያሉት አሁን ነው፡፡ በንግድ ምክር ቤቶች ከሚሰጡት በርካታ ሥልጠናዎች አንፃር ብዙ ተለውጧል ማለት አይቻልም፡፡ የሥልጠናዎች ግብ ያለመምታት በእኛ ብቻ ሳይሆን በመንግሥትም ደረጃ የሚታይ ነው፡፡ ሥልጠና የሚሰጠው የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት ነው፡፡ ጥረቱ ግን ግቡን አልመታም፡፡
ሪፖርተር፡- የንግድ ምክር ቤቶችን የሚመሩ ሰዎች ብቃት ጥያቄ የሚያስነሳ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የንግድ ምክር ቤቶች ጠንካራ ያለመሆን ከአመራር ብቃት ጋርም ይያያዛል፡፡
አቶ ፈይሳ፡- ይህ በአንዳንድ ቦታዎች በግልጽ የሚታይ ነው፡፡ የአመራር ጥራቱ ባለፉት 10 ዓመታት ምን ደረጃ ላይ ነው ካልክ ወጥነት ያለው አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- አዳማ ንግድ ምክር ቤት ትልልቅ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ አደርጋለሁ ብሎ ነበር፡፡ ለምሳሌ የኤግዚቢሽን ማዕከል ግንባታ አንዱ ነው፡፡ ይህ ከምን ደረሰ?
አቶ ፈይሳ፡- ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል የባለስድስት ፎቅ የማስፋፊያ ሥራ እየሠራን ነው፡፡ የሕንፃው ዲዛይን አስነስተን ለአስተዳደሩ አቅርበን ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ የኤግዚቢሽን ማዕከሉን ለመገንባት የቀረበው የቦታ ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ የማዕከሉ ግንባታ ግን በንግድ ምክር ቤቱ ብቻ እንደማይሠራ በመገንዘባችን የማዕከሉ አገልግሎት ለከተማው አስተዳደርም ስለሆነ የመጀመሪያ ዲዛይናችንን ለውጠናል፡፡ ለብቻችን ሳይሆን ከከተማው አስተዳደር ጋር ለመሥራት ወስነናል፡፡ ሐሳባችንን ልንለውጥ የቻልነው ቋሚ ማዕከሉ በጋራ መሠራት ስላለበት ነው፡፡ ሐሳባችንን የለወጥነው ቋሚ ማዕከሉ ከተማውን ሊለውጥ በሚችል ደረጃ መሠራት አለበት የሚለውን አቋም ስናራምድ ነው፡፡
የማዕከሉ ግንባታ የሚጠይቀው ኢንቨስትመንት ግን በቻምበሩ የሚሸፈን ነው፡፡ ነገር ግን የመሬት አቅርቦትና ሌሎች ሎጂስቲኮች የሚጠበቀው ከመንግሥት ነው፡፡ ለግንባታ የሚፈለገው ቦታ ሰፊ በመሆኑ መንግሥት በሚገባ ሊያምንበት ይገባል፡፡
ሪፖርተር፡- ከዚህ በፊት ግን ሐሳባችን ተቀባይነት አግኝቷል ብላችሁ ነበር?
አቶ ፈይሳ፡- አዎ፡፡ ግን ቴክኒካል ሥራው ጊዜ ፈጀ፡፡ ያኔ እኛ እንዳሰብነው ባዘጋጀነው አጭር ትልመ ሐሳብ የሚያልቅ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ያቀረብነው ሐሳብ ብዙ ይዘቶችን ወለደ፡፡ አብረው የሚሄዱ በርካታ ጉዳዮች መጡ፡፡ አዳራሽ መሥራት ብቻ ሳይሆን የሌሎቹን አገሮች ቋሚ ኤግዚቢሽን ማዕከሎች ሁሉ ቀምሮ የሚሠራ ነው፡፡ ሌሎች ግንባታዎችን አካትቷል፡፡ ከአዳማ ፈጣን ዕድገት ጋር የሚመጥን ሥራ መሠራት አለበት ከሚል ለውጡ የተደረገው፡፡