Sunday, July 14, 2024

​​​​​​​‹‹በየጊዜው የሚለዋወጥ የአመራር ፍልስፍና ሊኖረን ይገባል››

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

አምባሳደር ወንድሙ አሳምነው፣ በሶማሊያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ  ሥልጣን አምባሳደር

አምባሳደር ወንድሙ አሳምነው የተወለዱት ትግራይ ክልል ሃ ነው፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በሃ ካጠናቀቁ በኋላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን መቐለ ከተማ ተምረዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ካጠናቀቁ በኋላ፣ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ግንኙነት አግኝተዋል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥራ የጀመሩት አምባሳደር ወንድሙ፣ ናይሮቢና ዋሽንግተን ዲሲ በተለያዩ ኃላፊነቶች ሠርተዋል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ዋና ዳይሬክተርም ነበሩ፡፡ አሁን በሶማሊያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሲሆኑ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደ 24 ዓመት አገልግለዋል፡፡ በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ደግሞ ከ2005 ዓ.ም. ነሐሴ ወር ጀምሮ ነው፡፡ አምና ‹‹የአመራር ሥነ ልቦና›› የተሸኘ መጽሐፍ ለንባብ አብቅተዋል፡፡ ይህ መጽሐፍ በዋነኝነት በአመራር ኃላፊነት ዙሪያ የሚታዩ የአመለካከት ችግሮችና መፍትሔያቸውን፣ ምን ዓይነት የአመራር ፍልስፍናና ዘይቤ እንደሚያስፈልግ፣ የማኅበረሰቦች ውድቀትና ትንሳዔ በአመራሩ ባህርይ የሚወሰን መሆኑን፣ ለመልካም አስተዳደር መስፈንና ግንባታ አመራር የሚጫወተው ቁልፍ ሚና፣ እየተለወጠ ከሚሄደው ዓለምና ከአዳዲስ አስተሳሰቦች ጋር መላመድ መቻል፣ አዲሱን ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባህርይ በቅጡ ማወቅ፣ ወዘተ በማካተት ለውይይት መንደርደርያ ሐሳቦች ከበርካታ ምሳሌዎች ጋር ቀርበውበታል፡፡ በተጨማሪም አገር በየጊዜው የምትመራበት ሐሳብና ፍልስፍና መሻሻል እንዳለበት፣ የትናንትና ሐሳብ ለዛሬ ጥያቄዎች መፍትሔ አለመሆኑ፣ የአመራር ፍልስፍና ከጊዜው ጋር ተለዋዋጭ መሆኑ፣ ወዘተ በመጽሐፉ ተወስተዋል፡፡ በመጽሐፉ ዙሪያ መላኩ ደምሴ አምባሳደር ወንድሙን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በዓለም አደገኛ ከሚባሉ ሥፍራዎች አንዱ ሶማሊያ ነው፡፡ በዚህ አደገኛ ሥፍራ መሥራት በግል ምን ዓይነት ስሜት ይፈጥርብዎታል?

አምባሳደር ወንድሙ፡- ከሙያ አንፃር ዲፕሎማትና ወታደር አንድ ነው፡፡ መንግሥትና ሕዝብ ወደላከው ቦታ ነው ሄዶ የሚሠራው፡፡ ከዚህ አንፃር መጀመርያውኑ ቃል ገብተን የጀመርነው ሥራ ስለሆነ ከሙያ አንፃር ችግር የለውም፡፡ ከግል አንፃር ግን በውጭ ጉዳይ ሶማሊያ ውስጥ መሥራት ቀላል አይደለም፡፡ ማኅበራዊ ግንኙነቶች በጣም ውስን ናቸው፡፡ በአንድ ግቢ ውስጥ ነው የምንኖረው፡፡ ለሥራ ካልሆነ ብዙም እንቅስቃሴ የለም፡፡ ከቤተሰብ ውጭ ነው እዚያ የሚኖረው፡፡ ከሕይወት አንፃር ከባድ ነው፡፡ ከተልዕኮ አንፃር ግን ክብር ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ስትራቴጂ ጥቅም አንፃር ሶማሊያ ትልቅ ቦታ አላት፡፡ ለዚያ ኃላፊነት ይበቃል ተብሎ አንድ ሰው ሲመደብ ከግልም ይሁን ከፕሮፌሽናል ሕይወት አንፃር ትልቅ ክብር ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ሶማሊያ ውስጥ ሰላም ለመፍጠር በተደረገው ጥረት ውስጥ የነበራት ሚና ምን ይመስላል? አሁንስ እንዴት ነው?

አምባሳደር ወንድሙ፡-  ሶማሊያ ቀውስ ውስጥ ከገባች 25 ዓመቷ ነው፡፡ በእነዚህ 25 ዓመታት ውስጥ የሶማሊያን የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት ወደ 18 የሰላም ሒደቶች ነበሩ፡፡ በ18 የሰላም ሒደቶች ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ነበረች፡፡ ከወታደራዊ ፀጥታ አንፃርም አልሸባብ አለ፡፡ ከዚህ በፊትም ብዙ ዓይነት ገጽታ ያላቸው የሰላም ችግር የፈጠሩ ኃይሎች ነበሩ፡፡ እነሱን ከማረጋጋትና ይኼን የፀጥታ ችግር ከመፍታት አንፃር ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ነበረች፡፡ ከፖለቲካውም ይሁን ከፀጥታው አንፃር ኢትዮጵያ በሶማሊያ ጉዳይ ላይ የማይተካ ሚና ነበራት፡፡ አላት ብለን ማለት እንችላለን፡፡

ሪፖርተር፡- በፖለቲካና በደኅንነት ብቻ ሳይሆን በዲፕሎማሲ መስክስ እዚያ አካባቢ ያላት ተቀባይነት ምን ይመስላል?

አምባሳደር ወንድሙ፡-  እንደሚታወቀው ከሶማሊያ ጋር የነበረን ግንኙነት በጣም ብዙ ችግሮች የነበሩበት ነው፡፡ አሁን መሠረታዊ ለውጥ አለ ማለት ይቻላል፡፡ ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ አንደኛ በታሪካችን ለመጀመርያ ጊዜ የወታደራዊ ስምምነት አሁን ነው የተፈራረምነው፡፡ ወታደራዊ ስምምነት የሚፈራረሙ አገሮች በከፍተኛ የመተማመን ደረጃ ላይ ያሉ አገሮች ናቸውና ግንኙቱ የደረሰበትን ከፍታ ማሳየት ይቻላል፡፡ ሁለተኛ ከዚህ ቀደምም ሆነ አሁን ሠራዊታችን ወደ ሶማሊያ ሲገባ በሶማሊያውያን ግብዣ ነው፡፡ ይኼ ሁለተኛ የመተማመን ደረጃ የሚያሳይ ነው፡፡ ከዲፕሎማሲና ከፖለቲካ ጉዳዮች አንፃርም ሲታይ ማንኛውም የፖለቲካ ችግር ሲፈጠር ሁለም የሶማሊያ ፖለቲካ ተዋናዮች በኢትዮጵያ ላይ ነው ዕምነት ያላቸው፡፡ ኢትዮጵያን ነው እንድትሸመግላቸው የሚጠይቋት፡፡ በአጠቃላይ ከፖለቲካና ከዲፕሎማሲ አንፃር በመሠረቱ ግንኙነታችን ተቀይሯል ማለት ይቻላል፡፡ ከሁለም በላይ ደግሞ ትልቁ ነገር በኢትዮጵያ ላይ ሶማሊያውያን ያላቸው አመላካከት ተቀይሯል፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት እነሱ በደከሙበት ጊዜ ከፖለቲካም ሆነ ከወታደራዊ አንፃር እነሱን ለመርዳት ባደረግነው ድጋፍ መሠረት አመለካከቱ ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል፡፡ ሶማሊያውያን አገራቸው ችግር ውስጥ ሆና ሲሰደዱ ልጆቻቸውን እንደ ልጆቻችን አድርገን ያስተናገድንበት ሁኔታ ይኼንን አመለካከት ለመቀየር ረድቷል፡፡ ከሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት፣ ከመንግሥት ለመንግሥትና ከሁሉም ግንኙነት አንፃር የኢትዮጵያና የሶማሊያ ግንኙነት ተለውጧል፡፡ ይህ በኢትዮጵያ የተለወጠው አዲሱ የትብብር የውጭ ፖሊሲ የፈጠረው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አልሸባብ በተለያዩ ጊዜያቶች በአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ኃይልና በኢትዮጵያ ወታደሮች ጥምር ጥቃት እንደደረሰበት በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ተዘግቧል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ እያንሰራራ የተለያዩ ጥቃቶች ሲፈጽም ይታያል፡፡ ሕገወጥ የመሣሪያ ዝውውሮችም አሉ፡፡ አልሸባብ አሁንም ለአካባቢው ሥጋት እንደሆነ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የወደፊቱ የሶማሊያ ተስፋ ምንድነው?

አምባሳደር ወንድሙ፡-  ሶማሊያ አሁን ያለችበትን ሁኔታና ለውጡን የምንገመግመው ከነበረችበት አንፃር ነው፡፡ እንደሚታወቀው ሶማሊያ የጦር አበጋዞች አገር ነበረች፡፡ በየወረዳውና በየጎሳው ራሳቸውን የቻሉ መንግሥታት ነበሩ፡፡ በየአካባቢው የተለያዩ ስም ያላቸው ስደተኞች ነበሩ፡፡ ሞቃዲሾ ሳትቀር በሽብርተኞች እጅ ነበረች፡፡ አሁን የተለወጠው ይህ ነው፡፡ አሁን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው መንግሥት አለ፡፡ አብዛኛዎቹ የሶማሊያ ከተሞች በመንግሥት እጅ ናቸው፡፡ አሁን ሽብርተኞቹ በማፈግፈግ ላይ ነው ያሉት፡፡ ይኼ ሲባል ግን እንደተባለው ችግር የለም ማለት አይደለም፡፡ የለውጥ አዝማሚያውን እያየን ነው ተስፋ አደረግን የምንለው እንጂ በሶማሊያ ሁሉም ነገሮች ተፈትተው፣ ሁሉም ነገሮች ቀና ሆነው እየሄዱ ነው ማለት አይደለም፡፡ ግን በእኛና በሌሎች አገሮች ድጋፍ ሶማሊያ ደህና አቅጣጫ ውስጥ አለች ማለት ይቻላል፡፡  

ሪፖርተር፡- በ2007 ዓ.ም. ‹‹የአመራር ሥነ ልቦና›› የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ አሳትመው ለንባብ አብቅተዋል፡፡ ይህንን መጽሐፍ ስያሜውንና ይዘቱን ጠቅለል አድርገው ቢገልጹልን?

አምባሳደር ወንድሙ፡-  ‹‹የአመራር ሥነ ልቦና›› በማለት መጽሐፉን ስያሜ ስሰጠው ሁለት ቃላት አሉ፡፡ አንዱ አመራር ነው፡፡ አመራር ሲባል መንግሥታዊ ፖለቲካዊ አመራር ብቻ አይደለም፡፡ አመራር ከግል ሕይወት አመራር ይጀምራል፡፡ ከቤተሰብ አመራር ይጀምራል፡፡ የማኅበራት፣ የድርጅቶች፣ በትልቁ ደግሞ የአገር አመራርን ይይዛል፡፡ አንደኛ ስለአመራር ነው መናገር የፈለግኩት፡፡ ሁለተኛ ሥነ ልቦና የሚል ቃል አለው፡፡ የአመራር ሥነ ልቦና ስንል ደግሞ የተለያየ መልክ ያለው አመራር፣ ስለኃላፊነትና ስለሥልጣን ያለውን አመለካከት የሚመለከት ነው፡፡ ሥልጣን ዓለማው ምንድነው? ኃላፊነት ዓላማው ምንድነው? ከምንመራው አካል ጋር ያለን ግንኙነት ምንድነው? ምን ዓይነት እሴቶች አሉን? በስኬትና በውድቀት ላይ ያለን ግንዛቤ ምንድነው? ይኼ የአመራር ሥነ ልቦናችን የአመራራችንን የውድቀትና የትንሳዔ ነገርን ይወስነዋል፡፡ ምክንያቱም በማንኛውም የሕይወት ዘርፍ ሐሳብ የተግባር እናት ነች፡፡ ሥነ ልቦናችንና አመለካከታችን በአመራርም ጭምር የውድቀትና የትንሳዔያችን መነሻ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ በአዲስ ምዕራፍ ውስጥ ነች፡፡ ይኼንን አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ለማስቀጠል ምን ዓይነት የአመራር ሥነ ልቦና ያስፈልጋል በሚል መነሻ የተጻፈ ነው፡፡ ስምንት ምዕራፎች አሉት፡፡ እነዚህን ነገሮች እያጣቀሰ የሚሄድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በመጽሐፉ መሠረታዊ ሐሳብ ተብለው ከተገለጹት ውስጥ ዋነኛው ትኩረትን የፖለቲካ አመራር ላይ ማድረግ ነው፡፡ በሌሎች የተለያዩ ዘርፎች ውስጥ የሚሳተፉ አመራሮችንም እንደሚያካትት ተገልጿል፡፡ ነገር ግን መጽሐፉ በአብዛኛው ትኩረቱ ፖለቲካ ላይ ነው፡፡ ይኼ የሆነው ለምንድነው?

አምባሳደር ወንድሙ፡-  ማለት የፈለግኩት ሁሉም ዓይነት ገጽታ ያለው አመራር የውድቀትና የትንሳዔ መሠረት ተመሳሳይ ነው፡፡ የፖለቲካ፣ የግል፣ የቢዝነስም አመራር ቢሆን ተመሳሳይ ነው፡፡ አብዛኛው ትኩረቱ ግን በፖለቲካ አመራር ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም የአገራችን ለውጥ የመጣው በአዲስ የአመራር ሥነ ልቦና ነው፡፡ ኢትዮጵያ የነበረችበትን፣ ለዘመናት የቆየችበትንና የችግሯ ምክንያት የሆነውን አመለካከት ቀርፎ በአዲስ አቅጣጫ መምራት የጀመረ የአመራር ትውልድ ስለመጣ ነው፡፡  ይህን የተለወጠ ሁኔታ ለማስቀጠል ደግሞ ከሁኔታዎች ጋር የሚመጥን ሕይወትና የተለወጡ አገሮች የሚጠይቁት የአመራር ጥያቄ የሚመልስ የአመራር ሥነ ልቦና ያስፈልጋል፡፡ ትኩረቴ የኢትዮጵያን የለውጥ ሒደት ለማስቀጠል ምን ዓይነት የፖለቲካ አመራር ያስፈልጋል የሚለው ላይ ነው፡፡ እዚያ ያሉት መሠረተ ሐሳቦች ለሁሉም ዓይነት የአመራር ዝርያዎች መሆን ይችላሉ ማለት ነው የፈለግኩት፡፡

ሪፖርተር፡- ከፈጣን የዓለም ለውጥ ጋር የሚመጡ አዳዲስ ሐሳቦች መጽሐፉ ውስጥ ተተንትነዋል፡፡ እነዚህ ሐሳቦች ምን ምን ያካትታሉ?

አምባሳደር ወንድሙ፡-  አንደኛው የአንድ ተግባር እናት ሐሳብ ነው እንዳልኩት፣ በየጊዜው አገር የምንመራበትን ሐሳብና ፍልስፍና ማሻሻል አለብን፡፡ የትናንትና ሐሳብ ለዛሬ ጥያቄዎች መፍትሔ አይሆንም፡፡ ስለዚህ በየጊዜው የሚለዋወጥ የአመራር ፍልስፍና ሊኖረን ይገባል፡፡ ሁለተኛው መርህ እያንዳንዱ ዘመን የየራሱ ዓይነት የአመራር ትውልድ ይጠይቃል፡፡ አሁን በአገራችን የመተካካት የአመራር ሥርዓት አለ፡፡ ያ ሥርዓት ይኼን ሥርዓት ለማስቀጠል በጣም ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ በመጽሐፉ ላይ ያለው ይኼ መሠረተ ሐሳብ ሆኖ የጀመርነው መልካም የመተካካት ሥራ በሚፈለገውና የአመራር ሳይንስ በሚጠይቀው ሥርዓት እየሄደ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ቆም ብለን እንድንመረምር የሚያስታውስ ነው፡፡ ሦስተኛው እኛ የምንሠራው በተለወጠ የዓለም ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡ በጣም ፈጣን የሆነ ‘ግሎባላይዝድ’ በሆነ ዓለም ነው፡፡ ደሴት ውስጥ አይደለም ይኼን ለውጥ እያስኬድን ያለነው፡፡ ከዚህ አንፃር የዓለም ወቅታዊ ሁኔታ ምን ይመስላል? በዚህ ሁኔታ የኢትዮጵያ ፖሊሲና ዲፕሎማሲ ምን መሆን አለበት? ይኼ ፖሊሲና ዲፕሎማሲ የአገራችንን ለውጥና ትንሳዔ ለማስቀጠል ምን ዓይነት ድጋፍ ይኖረዋል? እያለ ይሄድና ማሠሪያው ይኼን የለውጥ ሒደት ለመምራት የሚያስችል ክህሎትና ሥነ ምግባር ያለው የአመራር ትውልድ ያስፈልጋል የሚለው ነው፡፡ መርሆዎቹ በእነዚህ ሁኔታዎች ያጠነጥናሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የአመራር ክህሎት ማሳያ ከሚባሉ ጉዳዮች መካከል የዛሬን ኃላፊነት መወጣት ብቻ ሳይሆን፣ ተተኪን በብቃት ማፍራትና ብቃት ያላቸው ተቋማት መገንባት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር እርስዎ ያነሷቸው ነጥቦች እነዚህን እንዴት ያዳብራሉ?

አምባሳደር ወንድሙ፡-  በአፍሪካ ያለው ዋና ፈተና የትውልዶች የቅብብሎሽ ሰንሰለት ሰላማዊ አለመሆን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን የተጀመረው የመተካካት ሥራ ታሪካዊ ትርጉም አለው፡፡ አንደኛ ዘመን ከመለወጡ አንፃር አሁን ለዚህ የሚበቃ ትውልድ ለመፍጠር የተዘጋጀ አመራር አለን፡፡ ሁለተኛ ከሰላም አንፃር የሥልጣን ሽግግሩ ሰላማዊ እስካልሆነና ሥርዓት እስከሌለ ድረስ በሌሎች ሥፍራዎች እንደምናየው ሽግግሩ በጦርነት ላይ የተመሠረተ ይሆናል፡፡ ይኼ ሥርዓትና ይኼ ሽግግር መጀመሩ ጥሩ ሆኖ አንደኛ ለዘመኑ የሚበቃ የአመራር ትውልድ ከማብቃት አንፃር በቂ ሥራ እየሠራን ነው ወይ? ሁለተኛ ይኼን ለውጥ ያመጣ  ትውልድ እሴቶች ሕዝባዊነቱን፣ ቆራጥነቱን፣ የትግል መንፈሱን ለአዲሱ የአመራር ትውልድ ተቋማዊ በሆነ መልኩ እያሸጋገረ ነው ወይ? አዲሱን ትውልድ ለዘመኑ እያበቃነው ነው ወይ? የሚለውን ነገር ነው መጽሐፉ መልሶ መላልሶ የሚያነሳው፡፡ ከዚህ አንፃር ማየት ያለብን ነገሮች ይኖራሉ፡፡ በየጊዜው የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሉ የምንላቸው በእነዚህ ዙሪያ ያጠነጠኑ ናቸው፡፡ ለዘመኑ በትምህርትና በሥነ ምግባርም በየደረጃው የበቃ የአመራር ትውልድ መፍጠር ስላልቻልን ነው፡፡ እነዚህን ችግሮች መፍታት ካልቻልን መነሻ ሐሳቡን ያፈርሰዋል፡፡ ስለዚህ ይህንን ከግምት ውስጥ ማስገባት አለብን እያለ መጽሐፉ ይናገራል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን በተመለከተ የተነሱ ጉዳዮች አሉ፡፡ ችግሮች ወደ ቀውስነት ከመሸጋገራቸው በፊት መሠረታዊ የሆነ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ማድበስበስ፣ አቋራጭ መንገዶችን መፈለግና እንደገና መልሶ ሌሎች ችግሮችን አምጥቶ የማይወጡት አዘቅት ውስጥ መግባትን የመሳሰሉ ነገሮች ተጠቅሰዋል፡፡ እነዚህ የሚያሳዩት የአመራር ክፍተትን ነው? የብቃት ማነስን ነው? በተደራጀ መንገድ መምራት አለመቻልን ነው? ወይስ የአንድን ማኅበረሰብ መከፋፈል?

አምባሳደር ወንድሙ፡- የአንድ አመራር ዋና ኃላፊነት ሁኔታዎችን ከተከታዩ ቀድሞ፣ ፈጥኖና አርቆ ማየት ነው፡፡ ይህን ካላደረገ ከተከታዩ ምንም አይሻልም፡፡ በማንኛውም ደረጃ መንግሥታዊ፣ ድርጅታዊም ሆነ ግለሰባዊ አመራር ችግሮችን ቀድሞ ለይቶ መፍትሔ ማበጀት ካልተቻለ የአመራር ሚናውን ተጫወተ ማለት አይቻልም፡፡ ይኼን የማያደርጉ አመራሮች ኅብረተሰቡን ይዘው ይወድቃሉ፡፡ ቀድመው ችግሮችን ለይተው፣ ቀድመው መፍትሔ የሚያመጡ ደግሞ አገራቸውን ወደ ትንሳዔ ይመራሉ፡፡ አንዳንድ አመራሮች ቀድመው ችግሮችን ለይተው መፍትሔ የሚሰጡት፣ ሌሎቹ ደግሞ የሚወድቁ ለምንድነው በሚለው ዙሪያ መጽሐፉ ይናገራል፡፡ አንደኛው ችግር የሐሳብ ነው፡፡ ያለውን ሁኔታ መርምሮ ቀድሞ ለማወቅ አለመቻል ነው፡፡ ያለውን ሁኔታ መርምሮ ቀድሞ ለማወቅ አለመቻል  ተቋማዊ ድክመት ነው፡፡ ይኼ የሚመነጨው አንደኛ የምርምር ተቋማት በበቂ ሁኔታ በሌሉበት ሁኔታ ነው፡፡ ሁለተኛው ከምርምር ተቋማትና ከተለያዩ ምንጮች የሚወጡትን ሐሳቦች በጥሞና አድምጦ፣ ሐሳቦቹን ክብደት ሰጥቶ፣ ችግሮቹን ለይቶ መፍትሔ መስጠት የማይችል አመራር ሲኖር ነው፡፡ ሦስተኛው ብዙ ጊዜ ሁሉም ዓይነት የአመራር ትውልድ በኃላፊነት ላይ ሲኖር ሁኔታው ሁሌም የማይቀየር ይመስለዋል፡፡ ይኼ ግን አሳሳች ነው፡፡ ብዙ መንግሥታት ቀውስ ውስጥ የሚወድቁት እነሱ ያሉበትና የሚመሩበት ሁኔታ ሁሌ የተረጋጋና የማይቀየር እየመሰላቸው፣ ከታች እሳቱ እየተንቀለቀለ ኅብረተሰቡን የሚያቃጥልበት አጋጣሚ ሲፈጠር ነው፡፡ ስትራቴጂካዊ አመራር ይኼኛውን ዓይነት መፍታት አለበት፡፡ ባለበት ሁኔታ ያለመዘናጋት፣ የችግር ምልክቶችን ቀድሞ የማየትና ሕዝቡንም ሆነ የተለያዩ ሐሳቦችን ማዳመጥ ላይ ተመሥርቶ መፍትሔ መስጠት የግድ ነው፡፡ አንድ አመራር ችግሮችን ቀድሞ ያለማየት ምክንያቱ የተለያዩ ሁኔታዎች ድምር ነው፡፡ ይኼንን ማሸነፍ የቻሉ ማኅበረሰባቸውን፣ የሚመሩትን አገርና ድርጅት ማዳን ይችላሉ፡፡ ይህንን ማየት ያልቻሉ ደግሞ ተያይዘው ይወድቃሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በመጽሐፉ ውስጥ የጠቀሱት አንድ ምሳሌ አለ፡፡ የአፋር አርብቶ አደሮችና የትግራይ አርሶ አደሮች ከበረሃሌ የጨው ማውጫ ግመሎቻቸውን ጭነው እንዴት እንደሚነዱ፣ በእነሱ ሥልት ካልሆነ ግመሎቹን መንዳት እንደማይቻል ጠቅሰዋል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ማብራሪያ ቢሰጡን?

አምባሳደር ወንድሙ፡- አንድ አመራር የተሳካለት የሚሆነው የሚመራውን ሕዝብ ፍላጎት፣ ችግሮችና ባህሪያት አጥንቶና በዚያ ላይ ተመሥርቶ መምራት ሲችል ነው፡፡ እሱ በፈለገው መንገድ የሕዝቡንና የሚመራውን አካል ስሜትና ፍላጎት ሳያዳምጥ ለመምራት ቢሞክር ግን ተራራን መግፋት ነው የሚሆነው፡፡ እዚያ ምሳሌ ላይ የጠቀስኩት ግመል በጣም ኃይለኛና ጉልበተኛ እንስሳ ነው፡፡ ግን አንድ አርሶ አደር ወይም አርብቶ አደር መቶ ወይም ሁለት መቶውን ይህንን ግዙፍ እንስሳ በቀጭን ገመድ ጎትቶ የሚመራው በጉልበት አይደለም፡፡ የእንስሳውን ባህሪ አውቆ፣ አክብሮና ተስማምቶ ነው ይህን ሁሉ የሚያግተለትለው፡፡ አመራር የኃይል ጉዳይ ነው ብሎ የሚገምት ተላላ ግን እነዚህን ግመሎች አስገድጄ ልምራ ቢል ትርምስ ነው የሚፈጠረው፡፡ አንድ ጋት ሊያስኬዳቸው አይችልም፡፡ በማንኛውም ደረጃ ያለ አመራርም እንደዚሁ ነው፡፡ አመራር የኃይል ጉዳይ አይደለም፡፡ የሥልጣን ጉዳይም አይደለም፡፡ አመራር የመደመጥ ጉዳይ ነው፡፡ አመራር ከሚመራው ሕዝብ ስሜት ጋር ተስማምቶ የመሄድ ጉዳይ ነው፡፡ አመራር ውጤታማም ቀላልም የሚሆነው የትግራይ አርሶ አደሮችና የአፋር አርብቶ አደሮች ግመሎቻቸውን በሚመሩበት ሥልት ሲሄድ ነው፡፡ አመራር ትህትናን ይጠይቃል፡፡ የሚመራው ሕዝብን የማዳመጥ ጉዳይ ነው፡፡ ትህትና ከማንኛውም ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ ሥልጣን በላይ ኃይለኛ ነው፡፡ በዚህ ሥልት ነው ሕዝቡን ወደተፈለገው መዳረሻ ማድረስ የሚቻለው ለማለት የጠቀስኩት ምሳሌ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ ከአዳዲስ አስተሳሰቦች ጋር መጋፈጥና የዘመኑን ትውልድ ጥያቄዎች የመመለስ ፈተናዎች ይታያሉ፡፡ መጽሐፉ ውስጥ እነዚህን ነጥቦች የሚያነሱ ምሳሌዎች አሉ፡፡ ትንሽ ማብራሪያ ቢሰጡን፡፡

አምባሳደር ወንድሙ፡- በዓለም ውስጥ የተከሰቱት ማናቸውም ለውጦች ከቆየ አመለካከት ጋር በመቆራረጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያም አሁን ያለችበት ለውጥ ላይ የደረሰችው ኢትዮጵያን ሲመራ የነበረውን የዘመናት አስተሳሰብ ቆርጦ በመጣል ነው የተስፋ ምዕራፍ ውስጥ የገባነው፡፡ አሁንም ይህንን የተስፋ ምዕራፍ ማስቀጠል የሚቻለው ተጨማሪ ዘመኑን የሚጠይቁ አዳዲስ ሐሳቦች በመቀበልና በመውሰድ ነው፡፡ አዲስ ሐሳብ መውሰድ ግን ቀላል አይደለም፡፡ አንደኛ ድፍረትን ይጠይቃል፡፡ የቆየውን ሐሳብ ጥሎ አዲሱን መቀበል ትልቅ ድፍረት ይጠይቃል፡፡ ሁለተኛ ክፍት የሆነ ልቦናና የማዳመጥ ባህል ይጠይቃል፡፡ እኔ ኃላፊ ስለሆንኩ የምመራው ኃይል ከእኔ በላይ አያውቅም የሚለውን ትዕቢት መቅረፍን ይጠይቃል፡፡ ጥሩ አዲስ ሐሳብ ከማንኛውም አቅጣጫ ሊመጣ ይችላል ብሎ የመቀበል ትህትናን ይጠይቃል፡፡ ማንኛውም አዲስ ሐሳብ ሲመጣ እንደ ማርያም ጠላት ከመደብደብ ይልቅ ፍሬ ሊኖረው ይችላል ብሎ ለመስማት መዘጋጀትን ይጠይቃል፡፡ በማኅበራዊም ሆነ በፖለቲካዊ ባህላችን ግን አዲስ ሐሳብ ቶሎ የመቀበል ችግር አለብን፡፡ ይህንን ካልቀረፍን ደግሞ ለውጡ የሚጠይቀውን ሐሳብ በፍጥነት ማግኘት አንችልም፡፡ አንደኛ ይኼ ባህል መቀየር አለበት፡፡ ባህል መቀየር ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ በተለያዩ መስኮች ጥናትና ምርምሮች መኖር አለባቸው፡፡ ማንም በዘመናዊ ዓለም ውስጥ አገርን የሚመራ መንግሥት የሚጠቀመው ይኼንን ሥልት ነው፡፡ እየመሩ ሐሳብ ማፍለቅ አይቻልም፡፡ እየሮጡ አዲስ ሐሳብ መፍጠር አይቻልም፡፡ ከመንግሥት ኃላፊነቱ ራቅ ብለው ሙሉ ጊዜያቸውን ሐሳብ በመፍጠር ላይ ያደረጉ ነፃና ጥልቅ ዕውቀት ያላቸው የመስኩ ሰዎች ሊኖሩን ይገባል፡፡ እነሱ መኖራቸው ብቻ ሳይሆን የሚያመጡትን ሐሳበ ማዳመጥ ይጠይቃል፡፡ እነዚህ ተቋማዊና ባህላዊ ችግሮች አዳዲስ ሐሳቦችን ከመቀበል ስለሚያደናቅፉ ለመቅረፍ መዘጋጀት አለብን፡፡

ሪፖርተር፡- በመጽሐፉ መጨረሻ አካባቢ ኢትዮጵያንና ዓለም አቀፉን የኒዮሊበራዚም አስተሳሰብ የሚመከለቱ የተነሱ ጉዳዮች አሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ መንግሥታት መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እየተገፉ የፖለቲካውንና የዲፕሎማሲውን ሚና እየተነጠቁ ስለመሆናቸው የተነሳ ነገር አለ፡፡  እየተለወጠ ካለው ዓለም ጋር እኩል አለመራመድ በራሱ ትልቅ ፈተናና ችግር እንደመሆኑ መጠን ኢትዮጵያ የምትማረው ነገር አለ?

አምባሳደር ወንድሙ፡- ከዚህ አንፃር አገራችን በጣም ትክክለኛ የውጭ ፖሊሲ አላት፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ የሚያጠነጥነው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ አሁን በብዙ የአፍሪካ አገሮች እንደምናየው በአብዛኛው የውጭ ተፅዕኖ፣ የውጭ ጥቅም፣ የውጭ ኔትወርክ የሚነዳው ፖሊሲ አላቸው፡፡ አንደኛው  ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም አንፃር ተመሥርቶ እየሄደ ያለው ፖሊሲያችንን አጠናክሮ መቀጠል ዋናው ነገር ነው፡፡ ሁለተኛው ዓለም አሁን በጣም ፈጣን ለውጥ ውስጥ ነው ያለው፡፡ አሁንም ዞሬ ዞሬ የምለው ይኼንን አዲስ ፈጣን ዓለም የሚገነዘብ፣ በጥናትና በምርምር ላይ የተመሠረተ የውጭ ፖሊሲና ዲፕሎማሲ እንዲኖረን ይገባል ነው፡፡ ምክንያቱም በየጊዜው አዳዲስ ዓለም አቀፍ ክስተቶች አሉ፡፡ ይኼንን በጥናትና በምርምር እየለየን ፖሊሲያችንን በቀጣይ ማሻሻል አለብን፡፡ ሦስተኛው አገራችን አሁን ታላቅ አገር እየሆነች ነው፡፡ በጎረቤት አገሮች ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ደረጃም፡፡ ይኼ እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ ኃይል የሚመጥን የውጭ ፖሊሲና ዲፕሎማሲ እንዲኖረን ምን ዓይነት የዲፕሎማሲ ዕርምጃ እንውሰድ? ምን ዓይነት ሚናዎች በአካባቢያችን፣ በአፍሪካና በዓለም ይኑረን? የሚለውን በየደረጃው እያጠናን የፖሊሲ ግብዓት ማድረግ አለብን፡፡ በዚህ ዙሪያ የተጀመሩ ነገሮች አሉ፡፡ ይኼኛውን ግን የበለጠ ትኩረት ሰጥተን አጠናክረን መሥራት አለብን፡፡

ሪፖርተር፡- ከ90 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በሚኖርባት አገር ውስጥ የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ብሔሮች፣ ባህሎች፣ እምነቶችና የፖለቲካ አመለካከቶች እያሉ በአንድ አቅጣጫ ብቻ በመጓዝ ውጤታማ መሆን አይቻልም፡፡ ብሔራዊ መግባባት ፈጥሮ ሁሉንም ዜጎች በዚህ ዙሪያ ለማሳተፍ ምን ዓይነት ጥረት መደረግ አለበት ይላሉ?

አምባሳደር ወንድሙ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ብሔራዊ መግባባት ያስፈልጋል ከተባለ ዋናው ነገር በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ ብሔራዊ መግባባት የማስፈን ጉዳይ ነው፡፡ ሌሎች ዝርዝር የአመለካከት፣ የአቀራረብና የፖለቲካ አማራጭ ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በመሠረቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያስፈልገው በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ብሔራዊ መግባባት የመፍጠር ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ኃላፊነቱ የተወሰነ አይደለም፡፡ የመንግሥት ብቻ አይደለም፡፡ ሲቪል ማኅበረሰቡ፣ ሚዲያውና ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ለዚህ መሠረታዊ የብሔራዊ መግባባት ጥያቄ አስተዋጽኦ ማበርከት አለባቸው፡፡ አንዱ እየገነባ ሌላው የሚያፈርስበት ሁኔታ ካለ የብሔራዊ መግባባት ሒደቱ ይዘገያል፡፡ ልዩነቶቻችን እንዳሉ ሆነው ብዙ የሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች፣ የልማት ጉዳዮች፣ የዴሞክራሲ ጉዳዮችና አጠቃላይ የብሔራዊ ጥቅም ጉዳዮች አሉ፡፡ ብሔራዊ መግባባት ስለሚያስፈልገን በዚህ ዙሪያ ሁሉም አብሮ መሥራት አለበት፡፡ 

ሪፖርተር፡- በፖለቲካው ጎራ ከመቀራረብ ይልቅ መጠላላት፣ ከመደጋገፍ ይልቅ መጠላለፍ የበዛበት ጊዜ ነው፡፡ በተለይ ባለፉት 40 ዓመታት የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለሚታዘብ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ አንድ ላይ ቁጭ ብሎ ለመነጋገር ምን ዓይነት የፖሊሲ ማዕቀፍ ያስፈልጋል?

አምባሳደር ወንድሙ፡- አሁን ያለው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት የተለያዩ አመለካከቶችን ለማስተናገድ በቂ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ምናልባት በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ ጭምር ልዩነት ያለው ሰው፣ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ የመብት ክልል ውስጥ ሆኖ መነጋገር ይችላል፡፡ አሁን ሌላ አዲስ የውይይት መድረክ መክፈት አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡ ከብዙ ትግል በኋላ ማንኛውንም የአመለካከት፣ የፖለቲካና የማንነት ልዩነቶችን የሚያስተናግድ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አለ፡፡ በዚያ ክልል ውስጥ ሆኖ ማንኛውንም ችግር መፍታት ይቻላል፡፡ የጎደለ ነገር ካለ እንኳን ማሻሻል ይቻላል፡፡ በእኛ የፖለቲካ ባህል የሚታየው ችግር ማንኛውም ልዩነት ካለ፣ ጠቅላላውን አፍርሰው ከዜሮ ካልጀመሩ የማይሆንላቸው አሉ፡፡ በእኔ አመለካከት ይኼ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ሊሻሻል ይችላል፡፡ ግን ማናቸውም ዓይነት ልዩነቶችን ማስተናገድ እንችላለን፡፡ ይኼኛውን አጠናክረን የጎደለውን እየሞላን መሄድ የሚያስችል ሁኔታ አለ ብዬ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ድሮ ኢሕአዴግ ግማሽ መንገድ ድረስ በመሄድ ተገፋን ከሚሉ ወገኖች ጋር ለመነጋገርና ለመወያየት ዝግጁ ነኝ ይል ነበር፡፡ አሁን ግን ድፍንፍን ያለ ሁኔታ ነው የሚታየው፡፡ ከአብዛኛው  በተቃውሞ ፖለቲካ ካለው ወገን ደግሞ የምንቀሳቀስበት ስንዝር መሬት አጣን፡፡ ምኅዳሩ ጠበበ፡፡ በአጠቃላይ ከሰላማዊ ትግል ይልቅ ወደ ሌላ የሚገፋፉ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል የሚሉ ብሶቶች ናቸው የሚሰሙት፡፡ ይኼንን ተቃርኖ የሚያስታርቅ አንድ ማዕቀፍ እንዴት ሊፈጠር ይችላል?

አምባሳደር ወንድሙ፡- ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ምሥረታን ይፈቅዳል፡፡ እንደምሰማውና እንዳወቅኩትም ከ80 በላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተመዝግበዋል፡፡ እነዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ችግር አለብን የሚሉ እንኳን ከሆነ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ክልል ሆነው የዚህን የእንቅስቃሴ ምኅዳር መጣበቦች ማስፋት ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይኼን ስል ግን ሁሉም ነገር የተስተካከለ ነው ብዬ አይደለም፡፡ መጽሐፉ ላይም አስቀምጫለሁ፡፡ በአመራር ዙሪያ በዚህ መንፈስ ከመሥራት አንፃር በሥርዓቱ ውስጥ ያሉ ችግሮችም አሉ፡፡ የማይሻሻሉ ናቸው ብዬ ግን አላምንም፡፡ እኔ የምለው ለ40 ዓመታት ያህል ለመገንባት ብዙ መስዕዋትነትና ጥረት የተደረገበትን የፖለቲካ ሥርዓትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አስቀምጠን ወይም አስወግደን ሌላ እንገንባ ብለን ብንሞክር በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ ታሪክ ደግሞ በጣም ስስታም ነው፡፡ አንዴ የታጣ ነገር ሁለተኛ እስኪገኝ ትውልዶች ያስጠብቃል፡፡ አሁን ያለው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ችግሮች ካሉበት ማስተካከል እንጂ፣ እሱን አፍርሰን ሌላ ዓይነት እንፍጠር ብንል ሁሉንም እናጣለን ብዬ እገምታለሁ፡፡ ይኼ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ፍፁማዊ ባይሆንም ሊሻሻል የሚችልና ሊያሠራ የሚችል ነው፡፡ አሁን የሚታየው ዕውቅና የመስጠት ችግር ነው፡፡ የ40 ዓመቱ ፅንፈኛ የሆነ የእኔ ወይም ምንም የሚለው አመለካከት እየተቆጣጠረው ነው እንጂ፣ አሁን ከፖለቲካና ከሕገ መንግሥታዊ ሁኔታ አንፃር በጣም ትልቅ ለውጥ አለ ብዬ አምናለሁ፡፡ በተለይ በውጭ ያሉ ተቃዋሚዎች የሚያነሱትን ነገር ብዙ ጊዜ በጥርጣሬ ነው የማየው፡፡ ብዙ ጊዜ ለ40 ዓመታት የቆየ የፖለቲካ ቂም ለመወራረድ ከመፈለግ እንጂ፣ እውነት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማሻሻል ከመፈለግ የመነጨ አይመስለኝም፡፡ ማሻሻል ይቻላል የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ይኼ መጽሐፍ ከመንግሥት አካላትም ሆነ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ካነበቡት ሰዎች ያገኘው ግብረ መልስ ምን ይመስላል?

አምባሳደር ወንድሙ፡- በጣም ጥሩ ምላሽ ነው፡፡ በፖለቲካ አመራሮች ዘንድ ጥሩ አቀባበል ነበረው፡፡ ምናልባት በድርጅት መዋቅር ለውይይትም መነሻ ሊሆነን ይችላል የሚል ምላሽ የሰጡኝ አሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች በብዛት ወስደውታል፡፡ በተለይ የአመራር ኮርስ የሚሰጡት ወስደውታል፡፡ ብዙ የቢዝነስ ሰዎች ለቢዝነስ አመራር መሠረተ ሐሳቡ ስለሚረዳ ወስደዋል፡፡ በተለያዩ የመጽሐፍ መደብሮችም አለ፡፡ ችግሩ ግን እኔ ሞቃዲሾ ስለምኖርና አብዛኛውን ጊዜ እዚያ ስለሆንኩኝ ለማስተዋወቅ ጊዜ አላገኘሁም፡፡ ምናልባት በሚቀጥሉት ወራት በተለይ በክረምት ጊዜ ካገኘሁ አስተዋውቀዋለሁ፡፡ እስካሁን ምላሹ ጥሩ ነው፡፡ እኔም ይኼን መጽሐፍ ስጽፍ የተሟላና ያለቀለት ነው ብዬ አይደለም፡፡ ለውይይት መነሻ እንዲሆን ነው፡፡ ለሌሎችም ይኼ የአመራር ጥያቄ ቁልፍ ጉዳይ ስለሆነ እንዲጽፉ፣ እንዲወያዩበትና እንድንነጋገርበት  ከሚል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የተሳካልኝ ይመስለኛል፡፡ ፍላጎቶች አሉ፡፡ ውይይቶች ተጀምረዋል፡፡ በዚህ ዙሪያ ውይይቱ ቀጥሎ  በመንግሥት መዋቅር ብቻ ሳይሆን በቢዝነስ፣ በድርጅቶች፣ በግለሰብና በቤተሰብ አመራር ጭምር የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ሐሳቦችን ያካተተ ስለሆነ ውይይት ተደርጎበት ሊሰፋ ይችላል ብዬ እገምታለሁ፡፡ 

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -