Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአቶ ኤርሚያስ አመልጋ ላይ ለሰባተኛ ጊዜ የተጠየቀው ተጨማሪ ቀናት ተፈቀደ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ፖሊስ በጊዜ ቀጠሮ ላይ ገደብ አለመኖሩን ተጠቅሞ ምርመራውን እያንዛዛው ነው›› የአቶ ኤርሚያስ ጠበቃ

‹‹እንደተባለው ምርምራው በመንዛዛቱ ከማስጠንቀቂያ ጋር አሥር ቀናት እንሰጣችኋለን›› ፍርድ ቤት

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) መርማሪ ቡድን፣ በአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር መሥራችና ሊቀመንበር በአቶ ኤርሚያስ አመልጋ ላይ ለሰባተኛ ጊዜ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደለት፡፡

የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት መጋቢት 5 ቀን 2008 ዓ.ም. መርማሪ ቡድኑ ለሰባተኛ ጊዜ ከጠየቀው 14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ አሥር ቀናት ፈቅዷል፡፡ የአቶ ኤርሚያስ የሕግ አማካሪና ጠበቃ አቶ ሞላ ዘገዬ ደግሞ ‹‹ምርመራው ተንዛዛ›› በማለት ተቃውመዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ምርመራው መንዛዛቱን በመጠቆም ‹‹ከማስጠንቀቂያ ጋር›› በማለት በአሥር ቀናት ውስጥ ጨርሰው እንዲቀርቡ መርማሪ ቡድኑን አሳስቧል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የፈለገበትን ምክንያት ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው የምስክሮችን ቃል ተቀብሏል፡፡ ለተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች የበተናቸውን ደብዳቤዎች ምላሽ መሰብሰቡንም አክሏል፡፡ ነገር ግን ድርጊቱ ውስብስብ በመሆኑ ቀሪ ሥራዎች እንደቀሩት ጠቁሞ፣ አክሲዮን ማኅበሩን ኦዲት የሚያደርጉት ባለሙያዎች አለመጨረሳቸውን፣ በቂ ስንቅ በባንክ እንደሌለ እየታወቀ ቼክ የተጻፈላቸውን ሰዎች ቃል መቀበል ስለሚቀረው (ከ70 በላይ መሆናቸውን ጠቅሷል) ተጨማሪ ጊዜው እንደሚያስፈልገው ተናግሯል፡፡

አቶ ኤርሚያስ ከቼክ ጋር የተገናኙ ነገሮች ላይ በፍትሕ ሚኒስትሩ ፊርማ በተረጋገጠ የጽሑፍ ሰነድ ዋስትና እንደተሰጣቸው በተደጋጋሚ እየተናገሩ መሆኑን በሚመለከት መርማሪ ቡድኑ እንደገለጸው፣ የፍትሕ ሚኒስትሩ በዓቃቤ ሕግ በኩል ተጠይቀው ዓቃቤ ሕግ መክሰስ እንደሚችል እንዳረጋገጡለት እንደነገረው ቡድኑ አስረድቷል፡፡ አቶ ኤርሚያስ ቼኩን በሚመለከት ቃላቸውን መስጠት እንደማይፈልጉ ለመርማሪ ቡድኑ መናገራቸውንም አክሏል፡፡ በመሆኑም ከጉዳዩ ውስብስብነት አንፃርና አቶ ኤርሚያስ በዋስ ቢፈቱ ማስረጃ እንደሚያጠፉና ምስክር እንደሚያባብሉ በመግለጽ፣ የጠየቀው ጊዜ እንዲፈቀድለት በድጋሚ ጠይቋል፡፡

የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ በሕግ ገደብ ስላልተጣለበት፣ ፖሊስ ይኼንን ተጠቅሞ በደንበኛቸው ላይ የጀመረውን የምርመራ ጊዜ እያንዛዛው መሆኑን የተናገሩት የአቶ ኤርሚያስ ጠበቃ አቶ ሞላ፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት የተፈቀዱ የምርመራ ቀናት በቂ በመሆናቸው ተጨማሪ ሊፈቀድ እንደማይገባ በመግለጽ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

ለስድስት ጊዜያት መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ቀርቦ ያስረዳው የምርመራ ሒደት ተመሳሳይ በመሆኑ እሳቸውም የሚመልሱት ምላሽ ተመሳሳይ እንደሚሆን የተናገሩት አቶ ሞላ፣ ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ ሲባል ምርመራው ይቀጥላል የሚባል ከሆነ፣ አቶ ኤርሚያስ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆላቸው በውጭ ሆነው እንዲቀጥል ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ፖሊስ በተደጋጋሚ አቶ ኤርሚያስ በዋስ ቢለቀቁ ምስክሮች እንደሚያባብሉና ሰነድ ሊያሸሹ እንደሚችሉ ተናግሯል፡፡ አቶ ኤርሚያስ በስማቸው ምንም ነገር እንደሌላቸውና ይኼንንም ፍርድ ቤቱ በፈለገው መንገድ ሊያረጋግጥ ይችላል ብለዋል ጠበቃው፡፡ አላቸው የሚባለው ገንዘብ የሳቸው ሳይሆን የአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር በመሆኑ፣ እሱም ሚኒስትሮች በሚመሩት ዓቢይ ኮሚቴ አማካይነት ስለታገደ በማንኛውም መንገድ እሳቸው ሊደርሱበት እንደማይችሉም በተደጋጋሚ መግለጻቸውን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ዋስትናቸውን እንዲጠብቅላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪው ጠበቃ እንዳሉት የምርምራ ሒደቱ መንዛዛቱን በማስታወቅ፣ ከማስጠንቀቂያ ጋር በአሥር ቀናት ውስጥ ጨርሰው እንዲቀርቡ በመንገር ለመጋቢት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች