Thursday, September 21, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ሕዝብን ያሰለቹ ደመነፍሳዊ አሠራሮችን በሲስተም መተካት የወቅቱ ጥያቄ ነው!

በአሁኑ ጊዜ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ከሚባሉት ችግሮች መካከል አንዱ፣ የመንግሥታዊም ሆኑ የተለያዩ ተቋማት በሲስተም አለመመራት ነው፡፡ የሌሎቹን ትተን የመንግሥትን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ስንታዘብ፣ ብዙዎቹ ተቋማት በሲስተም ከመመራት ይልቅ ደመነፍሳዊ አሠራሮች ጎልተው ይታዩባቸዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ መንግሥት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚያወጣቸው አዋጆች፣ ደንቦችና መመርያዎች ሳይቀሩ የሲስተም መዛነፍ ይታይባቸዋል፡፡ ሕጎችም ሆኑ ማስፈጸሚያ መመርያዎች ሲወጡ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመምከር እንዴት? ለምን? መቼ? የት? ወዘተ. የመሳሰሉትን ጥያቄዎች መመለስ ሲገባ፣ ትርምስ የሚፈጥሩ ድርጊቶች ይበዛሉ፡፡ አንድ ተቋም በሲስተም ተገንብቶ መንቀሳቀስ ካልቻለ ይሽመደመዳል፡፡ ደመነፍሳዊ እንቅስቃሴ የውድቀት ምልክት ነው፡፡

መንግሥት ፖሊሲዎቹና ስትራቴጂዎቹ የፈለገውን ያህል ጠቃሚና አስፈላጊ ቢሆኑም ብቃት ባለው የሰው ኃይል፣ ተቋምና ሲስተም ካልተመሩ ውጤታቸው የተገላቢጦሽ ይሆናል፡፡ በአፈጻጸም እየተሳበበ ሲንከባለል የመጣው የብዙ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ችግር ምንጭ በሲስተም አለመመራት ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መነሻም ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት ሲስተም አለመፈጠር ነው፡፡ ከአንድ ተቋም አገልግሎት የሚሻ ዜጋ በአግባቡ እንዲስተናገድና አገልግሎት ሰጪውም ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ከተፈለገ በሲስተም መመራት አለበት፡፡ ግብር ከፋዩ ሕዝብ በአገልግሎት ሰጪው መብቱን እንዳይነፈግ፣ እንዳይመናጨቅና በደል እንዳይደርስበት ከተፈለገ ተቋማት በሲስተም መመራት አለባቸው፡፡ ለዚህም መንግሥት ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡

በመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በፍትሕ መነፈግና በሙስና ምክንያት አገር ችግር ውስጥ ወድቃ የመፍትሔ ያለህ ሲባል፣ የሚወሰዱት ዕርምጃዎች በሙሉ በጥናት ላይ የተመሠረቱ መሆን አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሲስተም ግንባታ ያስፈልጋል፡፡ አሠራሮች በተጠያቂነትና በኃላፊነት ስሜት እንዲከናወኑ ሲፈለግ ተቋማት ደግሞ አሠራራቸው በሙሉ ለዘመኑ አስተሳሰብ የሚመጥን መሆን ይኖርበታል፡፡ አንድ ሥራ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል? አገልግሎት ፈላጊው ለምን ያህል ጊዜ ይጠብቃል? ፈጻሚው ኃላፊነቱን ለመወጣት ምን ያህል ጊዜ ይሰጠዋል? ለብልሹ አሠራር ምክንያት የሆኑ ድርጊቶችን እንዴት ማስወገድ ይቻላል? ወዘተ. የሚሉትን ነጥቦች በማስቀመጥ የቁጥጥርና የዕርምጃ አወሳሰድ ሥርዓቱን ጠበቅ ማድረግ ይቻላል፡፡ ደመነፍሳዊ የሆኑ አሠራሮች ግን ለቁጥጥርም ሆነ ለዕርምጃ አወሳሰድ አዳጋች በመሆናቸው ውጤቱ የተበላሸ ነው የሚሆነው፡፡

በአመራር ደረጃም ሆነ በበታች ሠራተኞች የሚፈጸሙ ግድፈቶችና ጥፋቶች በተጠናከረ ሲስተም ካልተገመገሙ፣ የሚወሰዱት ዕርምጃዎችም ሆኑ ቅጣቶች ተዓማኒነት አይኖራቸውም፡፡ በሙስና የተጠረጠሩ ሰዎችም ሆኑ ፍትሕ በማዛባት የሚጠረጠሩ ከሥራ ሲታገዱ፣ ሲከሰሱ ወይም ሲታሰሩ ዕርምጃ አወሳሰዱ ፍትሐዊ የሚሆነው ገና ከጅምሩ የመቆጣጠሪያ ሥልቱ ሲበጅ ነው፡፡ ሲስተም በሌለበት የሚወሰዱ ግብታዊ ዕርምጃዎች ከውጤት ይልቅ ጥፋት ይጋብዛሉ፡፡ አንድ የሥራ ኃላፊ በጥፋት ከቦታው ተነስቶ በሌላ ሲተካ፣ ያጠፋው ጥፋት በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡ ነገር ግን በተድበሰበሰ መንገድ ሰዎች ከኃላፊነት ይነሱና ድንገት ሳይታሰብ ሌላ ቦታ ይሾማሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ኃላፊነት የጎደለው ዕርምጃ የበለጠ ምሬት በመፍጠር ሕዝብን ለአመፅ ይቀሰቅሳል፡፡

ብዙዎቹ የመንግሥት ዕርምጃዎች በጣም የዘገዩና ዘመቻ የሚበዛባቸው በመሆናቸው፣ በሕዝብ ዘንድ የሚያገኙት ዓመኔታ በጣም የወረደ ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥትን ከሚያራርቁ ጉዳዮች መካከል አንዱ የመንግሥት ሥራ በግልጽ አለመታወቁ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የመንግሥት ሥራ በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ እንደሚከናወን በይፋ ቢደነገግም፣ አሁንም የሚስጥራዊነት ባህሉ በጣም የተንዛዛ በመሆኑ ችግር ፈጣሪ ሆኗል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ ከላይ እስከ ታች ብዙ እየተባለ ነው፡፡ ችግሮቹ ላይ ብዙ ቢባልም ተቋማዊ ጥንካሬ ኖሮ አሳማኝ ዕርምጃ ለመውሰድ ያልተቻለው፣ ለዕርምጃ አወሳሰድ የሚመጥን ተቋማዊ ብቃትና ሲስተም ባለመኖሩ ነው፡፡ ለዓመታት ለሕዝቡ ተገቢውን አገልግሎት ሳይሰጡ የሚያበሳጩ፣ ፍትሕ የሚነፍጉ፣ በሕዝብ ሀብት እንደፈለጋቸው የሚፈነጩ የበዙት በሲስተም መመራት ባለመቻሉ ነው፡፡ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የጠፋው የቁጥጥር ሥርዓቱ ደካማና ደመነፍሳዊ በመሆኑ ነው፡፡

ዜጎች ከመንግሥት ጋር ያላቸው የተበላሸ ግንኙነት የሚሻሻለው በዘመቻ በሚካሄዱ ንቅናቄዎች ወይም ትርጉም በሌላቸው አሠራሮች አይደለም፡፡ በመጀመሪያ የተጠያቂነትና የኃላፊነት መንፈስ መፈጠር አለበት፡፡ ከሥር ጀምሮ እስከ ላይኛው የሥልጣን እርከን ድረስ ያሉ ሰዎች አሠራራቸው በሙሉ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ ግልጽነት ካለ ተጠያቂነት ይኖራል፡፡ ተጠያቂነቱ ደግሞ በመርህ እንጂ በገጠመኝ የሚመራ አይደለም፡፡ በተለይ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ራሳቸውን ከሕግ በላይ የሚያደርጉና ደንታቢሶች በብዛት ስለሚታዩ፣ አሠራሮች በሙሉ በሲስተም መመራት አለባቸው፡፡ ሥራውን በአግባቡ የማይወጣ ፈጻሚም ሆነ አስፈጻሚ በሕግ እንደሚጠየቅ፣ የየዕለት የሥራ ውጤቱ የሚመዘንበት መሥፈርት እንደሚኖርና በዚህ መሠረት የመንግሥት ሥራ በኃላፊነት ስሜት እንደሚከናወን ማረጋገጫ መኖር አለበት፡፡ ጥሩ የሠራ የደረጃ ዕድገትና ጥቅማ ጥቅም ሲያገኝ በደል የሚፈጽመው ደግሞ በሕጋዊ መንገድ የእጁን የሚያገኝበት ሲስተም ተዘርግቶ ሥራ ላይ መዋል ይኖርበታል፡፡

በመተማመን መጥፋት ምክንያት ሕዝብና መንግሥት ተቃርነዋል፡፡ ግጭት ተነሥቶ ሰዎች ሞተዋል፡፡ ከአሁን በኋላ ለዓመኔታ የሚተው ነገር የለም፡፡ እያንዳንዱ መዋቅር ውስጥ ያለ ሠራተኛና ሥራ መሪን የሚዳኘው ሲስተም መሆን አለበት፡፡ በተጨማሪ የብቃት ጉዳይ በጣም አንገብጋቢ ነው፡፡ በዚህ ከፍተኛ ፉክክር በሚደረግበት የውድድር ዓለም በአሸናፊነት ለመውጣት ብቃት (Merit) ወሳኝ ነው፡፡ የአንድ ሰው ብቃት በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በፆታ፣ በፖለቲካ አመለካከት ወይም በሌሎች ምክንያቶች ጥያቄ ውስጥ ሳይገባ፣ በብቃቱ ብቻ የሚገባውን ሥፍራ ማግኘት አለበት፡፡ መንግሥት ራሱን ማታለል የለበትም፡፡ በኮታ የሚሰጥ ሹመትም ሆነ ኃላፊነት ከአስተሳሰብ ውስጥ መውጣት ይኖርበታል፡፡ ከዘመኑ ጋር አይመጥንም፡፡ አለበለዚያ የሕዝብ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ሥነ ምግባርና ብቃት የሌለው እንኳን የመንግሥት ሥልጣን ቤተሰብ መምራት አይችልም፡፡ ይኼ አንዱ የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፡፡

መንግሥት በመላ አገሪቱ የምሬት መነሻ የሆነውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ ሲንቀሳቀስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡ በአንድ በኩል የሕዝቡን ተሳትፎ በትክክል ማግኘት ይኖርበታል፡፡ በሕዝብ ተሳትፎ ስም ለይስሙላ መድረክ ላይ የሚያጨበጭቡ አስመሳዮችና አድርባዮች ሊበቃቸው ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ከሕዝብ ጋር በሚደረግ ምክክር የሚገኙ ግብዓቶችን ከተጨባጩ ሁኔታ ጋር አዛምዶ መፍትሔ ለማግኘት፣ በሲስተም የሚመራ አቅጣጫ ሊኖረው ይገባል፡፡ ተቋማትን በሠለጠነ የሰው ኃይል፣ ዘመኑ ባፈራቸው ቴክኖሎጂዎችና አጋዥ መሣሪያዎች ማደራጀት ያስፈልጋል፡፡ በየቦታው የሚመዘበረውን ሀብት በመከላከል ተቋማቱ በቂ በጀት አግኝተው ሲደራጁ የሲስተም ግንባታው ዕውን ይሆናል፡፡ በየጊዜው ከሚለዋወጠው የዓለም ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የአዲሱን ትውልድ ፍላጎቶች መረዳት የግድ ነው፡፡ በዚህ ዘመን እንደፈለጉ አገር መግዛትም ሆነ ሕዝብ ማስገበር አይቻልም፡፡ ይኼ ዓይነቱ ደመነፍሳዊ አካሄድ ቆሞ ሲስተም መዘርጋት የወቅቱ ጥያቄ ነው!   

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...

በሰጥቶ መቀበል መርህ መደራደርና ሰላም ማስፈን ለምን ያቅታል?

በያሲን ባህሩ አገር ግንባታ የትውልድን ትልቅና ታሪካዊ ኃላፊነት የሚጠይቅ ተግባር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...

ለሕዝብና ለአገር ክብር የማይመጥኑ ድርጊቶች ገለል ይደረጉ!

የአዲሱ ዓመት ጉዞ በቀናት ዕርምጃ ሲጀመር የሕዝብና የአገር ጉዳይን በየቀኑ ማስታወስ ግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ልማትና ዕድገት ያስፈልጋሉ ከሚባሉ ግብዓቶች...