Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከኦዲት ሪፖርቶች ጋር በተገናኘ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የሰላ ትችት ተሰነዘረበት

ተዛማጅ ፅሁፎች

በፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የሚቀርቡ የኦዲት ግኝቶችን መሠረት በማድረግ በዋና ዋና ግዙፍ ጉዳዮች ላይ ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ፣ በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጓል በማለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴርን ተቹ፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አቶ አብዱላዚዝ መሐመድ ማክሰኞ መጋቢት 6 ቀን 2008 ዓ.ም. በምክር ቤቱ የሚኒስቴሩን የስድስት ወራት አፈጻጸም ባቀረቡበት ሪፖርት፣ መሥሪያ ቤታቸው የ2006 ዓ.ም. የዋና ኦዲተርን የኦዲት ግኝቶች አስመልክቶ የወሰዳቸውን ዕርምጃዎች ያቀረቡ ቢሆንም ከምክር ቤት አባላቱ በርካታ ጥያቄዎች ተነስተውባቸዋል፡፡

ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው እንደገለጹት በዋና ኦዲተር የ2006 ዓ.ም. የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች የአዲስ ግኝቶች ላይ መውሰድ ስላለባቸው የማስተካከያ ዕርምጃዎች መርሐ ግብር በማዘጋጀት የሚመለከታቸው ሁሉ እንዲያውቁት የተደረገ ሲሆን፣ በመርሐ ግብሩ መሠረት በተመረጡ 41 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ ቡድኖችን በማሰማራት በግኝቶቹ ላይ ማረሚያ ስለመደረጋቸው የክትትል ኦዲት ተደርጓል፡፡ አቶ አብዱላዚዝ የክትትል ኦዲት ውጤቶች ናቸው ያሏቸውን ሰባት ዋና ዋና ጉዳዮችን በዋቢነት  በሪፖርታቸው ዘርዝረዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በዋና ኦዲተሩ ቀርበው የነበሩ ያልተወራረዱ ሒሳቦችን በመጠኑ ስለማወራረድ፣ በወጪ ተመዝግበው ነገር ግን በተሰብሳቢነት በመሥሪያ ቤት የተመዘገቡ ሰነዶችን ማስተካከል፣ ውዝፍ ገቢን በተለይም በዩኒቨርሲቲዎች እንዲሰበሰቡ የማድረግ ሥራና ሌሎች ጉዳዮችም ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪም በክትትል ኦዲቱ የተሸፈኑት መሥሪያ ቤቶች በኦዲት ግኝቱ የወሰዱትንና ያልወሰዱትን ዕርምጃ የሚገልጽ ሪፖርት ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት፣ ለቋሚ ኮሚቴዎች፣ ለሚኒስትሮች ምክር ቤትና ለዋናው ኦዲተር መሥሪያ ቤትና ለሚመለከታቸው ሁሉ ተገቢውን ዕርምጃ እንዲወስዱ ሪፖርት እንዲደርሳቸው መደረጉን ጨምረው ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን በሚኒስትሩ ሪፖርት የተዘረዘሩት የክትትል ኦዲትና ዕርምጃዎችን የምክር ቤት አባላቱ እንደ በጎ ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ አብጠልጥለዋቸዋል፡፡ ለአብነትም ያህል አቶ ዘለቀ መሀሪ የተባሉ የምክር ቤት አባል ዋናው ኦዲተር በስፋት ካቀረቧቸው የኦዲት ግኝቶች አንፃር የሚኒስቴሩ ሪፖርት ‹‹ከዛፍ ላይ ቅጠል የማራገፍ ያህል ነው፤›› በማለት፣ ሚኒስትሩ ያቀረቡት የክትትል ኦዲት አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እንዲሁም አቶ ክፍሌ ለማ የተባሉ የምክር ቤት አባል ደግሞ የሚኒስትሩን ሪፖርት ከዋና ኦዲተር የኦዲት ግኝት ጋር በማነፃፀር ‹‹ውስን›› ነው በማለት ተችተዋል፡፡ ‹‹ሪፖርቱ ላይ የቀረበውን ከዋናው ኦዲተር የኦዲት ግኝቶች አንፃር ስመለከተው ውስን ሊባል የሚችል ነው፡፡ ግኝቶች ተብለው አሁን የቀረቡትም በጣም ጉድለቶች አሉባቸው፡፡ እነዚህ ግኝቶችን መሥሪያ ቤቶች ፈጥነው ዕርምጃ የማይወስዱበት፣ ማስተካከያ የማያደርጉበት፣ በሪፖርቱም ላይ ስድስት ሺሕ ብርና የሚቀራረቡ አነስተኛ መጠን ያላቸው ገንዘቦች ስለመመለሳቸውና ስለመሰብሰባቸው ነው የተቀመጠው፡፡ ነገር ግን በርካታ ችግሮች ስለመኖራቸው በዋናው ኦዲተር ከቀረበው ሪፖርትም ሆነ እኛ ራሳችን በምናደርጋቸው ክትትሎች አስተውለናል፤›› በማለት አቶ ክፍሌ አስረድተዋል፡፡

አቶ ዘለቀም ተመሳሳይ ትችት ያቀረቡ ሲሆን፣ ቀድመው አስተያየታቸውን መግለጽ የጀመሩት የሚኒስትሩ ሪፖርት በራሱ ከአቀራረቡም ቢሆን ችግር የነበረበትና ከምክር ቤቱ የአባላትና አሠራር ደንብ የሚፈቅደውን አካቶ መቅረብ እንደነበረበት ገልጸዋል፡፡

‹‹ይህ ሪፖርት የራሱ የሆነ ጥንካሬ ቢኖረውም ብዙ ድክመቶችም አሉበት፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹አጠቃላይ ሪፖርቱን ስናይ በዋና ኦዲተር ከቀረቡት በቢሊዮን ብር የሚገመቱ ግኝቶች አንፃር የሚኒስትሩ ሪፖርት ነካ ነካ በማድረግ ነው የቀረበው፡፡ ዋና ዋና ጉዳቶችን በግዝፈት አላየም፡፡ በዋና ኦዲተር በቀረበው ሪፖርት እስከ 1.038 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ውዝፍ ገቢ አለመሰብሰቡን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል፤›› ያሉት አቶ ዘለቀ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ምን እየሠራ እንደሆነ በአግባቡ አለመግለጹን አመልክተዋል፡፡

‹‹በእናንተ በኩል ጥቃቅን ጉዳዮችን በሺሕ ብር የሚቆጠሩ ገንዘብ አስመልሰናል ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ በዚያ ውስጥም ቢሆን አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ፈልገው የፈጸሙትን እንጂ አንፈጽምም፣ አንሠራም ያሉ መሥሪያ ቤቶችን ምን እንደመጣባቸውና ምን እንደሚጠብቃቸው አላመላከታችሁም፡፡ ምናልባት በእናንተ በኩል የተሰጠው አስተያየት ‹አሳስቦናል› የሚል ነው፡፡ ይኼ አሳስቦናል የሚል ነገርን ዋና ኦዲተሩንም፣ ምክር ቤቱንም፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱንም ሲያሳስብ የመጨረሻው ሰው ምን አድርጎ ሊሄድ እንደሚችል የሚያስጨብጥ ነገር የለም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

አቶ ዘለቀ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በራሱ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ የሰጠውን ብድር፣ ወለድንና ቅጣትን ሳይጨምር ማስመለስ አለመቻሉ የገለጸውን በማንሳት ድክመቱን ተችተዋል፡፡

በገቢዎችና ጉምሩክ በኩልም ቢሆን ያልተሰበሰቡ ገቢዎች መኖራቸውን አባላቱ አንስተዋል፡፡ ከኦዲት ግኝቶች በተጨማሪ በመንግሥት ግዢ፣ ንብረት አስተዳደርና አወጋገድ እንዲሁም የማክሮ ኢኮኖሚና የፋይናንስ ተቋማትን ጨምሮ በርከት ያሉ ጥያቄዎች ለአቶ አብዱላዚዝ ቀርበውላቸዋል፡፡ ሚኒስትሩም በቀረቡት ጥያቄዎችና ትችት አዘል አስተያየቶች የራሳቸውን ማብራሪያ የሰጡ ቢሆንም፣ ከኦዲት ግኝቶች ጋር ተያይዘው የቀረቡላቸውን ትችቶች በሪፖርታቸው የተነሱ በመሆናቸው ብዙም ማብራሪያ ሳይሰጡባቸው አልፈዋል፡፡ ይልቁንም ሰፊ ጊዜ ሰጥተው መልስ የሰጡባቸው ጉዳዮች የመንግሥት ግዢና ንብረት አወጋገድን በተመለከተ ነበር፡፡

በተለይ የወጪ አስተዳደርንና ወጪ ቁጠባን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፣ መሥሪያ ቤታቸው በመንግሥት ግዢ፣ ንብረትና ወጪ አስተዳደር ረገድ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅን ለማሻሻል ረቂቅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የተላከ መሆኑን፣ በሥራ ላይ ያለውን የመንግሥት ግዢና ንብረት አስተዳደር አዋጅ የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጅቶ በቅርቡ እንደሚላክ ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ወጪን ለመቀነስ ማድረግ ስለሚገባቸው ጉዳዮች ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ አብራርተዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ እንደ ምሳሌ ባቀረቡት ማብራሪያቸው ማንኛቸውም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከግል ባለሀብቶች ቢሮ መከራየት ሲፈልጉ ብዙ ወጪ የማያስወጣ ሕንፃ መከራየት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡ በተለይም ማንኛውም መሥሪያ ቤት ከኪራይ ዋጋ ውድነት አንፃር ቦሌ አካባቢ መከራየት እንደሌለበት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንደሚያሳስብ አቶ አብዱላዚዝ ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች