Tuesday, February 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ቋንቋ ዕውቀት ባይሆንም ዕውቀት ግን ቋንቋ ነው

በመርዕድ አሸናፊ

አንድ አስገራሚ መጽሐፍ ርዕሱ ‹‹ቋንቋ ዕውቀት አይደለም›› ይላል፡፡ ይህ መጽሐፍ በ2010 ዓ.ም. የታተመ ሲሆን፣ በተለያ ንዑሳን ርዕሶች በ151 ገጾች የተዘጋጀ ነው፡፡ ደራሲው አንድነት ኃይሉ በዚህ መጽሐፍ አማካይነት ቋንቋ ዕውቀት ቢሆን ኖሮ ትምህርት ባልኖረ ነበር ይለናል፡፡ ቋንቋን ከብሔር፣ ከኢኮኖሚያዊ ግንኙነት፣ ከዕውቀት፣ ከፍላጎትና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ይተነትናል፡፡ የሰውን ልጅ በቋንቋው ስንለያይ እንዳንነጣጥል፣ አንድ ስናደርግም እንዳንቀላቅል የሚያደርገን ትልቁ ማዕዘን ሰው መሆናችንና የዕውቀት ፍላጎት ባለቤት መሆናችን እንደሆነ፣ አገር ማንንም የምትፈልገው በእያንዳንዳችን ውስጥ ያለውን ልዩነት በሥራ ላይ ለማዋል ነው ሲልም አፅንኦት ይሰጣል፡፡ ደራሲው በዚህ መነሻ የሰው ልጅ በዓለም ላይ የሚገኝን የትኛውንም ነገር እየተጠቀመበት ያለው እንደገባውና እንዳለፈበት የሕይወት ተሞክሮ መሆኑን በመጠቆም፣ የሰው ልጅ እየተግባባ ያለው በቋንቋ ብቻ ይመስለዋል ይላል፡፡ በዚህም መሠረት የሰው ልጅ ለመግባባት ቋንቋው፣ ዕውቀቱና ፍላጎቱ ይጣጣሙ በማለት ያክላል፡፡

በደራሲው ዕይታ ሰው በዕውቀት አማካይነት ቋንቋውን ከሚያውቅም ከማያውቅም ጋር፣ ቋንቋውንም ዕውቀቱንም በመጠቀም ይግባባል፡፡ ይህ ማለት የሰው ልጅ የትኛውንም ሐሳቡን ለመግለጽ ቋንቋን እንደ ግብዓት ቢጠቀምም፣ ቋንቋ ሐሳብን ለመግለጽ ግብዓት ሆነ እንጂ ዕውቀት አልሆነም ብሎ ቋንቋ፣ ዕውቀትና ፍላጎት የሚመጋገቡበትን መንገድ ያሳያል፡፡ አንድን ዕውቀት ምንም ነገር ሳይቀንስና ሳይጨምር በተለያየ ቋንቋ መግለጽ መቻሉ የሚያሳየው፣ ዕውቀትና ቋንቋ የተለያዩ መሆናቸውንና ቋንቋ ለዕውቀት ግብዓት እንደሆነ ያስረዳናል፡፡

እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለበት በቋንቋ ለመግባባት የግድ ቋንቋ ማወቅ ይጠይቃል፡፡ ይሁንና ዕውቀት፣ ቋንቋና ፍላጎት ቢኖርም ለመግባባት መሠረቱ ዕውቀት ሆኖ ቋንቋውና ፍላጎቱ ለዕውቀት ግብዓት መሆናቸውን በዚህ መጽሐፍ ደራሲ ተሰምሮበታል፡፡ ያለ ዕውቀት ቋንቋም ፍላጎትም ምንም ናቸው ይለናል፡፡ በዚህ መነሻነት ሰው ምንድነው በማለት፣ በራሱ አተያይና እምነት መሠረት ሰው የሦስት ነገሮች ዉህድ ውጤት መሆኑን ይነግረናል፡፡ አካል፣ ነፍስና መንፈስ፡፡ ሠሪውም እግዚአብሔር መሆኑን መስክሮ በአካል ውስጥ ነፍስ፣ በአካልና በነፍስ ውስጥ ደግሞ መንፈስ እንዳለ ያስረዳል፡፡ ይህንን በስፋት ተንትኖ በዓለም ላይ የሰው ልጅ በሙሉ በአካልና በነፍስነቱ አንድ ሆኖ ሲወራረስ፣ በመንፈስ ግን ሁሉም የራሱን ነው ብሎ ከእናትና ከአባት የሚወረስ አንዳች ነገር የለም ይላል፡፡ በዚህም መሠረት ሰው በእምነት፣ በዕውቀትና በቋንቋ ተለያየ በማለት ያክላል፡፡

በዚህ እሳቤ መለያየቱ እንዴት ተፈጠረ? በመለያየቱስ ምን ተፈጠረ? ልዩነቱንስ እንዴት ነው የሚያስተናግደው? እንዴትስ ቢያስተናግደው ነው የሚጠቅመው? በማለት ምርምሩን ይቀጥላል፡፡ የሰው ልጅ መጀመርያ፣ መሀልና መጨረሻ አለው ይላል፡፡ መጀመርያ ውልደቱ ሲሆን፣ መሀሉ የሚኖረው ሕይወቱ (ቢያምንበትም ባያምንበትም) ነው፡፡ መጨረሻው ግን ግልጽ ነው፡፡ ሰው ተጨንቆና ተጠቦ ካልሠራቸው ነገሮች አንዱ ቋንቋ እንደሆነ፣ የሚናገረውን ቋንቋ ባለቤት የሆነበትን ምክንያት የሚረዳውም ራሱን ካገኘ በኋላ መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡ ታዲያ ልዩነትን እንዴት ቢያስተናግደው ነው የሚጠቅመው? በሰዎች መሀል የቋንቋ መለያየት መኖር ማለት ሰው በመሆን አንዱ ከሌላው ወይ ያንሳል አሊያም ይበልጣል አለመሆኑ ይታወቃል ሲልም ያስገነዝባል፡፡ በዚህ መንገድ የቋንቋ ልዩነት መስተናገድ ያለበት የዕውቀት አንድነት በመፍጠር ነው ሲልም ኅብር ይፈጥራል፡፡ የዕውቀት አንድምታ በሕግ አንድ እንደሚሆን ሁሉ፣ የቋንቋ አንድነትም በዕውቀት ነው ዕውን የሚሆነው ሲል ያዛምደዋል፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ መኖር የሚችለው በቋንቋ ሳይሆን በዕውቀት እንደሆነ፣ ሰው መገለጽ ያለበት በዕውቀት ስለሆነ ዕውቀት ቋንቋን ይበልጣል ይላል፡፡ ብዙ ምሳሌዎችን ይተነትናል፡፡

ጸሐፊው የብሔር ጭቆና ምንድነው? ብሔርስ ምንድነው? በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ዋና ዋና ነጥቦችን ያነሳል፡፡ በአገሪቱ ይህ ጉዳይ በበርካታ መንገዶች መገለጹን፣ በዓለም ላይ ከኢትዮጵያ በባሰ በከፍተኛ ሁኔታ መወሳቱን ይጠቁመናል፡፡ የብሔር ጭቆና ማለት ሰውን በቋንቋው፣ በባህሉ፣ በእምነቱ፣ ወዘተ መናቁና አገራዊ ተሳትፎው መገደቡ ብቻ አይደለም ይላል፡፡ ይልቁንም የመብቱ መረገጥ፣ ለመኖር የሚያደርገው ትግል መደናቀፍ፣ ከዓላማው መፈናቀል፣ ካፈራው መከልከልና እንደ ሰው አለመቆጠር ነው በማለት ይጨምርበታል፡፡ ይኼ ጉዳይ የዚህ ዘመን ሳይሆን አልፏል ይላል፡፡ በፊት በስፋት የሚታወቅ ቢሆንም ዛሬ ግን ቋንቋህ፣ ባህልህ፣ እምነትህ፣ ወዘተ ተከብሮልሃል ብቻ ሳይሆን አገር ከአንተ ከዚህ የበለጠ ስለምትፈልግ ዕውቀትህን፣ ጉልበትህን፣ ፍላጎትህን የገበያ ግብዓትና ተሳታፊ በማድረግ ኖረህ ለማኖር ታስፈልጋለህ ነው ጥያቄው በማለት ይሞግታል፡፡

በአገር ልማት ልዩነት አለመኖሩን በማንሳት በጥርጣሬና ባለመተማመን የሚመራ አገርና ኢኮኖሚ የለም፣ ቢኖርም አይገነባም ይላል፡፡ በብሔር ምክንያት የቋንቋ ልዩነት ሲኖር አንድ ሰው ከሌላው ጋር ያለውን ግንኙነት ለምን ከቋንቋ ጋር ያገናኘዋል በማለት ማብራሪያ ይሰጣል፡፡ ቋንቋውን የሚችል ሰው ወገን ወይም ዘመድ ማድረግ፣ ቋንቋ የማይችልን ደግሞ ማራቅ የጥላቻ ስሜት እንደሆነ ይገልጽና ሰዎች በቋንቋ ስለተግባቡ ብቻ በሁሉም ነገር ይግባባሉ ማለት አይደለም በማለት ይተነትናል፡፡ በቋንቋ አለመግባባት መለያየት እንዳልሆነ፣ ቋንቋ የሁሉም ነገር ገዥ ባለመሆኑም ለመግባባትም ሆነ ለመለያየት ብቁ እንዳልሆነ ያስረዳል፡፡ አንድ ቋንቋ የሚናገሩ ሁለት ሰዎች በመሀላቸው ፍፁም መመሳሰል አለ ተብሎ ማሰብ እንደማይቻል፣ ሁለቱም ግን የራሳቸው የሆነ ዕውቀትና ፍላጎት እንዳላቸው ግንዛቤ መኖር አለበት ይላል፡፡ ‹‹የሰውን ልጅ በቋንቋ ስንለያይም እንዳንነጣጥል፣ አንድ ስናደርግም እንዳንቀላቅል የሚያደርገን ትልቁ ማዕዘን ሰው መሆናችን፣ የዕውቀትና የፍላጎት ባለቤት መሆናችን ነው፤›› በማለት እንደገና ሐሳቡን ያፀናል፡፡

የሰው ልጅ ብሔር የሚባል ማንነት ወይም መገለጫ አለው? የአንድ ሰው ብሔሩ የሚባለው ምኑ ነው? ደምና አጥንቱ? ወይስ አስተሳሰቡ? ቋንቋስ ለሰው ልጅ ምኑ ነው? ብሔሩ ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን ያነሳል፡፡ ‹‹ደም እንዳንል ሁሉም ደም አንድ ነው፡፡ አጥንት እንዳንል ሁሉም አንድ ዓይነት ነው፡፡ ዕውቀት ከተባለም ሁሉም የየራሱ አለው፡፡ ቋንቋ አይባል አንድ ቋንቋ ተይዞ የተለያዩ ባህሎች፣ እምነቶች ይታያሉ . . . ›› በማለት መገረም የሚያጭር ዕይታ ያመጣል፡፡ አንድ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ብዛት በቁጥር ሲገለጽ ብሔር ሊባል ይችላል፡፡ አንድ ቋንቋ ከአንድ ሰው በላይ የሚናገረው ከሆነ ቁጥሩን ለመግለጽ ሲባል ብሔር ሊባል ይችላል፡፡ በተረፈ አንዳንዶች ብሔር ማለት የአንድ ማኅበረሰብ የማይነካ የሀብት ልዩ መገለጫ፣ እንዲያውም ከሰውየው በላይ ትልቅ መገለጫ ያደርጉታል በማለት ለየት ያለ ዕይታ ያመጣል፡፡ በዚህ መሠረት ብሔር የሚባለው ቋንቋውን፣ ባህሉንና እምነቱን አይደለም እያለ የመጽሐፉ ደራሲ አዲስ ሐሳብ ያመጣል፡፡

በዚህ መሠረት ሰው ባህልና እምነት እንዳለው፣ የማይነካና ልዩ እንደሆነ፣ ልዩነቱም እንዳለ መጠበቅ እንዳለበት፣ ለጋራ ጥቅም ተብሎ መዋሀድ ወይም መቀላቀል የማይቻል መሆኑን ያሰምርበታል፡፡ ይህም የዕውቀት ጥግ የሆነ እውነታ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ሰው በቋንቋ ቢለያይም አንድ ነው ሲባል ሰውን ከቋንቋ በላይ በትክክል ሊገልጸው የሚችለው ፍላጎቱ ነው በማለት፣ ፍላጎት ደግሞ በዕውቀት መመራት ይኖርበታል ይላል፡፡ ሰው የተለያየ ነው ሲባል ምክንያቱ የተለያየ ቋንቋ ስላለው ነው ከተባለ ፍፁም ስህተት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ሰውን ማሳነስ ነው ሲል ያስረዳል፡፡ ሰውን ከቋንቋ በላይ የሚገልጸው ዕውቀት አለው በማለት የሰውን ልጅ ክብር ያስገነዝባል፡፡ በአንድ አገር ውስጥ አንድ ግለሰብ ቋንቋ፣ እምነት፣ ዕውቀት፣ ፍላጎት፣ ወዘተ እንጂ ብሔር የለውም ሲልም ደፈር ብሎ ያስረግጣል፡፡ ምክንያቱን ሲያስረዳም፣ ‹‹ቋንቋውን ከሚናገሩ ሰዎች ውስጥ አንተ ስንተኛ ነህ? ቁጥርህስ ስንት ነው? አይባልም፡፡ እስካሁንም አልተባለም፡፡ ቋንቋን እንመርምረው ካልን አንጨርሰውም፡፡ ያለንንና የገባንን እንደሚጠቅመን አድርገን ካልተውነው የበለጠ የሚጠቅመንን ሀብት እናባክናለን፤›› በማለት ጸሐፊው ይገልጽልናል፡፡

የመጽሐፉ ደራሲ የቋንቋ ባለቤት ማነው? ሕግ፣ ገንዘብ፡- ገንዘብና የሰው ልጅ፣ ገንዘብና ግብይት፣ ድህነትና ገንዘብ፣ ቋንቋና ዓለም፣ ቱሪዝምና ቋንቋ፣ ከተሞቻችንና እኛ፣ የሰው ልጅ እንዲህ ነው፣ ከተሞቻችንና ክልሎቻችን፣ አንድ አገር ሥራዋን ከየት ነው የምትጀምረው? አሁን እየተፈጠረ ያለው የቋንቋ ችግር፣ ገንዘብና መንግሥት አገር በሚሉ ንዑስ ርዕሶች አማካይነት ቋንቋና ዕውቀትን ከፍላጎት ጋር አስተሳስሮ ምልከታውን አቅርቧል፡፡ ከዚህ ቀደምም ‹‹የአንድ አገር ሕዝቦች›› በሚል ርዕስ ሁሉም ሰው ስለአገሩ ሊያውቀው የሚገባ እውነት የሚተነትን መጽሐፍ አቅርቧል፡፡ ጸሐፊው በሁለቱም መጻሕፍት በራሱ ዕይታ በርካታ ጉዳዮችን ተንትኗል፡፡ በዚህኛው መጽሐፉ ‹‹. . . ሁሉም ሰው ውስጥ ሁሉም ቋንቋ አለ፤›› በማለት፣ ዕውቀት የጎደለው ሕዝብ ግም እንኳን ቋንቋና ባህል ሊኖረው አገር የለውም ይለናል፡፡ አንባቢያን ዝርዝሩን ከመጽሐፉ እንዲያነቡ በአክብሮት አሳስባለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles