Monday, October 2, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ተባበሩ ወይም ተባበሩ!

በሪያድ አብዱል ወኪል

የመፈታት ዘመን ለኢትዮጵያችን መጥቶ ታስረው የነበሩ ብዙ ነገሮች መፈታት ጀምረዋል፡፡ በዚሁ ከቀጠልንም እግር ተወርች አስረው የያዙንን ብሎም የአመለካከትና የተግባር ደዌ ሆነውብን የቆዩትን ግላዊና ማኅበራዊ ችግሮች እየፈታን እንደምንሄድ አያጠራጥርም፡፡ ይህ እንዲሆን ግን እንደ ድርሻችንና በየተሰማራንበት የሙያ መስክ ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ ኃላፊነት ይኖራል ብዬ አምናለሁ፡፡ ከእነዚህ ኃላፊነቶች አንዱ አገራችን የጋራ መግባባት የከሰመባት ትልቅ እስር ቤት እንድትሆን ያደረጓትን ችግሮች በመለየት ማስተካከያዎች እንዲመጡ መጠቆም መስጠት ይመስለኛል፡፡

      በቅርቡ ከረዥም ጊዜ የእስር ቆይታ በኋላ የተፈቱት ዕውቁ ፖለቲከኛ አቶ ተስፋ ሚካኤል አበበ (አበበ ቀስቶ) ከአንድ መጽሔት ለቀረበላቸው የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶቻችን ጊዜያዊ አቋምና ይዞታ ላይ ያተኮረ ጥያቄ መልስ ሲሰጡ፣ ተቃዋሚ (ተፎካካሪ) ድርጅቶቻችን ያሉበትን አሁናዊ ሁኔታ “ከመንደር ዕድርና ዕቁብ የተሻሉ አይደሉም” በማለት ነበር የገለጹት፡፡ የአንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ አባልና አመራር የነበሩት ዶ/ር ንጋት አስፋውም ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ወቅት ይህንኑ ጉዳይ አንስተው፣ “አብዛኛዎቹን ፓርቲዎች ስትፈትሻቸው ከሠፈር ዕድር የተሻለ ጥንካሬ የላቸውም፤” ብለው ነበር፡፡

የዚህ ጽሑፍ አሰናጅ ከአማካዩ ሜዳ (Golden Mean) “መድረክ” ክሽፈት በኋላ የየትኛውም ድርጅት አባልም ደጋፊም አይደለሁም፡፡ የጽሑፉ ዓላማም ይህንን ወይም ያንን መደገፍም መንቀፍም አይደለም፡፡ ኢሕአዴግን ጨምሮ ለአገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት ስምረት ድርሻ የሚወስዱትን የፖለቲካ ድርጅቶች ዳግም ውስጣቸውን በመፈተሽ፣ ያንሰራራው የነፃነት ተስፋ እንዳይሟሽሽ ለማንቃት ያለመ ነው፡፡ በተለይም በተቃውሞው ጎራ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ በመሥራት፣ የተተካኪነት ሚናን ለማግኘት ከኢሕአዴግ ጋር በመፎካከር የሕዝብን ዕምነት እንዲያፀኑ በግል የሚሰማኝን ተስፋ የጋራ እንዲሆን ለማድረግም ነው፡፡

ከወቀሳ የሚቀድም ክብርና ምሥጋና

 ቆየት ያለ የመሟገቻ ሐሳብ “ፖለቲካ ማለት. . . ከሁሉም በላይ በሥልጣን ላይ ባለውና እሱን ሊተኩ በሚፈልጉ ተፎካካሪ ስብስቦች መካከል የሚደረግ የሁለትዮሽ ትግል ነው፤” እንደሚለው ይህ ትግል የሐሳብ ሆኖ እንዲዘምን፣ ተመጣጥኖም ሚዛኑን እንዲጠብቅ ተፎካካሪ ድርጅቶቻችን በነባራዊው ዓለም ርዕዮተ ዓለሞች ቁጥር ልክ በሁለትና በሦስት ጥላ ሥር ሊሰባሰቡ ግድ የሚልበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡

      ዴሞክራሲ በጠነከረባቸው አገሮች ድርጅቶቹ ከተቃዋሚም ከተፎካካሪም ከፍ ብለው “ተጠባባቂ መንግሥታት (Alternative Government” ወይም “Government-In-The Waiting”) ነውና የሚባሉት፣ አሁን ኢትዮጵያውያን እውነተኛውን “ታማኝ ተቃዋሚ (“Loyal Opposition”) ፍለጋ ላይ ነን ብዬ አምናለሁ፡፡ ታማኝነቱም ለኢሕአዴግ ወይም ለገዢው ፓርቲ ሳይሆን፣ ለሕገ መንግሥቱና ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የሆነ በተለይም ለሕዝብና አገራቸው፣ ለህሊናና ለራሳቸው የታመኑትን ሁለት ወይም ሦስት ጠንካራ ድርጅታዊ አቅም ከሕዝባዊ መሠረት ጋር ታድለው ለአሳታፊ ዴሞክራሲ የሚሠሩትን የፖለቲካ ድርጅቶች እያፋለግን ነው፡፡

      ከወራት በፊት ኢትዮጵያችን ችግር ውስጥ በነበረችበትና ይኸው ችግርም በርትቶ በነበረበት ወቅት ሐዋሳ በሚገኘው የደቡብ መለስ አመራር አካዳሚ ለክልሉ ዓቃብያነ ሕግ ተዘጋጅቶ በነበረ ሥልጠና ላይ የመሳተፍ ዕድል አግኝቼ ነበር፡፡ በዚሁ የመንግሥት ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ላይ ባተኮረው ሥልጠና ማጠናቀቂያ ወቅትም በአካዳሚው ደንብ መሠረት እንደ መግቢያው ሁሉ የመውጫ ፈተና ይሰጣልና ሠልጣኞች ለፈተና ተቀመጥን፡፡ ለተፈታኙ በሙሉ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ የነበረው የመጨረሻው ጥያቄ ግን የምር ያስደነገጠኝና ተስፋ አስቆርጦ “ኢሕአዴግ በፍፁም የሚቀየር ድርጅት አይደለም!” እንድል ያደረገኝ ነበር፡፡

      ቃል በቃል ማስታወሱ ቢከብደኝም “የክላሱ ሰቃይ!” የተባልኩትን ጨምሮ በርካታ ዓቃብያነ ሕግ “ኤክስ” የሆንንበት ጥያቄ ከሞላ ጎደል፣ “በኢትዮጵያ የሚገኙ ተቃዋሚዎች በሙሉ ኪራይ ሰብሳቢዎች ናቸው፡፡ መከራከሪያው ትክክል ነው፣ በከፊል ትክክል ነው ወይም ትክክል አይደለም በማለት መልስ ስጡ ምክንያታችሁንም ጻፉ፤” የሚል ሲሆን፣ ፈተናውን ያረሙት ግለሰቦች በጥቂቱም ቢሆን ለዘብ ብለን “ጥያቄው በከፊል ትክክል ነው፤” የሚለውን አማካይ ቦታ እንኳ እንድንይዝ ያልፈቀዱ መሆናቸውን ሳስብ አሁን ድረስ ይገርመኛል፡፡ እንዲህ ያለው ከመንግሥት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሥልጠና ጎን ለጎን “Inject” የሚደረግበትና ተቃዋሚ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶችን ጥላሸት የመቀባቱ ሥራ በተለያዩ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ለሚገኙ ተማሪዎች በተለያዩ ወቅቶች መሰጠቱም ይታወቃል፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ተፎካካሪ ብለው የሰየሟችውና አብረውም ሊሠሩ፣ «ከኢሕአዴግ ውጪ ያሉ ፓርቲዎችን የምናይበት መነጽር እንደ ተቃዋሚ ሳይሆን፣ እንደ ተፎካካሪ፣ እንደጠላት ሳይሆን. . . አማራጭ ሐሳብ አለኝ ብሎ እንደሚመጣ አገሩን እንደሚወድ የዜጋ ስብስብ ነው፤» በማለት ቃል የገቡላችሁ የአገሬ ተቃዋሚ ድርጅቶች አባላትና አመራሮች ሆይ፣ ቃላት ገልጸው በማይገልጹት መከራ ውስጥ አልፋችኋልና       ከማንም በላይ፣ ከሁሉም በቅድሚያ ምሥጋና ይገባችኋል፡፡ ዕድሜያችሁን፣ ዕውቀትና ንዋያችሁን፣ መልካሙን ስማችሁን፣ ቤተሰባችሁን፣ ጉልበትና ሁለመናችሁን ስለዛሬው መልካም ቀን መምጣት ያለምንም ስስት ገብራችኋልና ስለብርቱው ትግላችሁ ስለማሸነፋችሁም እናመሠግናችኋለን!!!

የተከፈተ ግን የተዘጋ በር

      በአንዲት አገር ውስጥ የፖለቲካ ድርጅቶች መኖር ለሕዝቡ የፖሊሲ አማራጮችን በማቅረብ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ትልም ለሆነው የብዙ ድርጅት ዴሞክራሲ (Multiarty Democracy) ሥርዓት ግንባታ ውስጥ አይተኬ ሚና እንዲኖር የሚያደርግ ነው፡፡ በኢትጵያችን በንጉሡም ሆነ በደርጉ ጊዜ የተቃውሞ ፖለቲካ ለጥይት የሚዳርግ ነበር፡፡ በህቡዕ ከመንቀሳቀስ ውጪ ሕጋዊ ዕውቅና ኖሮት የዘለቀ የፖለቲካ ድርጅትም አልነበረም፡፡ ከደርግ ውድቀት በኋላ ኢሕአዴግ ሙሉ ለሙሉ ባይባልም በአገር ውስጥና በውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይመለከተናል ባዮችን ሁሉ የአብረን እንሥራ ጥያቄ አቅርቦ ዴሞክራሲያዊ ሒደቱ እስከተቀለበሰበት ጊዜ ድረስ፣ የተቃዋሚ ድርጅት አባላትን ጭምር ያካተተ የሽግግር መንግሥት እስከ መመሥረት ደርሶ ነበር፡፡

የተቃዋሚ ድርጅቶች በቁጥር በዝቶ መኖር ብቻውን ግን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ስለመኖሩ ማሳያ አይደለም፡፡ እንዲያውም ሥልታዊ ፀረ ዴሞክራሲ መገለጫ ይመስለኛል፡፡ አገሪቱ ውስጥ ካሉት ብሔር ብሔረሰቦች ቁጥር በላይ የሆኑትና በድርጅታዊ የገንዘብ አቅም፣ አባላትን በመመልመልም ሆነ ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ የአገሪቱ አካባቢዎች ቢሮ አልባ የሆኑ ድርጅቶችን ብዛት ብንቆጥር አንጨርሳቸውም፡፡ በቅርቡ በሒልተን አዲስ አበባ ሆቴል በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ተደርጎ በነበረ ውይይት ላይ የውይይቱን መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ እንደ ከዚህ በፊቱ ሁሉ “ድርጅቶቹ መተቸትን ብቻ መሠረት ያደረጉና አማራጭ የማያቀርቡ ናቸው፡፡ አማራጭ ሲያቀርቡ ሰምቼ አላውቅም፤” ቢሉም፣ መተቸትም አንዱ የዓለም አቀፍም ሆነ አገራዊ የፖለቲካ ሥራ እንደመሆኑ መጠን የእኛ ጥያቄ ትችቱ እንዳለ ሆኖ፣ የመፍትሔ አማራጮቻቸውን እንዲያሳውቁን መሆን ያለበት ይመስለኛል፡፡

      ቻይናውያኑ “ተራራው ወዳንተ ካልመጣ አንተ ወደ ተራራው ሂድ፤” እንደሚሉት፣ ተፎካካሪ ድርጅቶች በቅድሚያ ተደራጁና አባላትን አደራጁ፡፡ የረሳችሁትን ሕዝቡን የማንቃት ብሎም መብትና ግዴታውን ያወቀ ዜጋ የመፍጠር ሚናችሁንም ተወጡ፡፡ የመንግሥትን ስህተቶች ያለማሰለስ አጋልጡ፡፡ በዚያው ልክም የመፍትሔ ሐሳቦችን አምጡ፡፡ ግለሰባዊ ችግሮቻችሁንና የቆየውን ቁርሾ (Complex) እርሱት፡፡ እንታገለዋለን የምትሉትን ፀረ ዴሞክራሲ ሥርዓትና አሠራርም በቅድሚያ ከውስጥ ታግላችሁ አሸንፉት፡፡ “እኔ ሊቀመንበር ካልሆንኩ ድርጅቱ ፈርሶ ሁለት ይሆናል፤” የሚለው ብሂል የሚያሳየን ራስን ታግሎ ያለማሸነፍን ነውና ራሱን ያላሸነፈ ይህንንም ብስለቱን ያላሳየ “መሪ” ሌላውን ያሸንፋል ተብሎ በሕዝብ እምነት ይጣልበታል ለሥልጣንም ይታጫል ማለት ዘበት ነው፡፡ በ “መርህ ይከበር!” ተቃውሞ የቅንጅት ውልድ ከሆነው አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ወጥተው “ሰማያዊ ፓርቲ” ን የመሠረቱ ሰዎች በቅርቡ ዳግም ከድርጅቱ መገንጠላቸውን በማወጅ፣ “የኢትዮጵያውያን አገር ዓቀፍ ንቅናቄ – ኢሃን” የተሰኘ “አዲስ ፓርቲ” ፈጥረው ዕውቅና ፍለጋ ላይ ስለመሆናቸው አንብቤያለሁ፡፡ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት የነበረው ዕውቁ ፖለቲከኛ አንዷለም አራጌም ያንን ሁሉ መስዋዕትነት ከፍሎ ሲፈታ፣ “አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ የመመሥረት እንቅስቃሴ ላይ ስለመሆኑም. . . ” ለቢቢሲ ከሰጠው ቃል ተረድቻለሁ፡፡

      እንዲህ ዓይነት ነገሮችን ሳነብም ሆነ ስሰማ አቶ አብዱልራህማን አህመዲን ሰንደቅ ጋዜጣ ላይ “80 ሚሊዮን ሕዝብ ‘ንጉሥ’ የሆነባት አገር!” በሚል ርዕስ ከዓመታት በፊት የጻፉት መጣጥፍ ትዝ እያለኝ፣ በእርግጥም ኢትዮጵያውያን የየራሳችንን ሚጢጢ ዙፋን በኪሳችን ይዘን የምንዞር ሳንሆን አንቀርም እላለሁ፡፡ በጽሑፌ ጅማሮ ላይ የጠቀስኳቸው አቶ ተስፋ ሚካኤል አበበ (አበበ ቀስቶ) እና ዶ/ር ንጋት አስፋው፣ “አንዱን ፓርቲ መርጬ አጠናክራለሁ” በማለታቸው ደስ የተሰኘሁትን ያህል፣ “አዲስ ፓርቲ እፈጥራለሁ” በሚሉ ሰዎች ብከፋ እንዳትፈርዱብኝ፡፡ በተለይ ደግሞ እነዚህ “የአዲስ ትውልድ” ወረተኞች ወጣቱን ማዕከል እንደሚያደርጉና ለወጣቱ ተጠቃሚነት እንደሚተጉ ሲናገሩ ሳደምጥ ብስጭቴ ይንራል፡፡

እንደ መነሻና መድረሻ

      በወጣትነቱ ብዙ ችግሮችን የተጋፈጠው ፖለቲከኛ ዮናታን ተስፋዬ ከእስር መልስ ነገሮች እንዳይሆኑ ሆነው ሲጠብቁትና አባል የነበረበትን የሰማያዊ ፓርቲ ሁለት ትንንሽ የመሆን ጉዳይ ሲያስተውል፣ “ትንሽ ሐሳብ በሰማያዊ ፓርቲ ዙሪያ” በሚል ርዕስ  በ“የሐበሻ ወግ” መጽሔት ቅጽ 2 ቁጥር 80 የግንቦት 2010 ዕትም ላይ ከተነበበለት ሐተታ ውስጥ ከቀድሞው የአቶ ልደቱ አያሌው “ተባበሩ አትበሉን” አቋም ጋር የተማሰለብኝንና የ“ተባበሩ ወይም ተባበሩ!” ፍካሬን የሚያጣጥል መስሎ የታየኝ በመሆኑ፣ በሐሳቡ የማልስማማባቸውን ሐሳቦች በማስቀመጥ መልዕክቴን ልቋጭ፡፡ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ሐሳብ ማዋጣትና መሟገት እንፈልጋለን ለምትሉ ግን እዚሁ ገጽ ላይ መስተናገድ የምትችሉ ይመስለኛል፡፡

      ዮናታን “ተቋም የመገንባት ችግር የአገሪቱ አጠቃላይ ችግር” መሆኑን በመጥቀስ ጉዳዩን ቀለል ካደረገው በኋላ፣ “ወቀሳ አያስፈልግም አልልም፡፡ ‘በአንድ ካልተጨፈለቁ ሁሉም ከንቱ ነው’ የሚል እሳቤ ግን ትክክል ነው ብዬ አላምንም፡፡ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብም አይደለም. . . በማናቸውም ገፊ ምክንያት ይሁን በጫና ሁሉንም በአንድ ለመሰብሰብ መኳተን በራሱ መበተን ሊሆንም ይችላል፤” በማለት ነበር ሐሳቡን ያስቀመጠው፡፡

      ፖለቲካ አልወድም የሚለውን ፖለቲከኛ ሳይንቲስት አልበርት አንስታይን አገላለጽ ተውሼ የዚህ ሐሳብ አራማጆችን፣ “ሁልጊዜ የምትሠሩትን እየሠራችሁ አዲስ ነገር እንዲፈጠር አትጠብቁ፤” እላቸኋለሁ፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሥጋት ውስጥ የጣለንና አለመተባበራችሁ ይልቁንም መሰባበራችሁ ያሳየን አንድና ብቸኛ ነገር ቢኖር፣ ለአጉል ቀን የሚሆንና ለክፉ ቀን የሚታመን ድርጅት ከኢሕአዴግ ውጪ አለመኖሩንና በቅርቡም የማይኖር መሆኑን ነው፡፡ ተቃዋሚ፣ ተፎካካሪ ድርጅቶች አሁን ባሉበት ሁኔታ የገንዘብና የአባላት መጠናቸውን በጠራ ዓላማ ብቻ ያሳድጋሉ ማለት ስህተት ይመስለኛል፡፡ የዓላማ ትልቅነት አንድ ነገር እንጂ ሁሉም ነገር አይደለም፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች የግል መሆን የለባቸውም፡፡ የድርጅቶች ለሥልጣን መብቃት እንጂ የድርጅቶች በቁጥር መብዛት ዴሞክራሲን ለአገራችን አያሰፍንላትም፡፡ በኢትዮጵያችን ማኅበረሰባዊ ሁኔታና የመንግሥት አያያዝ ውስጥ ተቃዋሚዎች በግለሰብ ደረጃም አለመጥፋታቸው የማከብርላቸው ፅኑ ክፍላቸው ቢሆንም፣ ከድርጅት ድርጅት እየተገላበጡ መኖራቸው ግን ከብዙ በጥቂቱ ሦስት ነገሮችን ያሳያል ብዬ አምናለሁ፡፡

      አንደኛ በተቃውሞው ሠፈር ያሉት ሰዎቻችን ጋር አምነው ላስቀመጡት ዓላማና መርህ የመቆርቆር፣ ለዚህም ዓላማ እስከ መጨረሻው የመናት ችግር ስለመኖሩና በጠቅላላውም ባይባል በአብዛኛው የመርህ ሰው እንዳይሉ፣ ለትንሹም ለትልቁም አስኮራፊ ጉዳይ በተለይም ወንበሯ የምትነካባቸው ከሆነ ፓርቲ የመቀያየር አባዜ የተጠናወታቸው ስለመሆኑ የሚያሳይ ነው፡፡ ሁለተኛ ልክ እንደ ኢሕአዴጉ አያፈናፍኔ “የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት” ጠርናፊ አስተሳሰብ ሁሉ የሐሳብ ብዝኃነትንና የግለሰቦችን ግላዊ የመሪነት ብቃት መታገስ አለመቻላቸውን፣ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ ዕጦት መቸገራቸውን የሚያሳይም ነው፡፡ ሦስተኛ አሁን ላይ በዓለማችን ፀንተው ሥራ ላይ ካሉት ሁለትና ሦስት ርዕዮተ ዓለሞች፣ የፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መርሐ-ግብሮች አንፃር በተቃዋሚ ወይም ተፎካካሪ ድርጅቶቻችን መካከል ያን ያህል ለዕርቅና ለገላጋይ የሚያስቸግር የርዕዮተ ዓለምም ሆነ የመርሐ ግብር (Program) ልዩነት የሌለና ሊኖርም የማይችል መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ጠቅለል ስናደርገው ከኢሕአዴግ ሥውር እጆች በመለስ ተፎካካሪ ድርጅቶቻችንን እንዳይተባበሩ ሰቅዞ የያዛቸው በግለሰቦች መካከል ሲወርድ ሲዋረድ የመጣና አሁንም ተዳፍኖ ያለ የጥላቻ ፖለቲካ፣ ግለሰባዊ ቁርሾ፣ የተለየ ሐሳብን ለመስማት ያለመፈለግ ትዕቢትና ከዋንጫው ሞልቶ የፈሰሰ ወንበር ወዳድነት እንጂ፣ የዓላማና ርዕዮተ ዓለም አልያም የመርሐ ግብር ልዩነት አይደለም፡፡ እነዚህን ክፉ ደዌዎች በማሸነፍ የመፈታቱን ዘመኑን በመተባበር እንድትዋጁት ይሁን እላለሁ፡፡

እንደ ከዚህ በፊቱ “ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ!” አንላችሁም፡፡ ተፎካካሪዎች ሆይ! መሰባበራችሁ እኛንም፣ እናንተንም፣ የዴሞክራሲ ተስፈኛዋ አገራችንንም ጎድቷታል፡፡ የአፍሪካ የነፃነት ፀሐይ ከዚሁ ምድር እንደበራች ሁሉ የአኅጉራችን ዴሞክራሲ ተስፋም ከዚሁ ምድር እንዲንቦገቦግ አስተዋፅኦ ማበርከት ትችላላችሁ፡፡ አሁናዊው ምርጫም መተባበራችሁ ብቻ ነው፡፡ ጥያቄውም ከወራት በፊት በአንድ መድረክ ላይ እንደጠየቃችሁት ለጥቃት ተጋላጭ ከሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች (Vulnerable Groups) ውስጥ ይካተቱ ሳይሆን፣ ለጋራ ዓላማ “ተባበሩ ወይም ተባበሩ!” የሚል ነው፡፡ ማነህ ዲጄው የጋራ ሥራ ከሆኑ የሙዚቃ ስብስቦችህ ውስጥ “ሁሉም ቢተባበር. . . ”የሚለውን የትብብር ዜማ ይድረስ ለተፎካካሪ ድርጅቶቻችን ብለህ ጋብዝልኝማ፡፡

ሰላም ለእናንተ ይሁን!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በጉራጌ ዞን የወለኔ ወረዳ ዓቃቤ ሕግ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles