Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአጣብቂኝ ውስጥ የገባው የመድኃኒት አቅርቦት

አጣብቂኝ ውስጥ የገባው የመድኃኒት አቅርቦት

ቀን:

የመድኃኒት አቅርቦት ላይ የታየው የዋጋ መናር አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል፡፡ ለዚህም መንስዔ የውጭ ምንዛሪ እጥረት መሆኑ ይነገራል፡፡ መንግሥትም ሆነ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ደግሞ የዋጋው መናርና የውጭ ምንዛሪው በተለያዩ መድኃኒቶች ላይ ሆን ተብሎ ዋጋ ለመጨመርና በኮንትሮባንድ ለማስገባት ቀዳዳ ለመክፈት ነው እንጂ ይህን ያህል እንዳልሆነም ይናገራሉ፡፡

      በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የመድኃኒቶችና የሕክምና መሣሪያዎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ረጋሳ ባይሳ ‹‹የመድኃኒት አቅርቦት ከ83 በመቶ በላይ ከውጭ የሚገባ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ የሚመረተው ከ15 በመቶ በታች ነው፡፡ ይህም ሆኖ አምራቾቹ ጥሬ ዕቃውን የሚያስመጡት ከውጭ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ዘንዳ የውጭ ምንዛሪውን ችግር ቀርፈዋል ለማለት ይከብዳል፤›› ብለዋል፡፡

      መሰንበቻውን ከነበረው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ የአገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች ጥሬ ዕቃውን ከውጭ ማስመጣት አልቻልንም የሚል አቤቱታ ያቀርቡ እንደነበር ከዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ዓለም አቀፍ ግዥ ሲፈጸም የራሱ የሆነ ሒደት አለው፡፡ ይህም አንዱ የሚወሰደው ጊዜ ሲሆን፣ ግዥው ከተፈጸመና ወደ አገር ውስጥ ከገባ በኋላ ደግሞ የማጓጓዙ ሁኔታ መጓተት፣ ሳይጠቀስ የማይታለፍ ተግዳሮት መሆኑንም ዳይሬክተሩ አመልክተዋል፡፡ መጠነ ሙቀቱን (ቴሞፕሬቸሩን) በጠበቀ መጋዘን ማስቀመጥና ለዚህም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ መሆኑን ገልጸው፣ አለበለዚያ መድኃኒቶች ለብርሃን ወይም ለፀሐይ ከተጋለጡ ጥራታቸውና ብሎም ፈዋሽነታቸው አብሮ አጠያያቂ እንደሚሆኑ አስረድተዋል፡፡

የመድኃኒት አጠቃቀምን አስመልክቶ ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች እንዳሉ ከነዚህም መካከል እንደ ዋነኛው መድኃኒቱን የሚያዝ ሐኪም ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ መድኃኒቱን ለተጠቃሚው የሚያደርስ ባለሙያ (ፋርማሲስት) እና አገልግሎት ፈላጊው ወይም ተጠቃሚው ናቸው፡፡ የሦስቱ አካላት መቀናጀት የታዘዘው መድኃኒት ለበሽታው በአግባቡ እንዲውል በማድረግ ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አማካሪ አቶ ያሬድ ይገዙ የዓለም ገበያ ተለዋዋጭነት እንዳለው፣ በተለይ የዚህ ዓመት እንቅስቃሴ ብቻ ሲታይ የቻይናና የአሜሪካን እሰጥ አገባ በአገራችን ላይ ትልቅ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረ ተናግረዋል፡፡ በዓለም ውስጥ ትልቁን ጥሬ ዕቃ የምታቀርበው ቻይና እንደመሆኗ መጠን በተካሄደው እሰጣ ገባ የጥሬ ዕቃ ዋጋ 30 በመቶ ጨምሯል፡፡

በዚህም የተነሳ የግዥ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው የነበሩ አቅራቢዎች ‹አሁን በዚህ ዋጋ ማቅረብ አንችልም› ነው ያሉት፡፡ በዚህም የተነሳ 80 ከመቶ ያህሉ ከውጭ የሚገባ ከሆነ ይህ ጉዳይ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ፡፡ ከዚህም ሌላ የመድኃኒት ብክነትና ሕገወጥ የመድኃኒት ዝውውር፣ ቅንጅት አሠራር አለመኖር በይበልጥ ችግሩን እንዳባባሰው ጠቁመዋል፡፡

እንደ አማካሪው አገላለጽ፣ የአገር ውስጥ ምርት በሚፈለገው መጠን አለማደጉ ሌላው ችግር ነው፡፡ ይህንን ለማበረታታት ከአሥር ዓመት በፊት የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅድ ወጥቶ እየተተገበረ ቢሆንም ብዙም ለውጥ አልታየበትም፡፡ ግብፅ 80 በመቶ ያህሉን መድኃኒት ለአገር ውስጥ እንደምታቀርብ ይህም ሁኔታ የራሱን ፍላጎት አሟልታ የኛን ገበያ እየተቀራመተች መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ለተዘረዘሩት ችግሮች እንደ መፍትሔ ሐሳብ አድርገው የጠቆሙት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መንቀሳቀስ፣ የአገር ውስጥ አቅርቦትን ማጠናከር፣ አቅርቦቱን ከፍላጎት በአግባቡ የመለየትና በመጠን ማስላት ተገቢ የሆነ የግዥ ሥርዓት መተግበር፣ ማዕከላዊ መጋዘን የገቡ መድኃኒቶች ተገቢ የሆነ የክምችት አስተዳደር እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፡፡ ወደ ተጠቃሚው መሰራጨትና በአግባቡ ጥቅም ላይ ሊወሉ ግድ ይላል፡፡ ይህም ዓይነት ዑደት ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ከአቶ ያሬድ ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ እስካሁን ድረስ የሚያቀርበው መድኃኒት በውል አይታወቅም ነበር፡፡ ሁሉም ሴክተር የተግባቡት የግዥ መዘርዘር አልነበረውም፡፡ ይህም ሆኖ ግን ከሁለት ወራት በፊት ኤጀንሲው የሚያቀርባቸውን ግብዓቶች በጤና ፕሮግራምና በመደበኛ ክምችት ገዝቶ የሚያቀርበውን መድኃኒት አዘጋጅቷል፡፡ ግዥውም የተከናወነው የአገሪቱን የጤና ችግሮች ማዕከል ባደረገ መልኩ ነው፡፡

ኤጀንሲውም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለአገር ውስጥ አምራቾች ለ103 ዓይነት መድኃኒቶች የግዥ ትዕዛዝ ቢሰጥም የአምራቾቹ አፈጻጸም ግን 45.1 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው ነገር ቢኖር 16 በመቶ ያህሉ መድኃኒቶች ጨርሶ እንዳልቀረቡ ነው፡፡ አገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶች ደግሞ ከአገሪቱ ጤና ችግሮች በተለይ ተላላፊ ለሆኑ በሽታዎች ማከሚያ የሚውሉ ናቸው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው በተለይ የውጭ ምንዛሪ ጋር ተያይዞ በዚህ ዓመት በተለየ መልኩ እክል እንደገጠማቸው ነው፡፡

አንድ መድኃኒት ወደ አገር ከመግባቱ በፊት ደኅንነት፣ ጥራቱና ፈዋሽነቱ ተረጋግጦ ዕውቅና ሊሰጠው ወይም የገበያ ፈቃድ ሊያገኝ እንደሚገባ በአዋጅ መደንገጉን የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን የመድኃኒት ምዝገባና ፈቃድ ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰብለ ሻምበል አስረድተዋል፡፡

‹‹ለዚህ ተግባራዊነት ሦስት ሒደቶች እንከተላለን፡፡ የመጀመርያው መድኃኒቱ በተመረተበት አገር የመልካም አመራር ዘዴ ሊኖር ይገባል፡፡ ሁለተኛው የሰነድ ግምገማ፣ ሦስተኛው የጥራት ፍተሻ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ የሰነድ ግምገማው በሁለት አግባብ ነው የሚታየው፡፡ ይህም ማለት በዓለም ስታንዳርድ ተቀባይነት ያገኙ ጠንካራ ተቆጣጣሪ አካላት ፈትሸው ዕውቅና የሰጡት ከሆነ ያንን ፈትሾ ዕውቅና መስጠት፣ አለበለዚያም መድኃኒቱ እንስሳት ላይ ከተሞከረበት ጀምሮ ሰው ላይ ተሞክሮ፣ የገበያ ሰርቬይለንስ ተሠርቶለት ገበያ ላይ እስከሚወጣበት ድረስ ያለውን የአመራረት ዘዴና ጥናት የሚያመለክት የሰነድ ግምገማ ሥራ ማከናወን ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ያነሰ ሕዝብ ያላቸው አገሮች በጣም ብዙ የተመዘገዙ መድኃኒቶች እንዳላቸው፣ ከዚህ አንፃር ለ90 ሚሊዮን ሕዝብ የሚሆንና በቂ የሆነ መድኃኒት በአስቸኳይ ወደ ገበያ ሊደርስ የሚችልበት የተለያዩ ስትራቴጂዎች ኤጀንሲው ሲያዘጋጅ እንደቆየ ተናግረዋል፡፡

ከነዚህም አንዱ ዓምና ተዘጋጅቶ ዘንድሮ ዕውቅና የተሰጠው ‹ማርኬት ስትራቴጂ አውቶራይዜሽን› ነው፡፡ ይህ ዓይነቱም አውቶራይዜሽን መድኃኒቶች የገበያ ፈቃድ አግኝተው ወደ ገበያ ለመግባት ያለውን ሒደት የሚያሳጥር ነው፡፡

የተመዘገቡ መድኃኒቶችን በአግባቡ መያዝ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ኤጀንሲው የሚሰጠው ወይም ቫሊዲቲ ዴቱ ለአራት ዓመት ነው፡፡ ይህንንም የተፋጠነ ለማድረግ ሜዲስን ረጂስትሬሽን ኢንፎርሜሽን ሲስተም በቅርቡ ተግባራዊ እንዲሆንና ይህም በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የመጀመርያ ዌብ ቤዝድ የሆነ የመድኃኒት ምዝገባ ሥርዓት መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ይህ ዓይነቱ የምዝገባ ሥርዓት አመልካች የትኛውም የምዝገባ ፍሰት ተከትሎና የገበያ ፈቃድ አግኝቶ የግዥ ትዕዛዝ ፈቃድ እስኪያገኝ ድረስ ያለውን ፍሰት በግልጽ ለማሳየት የሚችል ነው፡፡ እንደ ምክትል ዳይሬክተሯ ማብራሪያ ቶሎ ፈጣን የገበያ ፈቃድ በመስጠት ሒደት ላይ ችግሮች አጋጥመዋል፡፡ ከችግሮቹ መካከል አንደኛው ኤጀንሲው በመመርያ ላይ ያስቀመጠውን ወይም የዓለም ጤና ድርጅት፣ እንዲሁም ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያገኙ ዓለም አቀፍ ደረጃ ድርጅቶች ባስቀመጡት መሠረት ዶክመንቱ አለመቅረብ ነው፡፡

የሚቀርበው ሰነድ ደግሞ ቅደም ተከተሉ አግባብነት የጎደለውና መረጃ በሚገባ አለማግኘት ከችግሮቹ መካከል ተጠቃሾች መሆናቸውን ገልጸው፣ ይህም ሁኔታ የሰነድ ገምጋሚውን ጊዜ እንዲባክንና አመልካቹም ቶሎ የገበያ ፈቃድ አግኝቶ መድኃኒቶችን ወደ ገበያ የማውጣት ሒደት ላይ አላስፈላጊ መልሶችን እንደሚፈጥሩ ከምክትል ዳይሬክተሯ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...