Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅትና ስሜክ በዱከም የሚገነባውን የነዳጅ ዲፖ ዲዛይን ለመሥራት ስምምነት ተፈራረሙ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኩባንያዎች በጨረታው ውጤት ላይ ቅሬታ አቅርበዋል

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በዱከም ከተማ አቅራቢያ በከፍተኛ ወጪ ለመገንባት ያቀደውን ግዙፍ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዲፖ የዲዛይንና ፕሮጀክት ክትትል ሥራ ውል ስሜክ ኢንተርናሽናል ከተባለ የአውስትራሊያ ኩባንያ ጋር ተፈራረመ፡፡ ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማሪያምና የስሜክ ኢንተርናሽል የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቅሬ ከበደ ናቸው፡፡

      ስምምነቱ በኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት ሰኔ 13 ቀን ተፈርሟል፡፡

      የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት እያደገ የመጣውን የአገሪቱን የነዳጅ ፍላጎት ለማርካትና የመጠባበቂያ ነዳጅ ማጠራቀሚያ አቅም ለማሳደግ የሚያስችል ዘመናዊ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዲፖ፣ በዱከም ከተማ አቅራቢያ ለመገንባት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

      አቶ ታደሰ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ድርጅቱ የሚገነባው ዲፖ 240 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ የማጠራቀም አቅም ይኖረዋል፡፡

      አገሪቱ አሁን ያሏት 13 የነዳጅ ዲፖዎች በአጠቃላይ የማጠራቀም አቅማቸው 367 ሚሊዮን ሊትር ነው፡፡ ይህም የአገሪቱን የነዳጅ ፍጆታ ለ35 ቀናት ይሸፍናል፡፡ አዲስ የሚገነባው ግዙፍ ዲፖ ሲጠናቀቅ አገራዊ የማጠራቀም አገራዊ አቅም ወደ 607 ሚሊዮን ሊትር የሚያድግ በመሆኑ የ65 ቀናት ፍጆታ ይሸፍናል፡፡

      በዱከም የሚገነባው አዲሱ ዲፖ ዘመናዊ የነዳጅ መቀበያ፣ ማከማቻና ማሠራጫ ተርሚናል ሲኖረው ቤንዚን፣ ናፍጣና የአውሮፕላን ነዳጅ ይይዛል፡፡ ዲፖው ከአዲሱ የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መስመር አጠገብ የሚገነባ በመሆኑ በባቡር ተጓጉዞ የሚመጣ ነዳጅ የመቀበል አቅም እንደሚኖረው የገለጹት አቶ ታደሰ፣ ዘመናዊ የነዳጅ መቀበያና መሙያ መሣሪያዎችና የተሟላ ዘመናዊ የእሳት አደጋ መከላከያ መሠረተ ልማት እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡

      ዲፖው ሙሉ በሙሉ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተደገፉ እንደሚሆን ገልጸው፣ የአካባቢ ብክለት እንዳይኖር የሚከላከሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እንደሚጠቀም አስረድተዋል፡፡ ‹‹የነዳጅ ስርገት እንዳይኖር ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡ ለአካባቢ ደኅንነት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን እንሠራለን›› ብለዋል፡፡

        አዲስ የሚገነባው ዲፖ 12 ትልልቅ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ጋኖች ሲኖሩት፣ እያንዳንዳቸው 20 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ የመያዝ አቅም ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ 3.3 ቢሊዮን ብር ይገመታል፡፡

      የዚህን ግዙፍና ዘመናዊ ፕሮጀክት ዝርዝር የንድፍ፣ የፕሮጀክት አስተዳደር፣ የማማከርና የክትትል ሥራ የሚያከናውን በመስኩ ልምድ ያለው ኩባንያ ለመቅጠር፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በኅዳር 2010 ዓ.ም. ግልጽ ዓለም አቀፍ ጨረታ አውጥቷል፡፡ ከ30 በላይ ኩባንያዎች የጨረታ ሰነድ የገዙ ቢሆንም፣ ስድስት ኩባንያዎች ብቻ በጨረታው ተሳታፊ እንደነበሩ ታውቋል፡፡

      አይኤልኤፍ ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ ተቀማጭነቱ በአቡዳቢ የሆነ የጀርመን ኩባንያ፣ ሳጋ ግሎባል ኮሰልታንትስ የህንድ ኩባንያ፣ ስሜክ ኢንተርናሽናል የአውስትራሊያ ኩባንያ፣ ቻይና ፔትሮሊየም ሎንግዌይ ኢንጂነሪንግ ማኔጅመንት የቻይና ኩባንያ፣ ጓንግዶንግ ቢዩልዲንግ ዲዛይን ኢንስቲትዩት የቻይና ኩባንያ አስፓየር ኤኮም ከተባለ ኢትዮጵያዊ ኩባንያ ጋር በመጣመርና ኢኩም ግሩፕ የተባለ የፈረንሣይ ኩባንያ የቴክኒክና የፋይናንስ ዕቅዳቸውን አቅርበዋል፡፡

      የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የጨረታ ኮሚቴ ባካሄደው የቴክኒክ ግምገማ አይኤልኤፍና ስሜክ ኢንተርናሽናል ብቻ እንዳለፉ አቶ ታደሰ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ አይኤልኤፍ 10‚900‚000 ዶላር፣ ስሜክ ኢንተርናሽናል 7‚731‚350 ዶላርና 26‚024‚934.18 ብር በማቅረባቸው ስሜክ ኢንተርናሽናል አሸናፊ ሊሆን እንደቻለ ገልጸዋል፡፡ ስሜክ ኢንተርናሽናል ዝርዝር የንድፍ ሥራ ለመሥራት አሥር ወራት እንደሚወስድበት ተገልጿል፡፡ ኩባንያው ኢትዮጵያ ውስጥ በመንገድ ግንባታና በግብርና ሥራዎች እንደተሰማራ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የጨረታው ውጤት ከተገለጸ በኋላ በጨረታው ሒደት ላይ ሁለት ኩባንያዎች ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ በጨረታው ሁለተኛ የወጣው አይኤልኤፍ “ዝቅተኛ ዋጋ ያቀረብኩት እኔ በመሆኔ እንደምን ለስሜክ ሊሰጥ ቻለ?›› ሲል ጥያቄ አቅርቧል፡፡

      የኩባንያውን ቅሬታ አስመልክቶ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ አቶ ታደሰ በመጀመሪያ አይኤልኤፍ 10‚900‚000 ዶላር፣ ስሜክ 10‚538‚000 ዶላር እና 26 ሚሊዮን ብር ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ስሜክ ባቀረበው የፋይናንስ ዕቅድ ላይ የቀመር ስህተት በመገኘቱ እንዲስተካከል መደረጉን ተናግረዋል፡፡

      ‹‹ስህተቱን ለኩባንያው አሳውቀን በመስማማቱ እርማት ተደርጓል፤›› ያሉት አቶ ታደሰ፣ በነጠላ ዋጋና ብዛት ላይ ካልሆነ በቀር የቀመር ስህተት ማስተካከያ ለማድረግ የጨረታ ሕጉ የሚፈቅድ በመሆኑ እርምት እንደተደረገ ተናግረዋል፡፡

      ማስተካከያው ከተደረገ በኋላ ስሜክ ያቀረበው ዋጋ 7‚731‚350 ዶላርና ለአገር ውስጥ ወጪው ብር 26‚024‚934.18 ብር በመሆኑ የጨረታው አሸናፊ ሊሆን እንደቻለ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ይህንንም በዝርዝር ለአይኤልኤፍ አስረድተን ተቀብለውናል፤›› ብለዋል፡፡

      ሳጋ ግሎባል የተሰኘው የህንድ ኩባንያ በበኩሉ የቴክኒክ ግምገማውን እንዴት ሊወድቅ እንደቻለ ማብራሪያ ጠይቋል፡፡ በተጨማሪም አሸናፊው ኩባንያ ያቀረበው ዋጋ የተጋነነ እንደሆነ በመግለጽ፣ እሱ ከዚህ ባነሰ ዋጋ ሥራውን ሊያከናውን እንደሚችል አስታውቋል፡፡

አቶ ታደሰ ከሳጋ ግሎባል ለቀረበው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ኩባንያው የቴክኒክ ግምገማውን ያላለፈ በመሆኑ የፋይናንስ ዕቅዱ እንዳልተከፈተ ተናግረዋል፡፡  ሳጋ በቴክኒክ ግምገማው ያገኘው 66.31 ፐርሰንት ነው፡፡ የማለፊያ ነጥቡ 70 ፐርሰንት ነው ያሉት አቶ ታደሰ፣ ኩባንያው ዝቅተኛ ነጥብ ሊያገኝ የቻለው ለፕሮጀክት ሥራው የሚፈለገውን የሠለጠነ የሰው ኃይል ባለማቅረቡ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹እኛ የምንፈልገው ፕሮጀክት ኢንጂነርና ዲዛይን ኢንጂነር ነው፡፡ ኩባንያው ያቀረበው የባለሙያ ሲቪ እንደሚያሳየው ኬሚስት ነው፡፡ ፕሮሰስ ኢንጂነር በመሆኑ በነዳጅ ማጣሪያ ውስጥ ሊሠራ የሚችለው ኬሚካል ኢንጂነር ነው እንጂ፣ እኛ ለፈለግነው የንድፍና ክትትል ሥራ ጋር የሚጣጣም አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም ሳጋ ግሎባል የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ሊገነባ ካቀደው ግዙፍ የነዳጅ ተርሚናል ጋር የሚመጣጠን የፕሮጀክት ሥራ ልምድ እንደሌለው አስረድተዋል፡፡

      አሸናፊው ኩባንያ የሰጠው ዋጋ የተጋነነ ነው፣ ለሚለው ቅሬታ የቴክኒክ ግምገማን ያላለፈ ኩባንያ ስለዋጋ አቤቱታ ማቅረብ እንደማይችል ተናግረዋል፡፡ ‹‹ኩባንያዎች የሚያቀርቡት ዋጋ በአገራቸው ካለው የሰው ኃይልና ሌሎች ወጪዎች ጋር ተያይዞ ሊለያይ ይችላል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ሳጋ የቴክኒክ ምዘና የወደቀ በመሆኑ የፋይናንስ ዕቅዱን መክፈትም አንችልም፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ኩባንያዎችን ከማጫረቱ በፊት ከሌሎች ፕሮጀክት ወጪዎች ልምድ በመውሰድ፣ አንድ ፕሮጀክት ምን ያህል ሊፈጅ እንደሚችል የራሱን ግምት አስቀድሞ እንደሚያሰላ ጠቁመዋል፡፡

ሳጋ ግሎባል ላቀረበው ጥያቄ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በጽሑፉ ምላሽ ቢሰጠውም፣ በተሰጠው ማብራሪያ ባለመርካቱ ለድርጅቱ የዳይሬክተሮች ቦርድ አቤቱታውን አቅርቧል፡፡ ድርጅቱ በበኩሉ ስለአጠቃላይ የጨረታው ሒደትና ሳጋ ግሎባል በቴክኒክ ምዘናው እንዴት ሊወድቅ እንደቻለ በዝርዝር ለቦርዱ በጽሑፍ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ኩባንያው ዋጋን በተመለከተ ያቀረበው አቤቱታ ተገቢ እንዳልሆነም አብራርቷል፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የሰጠውን ማብራሪያ ቦርዱ አጥጋቢ ሆኖ እንዳገኘው፣ አንድ የቦርድ አባል ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡  

የጨረታው አሸናፊ ስሜክ ኢንተርናሽናል በመጪዎቹ አሥር ወራት የነዳጅ ተርሚናሉን ዝርዝር የኢንጂነሪንግ ዲዛይን እንደሚሠራ ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የነዳጅ ተርሚናሉን የሚገነባ ኮንትራክተር ለመቅጠር በቀጣይ ጨረታ እንደሚያወጣ ታውቋል፡፡ ጨረታው የሚወጣው አማካሪ ድርጅቱ የጨረታ ሰነድ አዘጋጅቶ ካቀረበ በኋላ እንደሚሆን አቶ ታደሰ አስረድተዋል፡፡ የነዳጅ ተርሚናሉ ግንባታ ሦስት ዓመት ተኩል ሊፈጅ እንደሚችል ተገምቷል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ነዳጅ ከዓለም አቀፍ ገበያ በመግዛት ለኩባንያዎች የሚያከፋፍል ብቸኛ መንግሥታዊ ድርጅት ነው፡፡ የአገሪቱ አጠቃላይ ዓመታዊ የነዳጅ ፍጆታ አሥር በመቶ እያደገ መጥቶ 3.8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የደረሰ ሲሆን፣ መንግሥት ለነዳጅ ግዥ በዓመት ሦስት ቢሊዮን ዶላር ወጪ ያደርጋል፡፡ ይህም 80 በመቶ የሚሆነውን የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ይወስዳል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በአዋሽ፣ በሐረር፣ በባህር ዳር፣ በሻሸመኔ፣ በመቀሌ፣ በአዲግራት፣ በጋምቤላ፣ በነቀምት፣ በአጋሮና በወላይታ 13 የነዳጅ ዲፖዎች አሉት፡፡ ከእነዚህም መካከል ትልቁ በአዋሽ የሚገኘው 130 ሚሊዮን ሊትር የሚይዘው ዲፖ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት አነስተኛ የነዳጅ ዲፖዎችን በራሱ አቅም ሲገነባ እንደኖረ የገለጹት አቶ ታደሰ፣ በቅርቡ በአዋሽ ዲፖ ማስፋፊያ ሙሉ በሙሉ በራሱ አቅም በማካሄድ 30 ሚሊዮን ሊትር የሚዝ ዲፖ በመገንባት 100 ሚሊዮን ሊትር የመያዝ አቅም የነበረውን የአዋሽ ዲፖ፣ ወደ 130 ሚሊዮን ሊትር ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ በዱከም ከሚገነባው የነዳጅ ተርሚናል የዲዛይንና የግንባታ ሥራ ልምድ በመቅሰም በቀጣይ ድርጅቱ አብዛኛውን የዲፖ ግንባታ በራሱ አቅም ለማካሄድ ጥረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ ስሜክ ኢንተርናሽናል ከንድፍ፣ ከማማከርና ከፕሮጀክት ክትትል ሥራ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት አቅም የመገንባት ሥራ እንደሚሠራ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች