የኦሮሚያ ክልል ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረ ሚካኤል፣ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በምክትል ዋና ዳይሬክተርነት የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ ሆነው ተሾሙ፡፡
ባለፈው ሳምንት የተሾሙት ምክትል ኮሚሽነር ደመላሽ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የማዕከላዊ መረጃና ወንጀል ኢንተለጀንስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የኦሮሚያ ክልል ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡
በዘርፉ በቂ ልምድና ችሎታ እንዳላቸው የሚነገርላቸው ተሿሚው፣ እስካሁን በሠሩባቸው የኃላፊነት ቦታዎች በብቃትና በታማኝነት የተወጡ መሆናቸውን በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፉት ሁለት ወራት ለከፍተኛ የመንግሥት ተቋማት ብቁና ይመጥናሉ ያሏቸውን አመራር በመሾም ላይ ናቸው፡፡ ምክትል ኮሚሽነር ደምላሽም በተመሳሳይ ሁኔታ ከዕውቀታቸውና ከሥራ ልምዳቸው ጋር የተገናኘ ኃላፊነት ላይ እንደመደቧቸው አስረድተዋል፡፡
ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሌላው ተሿሚ ደግሞ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጄኔራል ዳይሬክተር የነበሩት አቶ አሰፋ በዩ ሲሆኑ፣ በምን ዘርፍና ማዕረግ እንደተሾሙ ለማጣራት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡
አቶ አሰፋ በቅርቡ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጄኔራል ዳይሬክተርነት ተነስተው በአቶ ያሬድ ዘሪሁን ቢተኩም፣ አቶ ያሬድም ብዙም ሳይቆዩ በአቶ ዘይኑ ጀማል መተካታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡