Saturday, September 23, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የሠራ ይሞገስ ያጠፋ ይወቀስ!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አገር የመምራት ኃላፊነት በይፋ ከተረከቡበት ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ ሦስት ወራት ባልሞላው ቆይታቸው በአብዛኞቹ የአገሪቱ ክልሎች በመዘዋወር ባደረጓቸው ንግግሮች፣ ከአገሪቱ ሕዝብ ውስጥ ቂምና ቁርሾ እንዲጠፋ እስረኞችን በማስፈታት፣ ነፍጥ ያነገቡ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንዲመለሱ በወሰዱዋቸው ዕርምጃዎች፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለዓመታት የቆየው ጥላቻና መጠፋፋት ወደ ሰላም እንዲቀየር በጀመሩት ጥረትና እያስገኘ ባለው ውጤት፣ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ነፃነት እንዲሰማቸው ባደረጉት መነቃቃት፣ መላ የአገሪቱ ዜጎች በይቅርታና በፍቅር እንጂ በፀብ እንዳይፈላለጉ በሰጡት የማይታክት ማሳሰቢያ፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አገራቸው ገብተው በነፃነት እንዲሠሩ ጥሪ በማቅረባቸው፣ መንግሥት ሲፈጽማቸው የኖሩትን በደሎችና ሕገወጥ ተግባራት በአደባባይ በማጋለጣቸው፣ ወዘተ. የሕዝብ ፍቅርና አክብሮት አግኝተዋል፡፡ ከዚህ በፊት በፍፁም ሊታሰብ የማይችል ለውጥ በአገሪቱ በሰላማዊና በሠለጠነ መንገድ ዕውን እንዲሆን ላደረጉት አስተዋጽኦም፣ ሕዝብ በድጋፍ ሠልፍ ዕውቅና ሰጥቷቸዋል፡፡ ይህ ዕውቅናም የበለጠ እንዲሠሩና የሕዝብ ድጋፍ እንደማይለያቸው ማሳሰቢያ ሆኖ ይቆጠራል፡፡ የሠራ ሲሞገስ እጅግ በጣም ደስ ይላል፡፡ ጅምሩም በዚህ ይቀጥላል ተብሎ ተስፋ ይደረጋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ሥፍራዎች ተገኝተው ባደረጉዋቸው ንግግሮች አፅንኦት የሰጡት ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ እንደሚያስፈልጋት ነው፡፡ ይህ ምኞት ዕውን የሚሆነው ደግሞ ኢትዮጵያውያን ከበቀልና ከጥላቻ ነፃ ሆነው በአንድነት ሲቆሙ ወይም በእሳቸው አባባል ሲደመሩ ነው፡፡ ይህ አንድነት በብሔር፣ በእምነት፣ በባህል፣ በቋንቋ፣ በፖለቲካ አቋምና በመሳሰሉት ልዩነቶች ችግር እንዳይገጥመው በተደጋጋሚ አሳስበዋል፡፡ በተለይ በደቡብ ክልል በሐዋሳ፣ በወላይታና በወልቂጤ ከተሞች ከሕዝብ ጋር መሰንበቻውን ባደረጓቸው ውይይቶች ኢትዮጵያውያን የሚያምርባቸው በአንድነት ሲቆሙ እንጂ ተለያይተው ሲጠፉ እንዳልሆነ አስረግጠዋል፡፡ የአገር መሪ ሕዝቡን መስሎ መኖር የሚችለው ሕዝቡን በሚገባ ሲያውቀው ነው፡፡ ይህ ዕውቀት የተገኘው ደግሞ በሹማምንት በሚቀርብ ሪፖርት ሳይሆን፣ ከበፊት ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች ከሕዝብ ጋር በነበራቸው ጥልቅ ግንኙነት እንደሆነም አጠቃላዩ ሁኔታ ያስገነዝባል፡፡ ሕዝቡን በእዚህ ደረጃ የሚያውቅ መሪ ሲገኝ ‹‹ተመሥገን›› ማለት ብቻ ሳይሆን፣ ዕውቅና ሰጥቶ ማሞገስ ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለረዥም ዘመናት ያጣችው ይህንን ፀጋ ነው፡፡

የኢትዮጵያ አስተዋይና ጨዋ ሕዝብ እርስ በርሱ በሚያደርጋቸው መስተጋብሮች ጥሩ የሠራን ማሞገስ፣ ያጠፋን መገሰጽ፣ እንዲሁም በዳይና ተበዳይን መዳኘት ይችልበታል፡፡ ይህ አኩሪና ምሥጉን የጋራ እሴት እየተናደ፣ እንደ ሸቀጥ ከውጭ በገባ የራስ ያልሆነ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ስብከት ምክንያት በርካታ በደሎች ደርሰውበታል፡፡ የሩቁን ጊዜ ትተን የቅርቡን ለትውስታ ብናይ እንኳ ከዘመነ ቀይ ሽብር እስከ ድኅረ ምርጫ 97፣ በዜጎች ላይ የደረሱ ውርጅብኞች እጅግ በጣም ያሳዝናሉ፡፡ የገዛ ወገንን በአቋም ልዩነት ምክንያት ወህኒ መወርወር፣ መግረፍ፣ ማሰቃየት፣ መግደል፣ እንዲሁም ማሳደድ አሳዛኝ የታሪካችን ጠባሳዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ጠባሳዎች ለታሪክ መዛግብት ትቶ በእርቅና በፍቅር አዲስ ምዕራፍ እንጀምር የሚል መሪ ሲገኝ መታደል ነው፡፡ ይህ መሪ ግን በስሜታዊነት ሳይሆን በምክንያታዊነት ሊደገፍ ይገባል፡፡ ሰው ሥራውን ሲያከናውን በአንዴ ሁሉንም ማስደሰት እንደማይችልና የሚሠራ ደግሞ ስህተት ሊፈጥር እንደሚችልም መረዳት ያስፈልጋል፡፡ እንደ አየሩ ፀባይ በመለዋወጥ ግራ መጋባት ውስጥ መግባት አያስፈልግም፡፡ ይልቁንም ለአገር ሰላምና ለብሔራዊ ደኅንነት ሲባል ኢትዮጵያውያን በጋራ በመቆም ለውጡ ፍሬ እንዲያፈራ መተባበር አለባቸው፡፡

የአገር ህልውና ለድርድር መቅረብ እንደሌለበት ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ይህንን ከልብ በማመን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጤናማ የሆነ ግንኙነት እንዲኖረው፣ በተቻለ መጠን ሴራ በመጎንጎን ለአገር ከማይበጅ ድርጊት ውስጥ መውጣት ተገቢ ነው፡፡ ሕዝብ ውስጥ በመሹለክለክ ግጭት መቀስቀስ፣ ጥርጣሬና መፈራራት መፍጠር፣ ጊዜ ባለፈበት የማታለያ ሥልት ሕዝብን ለማደናገር መሞከርና ለሕዝብ የሚበጁ ተግባራትን ማጣጣል ተቀባይነት የላቸውም፡፡ በዚህ ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉ ማንም ይሁኑ ማንም ሊወቀሱና ሊወገዙ ይገባል፡፡ ለሕዝብ አሳቢ መስሎ እንደ ቀበሮ ባህታዊ በማደናገር ሰላምና መረጋጋትን ማደፍረስም ወንጀል ነው፡፡ በተለይ አገርንና ሕዝብን ማዕከል ያላደረገ አጀንዳ ያላቸው ወገኖች በጥብቅ ሊያስቡበት የሚገባው፣ ሕዝብ የአገሪቱ ሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት ብቻ ሳይሆን ማን ምን እያደረገ እንደሚገኝ አብጠርጥሮ የሚያውቅ ተፈጥሮ የዕውቀት ፀጋን የቸረችው እንደሆነ ነው፡፡ ሥልጣንና የሚገኙ ጥቅማ ጥቅሞችን ብቻ በማሰብ ሕዝብ ላይ መፈናጠጥ እንደማይቻል የወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ ከበቂ በላይ ያስረዳል፡፡ በዚህ ዓይነቱ የተንጋደደ መስመር የሚመሩ ኃይሎች ከባድ ወቀሳና ተጠያቂነት ጭምር እንዳለባቸው ይገንዘቡ፡፡

ኢትዮጵያውያን ከምንም ነገር በላይ ሊያሳስባቸው የሚገባው፣ በመታየት ላይ ያለው ለውጥ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲቀጥል ምን ይደረግ የሚለው መሆን አለበት፡፡ በመጀመርያ ደረጃ የሚሠሩ ሰዎች ሲመሠገኑና የበለጠ እንዲተጉ ሲበረታቱ፣ በተቻለ መጠን ለውጡን ማስቀጠል የሚችሉ ተቋማት ተጠናክረው እንዲወጡ ማሰብ የግድ ይሆናል፡፡ ለውጡ ፍሬ እንዲያፈራ ከተፈለገ ዓላማና ግብ ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንን ዓላማና ግብ የሚያሳኩ ጠንካራ ተቋማት ሲኖሩ፣ ለውጡ ግለሰቦች ትከሻ ላይ ብቻ አይንጠለጠልም፡፡ ለውጡ ተቋማዊ እየሆነ ሲሄድ አንድ መሪ ጊዜውን ጨርሶ ሲሸኝ ሌላ መሪ በከፍተኛ ዝግጅትና ልምድ ያስቀጥለዋል፡፡ አቶ እከሌ ወይም ወይዘሮ እከሊት ስላሉ ተብሎ የሚተው ጉዳይ ሳይሆን የመንግሥት ተቋማት፣ ዴሞክራቲክ ተቋማት፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ የሙያ ማኅበራት፣ ወዘተ. በነፃነትና በገልተኝነት ተደራጅተው በሕግ የበላይነት ብቻ የሚሠሩበት ሲስተም መዘርጋት አለበት፡፡ ይህ ሳይሆን ሲቀር የተወደሰ ግለሰብ መልሶ ለወቀሳ ይዳረጋል፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ ሕግ አውጭው አካል፣ አስፈጻሚውና ተርጓሚው እርስ በርስ ቁጥጥር እያደረጉና እየተናበቡ የሚሠሩበት ጠንካራ አሠራር መፈጠር ይኖርበታል፡፡ ይህ ተግባራዊ ሲደረግ ሥልጣን መረን ስለማይለቀቅ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት በተግባር ይረጋገጣል፡፡ እስከ ዛሬ የነበረው አሠራር ለከፍተኛ ወቀሳና ትችት የተዳረገው ተጠያቂነት የሌለበት አሠራር በመስፈኑ ነው፡፡

ኢትዮጵያ አገራችን መልካም አጋጣሚዎች እጇ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በዚህች ታሪካዊት አገር ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከመገንባት ታልፎ ምሥራቅ አፍሪካን ከጦርነት፣ ከድህነትና ከኋላቀርነት ማላቀቅ የሚያስችል ታላቅ ዕምቅ ኃይል አለ፡፡ ኢትዮጵያውያን ሲከባበሩ፣ ሲፈላለጉና ለአገራቸው ዕድገትና ብልፅግና አንድ ላይ መቆም ሲችሉ ተዓምር መፍጠር እንደሚቻላቸው፣ ታላቁ ፀረ ቅኝ አገዛዝ የዓድዋ ድል ምስክር ነው፡፡ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ህያው ተምሳሌት የሆነውን ታሪካዊውን የዓድዋ ድል በጀግኖች ልጆቿ መስዋዕትነት ያረጋገጠች አገር፣ በዚህ ዘመን ልጆቿ አንድ ላይ ቢቆሙ ምን ይቸግራቸዋል? ኢትዮጵያውያን አንድ ላይ ሲቆሙ እንዲህ ዓይነቱን አንፀባራቂ ድል በዚህ ዘመን ማስመዝገብ እንደሚችሉ ማንስ ይጠራጠራል? ስለዚህ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ጥላቻን፣ ቂምን፣ በቀልን፣ ሴራንና አሻጥርን በማስወገድ ለዚህ ለተከበረ አስተዋይ ሕዝብና ለታሪካዊቷ አገራቸው ህልውና ሲሉ በአንድነት ይቁሙ፡፡ እርስ በርስ በወሰንና በመሳሰሉ ጉዳዮች መናከስና መባላት ለድህነትና ለኋላቀርነት ከመዳረግ ውጪ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ለውጡ ዕውን የሚሆነው ደግሞ እያጠፉ በሚፀፀቱና በሚወቀሱ ሰዎች ሳይሆን፣ ሕዝብ ከልቡ በሚያመሠግናቸው ብቻ ነው፡፡ የሠራ ይሞገስ ያጠፋ ይወቀስ! ኢትዮጵያ ወደፊት የምትራመደው በዚህ መንገድ ብቻ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...

በሰጥቶ መቀበል መርህ መደራደርና ሰላም ማስፈን ለምን ያቅታል?

በያሲን ባህሩ አገር ግንባታ የትውልድን ትልቅና ታሪካዊ ኃላፊነት የሚጠይቅ ተግባር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...

ለሕዝብና ለአገር ክብር የማይመጥኑ ድርጊቶች ገለል ይደረጉ!

የአዲሱ ዓመት ጉዞ በቀናት ዕርምጃ ሲጀመር የሕዝብና የአገር ጉዳይን በየቀኑ ማስታወስ ግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ልማትና ዕድገት ያስፈልጋሉ ከሚባሉ ግብዓቶች...