የኢትዮጵያ መንግሥት ለከተሞችና ለጂኦተርማል ልማት ኃይል 18 ሚሊዮን ዩሮ (569.6 ሚሊዮን ብር) ዕርዳታ አገኘ፡፡ ዕርዳታው የተገኘው ከፈረንሣይ መንግሥት አሥር ሚሊዮን ዶላር፣ ከአውሮፓ ኅብረት ስምንት ሚሊዮን ዩሮ በአጠቃላይ 18 ሚሊዮን ዩሮ ነው፡፡
በአሥር ሚሊዮን ዩሮ ከዚህ ቀደም በዓለም ባንክ ድጋፍ ሲካሄድ ለቆየው የከተሞች አቅም ግንባታ ፕሮጀክት ማጠናከሪያ የሚውል ነው ተብሏል፡፡ ቀሪው ስምንት ሚሊዮን ዩሮ ደግሞ በአፋር ክልል ተንዳሆ አካባቢ ለሚካሄደው የጂኦተርማል ኃይል ፕሮጀክት ድጋፍ የሚውል መሆኑ ተገልጿል፡፡
ሐሙስ ሰኔ 14 ቀን 2010 ዓ.ም. የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ አበበ፣ ከኢትዮጵያ የፈረንሣይ አምባሳደር ሚስተር ፍሬድሪክ ቦንታምስ የዕርዳታ ስምምነቱን ተፈራርመዋል፡፡
ለከተሞች ልማት የሚውለው ገንዘብ ቀደም ሲል በ44 ሁለተኛ ከተሞች የተጀመረው የፋይናንስ፣ የግዥ፣ የአካባቢና የማኅበራዊ ጉዳዮች ኦዲት የማድረግ ብቃት ነው፡፡ አንድ ከተማን ከተማ የሚያሰኙ ጉዳዮችን እንዲያሟላ ለማድረግ የተጀመረውን ሥራ በማሳደግ፣ 73 ተጨማሪ በማካተት በአጠቃላይ በ117 ከተሞች ይህንኑ ሥራ ለማካሄድ ነው፡፡
ይህን ሥራ ለማከናወን የዓለም ባንክ ከፍተኛ ገንዘብ የመደበ ሲሆን፣ የፈረንሣይ መንግሥት በፈረንሣይ ልማት ድርጅት በኩል አሥር ሚሊዮን ዩሮ ሰጥቷል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት በፈረንሣይ ልማት ድርጅት እንዲተዳደር የሰጠው ስምንት ሚሊዮን ዩሮ ጥልቀታቸው 2‚500 ሜትር የሆኑ የጂኦተርማል ኃይል ማመንጫ ጉድጓዶችን ለመቆፈርና ተጨማሪ የጂኦተርማል ኃይል ፍለጋ ለማካሄድ ይውላል ተብሏል፡፡
አቶ አድማሱ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ እያመራች ስለሆነ ይህ ድጋፍም ይህንን ሽግግር ለማሳካት ትልቅ ድርሻ አለው፡፡
‹‹የተሰጠው ገንዘብ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለታለመለት ዓላማ ይውላል፤›› ሲሉ አቶ አድማሱ በሥነ ሥርዓቱ ላይ አብራርተዋል፡፡