Tuesday, December 6, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤቱታ አቀረቡ

  የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤቱታ አቀረቡ

  ቀን:

  ጥያቄያቸው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ምላሽ ካላገኘ ከሥራ እንደሚለቁ አስታውቀዋል

  የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች ለረዥም ዓመታት ሲያገኙዋቸው የነበሩ የሙያ ዕውቅና፣ የደመወዝና የተለያዩ የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች ምላሽ ያገኙ ዘንድ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የአቤቱታ ደብዳቤ አስገቡ፡፡ ጥያቄያቸው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ምላሽ ካላገኘ ከሥራቸው እንደሚለቁ አስጠንቅቀዋል፡፡

  በአገሪቱ ከሚገኙ ከ120 እስከ 125 ከሚሆኑ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች 118 የሚሆኑት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ ‹‹ላለፉት ስምንት ዓመታት ከቀድሞው የትራንስፖርት ሚኒስትር አቶ ጁነዲን ሳዶ ጀምሮ የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ብናቀርብም፣ ምንም ዓይነት አጥጋቢ ምላሽ አላገኘንም፡፡ በቅርብ ጊዜያት ደግሞ የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. በወቅቱ የትራንስፖርት ሚኒስትር ለነበሩት አቶ አህመድ ሺዴ፣ በመቀጠልም በቅርቡ በእርስዎ ለተሾሙት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ግንቦት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ጥያቄ ብናቀርብም፣ ምንም ዓይነት ምላሽ አላገኘንም፤›› በማለት፣ በርካታ ዓመታት የወሰደውን ጥያቄያቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲፈቱላቸው አቤት ብለዋል፡፡

  ‹‹አንድ አውሮፕላን አብራሪ ካፒቴን በበረራ ላይ ሲሆን በአውሮፕላኑ ውስጥ ላሉ ሰዎች ሕይወት ኃላፊነት የሚወስድ ሲሆን፣ አንድ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ግን በአንድ ጊዜ በአማካይ አሥርና ከዚያ በላይ የሆኑ አውሮፕላኖችንና በውስጣቸው ያሉ ሰዎችን ሕይወት፣ የአገር ሀብትና የአገርን አየር ክልል ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ወስዶ በከፍተኛ ትጋት የሥራውን ጫናና ውጥረት ተቋቁሞ የሚሠራ፣ እንዲሁም ከባድ ኃላፊነት የሚሸከም ሙያተኛ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፤›› ሲሉ ሠራተኞቹ ምን ዓይነት ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

  ‹‹ምንም እንኳን እንዲህ ዓይነት ውጥረት በበዛበት የሥራ ከባቢ ውስጥ ብንኖርም፣ የሚከፈለን ክፍያ ግን ከደረጃው በታች ነው፤›› በማለት የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ጥያቄያቸው በአፋጣኝና መፍትሔ እንዲያገኝ አቤቱታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበዋል፡፡

  አቤቱታ አቅራቢዎቹ ባለሙያዎች፣ ‹‹የአየር ትራንስፖርት ዕድገት ፈጣን በሆነበት፣ በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድና ሌሎች አየር መንገዶች ከዕለት ዕለት ለውጣቸው በፍጥነት እየጨመረ ባለበት ሁኔታ፣ ይህንን ፈጣን ለውጥ ታሳቢ በማድረግ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ዕድገቱ ከሚያመጣው ጫና ጋር የተገናዘበ ምንም ዓይነት ጥቅም ባለማግኘታችን፣ ይህን ጫና መቋቋም የማንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፤›› ሲሉም እየደረሰባቸው ባለው የሥራ ጫና የማይመጥን ክፍያና ጥቅማ ጥቅም መፍትሔ እንዲሰጣቸው አሳስበዋል፡፡

  በመሆኑም ለሚከተሉት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ቢያንስ አንድ ሺሕ ፐርሰንት የደመወዝ ጭማሪ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሙያው የሚገባውን ጥቅማ ጥቅም ለምሳሌ የውጥረት አበል (Stress Allowance) የሙያ ፈቃድና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ያለምንም መሸራረፍ እንዲፈጸሙላቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

  ‹‹ለረዥም ዓመታት ተገቢ ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎቻችን ትኩረት ተሰጥቷቸው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንዲመለሱልን እየጠየቅን፣ ጥያቄዎቻችን ምላሽ የማያገኙ ከሆነ ለሚፈጠሩት ችግሮች ኃላፊነት የማንወስድና የምንወደውን ሥራችንን በገዛ ፈቃዳችን ለመልቀቅ የምንገደድ መሆኑን አናሳውቃለን፤›› ሲሉም ጥያቄያቸውን አጠቃለዋል፡፡

  ሚያዝያ 9 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንና በአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች መካከል ተፈጥሮ በነበረው አለመግባባት ሳቢያ፣ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡም ሆነ ከአገር የሚወጡ ሁሉም በረራዎች ለሁለት ሰዓታት ያህል በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ተቋርጠው እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...