Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ስፖርትበነበር እና በንትርክ የዘለቀው የኢትዮጵያ እግር ኳስ በቀጣይስ?

  በነበር እና በንትርክ የዘለቀው የኢትዮጵያ እግር ኳስ በቀጣይስ?

  ቀን:

  የኢትዮጵያ እግር ኳስ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከአመራር ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ትችትና ወቀሳ እያስተናገደ ይገኛል፡፡ ተቋሙ ከሙያው ጋር ምንም ዓይነት ዕውቀትም ሆነ ትውውቅ በሌላቸው፣ ተቋሙ ከጡረታ መልስ በሚሰባሰቡ አመራሮችና ሙያተኞች ስለሚተዳደር እግር ኳሱ የሚፈልገው የአሠራር ሥርዓት ከወቅቱና ጊዜው ጋር መጣጣም ተስኖት ሁሌም ዘልማዳዊ በሆኑ ነገሮች ተተብትቦ ዕድሜውን ብቻ እንዲቆጥር ምክንያት ሆኖት ስለመገኘቱም የሚናገሩ አሉ፡፡ በየአራት ዓመቱ የሚቀያየሩ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አመራሮች ለምርጫ የሚጠቀሙባቸው ስትራቴጂካዊ ዕቅዶች ሥልጣኑን በተረከቡ ማግሥት ወደ ሸልፍ የሚወረወሩበት አጋጣሚ እየበዛ እግር ኳሱ ሀብት ከማመንጨት ይልቅ አሁን አሁን ለሰዎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር እንቅፋት በመሆን ላይ ይገኛል፡፡ ለከፍተኛ የሰውና ንብረት ውድመት ምክንያት እየሆነ መምጣቱ ይታመናል፡፡ በቅርቡ ከወራት ንትርክና ውዝግብ በኋላ የፈዴሬሽኑን የአመራርነት ኃላፊነት የተረከበው ካቢኔ አባል የሆኑት አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ተቋሙን ለሁለተኛ ጊዜ ለመምራት ከተመረጡት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ እንደ አቶ ዮሴፍ ፌዴሬሽኑ ከእንግዲህ ቀደም ሲል በነበረበት ዓይነት አካሄድ ሊቀጥል አይገባውም፡፡ በተቻለ መጠን  ወቅቱና ጊዜው ወደ ሚጠይቀው የአሠራር ሥርዓት መግባት እንደሚኖርበት ያምናሉ፡፡ ግን እንዴት? በእነዚህና በሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ደረጀ ጠገናው ከአቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

  ሪፖርተር፡- ፌዴሬሽኑን ለሁለተኛ ጊዜ ለመምራት ከተመረጡት  መካከል እርስዎ አንዱ ነዎት፡፡ በመሆኑም በቀጣዩ አራት ዓመትም ምንም አዲስ ነገር እንደማይኖር የሚናገሩ አሉ፣ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?

  አቶ ዮሴፍ፡- ቀደም ሲል የነበረው አመራር በነበረው የአገልግሎት ዘመን አቅዶት የነበረውን ስትራቴጂካዊ ዕቅድ በተወሰነ መልኩ ያሳካው አለ፣ ያላሳካውም አለ፡፡ ከዚህ አኳያ ባለፉት አምስት የአገልግሎት ዓመታት የነበረኝን ልምድ በመጠቀም ለቀጣዩ ዓመታት የተሻለ ነገር ለመሥራት ተሞክሮው ይጠቅመኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ እንደ ተባለው ከቀድሞ በአዲሱ አመራር ውስጥ የተካተትን አለን፡፡ ይህ ማለት ግን የነበረው አሠራር በነበረው መልኩ ይቀጥላል ማለት እንዳልሆነ ሊወሰድ ይገባል፡፡ የቀድሞ በአንድም ሆነ በሌላ የራሱ የሆነ ደካማና ጠንካራ ጎን ቢኖረውም አሁን የተዘጋ ፋይል ሆኗል፡፡ አሁን የሚያስፈልገው አዲስ አስተሳሰብና አዲስ ሥራ ነው፡፡ እንደሚታወቀው እግር ኳሱ ብዙ ይፈልጋል፣ ለዚህ የሚመጥን ከአደረጃጀት ጀምሮ ጠንካራ የሆነ አቅም እንደሚጠይቅ የሚያከራክር አይደለም፡፡ በእርግጥም ይህን ተፈጻሚ ማድረግ የግድም ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አሁን ያለው አመራር አንድ ሆኖ መሥራት ይጠበቅበታል ካልሆነ ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም እግር ኳሱ የክልልና የክለብ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት ጫፍ  ደርሷል፡፡ ይህንን መሸከም የሚችል አደረጃጀት መፍጠር የዚህ አመራር ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው፡፡ በእርግጥም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ እስካሁን በስፋት ባንነጋገርም በተወሰነ መልኩ ግን ለነገ ብለን የማናልፈው ከባድ ሥራና ኃላፊነት እንደሚጠብቀን መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡

  ሪፖርተር፡- ኃላፊነትን ከተረከባችሁ ከቀናትም ወደ ወር ተሸጋግራችኋል፣ እስካሁን ስንት ጊዜ ተገናኝታችሁ ተወያይታችኋል?

  አቶ ዮሴፍ፡- አንድ ጊዜ ተገናኝተን ተወይተናል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እኛ ወደ እዚህ ኃላፊነት የመጣንበት ወቅት ውድድሮች ሊጠናቀቁ ከባድ ትንቅንቅ ብቻ ሳይሆን እስካሁን ዋንጫ የሚወስደው ቡድን በውል ያልታወቀበት፣ ወራጁ ያልተለየበት በመሆኑ ያንን ከአሉባልታና ሁካታ በፀዳ መልኩ ማከናወን ስላለብን ትኩረት አድርገን ተነጋግረንበታል፡፡ በተለይ ምስጋና የማይገኝለት የዳኝነት ጉዳይ፣ እኛም እንደ አመራር የምናውቃቸው ችግሮች ስላሉ ከዚህ በፊት ከነበረው ለየት ባለ መልኩ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ እንዳለብን መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡ ከዚህ ባለፈ ውድድሮች ወደ ክረምት እንዳይገቡ በተቻለ መጠን ፈጥነው እንዲጠናቀቁ ማድረግ እንዳለብንም ተነጋግረናል፡፡ ሌላው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንደሚታወቀው አሠልጣኝ የለውም፡፡ ከዳኝነትና ከውድድር ሥርዓቱ ባልተናነሰ ሁለተኛ አጀንዳ አድርገን ተነጋግረንበታል፡፡ ምክንያቱም ከአንድ ዓመት በኋላ ኢትዮጵያ የአፍሪካ አገሮች ብሔራዊ ቡድኖች ዋንጫ (ቻን) እንድታስተናግድ ዕድሉን አግኝታለች፣ ኢትዮጵያ ከመስተንግዶ ባለፈ ጠንካራና ተፎካካሪ ቡድንም ማዘጋጀት ይጠበቅባታል፡፡ ለዚህ ደግሞ በቂ ዝግጅት ማድረግ ስለሚያስፈልግ በቀናት ጊዜ ውስጥ የዋና አሠልጣኝ ምርጫና ቅጥር ይፈጸማል፡፡

  ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ይህንን ዝግጅት ለማስተናገድ አራት አሠርታትን ጠብቃለች፣ እንደሚታወቀው በተለይ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከመቸውም ጊዜ በባሰ ወቅታዊ አቋሙ ወርዷል፡፡ ከኢንተርናሽናልና አኅጉራዊ ውድድሮች ለወራት ያህል መራቁና ያለፈው አመራር ለጉዳዩ ትኩረት ሳይሰጥ መቆየቱ እንደሆነ በዋናነት የሚናገሩ አሉ፣ ቡድኑ አሰልጣኝ ከሌላቸው ጥቂት አገሮች አንዱ ስለመሆኑ፣ ለዚህም ቢሆን አሁንም በዋናነት ተጠያቂው የቀድሞ አመራር መሆኑ ይነገራል፡፡ ከዚህም በላይ ተቋሙ ጠንካራ የቴክኒክ ዲፓርትመንትና ዳይሬክተር የለውም፣ ምን ይላሉ? 

  አቶ ዮሴፍ፡- ለዚህ የቀድሞ ጥፋት ተደርጎ ሊወሰድ ከሆነ በግሌ መቀበል ክፋት ያለው አይመስለኝም፡፡ ይሁንና አሁንም እነዚህ ጉዳዮች በአጭር ጊዜ ውስጥ እልባት ሊያገኙ የሚገባቸው እንደሆኑ እወስዳለሁ፣ ተነጋግረንበታልም፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ እኛ ስለፈለግን የምናረዝመውና የምናሳጥረው ሳይሆን ግዴታም ስለሆነ  ነው፡፡ እዚህ ላይ በዋናነት ሊወሰድ የሚገባው ኢትዮጵያ የቻንን ዝግጅት ስትቀበል ከመስተንግዶ ባለፈ የፉክክሩ አካል መሆን ይጠበቅባታል፡፡ ለዚህም ነው ዝግጅቱ ከወዲሁ መጀመር ይኖርበታል የምንለው፡፡ የቴክኒክ ዲፓርትመንትና የቴክኒክ ዳይሬክተር ስለሚባለው አመራሩን ጨምሮ ፍላጎታችን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከሆነ የውድቀቱም ሆነ የዕድገቱ መሠረት ይህ  ክፍል ነው፡፡ ዲፓርትመንቱ በሌለበት ውጤቱን እያየነው ነው፡፡ ከዚህ በላይ ማሳያ የሚያስፈልግም አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም ከተቋሙ ሁለንተናዊ ዝግጅት ባልተናነሰ የዲፓርትመንቱንና የዳይሬክተሩን ጉዳይ መፈተሽና ማስተካከል እንዳለብን ይሰማኛል፣ ግዴታም ነው ብዬ እወስዳለሁ፡፡ ከዚህ አኳያ የአገር ውስጡን አቅም አሟጠን መጠቀም ይኖርብናል፣ እንዳስፈላጊነቱ ከውጭም ቢሆን ለዚህ ዲፓርትመንት ማድረግ ያለብንን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ ምክንያቱም አሁን የእገሌና የእገሌ ብለን የምናልፈው ጉዳይ ሳይሆን ጉዳዩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ጉዳይ ነው ተብሎ ሊወሰድ ይገባል፡፡ በፌዴሬሽኑ ሥር ነቀል ለውጥ መምጣት ካለበት እዚህ ክፍል ላይ ሊሆን ይገባል፡፡ መዋቅሩ ጭምር መጠናከር ይኖርበታል የሚል አቋም ነው ያለኝ፡፡ በፌዴሬሽኑ ያሉት ሌሎችም ዲፓርትመንቶች መፈተሸና መስተካከል ያለባቸው ናቸው፡፡ በፌዴሬሽኑ ለወራት የዘለቀው በተለይ ከምርጫ ጋር ተያይዞ ሲደመጥ የነበረው ጉዳይ ተዘግቷል፣ መጠየቅም ካለብን ወስደን እግር ኳሱን መካስ እንዳለብን ይሰማኛል፣ ካልቻልን የግድ አራት ዓመት  ጠብቁን የምንልበት አሠራር ሊኖር አይገባም፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን አጠናክረን ክፍተቶችን በማረም ተቋሙንና ኅብረተሰቡን የሚመጥን ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የቻንን ዝግጅት እንደ ጥሩ አጋጣሚ ወስደን አቅማችንን ማሳየት እንዳለብን ይሰማኛል፡፡

  ሪፖርተር፡- የክለቦችና የተጨዋቾች የጥራት ጉዳይስ እንዴት ይታያል?

  አቶ ዮሴፍ፡- ጥያቄውን በበቂ ሁኔታ ለመመለስ በቂ ጥናት እንደሚያስፈልግ ባምንም፣ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት የተጨዋች ጥራት ያን ያህል ችግር ይሆናል ብዬ አልወስድም፡፡ ምክንያቱም ተጨዋቾቻችንን በተገቢው አቅምና ሰብዕና ከተጠቀምንባቸው አቅሙም ብቃቱም ያላቸው ወጣት ተጨዋቾች አሉን፣ ይሁንና ፌዴሬሽኑ አሁንም ቢሆን ማድረግ ይኖርበታል ብዬ የማስበውና ማድረግም ያለበት፣ ለዚህ የሚመጥን ጠንካራ ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ማቋቋም እንዳለበት ነው፡፡ ይህ ኮሚቴ ለቀጣዩ የቻን ዋንጫ ይዘናቸው የምንቀርበው ምን ዓይነት ተጨዋቾችን ነው? የመምረጫ መስፈርታችንስ መሆን ያለበት እንዴትና በምን መልኩ ነው? የሚለውን አሳማኝ ትንታኔ ሊሰጥ የሚችል አካል መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ይህንኑ መሠረት አድርገን መሄድ ከቻልን የሚባለው የጥራት ጉዳይ ችግር ሊሆንብን እንደማይችል ይሰማኛል፡፡ ከዚህ ውጪ እንደ ዮሴፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ተጨዋች አለ ወይ ብለህ ብጠይቀኝ አለ፤ ነገር ግን ሊታረም የሚገባው በቀድሞ አመራር በነበርኩበት ጊዜ በአንድ የውድድር ዓመት ብቻ ሁለትና ሦስት አሠልጣኞችን ቀያይረን ተመልክተናል፣ በእኔ እምነት ይኼ ዓይነቱ አሠራር መቀጠል እንደሌለበት ነው፡፡ ለብሔራዊ ቡድኑም ሆነ አሠልጣኙ ጊዜ ተሰጥቷቸው ኅብረተሰቡ ሊተቻቸው ይገባል እንጅ በስሜት እየተነሳን አንተ ውጣ አንተ ግባ የምንልበት ሁኔታ መቅረት እንዳለበት አምናለሁ፡፡

  ሪፖርተር፡- ሊጉ ከፌዴሬሽኑ መውጣት አለበት የሚለው ጥያቄ ቀደም ብሎ የተጀመረ ቢሆንም፣ ነገር ግን እስከ አሁን ተፈጻሚ አልተደረገም፣ አንዳንድ ክለቦች ችግሩ የፌዴሬሽኑ እንደሆነ ሲገልጹ፣ በሌላ ወገን ያሉ ደግሞ ክለቦቹ ያሉበት ተክለ ቁመና ሊጉን ለመምራት የሚያስችለቸው አይደለም ሲሉ የሚደመጡ አሉ፣ በእርስዎ ለእግር ኳሱ የሚበጀው የቱ ነው ብለው ያምናሉ?

  አቶ ዮሴፍ፡- ሊግ መቋቋም አለበት የለበትም ከሚለው ክርክር በፊት መታየት ያለበት የሚመስለኝ፣ የፌዴሬሽኑና የክለቦች መዋቅራዊ ይዘት ምን ይመስላል? እንዲቋቋም የምንሻው ሊግስ በቅድመ ሁኔታነት ምን ይፈልጋል? የሚለውን ብንመለከት የተሻለ እንደሚሆን ይሰማኛል፡፡ ጥናት ይፈልጋል፣ ሊግ ብንመሠርት እንደ ክለብና እንደ አገር ጥቅምና ጉዳቱ ምንድነው? ብለን መነጋገርና መተማመን ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡ ለሁሉም ባለ ድርሻ  ሰፋ ያለ መድረክ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ከግለሰቦች ፍላጎት በፊት እግር ኳሱን መነሻ ያደረገ የአገር ፍላጎትን አስቀድሞ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ባረጀ አስተሳሰብ መቀጠል የለብንም፣ የሚጠቅመውን መርጠን መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡ እንኳን እግር ኳስ አይደለም የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ አካሄድ እየተቀየረ ነው፡፡ ለውጡን ፈጥነን መቀላቀል ካልቻልን እንቸገራለን፡፡ መንግሥት ስፖርቱን ጨምሮ ወደ አዲስ ምዕራፍ መግባት እንደሚያስፈልግ አቅጣጫ እየሰጠና እያስቀመጠ ነው፡፡ እግር ኳሱ ሰላማዊ መልክ ይዞ በተለይም ከክልልና ጎጥ አስተሳሰብ ወጥተን መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል፡፡ እስካሁን የተጓዝንበት መንገድ አላዋጣንም፣ እግር ኳሳችንን ክፉኛ እየጎዳው ነው፡፡ ለኢትዮጵያ አግር ኳስ ይጠቅማል ተብሎ ከታመነበት የውድድር ይዘቱ ጭምር የማይፈተሽበት ምክንያት መኖር የለበትም፡፡ በግሌ ሊጉ አሁን ከሚመራበት ይልቅ ንግድ ተኮር እንዲሆን ነው፡፡ ያለው የሊግ ውድድር ክለቦች በጀት በጅተው በውድድር ዓመቱ በጀቱ መጠናቀቅ እንዳለበት ነው፡፡ ከዚህ አስተሳሰብ መውጣት ያስፈልጋል፡፡ እኛም እንደ ፌዴሬሽን 20 እና 30 ሚሊዮን ብር ለሚበጅት ክለብ በዓመቱ መጨረሻ ፈጽሞ ሊመጣጠን የማይችል የሜዳ ገቢና መሰል ሽልማቶችን እየሰጠን መቀጠል አለበት ብዬ አላስብም፡፡ ለዚህ ደግሞ ፌዴሬሽኑም ሆነ ክለቦች መጀመርያ የራሳቸውን የቤት ሥራ መሥራት ይጠይቃል፡፡ ፈዴሬሽኑ በባለሙያ፣ በፋይናንስና መሰል አደረጃጀቶች መጠናከር ይኖርበታል፡፡ ክለቦችም በተመሳሳይ፡፡ የፌዴሬሽኑ አደረጃጀት አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ከዘመኑ ጋር እኩል መራመድ የሚችል መሆን መቻል ይኖርበታል፡፡ ሌላው ክለቦቻችን አሁን ባለው ቁመናቸው ሊጉን አክሲዮን ማኅበር እናድርገው ብለው ቢሉ ዞሮዞሮ ዕዳው ለራሳቸው ነው፤ ስለሆነም ጥያቄውን የሚመጥን ጥናት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

  ሪፖርተር፡- በዚህ ወቅት ለሊጉ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የሆነ ለፌዴሬሽኑ ጭምር በፕሮፌሽናል ሰዎች የሚመራ ጥናት ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ከዚህ አኳያ ይህን ሊሸከም የሚችል አቅም ፌዴሬሽኑ ይኖረዋል ብለው ያምናሉ?

  አቶ ዮሴፍ፡- ይህን ማድረግ ካልቻለ እስካሁን የተነጋገርንባቸው በሙሉ ዋጋ አይኖራቸውም፣ መለወጥ አለብን ስንል እኮ እነዚህ ጭምር ታሳቢ አድርገን መሆን ይኖርበታል፡፡ እዚህ ላይ ጥናት ሲባል እንደ እስከ ዛሬው የሚጠናው ጥናት ሸልፍ ላይ እንዲውልም አይደለም፡፡ ተፈጻሚ መሆን መቻል ይኖርበታል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተለይም አሁን ያለነው አመራሮች ነገሮችን በዚህ ደረጃ ለማስኬድ መነጋገር እንዳለብን አስባለሁ፡፡ እኔም ከነበረኝ ልምድ በመነሳት ከእንግዲህ በመተዋወቅ ሥራዎች እንሠራለን ብለን የምናስብ ካለን ከጅምሩ ኃላፊነትን መተው የእኔ ምርጫ ነው፡፡ ተቋሙ በሙያና በባለሙያ የሚሠራበት ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ባለሙያው ሙያውን ሲያፈስ ለእግር ኳሱ ዕድገት እንጅ ለዮሴፍ ወይም ለሌሎች ሰዎች ፍላጎት ብሎ መሆን የለበትም፡፡ ከዚህ በኋላ የሁሉም ፍላጎት ተደምሮ የእኛ ብለን የምንመካበት እግር ኳስ እንዲኖረን በጋራ መሥራት፣ አቅም ያለውን አክብረን አቅሙን መጠቀም መቻል ይኖርብናል፡፡ ተነጋግረን፣ ተወያይተንና ተማምነንና የተሻለውን ሐሳብ የምንወስድበት ሥርዓት መፍጠር ካልቻልን እንቸገራለን፡፡ ይህን ስል አሁን ባለው ሁኔታ ፌዴሬሽኑ ይህንን ሥርዓት ማስፈን የሚችል ጠንካራ አደረጃጀት ፈጥሯል እያልኩ እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በጣም በጣም ይቀረዋል፡፡ ተቋሙ አሁን ባለው ሁኔታ ባለሙያ አለበት ብለን የምናስበው ዲፓርትመንት ሳይቀር በግለሰቦች መልካም ፈቃደኝነት ካልሆነ በራሱ እግር ቆሞ መሆን ስላለበት መናገርና መወሰን የሚችል አይደለም፡፡ ይኼ መለወጥ ይኖርበታል፣ በብዙ ባለሙያዎች መዋቀርና መታገዝ እንዳለበት መታመን ይኖርበታል፡፡ ፌዴሬሽኑ በራሱ አቅም የሚሠራውንና የማይሠራውን መለየት ያስፈልጋል፡፡ 

  ሪፖርተር፡- ከአሠራር ጋር ተያይዞ ብቻ ሳይሆን ሙያን ለባለሙያ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ በፌዴሬሽኑ ይተገበራል እያሉን ነው?

  አቶ ዮሴፍ፡- ባለፉት አራትና ከዚያም በላይ ለሆነ ዓመታት በፌዴሬሽኑ የአመራርነት ሚና ኖሮኝ ቆይቻለሁ፡፡ አሁንም በድጋሚ ተመርጬ ለተመሳሳይ ኃላፊነት በቅቻለሁ፡፡ በነበረኝ ቆይታም ጥሩ የሚባል ልምድና ተሞክሮ አግኝቼበታለሁ፡፡ መሥራት ካለብኝ እሠራለሁ ካልቻልኩ አልቻልኩም ለማለት ወደ ኋላ የምልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላለፉት ስድስትና ሰባት አሠርታት ብዙ ተብሏል፡፡ የመጣ አንዳች ነገር የለም፡፡  እንዲያውም ዕድገታችን ቁልቁል ሆኗል፡፡ ሁላችንም ለለውጥ ለሚበጁ ነገሮችና አስተሳሰቦች እጅ መስጠት ይኖርብናል፡፡ በስሜት ብቻ የሚነዳ እግር ኳስ ሊበቃ ይገባል፡፡ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ያለበት ሥርዓት መፍጠር ይኖርብናል፡፡ እግር ኳሱን በበላይነት ከሚመራው ጠቅላላ ጉባዔ ጀምሮ እስከ ታችኛው ክለብና ማኅበር ድረስ ምልከታችን ለእግር ኳሱና ለእግር ኳሱ ብቻ መሆን እንዳለበት ማመን ይኖርብናል፡፡ ከእኔ መጀመር እንዳለበት እየተናገርኩ ነው፡፡ ሌሎች ባልደረቦቼም ሐሳቤን እንደሚጋሩት አምናለሁ፡፡      

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...