በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የኢሮብ ብሔረሰብ ተወላጆች በአልጀርስ ስምምነት መሠረት የተቋቋመው የኢትዮጵያና የኤርትራ የድንበር ኮሚሽን የውሳኔ አፈጻጸምን በተመለከተ ሰላማዊ ሠልፍ ጠርተው እንደነበር ይታወሳል፡፡
በመሆኑም ሰኔ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሊካሄድ የነበረው ሠልፍ ስለተሰረዘበት ሁኔታ የተለያዩ ወገኖች ጥያቄ በማንሳት ላይ ይገኛሉ፡፡ ታቅዶ ስለነበረው ሠልፍ ዓላማና ስለተሰረዘበት ምክንያት አስተባባሪ ኮሚቴው ለመላው ኢትዮጵያዊያን የሚከተለውን አጭር ማብራሪ ማስተላለፍ ይፈልጋል፡፡
የኢሮብ ብሔረሰብ የራሱ ባህል፣ ቋንቋ፣ ወግ፣ እሴትና አኩሪ ኢትዮጵያዊ ታሪክ ያለው ሕዝብ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሕዝባችን ከአጎራባች የኤርትራ ሕዝብ ጋር በፍቅርና መከባበር ላይ የተመሠረተ መልካም ጉርብትና ቢኖረውም፣ በማናቸውም ዘመን ከኢትዮጵያ አስተዳደር ውጪ ሆኖ አያውቅም፡፡ በኤርትራ ሥር ተዳድሮ የሚያውቅ አንድም የኢሮብ መንደር የለም፡፡
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፣ በታኅሳስ 1993 ዓ.ም. አልጀርስ ላይ በተፈረመው ስምምነት መሠረት፣ የተቋቋመው ድንበር ኮሚሽን ብሔረሰባችንን ለሁለት በመክፈል ግማሹ ወደ ኤርትራ እንዲከለል መወሰኑ ይታወቃል፡፡ የውሳኔው መተግበር ሕዝባችን አባላት ቋንቋ፣ ባህል፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር፣ እንዲሁም በጋራ እሴቶች ቀጣይነት ላይ አደጋ ይፈጥራል፡፡ በጦርነቱ ወቅት በኤርትራ መንግሥት ጥርስ ውስጥ በገባው ሕዝባችን ላይ የበቀል ዕርምጃ እንዲወሰድበት አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ይህን የተገነዘበው ሕዝባችን፣ ውሳኔው እንዳለ እንዳይተገበርበት ሲታገል መቆየቱም ይታወሳል፡፡ በተለይም ውሳኔው ከተሰጠበት ጊዜ አንሰቶ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ባለ አምስት ነጥብ የሰላም ሐሳብ እስከቀረበበት ጊዜ ድረስ ከፍተኛ ትግል አድርጓል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ሕዝባችን ችግሩ በዚያው መሠረት በውይይትና በሰጥቶ መቀበል መርህ ይፈታል ብሎ ተስፋ በማድረጉ፣ ጉዳዩን በቅርበትና በተስፋ ከመከታተል ውጭ የጎላ እንቅስቃሴ ከማድረግ ጋብ ብሎ ቆይቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ የአልጀርሱን ስምምነት ተከትሎ በድንበር ኮሚሽኑ የተሰጠውን ውሳኔ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ መቀበሉን አስታውቋል፡፡ ሕዝባችን በጦር ቀጣና ውስጥ ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ተዳርጎ የሚኖር በመሆኑ፣ ሰላም እንዲወርድ እጅጉን ይሻል፡፡ ሆኖም ተፈላጊው ሰላም በአስተማማኝ መሠረት ላይ እንዲኖር፣ በድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ትግበራ ላይ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ ደግሞ በድንበር አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን ፍላጎትና ሐሳብ ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለበት ሕዝባችን ያምናል፡፡
በመሆኑም ይኼን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ አቅርቦ የመላው ኢትዮጵያዊያንና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትን ድጋፍ ለመሻት የኢሮብ ሕዝብ ከሚኖርባቸው የገጠር ቀበሌዎች አንስቶ በየአካባቢው ሰሞኑን ሠልፍ ማካሄዱ ይታወሳል፡፡ ሰኔ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በብሔረሰቡ ተወላጆች ሊደረግ ታቅዶ የነበረው ሠልፍም የዚህ እንቅስቃሴ አካል ነበር፡፡
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ የሠልፉ ዓላማ አንድን ፖለቲካዊ ቡድን የመደገፍና ሌላውን የመቃወም እንቅስቃሴ ነው በማለት ከፍተኛ ዘመቻ በማኅበራዊ ሚዲያ ተደርጓል፡፡ አልፎ ተርፎም ሠልፉ እንዲካሄድ ፈቃድ ሰጥቶ የነበረው አካል በአጠቃላይ ጥሩ ሁኔታ እንደሌለና የፀጥታ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ለአስተባባሪው ኮሚቴ አሳወቋል፡፡ አስተባባሪ ኮሚቴው በዚህ ዓይነት ድባብ ውስጥ የሚደረግ ሠልፍ ለኢሮብ ሕዝብ ተፈላጊውን ድጋፍ ከኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ እንደማያስገኝለት ተገንዝቧል፡፡ በተለይ ደግሞ በኢሮብ ሕዝብ ስም በተጠራ ሠልፍ ሳቢያ አንድም ኢትዮጵያዊ መጎዳት ይቅርና መደንገጥ እንደ ሌለበት የኮሚቴው አባላት በጋራ መግባባት ላይ ስለደረሱ፣ ሠልፉ መሰረዙን ኢትዮጵያዊያን በመላ እንዲያውቁልን እንሻለን፡፡
በዚህ አጋጣሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰኔ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉትና ገለጻ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስለድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ የወሰደው አቋም ይፋ የተደረገው፣ አሁን እየተካሄደ ያለውን ዓይነት ውይይት ለመጫርና ግልጽነትን ለማረጋገጥ እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሐሳብና ይሁንታ ሳይታከልበት ውሳኔው ተግባራዊ እንደማይደረግ መግለጻቸው፣ ለሕዝባችን ጥሩ ተስፋ መስጠቱንና ደስ ያሰኘን መሆኑን መግለጽ እንፈልጋለን፡፡
በተጨማሪም የሕዝባችንን ጥያቄ በሰከነና በሰላማዊ መንገድ ለሚመለከታቸው ሁሉ ማቅረባችንን እንደምንገፋበት ስንገልጽ፣ መላ ኢትዮጵያዊያን የሕዝባችንን ችግር እንዲገነዘቡልንና በተቻላቸው ሁሉ እንዲረዱን የድጋፍ ጥሪ በማድረግ ነው፡፡
(ሥዩም ዮሐንስ፣ የጊዜያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ)