Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

በቀደም ዕለት ከወዳጆቼ ጋር የምሣ ግብዣ ነበረን፡፡ የምሣ ላይ ጨዋታ ከሚያስደስቱኝ ነገሮች መካከል በዋነኝነት ይመደባል፡፡ አጠር ባለ ሰዓት ውስጥ ወዝ ያለው ጨዋታ እየተጨዋወቱ ምሣን ማጣጣም ደስ ይላል፡፡ እነዚህ ወዳጆቼ ደግሞ ከተለያዩ አካባቢዎችና የሥራ መደቦች የተሰባሰቡ በመሆናቸው፣ በዚያች አጭር የምሣ ወጋችን እጅግ በጣም የሚያዝናኑ ገጠመኞቻቸውን እየነገሩን ቀኑን ደመቅ አደረጉልን፡፡ እንደ እሳት የሚጋረፈው ኑሯችንና በውጥረት የተሞላው እንቅስቃሴያችን ዘና ካላልንበት ለጤናችን ጠንቅ ነው፡፡ የጤና ጠንቅ ሲባባስ ዕድሜ ስለሚያሳጥር ዘና ብንል ይሻለናል፡፡ ሁልጊዜ እንደ ግስላ እየተቆጡ ሰላም አጥተው ሰላም ከሚያሳጡን ይከልለን እያልን፣ ነፍሳችንን በደስታ ብናረሰርሳት ይሻለናል፡፡ ክፋትና ተንኮል ያጨቁ ነፍሶች ለአገር ዕድገት አይጠቅሙምና፡፡

በአንድ ወቅት አንድ በጣም የምወደው ጓደኛዬ ደስታ ርቋቸው የሰው ደስታን ለመግፈፍ የሚነሱ፣ ከአስተዳደጋቸው ችግር ያለባቸው ናቸው ይለኝ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ይህ ጓደኛዬ በሥነ ልቦናዊ ጉዳዮች ላይ ጠለቅ ያለ ዕውቀት ያለው ስለሆነ፣ በየቦታው ሰውን ለማስከፋትና ከመልካም ነገሮች በተቃራኒ አሳዛኝ ድርጊት የሚፈጽሙ ካስተዳደጋቸው ባጋጠማቸው ችግር እንደሆነ ይነግረኝ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ደግሞ አንድ ታዋቂ ሰው ስለዚህ ጉዳይ በአንደኛው የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ ሲናገሩ መስማቴን አስታወስኩ፡፡ እሳቸው እንዳሉት ሰዎች በልጅነታቸው በሙዚቃ፣ በስፖርትና በአዝናኝ ነገሮች እየተኮተኮቱ ካላደጉ ክፋት ይፀናወታቸዋል፡፡ ‹‹በተለይ በተለያዩ የመንግሥት መሥርያ ቤቶች ውስጥ እምቢ ማለት የሚቀናቸውና ሥራን በተቀላጠፈ መንገድ ለማስኬድ የማይፈልጉ፣ በልጅነታቸው ከአዝናኝ ነገሮች በመገለላቸው ነው፤›› ብለው ነበር፡፡ በእርግጥም እሳቸውም ሆኑ ጓደኛዬ ያሉት ትክክለኛ ነገር ነው፡፡ ደስታን ሳያውቁ ያደጉ ከክፋት በስተቀር ምን ይኖራቸዋል?

በማኅበረሰባችን ውስጥ የምናውቃቸው ስመ ጥሩዎች ሰዎችን በጥሩ ሁኔታ የሚቀርቡ፣ ለተቸገረ የሚደርሱ፣ አብረዋቸው ለሚሠሩ ሰዎች ልዩ ፍቅርና ከበሬታ ያላቸው፣ በማንኛውም ጊዜ ለሚቀርብላቸው የዕርዳታም ሆነ የትብብር ጥያቄ በጎ በጎውን እያሰቡ ምላሽ የሚሰጡ ናቸው፡፡ በክፋት የምናውቃቸው ደግሞ ለሰው አክብሮትና ፍቅር የሌላቸው፣ ህሊናቸው በጥላቻ የተሞላ፣ መልካም ነገር ለማድረግ በፍፁም የማይፈልጉ፣ የሥራ ጓደኞቻቸውንና የበታቾቻቸውን እንደ ጠላት የሚመለከቱ፣ ራሳቸውን ለገንዘብና ላልተገቡ ጥቅሞች ያስገዙ፣ በቅናትና በመጥፎ ስሜት አዕምሮአቸው የታወከ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰውን ማሰቃየት ደስታ የሚሰጣቸውና ለአገር ደንታ ቢሶች ናቸው፡፡ ከሥልጣንና ከጥቅማ ጥቅሞች በስተቀር ለወገን ቅንጣት ያህል የማይሰማቸው፣ በአገር ላይ ምን ያህል በደል እንዳደረሱ እናውቃለን፡፡

የሥነ ልቦና ሊቁ ጓደኛዬ አምባገነንነት የሚፈጠረው በእንዲህ ዓይነቶቹ ክፉ ግለሰቦች አዕምሮ ውስጥ ነው ይላል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ፈሪዎች፣ ተጠራጣሪዎችና የከፋ ነገር ከመጣ ደግሞ በቀላሉ የሚሸነፉ ናቸው፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ አስፈሪና የጨለመ ድባብ ውስጥ ስለሚኖሩ ያገኙትን በሙሉ እየጨቆኑ መኖር፣ ማስራብ፣ ማሰርና መግደል ይፈልጋሉ፡፡ በደህና ጊዜ የማያውቋቸውን ሰዎች ዓይን ማየት ስለማይፈልጉ፣ መጀመርያ እነሱን በጠላትነት በመፈረጅ ከምድረ ገጽ ማጥፋት ይፈልጋሉ፡፡ በሥራ ቦታም ሆነ በሌላ የበላይ ከሆኑ ደግሞ ሁልጊዜም የሚያሴሩት ሰዎች በራሳቸው እንዳይተማመኑ ማድረግ፣ ራሳቸው ሊሠሩት የማይችሉትን ሥራ ሌሎች እንዲሠሩት ቅጥ አምባሩ የወጣ ትዕዛዝ መስጠት፣ አካባቢያቸውን በፍርኃት ማሸበርና የተሻሉና ብቃት ያላቸው ሰዎች ዕድገት እንዳያገኙ ማድረግ ዋነኛው ተግባራቸው ነው፡፡ ከቢጤዎቻቸው ጋር ተደራጅተው እንደ ጅብ መንጋ የአገር ሀብት ይግጣሉ፡፡ የሚቀናቀኑዋቸውን በተለያዩ መንገዶች ያሰቃያሉ፡፡ ፍፁም አምባገነኖች ናቸው፡፡ እነዚህን ለመታገል ጥረት ያደረጉ ምን እንደደረሰባቸው የምናውቅ ይመስለኛል፡፡

የበቀደሙ ምሳችን ላይ አንድ ጓደኛችን እንዲህ ዓይነቶቹ ሥልጣን ሲያገኙ የናዚ ሒትለርን ዓይነት ሰቆቃ ይፈጽማሉ ብሎን፣ አንድ በአምባገነኖች ላይ የተነገረ ቀልድ ነገረን፡፡ በአንድ አገር አንድ አምባገነን መሪ አንድ የሕፃናት ትምህርት ቤት ሊጎበኝ ይሄዳል፡፡ አንድ የመማሪያ ክፍል ውስጥ ይገባና ተማሪዎቹ ጥያቄ እንዲያቀርቡለት ይጠይቃል፡፡ አንድ ‹‹ቶም›› የተባለ ሕፃን ተማሪ፣ ‹‹ክቡር ፕሬዚዳንት የመጀመርያው ጥያቄዬ ለምን እብሪተኛ ይሆናሉ? ሁለተኛው ጥያቄዬ አገሪቱን ለምን ያደኸያሉ?›› በማለት ጥያቄ ያቀርባል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ወዲያው ተማሪዎቹ እረፍት እንዲወጡ ያዛል፡፡ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ተማሪዎች ከእረፍት ሲመለሱ ፕሬዚዳንቱ ተጨማሪ ጥያቄ እንዳለ ይጠይቃል፡፡ አንዲት ተማሪ በድፍረት፣ ‹‹የመጀመርያው ጥያቄዬ ለምን እብሪተኛ ይሆናሉ? ሁለተኛው ጥያቄዬ አገሪቱን ለምን ያደኸያሉ? ሦስተኛው ጥያቄዬ ደግሞ ቶም የተባለውን ጓደኛችንን በእረፍት ሰዓት የት ወሰዱት?›› አለች ሲለን ሁላችንም ደነገጥን፡፡ ክፉዎችንና አምባገነኖችን እንደ እንቁላል የሚፈለፍለው ፍርኃት እንኳን ለአዋቂዎች ለሕፃናት አይመለስም ማለት ነው፡፡

እና ምን ለማለት ነው? አምባገነኖችን የምናፈራው እኛው ራሳችን ነን፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገራችን እያየን ያለው ለውጥ በምክንያታዊነት የተነሱ ሰዎች ያመጡት ነው፡፡ ይህንን ለውጥ ግን ሌሎች አምባገንነኖችን ለመፍጠሪያ እንዳንጠቀምበት ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ ግለሰባዊ አምልኮ ሳይሆን አገራዊ ራዕይ እንዲኖረን ከስሜታዊነት በመቆጠብ ለአገር ግንባታና ለተቋማት መጠናከር፣ ለሕግ የበላይነት፣ ለኢትዮጵያዊነት ማበብ፣ ለጋራ እሴቶች ጥንካሬና ለዴሞክራሲያዊት አገር መፈጠር መትጋት አለብን፡፡ መልካም አጋጣሚዎችን በከንቱ አበላሽተን ከመፀፀት በድፍረትና በፅናት ለውጡንና የለውጡን መሪዎች መደገፍ ይገባል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ በሁለት እግራ መቆም የምትችለው በምክንያታዊ አስተሳሰብ እንጂ በግልብነትና በዘፈቀደ መውረግረግ አይደለም፡፡ ስክነት ደግሞ የብስለት ማሳያ ስለሆነ በማስተዋል የተጀመረውን ለውጥ ከዳር እናድርስ፡፡ አጉል ሆያ ሆዬ መልካም አጋጣሚዎችን ከማበላሸት የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ ለፋይዳ ቢስ ነገር ማገዶ መጨረስም አይገባም፡፡

 (ብሩክ ሰይፈ ሚካኤል፣ ከሲኤምሲ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...