Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየአዲስ ክልል አመሠራረት ሕግ የሲዳማ ጥያቄ እንደመነሻ

የአዲስ ክልል አመሠራረት ሕግ የሲዳማ ጥያቄ እንደመነሻ

ቀን:

በውብሸት ሙላት

ሰሞኑን በወልቂጤ፣ በወላይታ ሶዶና በሐዋሳ ከተማ በተከሰቱ ግጭቶች የሰው ሕይወት መጥፋቱ፣ የአካል ጉዳት መድረሱና ንብረት መውደሙ ይታወቃል፡፡ የሚያመሳስላቸው ቢኖርም የግጭቶቹ መንስዔዎች የሚያለያያቸው ባህሪያት መኖሩ ግልጽ ነው፡፡ ግጭቶቹን ለመቀስቀስ ሰበብ የሆነው አቀጣጣይ መንስዔዎች እንደየአካባቢው ይለያያሉ፡፡

ይሁን እንጂ በተለይ የሲዳማ ብሔር ተወላጆች በዋናነት ሲያነሱ የነበረውና ለብሶታቸው መንደርደሪያ የሆነው ምክንያት ለ16 ዓመታት ገደማ ሲንከባለል የኖረው የክልልነት ጥያቄ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሲዳማ ተወካዮችን ባነጋገሩበት ወቅት ተወካዮቹ በምሬት እንደተናገሩት የሲዳማ የክልልነትን ጥያቄ ማንሳት ለብዙ የሲዳማ ተወላጆች ስቃይ፣ እንግልት፣ ሞት፣ እስራትና ስደት ወዘተ. ዳርጓል፡፡ ጥያቄው የቆየ ቢሆንም፣ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደውና በተቀመጡት ሥነ ሥርዓቶች መሠረት አልተስተናገደም፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ክልል እንዴት እንደሚመሠረት ማሳየትና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን መጠቆም ነው፡፡

ከብር መርጦ ለክልል?

የክልሎቻችን አመሠራረት ስናይ አራት አካሄዶችን እንታዘባለን፡፡ የመጀመርያው ሰፋ ያለ ቦታ ይዘው በአንድ አካባቢ ተከማችተው የሚገኙ ቁጥራቸው ከሌሎቹ በዛ ያሉ ብሔሮች በስማቸው ክልል መሥርተዋል፡፡ በውስጣቸው ሌላ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች ቢኖሩም ስም አወጣጡን ለራሳቸው አድርገዋል፡፡ ይህንን አካሄድ የተከተሉት ትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ናቸው፡፡ በትግራይ ውስጥ ኩናማና ኢሮብ፣ በአማራ ኦሮሞ፣ አገው ኻምራ፣ አገው አዊ፣ አርጎባ፣ ወይጦ፣ ቅማንት፤ በኦሮሚያ ትግረ ወርጂና ዛይ፣ በአፋር አርጎባ ቢገኙም ማለት ነው፡፡

ሁለተኛው ከ56 ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በላይ የያዘው የአሁኑ የደቡብ ክልል ደግሞ በሽግግሩ ወቅት ክልል ሰባት (ጉራጌ፣ ሐዲያ፣ ጠምባሮ፣ የምና ሐላባ)፣ ስምንት (ሲዳማ፣ ኮሬ፣ ጌዲኦና ቡርጂ)፣ ክልል ዘጠኝ (ወላይታ፣ ዳውሮና ኮንታ ወዘተ.)፣ አሥርና (ባስኬቶ፣ ሙርሲና ሐመር ወዘተ.) ክልል 11 (ካፋና ሸካ ወዘተ.) ተብለው ተዋቅረው የነበሩት አምስት ክልሎች በመጠቅለል የተመሠረተ ነው፡፡ የብሔሮቹ ማንነት ላይ ሳይገደብ በአስተዳደራዊ ምቹነትን ከግምት በማስገባት የተቋቋመ ይመስላል፡፡ አንዳንድ የክልሉ ተወላጆችም ደቡብ የሚለው ስያሜ አቅጣጫን ከመጠቆም በስተቀር ማንነትን አያመለክትም በማለት ይተቹታል፡፡ ሦስተኛው አካሄድ ደግሞ አምስት አምስት ነባር ብሔረሰቦች ኑሯቸው ነገር ግን አንደኛቸውም ከግማሽ ያልበለጠባቸው የጋምቤላ ሕዝቦችና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ናቸው፡፡ ቤኒሻንጉል፣ የበርታ ሕዝቦች ሌላኛው መጠሪያ ሲሆን፣ ጉምዝን በመጨመር በሁለቱ ብሔረሰቦች ብቻ የተሠየመ ነው፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 ላይ ውይይት ሲደረግ ይህንን አሰያየም በተመለከተ ተቃውሞ ቀርቦ ነበር፡፡ አምስት ነባር ብሔረሰቦች እያሉ በሁለቱ ብቻ መሰየም ሌሎቹን መካድ ነው የሚል ነው፡፡ በጋምቤላም አምስት ነባር ብሔረሰቦች ቢኖሩም፣ እንደሽግግር ዘመን አጠራሩ ብሔረሰብን ሳያመለክት ብዙ ሕዝቦች እንዳሉት ብቻ በማሳየት ተሰየመ፡፡ እነዚህን ሁለት ክልሎች በሚመለከት ሳይነሱ መታለፍ የሌለባቸው ሁለት ግራ አጋቢ ጉዳዮች አሉ፡፡ የመጀመርያው እነዚህን ክልሎች ከመሠረቱት አምስት፣ አምስት ብሔረሰቦች መካከል  በሁለቱም ክልሎች ዘንድ የሚገኝ አንድ የጋራ ብሔረሰብ (ኮሞ) መኖሩ ነው፡፡ ከሌሎቹ ክልሎች የሚለዩባቸው ነጥቦች አንዱ መሆኑ ነው፡፡  በ1999 ዓ.ም.  ሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት መሠረት በጋምቤላ ነዋሪ የሆኑ የኮሞ ነዋሪዎች 224 ሲሆኑ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ደግሞ 7,773 ናቸው፡፡ ሌላኛው ጉዳይ ደግሞ እነዚህን ክልሎች የሚመለከትና ሁለቱ ክልሎች የሚዋሰኑበት ድንበር ባይኖራቸውም (በመካከላቸው ኦሮሚያ ክልል አለ) በሁለቱም ክልሎች ሕግጋተ መንግሥታት አንቀጽ ሁለት  ላይ ግን እንደሚዋሰኑ ተጽፏል፡፡

አራተኛው የሐረሬ ክልል የተመሠረተበት ሁኔታ ነው፡፡ የሐረር ክልልነት ለብዙዎች ግራ አጋቢ ነው፡፡ ስለሐረር የጻፉ አብዛኛዎቹ የሐረር ጉዳይ ግራ አጋቢ እንደሆነ በመግለጽ ያልፉታል፡፡ የአመሠራረት ታሪኩን ስናይ በሕዝብ ብዛት አይሉት በ1999 .. በተደረገው የሕዝብና ቤት ቆጠራ (ቁጥሮቹ ወደ ሺሕ ቤት ተጠጋግቷል) እንኳን የክልሉ አጠቃላይ ሕዝብ 200,000 አይሞላም፡፡ ከዚህ ውስጥ የሐረሪ ብሔረሰብ አጠቃላይ ቁጥር ደግሞ 32,000 አካባቢ ሲሆን፣ በክልሉ የሚኖረው ወደ 16,000 የሚጠጋው ብቻ ነው፡፡ በሐረሪ ክልል ውስጥ 103,000 ኦሮሞና 42,000  አማራ እያንዳንዳቸው 7,000 የማያንስ ሶማሌና ጉራጌዎች ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም 40 በላይ የሚሆኑ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከሐረሬዎች የበለጠ የሕዝብ ብዛት እያላቸው፣ አንዳንዶቹ የራሳቸውን ልዩ ወረዳ ወይም ዞን መመሥረት እንኳን ሳይችሉ ሐረሬዎች ግን ክልል መሥርተዋል፡፡

የሐረሪን ክልልነት በሚመለከት የተለያዩ ግምቶችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ሐረር በኦሮሚያ ክልል የተከበበች ነች፡፡ ሐረር ክልል ካልሆነች ቀሪው አማራጭ በኦሮሚያ ክልል ሥር መጠቃለል ነው፡፡ በኦሮሚያ ሥር ለመጠቃለል ደግሞ ሐረሮች መስማማት መቻል አለባቸው፡፡ ከዚያ በትግራይ ወይም በአማራ ክልል ውስጥ እንደሚገኙት ብሔረሰቦች ይሆናሉ፡፡ እንደ ትግራይ ክልል ከሆነ ልዩ ዞን ወይም ልዩ ወረዳ ሳይኖራቸው፣ እንደ አማራ ክልል ከሆነ ደግሞ ወይ ልዩ ዞን ወይም ልዩ ወረዳ ኖሯቸው ነገር ግን በኦሮሚያ ክልል ሥር ሆኖ መቀጠል ነው፡፡

ይሁን እንጂ ከሌላው ብሔረሰብ በተለየ ሁኔታ ከሌላ ብሔር ጋር ሳይዋሃዱና ሳይቀላቀሉ የተለየ ማንነታቸውን ይዘው የቆዩ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ከታሪክ አንፃርም ቢታይ የጆገል ግንብ የተገነባው ከጠላቶቻቸው ለመከላከል ጭምር ነው፡፡ ጀጎል ሲገነባ የሐረሮች በሌሎች ሕዝቦች ከመዋጥ ራሳቸውን ለመጠበቅ ጭምር ስለነበር በአንድነት በአንድ ክልል አብሮ ለመኖር የሐረሬዎች ዝግጁነት እጅግ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ሐረሪዎች ልዩነታቸውን ጠብቀው የማስቀጠል ከፍተኛ ፍላጎት ካለና በሌላ ክልል ውስጥ ካለው ኅብረተሰብ ጋር በመቀላቀል ለመኖር ፍቃደኝነቱ ከሌለ፣ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትና ከእሱ በፊት በነበረው አዋጅ ቁጥር 7/1984 መሠረት የብቻ ክልል መመሥረቱ አማራጭ የለውም፡፡  ከጥንት ጀምሮ የራሳቸው የተለዬ አስተዳደር መኖር የታወቀ የመሬት ይዞታ ያላቸው መሆኑ የብቻቸው ክልል የመመሥረት መብታቸው ቢጠበቅና ቢተገበር ከብዙ ጣጣ ሊታደግ ይችላል፡፡ እነ ሲዳማና ሌሎችም ብሔሮች ክልልነት ህልም ሆኖባቸው መቅረቱን ስናይ ደግሞ እውነትም ‹ከእንጨት መርጦ ለታቦት ከብሔር መርጦ ለክልልነት› ብንል ተገቢነቱ ያነሰ አይመስለኝም፡፡

የክልልነት መከለያዎች

ፌዴሬሽኖች ለክልል ምሥረታ ምን ምን ሁኔታዎችን ከቁብ ይቆጠራሉ? ከሕዝብ ብዛት ምጥጥን፣ ከአስተዳደራዊ ምቹነት፣ ከተፈጥሮ ሀብት፣ ከቆዳ ስፋትና ከልማት አንፃር የክልሎቻችንን አወቃቀር የሰላ ትችት የሚያቀርቡ አሉ፡፡ እኛም ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑትን መርጠን በአጭሩ እናይና ወደ መሥፈርቶቹ እንሄዳለን፡፡

የኢትዮጵያ የፌዴራል አወቃቀር በሰፊው ከሚወቀስበት አንዱ ለክልልነት የተወሰዱት መሥፈርቶች ናቸው፡፡ በእርግጥ በዓለም ላይ አንድ ወጥ መሥፈርት የለም፡፡ አሜሪካ፣ አውስትራሊያና ጀርመንን ብናይ በዋናነት መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥን ከግምት ያስገባ ሲሆን፣ ናይጀሪያ፣ ስፔን፣ ቤልጂየምና ህንድ በተወሰነ መልኩ ካናዳ ደግሞ ከመልከዓ ምድር በተጨማሪም ብሔርን ከግምት አስገብተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቅይጥ ነው ማለት ይቻላል፡፡  በኢትዮጵያ ለክልል ምሥረታ ከግምት መግባት ያለባቸው፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 46(2) መሠረት፣ አራት መሥፈርቶች ያሉ ሲሆን፣ እነሱም የሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነትና ፈቃድ ናቸው፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት መሥፈርቶች አንፃር አንድ ብሔር በዛ ብሎ የሚገኝባቸው (ትግራይ፣ አፋር፣ አማራ፣ ኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ) ማንነትና ቋንቋ ገነን ብለው ይታያሉ፡፡ በደቡብ፣ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ደግሞ ፖለቲካዊ ሁኔታ፣ ኢኮኖሚና የመሳሰሉት መሥፈርቶች ቢኖሩም መልከዓ ምድር ጎልቶ ይታያል ማለት ይቻላል፡፡ በአንድ አካባቢ መገኘታቸው እንጂ ቋንቋቸው ወይም ማንነታቸው አይደለም፡፡ ፈቃድንም በተመለከተ እነሲዳማ፣ ከፋ፣ ጋሞ፣ ጉሙዝ፣ በርታና ጉራጌ በተለያዩ ወቅቶች የራሳቸውን ክልል ለመመሥረት ጥያቄ አንስተው የነበሩ መሆኑን ስናይ፣ ወደውና ፈቅደው ነው ክልሎቹን የመሠረቱት ማለት ሊያጠራጥር ይችላል፡፡ በመሆኑም ቅይጥ እንጂ ብሔር ላይ ብቻ ተመርኩዞ ተመሠረቱ ማለት አዳጋች ነው፡፡

የክልል አመሠራረትን በተመለከተ የሕገ መንግሥቱ ውይይት ላይ እንደ አማራጭ መከራከሪያነት ቀርቦ የነበረው በአፄ ኃይለ ሥላሴ ወቅት የነበረው መልከዓ ምድርን መሠረት ያደረገው ጠቅላይ ግዛታዊ/ክፍለ አገራዊው አወቃቀር ነበር፡፡ ማለትም ለመልከዓ ምድራዊ አቀማመጥና ለአስተዳደራዊ ምቹነትና ቅልጥፍና ቅድሚያ መስጠት ማለት ነው፡፡ አሁን ያለውን አከላለልን በተመለከተ አንድ የማይታበል ሀቅ አለ፡፡ እሱም በቆዳ ስፋትና በሕዝብ ብዛት ያለመጣጣም ችግር፡፡ በቆዳ ስፋት የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ከኦሮሚያ ቀጥሎ ሁለተኛ ነው፡፡ በሕዝብ ብዛት ሲታይ ደግሞ የደቡብ ክልልን 1/3ኛ፣ ወይም ከትግራይ ጋር የተቀራረበ ነው፡፡ ከቆዳ ስፋት አንፃር ደግሞ ኦሮሚያ 33.05 በመቶ፣ ሶማሊያ 19.82 በመቶ፣ አማራ 17.34 በመቶ፣ ደቡብ 10.28 በመቶና ትግራይ ደግሞ 5.53 በመቶ ኢትዮጵያን ይጋራሉ፡፡ በሕዝብ ብዛት ደግሞ ኦሮሚያ 36.7 በመቶ፣ ሶማሊያ ስድስት በመቶ፣ አማራ 23.3 በመቶ፣ ደቡብ 20.4 በመቶና ትግራይ 5.8 በመቶ ነው፡፡

የቆዳ ስፋት ድርሻን ከሕዝብ ብዛት ድርሻ ጋር ስናነፃፅረው እንዲሁም ክልሎቹ ያሉበትን የልማት ደረጃ ከግምት ስናስገባ በጀት ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ መኖሩ አሌ የሚባል አይደለም፡፡ ነገሩ የሚከፋው ክልሎች አብዛኛው በጀታቸው የሚሸፈነው ከፌዴራል መንግሥቱ በሚያገኙት ድጎማ መሆኑ ነው፡፡ በዚህን ጊዜ አንዱን ማስደሰቱ ሌላውን ቅር ማሰኘቱ አይቀርም፡፡ ክልል መሆንም በራሱ በርካታ ጠቀሜታ እንዳለው መገንዘብ አይከብድም፡፡ ስለሆነም የግድ መሥፈርቱ ወደ አንዱ የሚያጋድል መሆን ያለበት ይመስላል፡፡ ለዚያም ነው ሕገ መንግሥቱ ሲፀድቅ ከሁለት አንዱ የተመረጠው፡፡

አዲስ ክልል እንዴት ይመሠረታል?

በሽግግሩ ወቅት 14 ክልሎች ነበሩ፡፡ ተሸጋግረን ስንጨርስ ወደ ዘጠኝ ክልሎችና አንድ የከተማ መስተዳደር፣ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ አንድ የከተማ መስተዳድር ተጨምሮ ሁለት ሆኑ፡፡ ከዚያ በኋላ የተለያዩ ብሔሮች ክልል ለመመሥረት ፈልገው ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ ወይም ትተውታል፡፡ ሲዳማ፣ ጌድኦ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ በርታና ጉሙዝ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በጣም በመግፋትና በማምረር እንዲሁም ገሀድ በማድረግ ብሎም ለግጭትና ሕይወት መጥፋት ምክንያት በመሆን የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ግምባር ቀደም ነው፡፡

ለመሆኑ ክልል እንዴት ነው የሚመሠረተው? በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠው ሥነ ሥርዓት ምን ይመስላል? ቀጥለን እንያቸው፡፡

ክልል ለመሆን መሥፈርቶቹን ከላይ ዘርዝረናል፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ወይም ሕዝቦች በማናቸውም ጊዜ ክልል የመመሥረት መብታቸው ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና አግኝቷል፡፡ በሽግግሩ ዘመን ሥራ ላይ በነበረው አዋጅ ቁጥር 7/1984 መሠረት ወረዳን ጨምሮ ወደ ላይ ያሉ መስተዳድሮችን ማቋቋም የማይችሉት ተዘርዝረው ነበር፡፡ በሕገ መንግሥቱ ይህ ገደብ ተነስቷል፡፡ በተጨማሪም ክልል መመሥረት እንደመገንጠል ሁሉ ገደብ የለውም፡፡ ለነገሩ ክልል መመሥረትም ጉዳዩ ከክልል መሆኑ ነው እንጂ ያው መገንጠል ነው፡፡ ገደብ አለመኖሩን ለማመልከት ‹‹በማናቸውም ጊዜ›› የሚል ቃል ተጠቅሟል፡፡

ጠያቂው ብሔሩ፣ ብሔረሰቡ ወይም ሕዝቡ ነው፡፡ ጥያቄው የሚቀርበውም ለራሱ ብሔር ወይም ብሔረሰብ  ወይም ሕዝብ ምክር ቤት ነው፡፡ ይህ ምክር ቤት የክልሉ ምክር ቤት ማለት አይደለም፡፡ በምሳሌ እንመልከተው፡፡ የሲዳማ ሕዝብ የክልልነት ጥያቄ ማቅረብ ያለበትና የሚችለውም ለሲዳማ ዞን ምክር ቤት ነው፡፡ የሲዳማ ሕዝብ ልዩ ዞን ስላለው የዞን ምክር ቤት አለው፡፡ በአማራ ክልል ቢሆን ደግሞ የአርጎባ ልዩ ወረዳ፣ የአዊ፣ የዋግ ኽምራና ኦሮሞ ብሔረሰቦች ደግሞ የልዩ ዞንና ወረዳ ብሔረሰብ ምክር ቤት ስላላቸው ለእነዚህ ይቀርባል ማለት ነው፡፡ ከዚያ ከዚህ ምክር ቤት የሁለት ሦስተኛ ድምፅ ድጋፍ ማግኘት አለባቸው፡፡ ይህንን ድጋፍ ካላገኘ ጥያቄው ውድቅ ይሆናል፡፡ ስለሆነም ክልል ምሥረታን በተመለከተ ይህ ምክር ቤት ቁልፍ ሚና አለው ማለት ነው፡፡

ቀጥሎ የብሔሩ ምክር ቤት በጽሑፍ ወደ ክልል ምክር ቤት ጥያቄውን ይቀርባል፡፡ ለክልል ምክር ቤት ጥያቄ የሚያቀርበው የብሔሩ ምክር ቤት ስለመሆኑ አዋጅ ቁጥር 251/1993 ተገልጿል፡፡ ጥያቄው የቀረበለት የክልል ምክር ቤት ሕዝበ ውሳኔ ከማዘጋጀት የዘለለ በሕግ የተቀመጠ ሥልጣን የለውም፡፡ ጥያቄውን ለማብረድ ፖለቲካዊ ሥራ ሊሠራ ይችል ይሆናል፡፡ ጥያቄው በደረሰው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ድምፀ ውሳኔ ማዘጋጀት አለበት፡፡ በድምፀ ውሳኔው የሚሳተፉትን ሰዎች በተመለከተ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47(3)(ሐ) መሠረት ጥያቄውን ያቀረበው ብሔር ወይም ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ አባላት ናቸው በማለት ገልጿል፡፡ የሕገ መንግሥቱ የአማርኛውና የእንግሊዝኛው አገላለጽ ድምፅ የሚሰጡትን በተመለከተ ልዩነት ያላቸው ይመስላል፡፡ እንግሊዝኛው በደፈናው በአብላጫ ድምፅ ሲደገፍ ስለሚል ድምፅ የሚሰጡት አጠቃላይ ነዋሪው ይሁን የብሔሩ አባላት ግልጽ አይደለም፡፡ አማርኛው ግን በብሔሩ፣ በብሔረሰቡ ወይም በሕዝቡ የሚሉ ቃላት ስላለው ሌሎችን አያካትትም፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ (251/1993) አንቀጽ 19(3)(ሐ) ላይ በአማርኛው መንፈስ አስቀምጦታል፡፡

በዚያ ዞን ወይም ወረዳ የሚገኙ የሌሎች ብሔር ተወላጆች ድምፅ መስጠት የሚችሉ አይመስልም፡፡ ድምፅ ከሰጡት ውስጥ ከግማሽ በላይ ከደገፉት ክልል የመመሥረት ጥያቄው አለቀ ማለት ነው፡፡ የሚቀረው ጉዳይ ከመገንጠሉ በፊት አብሮት ይኖርበት የነበረው ክልል ሥልጣኑን ለአዲሱ ክልል ማስተላለፍ ብቻ ነው፡፡ ክልል ምሥረታ ላይ ሕገ መንግሥቱ ስለንብረትና ዕዳ ክፍፍል የሚያነሳው ነገር የለም፡፡ መነሳትና መደንገግ የነበረበት ግን ይመስላል፡፡ ለአብነት ሲዳማ ዞን ክልል ሲሆን፣ ሐዋሳን ይዞ ይገነጠላል እንበል፡፡ የደቡብ ክልል ሐዋሳ ላይ ብዙ የመሠረተ ልማትና የቢሮ ግንባታዎችን አከናውኗል፡፡ በአጠቃላይ በደቡብ ክልል ውስጥ ለሚኖሩት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሲባል የተገነቡና ወጪ የተደረገባቸው ናቸው፡፡ ሲዳማ እነዚህን መሠረተ ልማትና ቢሮዎች ይዞ ከደቡብ ሲገነጠል ደቡብ ከእንደገና በሚመሠረተው ዋና ከተማ ላይ ከዓመታዊ በጀቱ እየቆነጠረ ለሌሎች የልማት ሥራዎች ማዋል የሚችለውን ለቢሮና ለመሳሰሉት ግንባታዎች ሊያውለው ነው፡፡ ሲዳማ ግን ከእነዚህ ተገላግሏል፡፡ ከዚህ አንፃር ደቡብ ሲጎዳ ሲዳማ ይጠቀማል ማለት ነው፡፡ ፌዴራል መንግሥቱም ለአዲሱ ክልል ወይም ለቀሪው የክልል መሆኛ ወጪ እንዲደጉም ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ አልተጣለበትም፡፡ በተጨማሪም ክልሉ የተበደረው ገንዘብ ቢኖርበትና በተለይም ብድሩ የዋለው (እንበልና) የሲዳማ ዞንን የሚጠቅም ተግባር ላይ ከሆነ ይህንን ብድር ከተገነጠለ በኋላ የመክፈል ወይም የመጋራት ግዴታ  ይኑርበት ወይም አይኑርበት የሚገልጽ ሕግ የለንም፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ክልሉ ሥልጣኑን እንደሚያስረክብ እንጂ ሌሎች ንብረትና ገንዘብን በተመለከተ የገለጸው ነገር የለም፡፡ እንበልና ክልሉ የተመሠረተው ጥር ወር ላይ ቢሆን እስከሚቀጥለው በጀት ዓመት መድረሻ ለዞን ከተመደበው ተጨማሪ ገንዘብና ሌሎች እንደተሽከርካሪ የመሳሰሉ ንብረቶች ስለሚያስፈልጉት የድርሻውን እንዴት እንደሚያገኝ ሕግ ሊኖር ይገባ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ልዩ ዞን ወይም ወረዳ በሚመሠረትበት ጊዜ ምን መሆን እንዳለበት የደቡብ ክልል ያወጣውን ሕግ እንይ፡፡ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግሥት የብሔረሰቦች ምክር ቤትን ለማጠናከርና ሥልጣንና ተግባሩን ለመዘርዘር የወጣው አዋጅ ቁጥር 60/1995 በዝርዝር ባያብራራውም፣ በድምፅ ውሳኔው መሠረት ለብቻቸው ተለይተው ራሳቸውን ማስተዳደር የሚጀምሩት ብሔረሰቦች ቀድሞ ከነበሩበት ዞን ወይም ወረዳ ፍትሐዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል ሊያደርጉ እንደሚችሉ አስቀምጧል፡፡ በፌዴራሉ ሕግ ክልል ሲመሠርቱ ስለንብረት ክፍፍል የረሳውንና ያልተቀመጠውን፣ በደቡብ ክልል ውስጥ ዞንና ወረዳ (ልዩም ይሁን አይሁን) ሲመሠርቱ የንብረት ክፍፍል እንዲደረግ ያስቀምጥና ስለተግባራዊነቱም የብሔረሰቦች ምክር ቤት እንደሚከታተል ይህ አዋጅ በአንቀጽ 26 ገልጾታል፡፡

ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ወይም በሌላ ሕግ እልባት መስጠት ከግጭት ይገላግላል፡፡ የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ እያሰቡ ማውጣት እንዳይሆን እንጂ፡፡ ሌላው ሕገ መንግሥቱ ክልሉ ለአዲሱ ክልል ‹‹ሥልጣኑን ሲያስረክብ›› የሚል አገላለጽ ከመጠቀም ውጭ በምን ያህል ጊዜ ማስረከብ እንዳለበትም አይገልጽም፡፡ ድምፀ ውሳኔው ከተከናወነ በኋላ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ የሥልጣን ርክክብ መከናወን አለበት? የሚለው ጉዳይ አልተመለሰም፡፡ ይህም ሌላው በሕግ መቀመጥና መታወቅ ያለበትና የነበረበት ጉዳይ ነው፡፡

ከክልል ምሥረታ ጋር በተያያዘ ሌሎች ሦስት ጭብጦችን እናንሳና ሐተታችንን እንቋጭ፡፡ የመጀመርያው፣ ጠያቂው ሕዝብ ስንት መሆን አለበት? ሁለተኛው፣ ክልል ምሥረታ ውድ ነውና የጠየቀው ሁሉ ሊፈቀድለት ይችላል ወ? ሦስተኛው፣ ድንበር ማስመርና መለየትን የሚመለከት ነው፡፡ ከላይ በተጠቀሰው አዋጅ አንቀጽ 21(1) መሠረት የራስን ዕድል በራስ መወሰን ጥያቄ (መገንጠልንም ክልል መመሥረትንም የሚያካትት ስለሆነ) ከብሔረሰቡ አምስት በመቶ የሚሆነው ስም፣ ፊርማና አድራሻ ተገልጾ፣ እንደነገሩ ሁኔታ ደግሞ ጥያቄውን ባቀረበው መስተዳድር ማኅተም ማድረግንም ሊጨምር እንደሚችል አክሎበታል፡፡ የሲዳማ ሕዝብ ሦስት ሚሊዮን ገደማ ነው ቢባል  200 ሺሕ ሕዝብ ስም፣ ፊርማና አድራሻ ተገልጾ መቅረብ አለበት ማለት ነው፡፡ ክፋቱ ደግሞ ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱትን እንኳን አልተዋቸውም፡፡ ፐርሰንቱ ላይ ይታሰባሉ፡፡ ነገር ግን ከጠያቂዎቹ ውስጥ ሊካተቱ አይችሉም፡፡ ስማቸው አይጻፍም፡፡ አይፈርሙምም፡፡ ይኼም ቢስተካከል ጥሩ ይመስላል፡፡ የማይፈርሙን፣ ስማቸው የማይጻፍን ሥሌት ውስጥ ማስገባት ምክንታዊ አይደለም፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ግልጽ መሆን ያለበት ሌላው ጣጣ፣ ቁጥሩም ሆነ ፊርማው የሚሰላውና የሚፈረመው በዚያው አካባቢ ከሚኖረው ከብሔሩ አባላት ብቻ ነው ወይስ በሌላ ቦታና አካባቢም የሚኖረውን ይጨምራል የሚለው ነው? ይህም ቢሆን እልባት ማግኘት አለበት፡፡

ሁለተኛው ጭብጥ ደግሞ እንደሚታወቀው ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በማናቸውም ጊዜ ክልል የመመሥረት ሕገ መንግሥታዊ የሆነ መብት አላቸው፡፡ ነገር ግን አገራችን ከሰማኒያ በላይ ክልል የማቋቋም አቅም አለን ወይ? እንኳን ክልልና ወረዳና ዞን መቋቋምም ከወጭ አንፃር ከባድ ነው፡፡ በ1999ኙ የሕዝብ ቆጠራ ውጤት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ50 በላይ የሚሆኑት ብሔረሰቦች ቁጥራቸው ከ100,000 በታች ሲሆኑ 21ዱ ደግሞ ከ10,000 በታች ናቸው፡፡ ለቀበሌና ለወረዳ የመሳሰሉት አስፈላጊ የሆኑ ተቋማትንስ መቋቋም ይቻላልን? የበጀት፣ የሰው ኃይልና የመሳሰሉትን ፍላጎቶች መሸፈን መቻሉ አጠራጣሪ ነው፡፡ መተግበር የማይቻል መብት ውሎ አድሮ ቅያሜ ማምጣቱ አይቀርም፡፡

ሦስተኛው ጭብጥ የክልሎችን ድንበር ይመለከታል፡፡ አሁን ላሉት የተወሰኑ ክልሎች ለድንበሮቻቸው በአግባቡ ዱካ አልተበጀላቸውም፡፡ በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሚያ፣ በደቡብና በኦሮሚያ፣ በአማራና በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ወዘተ. የድንበር ጭቅጭቁ ወይም ይገባኛል ጥያቄው አላለቀም፡፡ በየጊዜው የሚያገረሹ የድንበር ግጭቶች አሉ፡፡ ምክንያታቸው የተለያየ ሊሆን ቢችልም የግጭቱ መኖር ግን ሀቅ ነው፡፡ እነዚህ ድንበሮች ተለይተው መካለል አለባቸው፡፡ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መካከል በተወሰኑ ወረዳዎች እንደተደረገው ድንበሩ መለየት አለበት፡፡ ችግሩ የሚከፋውና ግጭቱም ላይበርድ የሚችለው የመገንጠል ጥያቄ ከተነሳ ነው፡፡ በሰላሙ ወይም በአማኑ ቀን ያበጀነው ለክፉ ቀንም ይረዳል፡፡ ድንበር ማካለል ያው ውል መዋዋል ማለት ነው፡፡ ውል ደግሞ ሰላምን ያበዛል፣ ፍቅርን ያጠነክራል እንጂ አያጣላም፡፡ ‹‹ችካል ተነቃይ ነው፣ ወረቀት ተቀዳጅ ነው በሰላም በመተማመን ከኖርን በቂ ነው›› የሚለው አይበቃንም፡፡

‹‹ፊርማና ወረቀት ቀሪ ነው ተቀዳጅ፣

መተማመን ብቻ ይበቃል ለወዳጅ፤››

የሚለው የጥንት ዘፈን ለክልልና ለአገሮች ይቅርና ለሁለት ጓደኛሞች ወይም ባለትዳሮች እንኳን በቂ አይደለም፡፡ ስለሆነም፡

‹‹ፊርማና ወረቀት ቢሆንም ተቀዳጅ

መተማመን ብቻ አይበቃም ለወዳጅ፡፡››

በማለት ድንበራችንን አሰማምረን መጠበቅ አለብን፡፡ መገንጠል ካልመጣ እሰየው ከመጣ ደግሞ አደጋና ግጭትን የሚቀንሱ ዘዴዎችን ቀድመን ሥራ ላይ ማዋል ይበጀናል፡፡ መገንጠል ሲመጣ ‹‹በያዝከው እርጋ›› (Uti Possidetis Juris) የሚለው ዓለም አቀፋዊ መርሕ ሥራ ላይ ለማዋል የያዝነውን ቀድመን መለየት ተገቢ ነው፡፡ ነገሩ ለክልልም ይሠራል፡፡ በፌዴራላዊ ሥርዓት ማዕከላዊው መንግሥት ለአስተዳደር እንዲመቸው በማሰብ የሚወስነው የአስተዳደር ወሰን አይኖርም፡፡ ከዚያ ያለፈ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...