Wednesday, September 28, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  ‹‹የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ማንም ኢትዮጵያዊ የሚዘለው ጉዳይ አይደለም››

  ያዕቆብ ኃይለ ማርያም (ዶ/ር)፣ የሕግ ባለሙያና ፖለቲከኛ

  ያዕቆብ ኃይለ ማርያም (ዶ/ር) ታዋቂ የሕግ ምሁር፣ ፖለቲከኛና ጠበቃ ናቸው፡፡ በናይጄሪያና በካሜሩን መካከል ተከስቶ የነበረውን የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ለመፍታት በሥፍራው ከተሰማሩ ባለሙያዎች አንዱ ነበሩ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሩዋንዳውን የዘር ጭፍጨፋ ተከትሎ በተቋቋመው ችሎት ውስጥ በዳኝነት ከተሳተፉ ባለሙያዎች አንዱ ናቸው፡፡ ‹‹አሰብ የማን ናት?›› የሚል መጽሐፍ ደራሲም ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ ግንኙነቶች፣ በባህር በር ጥያቄና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ጽሑፎች አቅርበዋል፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ ለዓመታት የዘለቀውን ሰላምም ጦርነትም የሌለበትን የሁለቱን አገሮች ሁኔታ ለመቅረፍ ለመደራደር ፈቃደኛነታቸውን አሳይተዋል፡፡ በሁለቱ አገሮች አዲስ የመደራደር ፍላጎት፣ በአልጀርሱ ስምምነትና በአሰብ ጉዳይ ላይ ከነአምን አሸናፊ ጋር ያደረጉት ቆይታ የሚከተለውን ይመስላል፡፡  

  ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያና ኤርትራ በድንበር ጉዳይ ወደ ጦርነት በመግባታቸው በበርካታ ዜጎች ሕይወት መጥፋት በኋላ የአልጀርስ ስምምነት ተፈርሞ ነበር፡፡ በአጠቃላይ የአልጀርሱን ስምምነት ታሪካዊ ዳራና በሁለቱ አገሮች ላይ ያስከተለውን ተፅዕኖ ወደኋላ መለስ ብለው እንዴት ይገመግሙታል?

  ዶ/ር ያዕቆብ፡- ስምምነቱ በእውነት ሁለቱም አገሮች ወይም የሁለቱ አገሮች መሪዎች አምነውበት የመጣ ነገር አይደለም፡፡ ሁኔታው አስገድዷቸዋል፡፡ የደረሱበትም ስምምነት ወንድምነትን የሚያጠናክር ወይም ደግሞ ለወደፊቱ ሰላም የሚያረጋግጥ ዓይነት አይደለም፡፡ እነዚህ ሁለት ወንድም ሕዝብና አንድ አገር ከዚያ በላይ መሄድ ነበረባቸው፡፡ ያኔ እርግጥ ነው ጦርነት ተካሂዷል፡፡ ፍፁም አላስፈላጊ ጦርነት ነበር፡፡ የአፍሪካ ኅብረት በላከው መልዕክተኛ መሠረት ጦርነቱን የቀሰቀሰችው ኤርትራ ነች፡፡ ከዚያ በኋላ ጦርነቱ በኢትዮጵያ አሸናፊነት ተደመደመ፡፡ ማንኛውም ጦርነት ሲያከትም ዞሮ ዞሮ ወደ ክብ ጠረጴዛ ይኬዳል፡፡ እንግሊዝና ፈረንሣይ ለመቶ ዓመታት ተዋግተው መጨረሻ በጠረጴዛ ዙሪያ ነው ለችግሩ ዕልባት ያደረጉለት፡፡ ጦርነት የትም እንደማያደርስ ይህ ራሱ አንድ መልካም አብነት ነው፡፡

  ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ሕዝብና የኤርትራ ሕዝብ ወንድማማች ነው፡፡ አብሮ የኖረ ሕዝብ ነው፡፡ ወደፊትም የግድ መተሳሰር ያለበት ሕዝብ ነበር፡፡ የአልጀርስ ስምምነት ተፈላጊውን ርቀት ባይሄድ እንኳን ጦርነት ማቆም መቻሉ አንድ ትልቅ ነገር ነበር፡፡ ከአልጀርስ የመጀመርያው ጦርነቱን ማቆም ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደ ድርድር ሄዱ፡፡ ያ ድርድር በሙሉ በጥሩ ሁኔታ አልሄደም፡፡ መጀመርያውኑ ድርድሩ መከናወን የነበረበት በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንጂ፣ ገንዘብ ወደሚከፈላቸው የድንበር ኮሚሽን መሆን አልነበረበትም፡፡ የድንበር ኮሚሽኑ ደግሞ በጣም በችኮላ በስምንት ወራት ውስጥ አጠናቀቀ፡፡ ነገር ግን ይኼን የመሳሰለ ጉዳይ ብዙ ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ለምሳሌ የካሜሩንና የናይጄሪያ የድንበር ጉዳይ እኔ ራሴ የሕግ አማካሪ ሆኜ የሠራሁበት ነበር፡፡ የተጠናቀቀውም በ12 ዓመት ነበር፡፡ የአልጀርስ ስምምነት ብዙ ድክመት የነበረው ነው፡፡ ኢትዮጵያም በአግባቡ አልተወከለችም፡፡ በዚህም የተነሳ ብዙ ብዙ የኢትዮጵያ ጥቅሞችና መብቶች ዝም ብለው ተዘለው የታለፉ አሉ፡፡

  ሪፖርተር፡- እርስዎም ከላይ እንደገለጹት ሁሉ ሌሎች ምሁራንም የኢትዮጵያን በአግባቡ አለመወከል ይጠቅሳሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ በአግባቡ ሳትወከል የአልጀርሱን ስምምነት እንድትፈርም ያደረጓት ገፊ ምክንያቶች ምን ነበሩ?

  ዶ/ር ያዕቆብ፡- እንግዲህ ገፊ ምክንያቶች መካከል ከሆኑት አንዱ የውጭ ኃይል ነበር፡፡ አሜሪካኖች በዚህ ነገር ላይ እጃቸውን አስግብተው ነበር፡፡ ጦርነት ቆሞ ወደ ስምምነት መሄድ አለባችሁ የሚለው የአሜሪካኖች ግፊት ነበር፡፡ ደግሞም መሪዎቹም በጊዜው የታያቸው ይኼው ነበር፡፡ ከዚያ አልፈው መሄድ እንደማይችሉ የተገነዘቡት ይመስለኛል፡፡ ወይም ደግሞ በመሪዎቹ መካከል ከዚያ አልፎ መሄድ የሚፈልጉ አልነበሩም፡፡ በሁለቱም በኩል ተኩስ ይቆማል፣ የድንበር ኮሚሽን ይቋቋማል፡፡ የድንበር ኮሚሽኑ የሰጠውን ውሳኔ እናየዋለን በሚል ነው የደመደሙት፡፡ ሕዝብ ተማክሮበት፣ በመስኩ ዕውቀት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ተነጋግረውበትና ጊዜ ወስዶ የተደረገ አልነበረም፡፡ ሕዝብ ምንም ሳያውቅ ድንገት የአልጀርስ ስምምነት ተደረገ ነው የተባለው፡፡ ፓርላማው እንኳን የመከረበት ጉዳይ አልነበረም፡፡ በወቅቱ እርግጥ ፓርላማው የአልጀርስ ስምምነትን ተቀብሎ አፅድቋል፡፡ ግን ሰፊ ምክክር ተደርጎበት ይህን ያህል ርቀት በድርድሩ እንሄዳለን ያለበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ነገሩ እንዲያው የይድረስ ይድረስና የይምሰል ዓይነት ነገር ነበር የሆነው፡፡

  ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ በአግባቡ አልተወከለችም ሲባል ምን ማለት ነው? እንዴትስ ነው መወከል የነበረባት? ምንስ መጠየቅ ትችል ነበር?

  ዶ/ር ያዕቆብ፡- ኢትዮጵያ ልትጠይቃቸው የምትችለው ብዙ ነገሮች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ጦርነቱ ሲደመደም ኢትዮጵያ እስከ ደቀመሃሪ ድረስ ዘልቃ ገብታ ነበር ነው የሚባለው፡፡ ደቀመሃሪ ከአስመራ 50 ኪሎ ሜትር ነው የሚርቀው፡፡ በሌሎች አገሮች እንደተደረጉ ጦርነቶች አንድ ኃይል ሲያሸንፍ ተኩስ ይቁም ይባላል፡፡ ግን ባለህበት ዕርጋ ነው የሚባለው፡፡ ባለበት ረግቶ ከዚያ በኋላ ድርድር ይጀመራል፡፡ ወደ ፊት ወረራ እንዳያጋጥም ለምናልባት ድንበር መካለል ይመጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አሸናፊ ሆኖ የወጣው አገር በጣም አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን አካባቢዎች ይዞ ሊቆይ ይችላል፡፡ የመጨረሻ ድርድር እስከሚደረግ ድረስም ይዞ ይቆያል፡፡ ኢትዮጵያ ግን ኤርትራ ግዛት ውስጥ ዘልቃ ከገባች በኋላ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ጦሩ እንዲመለስ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተመለሱ አሉ፡፡ ይህ በፍፁም ያልተለመደ ነገር ነው፡፡

  ለምሳሌ እስራኤልና ሶሪያ ጦርነት አድርገው በእስራኤል አሸናፊነት ሲደመደም በስምምነት የሶሪያን ግዛት ለቃ ስትወጣ የጎላን ኮረብታዎችን ግን አልለቅም አለች፡፡ ለምንድነው ይህን አልለቅም ያለችው? ወደፊት የሚደርስብኝን ጥቃት ለመከላከል ያስችለኛል በሚል ምክንያት ነበር፡፡ እስካሁንም ድረስ ይዛለች፡፡ ብዙም የተቃወማት የለም፡፡ ምክንያቱም ለመከላከል ያስፈልጋታል ከሚል እምነት ነው መሰለኝ፡፡ ወይም ደግሞ ከምዕራባውያን ጋር ባላት ቅርበት ምክንያት ይህን ሥፍራ አልለቀቀችም፡፡ ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት ነገር እንዳታደርግ ከመጀመርያውኑ የተበላሸ ነገር ነበር፡፡ ከዚያ ደግሞ ጦርነቱ እንደቆመ ወደ አልጀርስ አቀኑ፡፡ አልጀርስም የድርድሩ ቀጣና መሆን አልነበረበትም፡፡ የአልጄሪያ ፕሬዚዳንት አብዱልአዚዝ ቡተፍሊካ ኤርትራን ለማስገንጠል ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲኳትኑ የኖሩ ሰው ናቸው፡፡ አልጄሪያ የኢትዮጵያና የኤርትራን መለያየት በብዙ መድረክ ደክማ የሠራችበት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ወደዚያ አገር መሄድ አስፈላጊ አልነበረም፡፡ ሌሎች በርካታ አፍሪካ አገሮች አሉ፡፡ እዚያ ይደረግ ይችል ነበር፡፡

  በእርግጥ በዚያን ጊዜ ቡተፍሊካ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ነበሩ፡፡ ግን ይህ ጉዳይ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር የሚያገናኘው አይደለም፡፡ በሁለቱ መካከል የሚደረግ ድርድር እንጂ፡፡ በክርክሩም ውስጥ ብዙ የኢትዮጵያ ጥቅሞችን አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ በግልጽ መጥቀስ የሚቻለው ኢትዮጵያን የወከሉ ጠበቆች ፆረና የኢትዮጵያ ግዛት አይደለም ብለው ነው የተከራከሩት፡፡ ይህ በእውነት በአገር ክህደትም ሊስጠይቅ የሚያስችል ነው፡፡ የኢትየጵያ የባህር በር መብት ጉዳይ በፍፁም አልተነሳም፡፡ በስምምነቱ በሙሉ በተጻፈው ሁሉ አሰብ የሚል ቃል አንድም ቦታ የለም፡፡ ወይም የኢትዮጵያ የባህር በር መብት የሚል ቃል አንድም ቦታ የለም፡፡ ይህ መነሳትና ለድርድር መቅረብ የነበረበት ጉዳይ ነው፡፡ ብዙ አገሮችን በምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡

  ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የቬርሳይ ስምምነትን የአወሮፓ አገሮች ሲፈራረሙ ፖላንድ ወደብ አልባ ነበረች፡፡ እናም ከጀርመን መተላለፊያ (ኮሪዶር) ተሰጥቷት ወደብ እንድታገኝ ተደረገ፡፡ አፍሪካ ውስጥም ለምሳሌ ኮንጎ ኪንሻሳና ኮንጎ ብራዛቪልን ማንሳት ይቻላል፡፡ ኮንጎ ኪንሻሳ የቤልጂም ግዛት ነበር፡፡ ብራዛቪል ደግሞ የፈረንሣዮች ነበር፡፡ ኮንጎ ብራዛቪል ወደብ አልነበረውም፡፡ ሁለቱም ተስማምተው ከኮንጎ ኪንሻሳ የተወሰነ መሬት ወስደው ኮንጎ ብራዛቪል ወደ ባህር እንድትዘልቅ ተደረገ፡፡ ይህ ከመጀመርው ኢትዮጵያ ውስጥ መነሳት የነበረባት ጉዳይ ነው፡፡ ለድርድርና ለስምምነት መቅረብ ነበረበት፡፡ ለኢትዮጵያ እንዲያውም ትልቁና አንገብጋቢው ጉዳይ እሱ ነው፡፡ የወደብ ጥያቄ ድርድሩ ላይ አለመነሳቱ ለወደፊቱም የሰላም ጠንቅ ሊሆን የሚችል ነገር ነው፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ነገር ኢትዮጵያ በዓለም ወደብ አልባ ከሚባሉ አገሮች ትልቋ ነች፡፡ ሁለተኛዋ ኡጋንዳ ስትሆን የኢትዮጵያን አንድ ሦስተኛ ሕዝብ ነው ያላት፡፡ በኢትዮጵያ ወሰንና በባህሩ ጠርዝ መካከል ያለው ርቀት ከ60 ኪሎ ሜትር ያነሰ ነው፡፡ በዓለም ትንሹ ርቀት የሚባለውም ይኼው ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- ከላይ የኤርትራና የኢትዮጵያ ስምምነት በአልጄሪያ መፈረም የለበትም ነበር ብለዋል፡፡ የአልጄርያ ፕሬዚዳንት አብዱልአዚዝ ቡተፍሊካንም ኢትዮጵያና ኤርትራን ለመነጣጠል ዕድሜ ልካቸውን ሲሠሩ የኖሩ ናቸው ይሏቸዋል፡፡ የዚህ ዋነኛ ምክንያት ምንድነው?

  ዶ/ር ያዕቆብ፡- መቼም ዓረቦች ብዙ ጥረቶች አድርገዋል፡፡ ኤርትራ በፌዴሬሽን ስትቀላቀል ግብፆች የእኛ ነች ብለው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ዓረቦች ብዙ ጊዜ ኤርትራን ወደ እነርሱ የማጠፍ ዝንባሌ አላቸው፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ በደም፣ በቋንቋ በባህል መተሳሰሩን ብዙም ዋጋ አይሰጡትም፡፡ ዓረቦች ብዙ ጊዜ ኤርትራን ወደ ዓረብ አገር ለማጠፍና ቀይ ባህርን የዓረብ ሐይቅ ለማድረግ ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡ አሁን ከሞላ ጎደል ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ ኤርትራ አሁን የዓረብ ሊግ ውስጥ የታዛቢነት ሚና አላት፡፡ አሁን የዓረብ ሊግ አገሮች ቀይ ባህርን ይቆጣጠራሉ ማለት ይቻላል፡፡ ጂቡቲ አባል ነች፡፡

  ሪፖርተር፡- ወደ አሰብ ጉዳይ ልመልስዎትና የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአልጀርሱን ስምምነት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ እንደሚቀበል ሲገልጽ፣ ብዙዎች ባድመን ከሰጠን አሰብ ይመለስልን የሚል አስተያየት ሲሰጡ ተስተውሏል፡፡ ከሕግ አንፃር በአልጀርሱ ስምምነት መሠረት አሰብን የመጠየቅ መብት ይኖራል?

  ዶ/ር ያዕቆብ፡- ለአሰብ ሕጋዊ መብት የሚሰጡን አንዳንድ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ በ1964 ዓ.ም. የአፍሪካ መሪዎች ካይሮ ላይ ተሰብስበው ሁሉንም አፍሪካዊ አገር የሚገዛ ሕግ አውጥተው ነበር፡፡ ይህም ሕግ ምንድነው የሚለው? የአፍሪካ አገሮች ነፃ በሚወጡበት ጊዜ ያንን የያዙትን ግዛት ብቻ ይዘው ነፃ እንዲወጡ የሚል ነበር፡፡ ኤርትራ ነፃ በወጣችበት ጊዜ አሰብ የኤርትራ አካል አልነበረችም፡፡ ራስ ገዝ ተብላ ለብቻዋ የቆመች ነበረች፡፡ አሰብ ደግሞ ከኤርትራ በብዙ የምትለይበት ነገር አለ፡፡ አንደኛ ሕዝቡ አፋር ነው፡፡ ዘጠና ከመቶ አፋር የሚኖረው ኢትየጵያ ውስጥ ነው፡፡ ከዚያ ደግሞ አሰብ ከኤርትራ ጋር የተቀላቀለው በተለየ ሁኔታ ነው፡፡ መጀመርያ የሩቢታኖ የሚባል የጣሊያን ኩባንያ ወደቡን ገዛው፡፡ የሸጠለትም ሡልጣን ኢብራሒም የሚባል የአፋር ባላባት ነው፡፡ አፄ ምኒልክም አላወቁም፡፡ በዚያ ጊዜ ግንኙነቱ የላላ ነው፡፡ ግብር በየዓመቱ አምጥቶ እስከከፈለ ድረስ ሌላ ጥያቄም አልነበረም፡፡ አፄ ምኒልክ ሳያውቁ አሰብ ተሸጠ፡፡ ከ15 ዓመታት በኋላ ኤርትራ ስትመሠረት ጣሊያኖች አሰብን ከኤርትራ ጋር አቀላቀሉት፡፡ በታሪክም ቢሆን ኤርትራና አሰብ የተለያዩ ናቸው፡፡ ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ድርድር መደረግ ይኖርበታል፡፡ በእርግጥ የአልጀርስን ስምምነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንፈጽማለን ሲሉ ድርድሩ በፍፁም የሚቀር ነገር አይደለም፡፡ ሊቀርም አይችልም፡፡

  ሪፖርተር፡- የኤርትራ መንግሥት ከኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም ጥሪ ከቀረበለት በኋላ በኢትዮጵያ ያለውን ለውጥ የሚገመግም የልዑካን ቡድን ወደ አዲስ አበባ እንደሚልክ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ይፋ አድርጓል፡፡ የኤርትራ መንግሥት የአቋም ለውጥ እንዲያደረግ ያደረገው ምክንያት ምን ይመስልዎታል?

  ዶ/ር ያዕቆብ፡- ይህ የአቋም ለውጥ የመጣው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው ዶ/ር ዓብይ ለሰላም፣ ለመልካም ጉርብትና፣ ለትብብር ባላቸው ጉጉት የተቀሰቀሰ ነገር ነው፡፡ ከዚህ በፊት ስምምነቱ እንደወረደ መፈጸም አለበት፡፡ ስብሰባም፣ ድርድርም፣ መገናኘትም አያስፈልግም ነበር የሚባለው፡፡ አሁን አቶ ኢሳያስ እስቲ እንወያይ፣ እንገናኝ ብለው ሰው መላካቸው የሚመሠገንና በጉጉት የሚፈለግ ነገር ነው፡፡ አቶ ኢሳያስ ሰው ሲልኩ ለሽርሽር አይደለም፡፡ አንዳንድ ነገሮችን ለመነጋገር ነው፡፡ እዚህ ደረጃ መድረስ ትልቅ ዕርምጃ ነው፡፡ ምን ያህል እንደሚሄዱ ገና በሒደት የሚታይ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ተገናኝተው መወያየቱ የሰላም መጀመርያው ነው፡፡ ብዙ ርቀት እንደሚኬድ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ምናልባት በሒደት ወደ ፌዴሬሽንም ወደ ኮንፌዴሬሽንም መሄድ ይቻል ይሆናል፡፡ እስከዚያም ድረስ ባንሄድ እንኳን የኢትዮጵያ የባህር በር መብት መከበር አለበት፡፡

  ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶር) ከመጀመርያው ዕለት የፓርላማ ንግግራቸው አንስቶ የኤርትራን ጉዳይ መፍታት እንደሚሹ፣ ይህንንም በማድረግ ለሁለቱ ሕዝቦች ዘላቂ ሰላም ማምጣትና ወንድማማችነትን ማደስ እንደሚስፈልግ እንፅንኦት ሰጥተው ሲናገሩ ነበር፡፡ አሁን ጥያቄው በኤርትራ መንግሥት ተቀባይነት አግኝቶ ልዑካን ወደ አዲስ አበባ ሊመጡ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ጅማሮዎች የሚፈለገውንና የሚጠበቀውን ሰላምና ወንድማማችነትን መመለስ ይችላሉ?      

  ዶ/ር ያዕቆብ፡- እኔ ይቻላል ባይ ነኝ፡፡ በጣም ተስፋ የሚሰንቅ ነገር ነው፡፡ በእርግጥ አሁን በተጨባጭ የታየ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ተገናኝተው መነጋገር መቻላቸው አንድ ትልቅ ዕርምጃ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ብዙ የሚደራደሩባቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ብዙም አዳጋች የማይሆኑ፣ ለምሳሌ ለኤርትራውያን የኢትዮጵያን ገበያ ክፍት ማድረግ፡፡ የኤርትራ ዕቃ ያለ ታክስ ወደ ኢትዮጵያ ቢገባ፣ የኢትዮጵያም እንዲሁ፡፡ ሕዝቡ ያለ ቪዛ ወደ ኤርትራና ወደ ኢትዮጵያ መንቀሳቀስ ቢቻል፡፡ ከእነዚህ ነገሮች ቢጀመር ሌላው የወደብ ጥያቄ፣ ወሰን የማካለሉ ጥያቄ፣ ከዚያ በኋላ ሰላም፣ መግባባት፣ ወንድማማችነት ከተመሠረተ በኋላ ድርድሩ ቀላል ይሆናል፡፡ ይህንን ግን ለኤርትራውያኑ በግልጽ ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅነትና ወንድምነት ቢመሠረት የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆኑት ኤርትራውያን ናቸው፡፡

  ሪፖርተር፡- የሰላም ጥሪውን ተከትሎ ከኤርትራ የሚመጡ የልዑካን ቡድን አለ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ደግሞ በኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት ላይ የተለያዩ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ከወደብ፣ እንዲሁም ከባድመ ጋር በተያያዘ፡፡ እንደ አንድ የሕግ ባለሙያና ጉዳዩን በቅርብ ሲከታተል እንደነበረ ሰው፣ በልዑካን ቡድኑና በመንግሥት መካከል በሚኖረው ውይይት ላይ መነሳት ይኖርበታል የሚሉዋቸው በጣም ጠቃሚ ነጥቦች ምን ምን መሆን አለባቸው?

  ዶ/ር ያዕቆብ፡- ከእነዚህ ተደራዳሪዎች ጋር መነሳት ያለበት በጣም አንገብገባቢና ዋነኛ ጥያቄ የሚሆነው የኢትዮጵያ ወደ ባህር በር የመዝለቅ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ላይ ድርድርና ስምምነት መደረግ አለበት፡፡ ብዙ ዓይነት ስምምነት ሊኖር ይችላል፡፡ ምናልባት በኤርትራውያን በኩል ተቀባይነት ባይኖረውም፡፡ ግን በሐሳብ ደረጃ ሊቀርብ የሚችለው ከኢትዮጵያ የተወሰነ መሬት ቆርሶ ሰጥቶ በለውጡ ደግሞ አሰብን መጠቀም፡፡ ነገር ግን ይህ ተግባራዊ ላይሆን ይችላል፡፡ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው አሰብን የሁለቱም ሉዓላዊ ግዛት እንዲሆን ማድረግ፡፡ አሰብ የራሷ አስተዳደር ይኖራታል፡፡ ግን ሁለቱም አገሮች በእኩልነት እንዲጠቀሙት ማድረግ ሕዝቡንም ያቀራርባል፡፡ ለወደፊቱም ደግሞ ኢትዮጵያና ኤርትራ በኮንፌዴሬሽን ወይም በፌዴሬሽን እንዲተሳሰሩ ሊረዳ ይችላል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ማንም ኢትዮጵያዊ የሚዘለው ጉዳይ አይደለም፡፡ ዛሬ ባይነሳ ነገ መነሳቱ የማይቀር ነገር ነው፡፡

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ በተመድ ጉባዔ ‹‹የትግራይ መንግሥት›› በማለት ላደረጉት ንግግር ማስተካከያ እንዲደረግ ኢትዮጵያ ጠየቀች

  በስዊዘርላንድ ጄኔቭ እየተካሄደ በሚገኘው 51ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)...

  የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ሕገወጥ ገንዘብ አስተላላፊዎችን አስጠነቀቀ

  የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በሕገወጥ የገንዘብ ማስተላለፍ ድርጊት ተሰማርተዋል ያላቸው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  ኦፌኮ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ ስምንት አመራሮች እንደታሰሩበት አስታወቀ

  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለክልሉ ደብዳቤ ጽፏል የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ...

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ‹‹ነዳጅ በዋጋ ጭማሪ ምክንያት አቅርቦቱ ዝቅተኛ ስለሆነ አማራጮችን መፈለግ አለብን›› መንግሥቱ ከተማ (ፕሮፌሰር)፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ

  ከስድስት ወራት በፊት በሁለቱ የአውሮፓ አገሮች በሩሲያና በዩክሬን መካከል ጦርነት ሲጀመር፣ የዓለም ኢኮኖሚ እያገገመ ከነበረበት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተፅዕኖ ለመላቀቅ እየተፍጨረጨረ ነበር፡፡ ሆኖም ጦርነቱ የዓለም...

  ‹‹የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቢኖሩ ግጭቶች ላይከሰቱ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ይሆን ነበር›› አቶ ፋሲካው ሞላ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር

  የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ከአራት ዓመት በፊት ወደ ሥልጣን ከወጣ በኋላ ሪፎርም ካደረገባቸው የዴሞክራሲ ተቋማት መካከል ቀዳሚው የሲቪል ማኅበረሰብ ዘርፉን የሚመራው ባለሥልጣን...

  ‹‹በንግድ ሕጉ የተናጠል ክሶችን ማቋረጥ አንዱ ዓላማ ብክነትን ለማስቀረት ነው›› አቶ ፍቃዱ ጴጥሮስ፣ የሕግ ባለሙያ

  ኢትዮጵያ ከ60 ዓመታት በኋላ የንግድ ሕጓን አሻሽላለች፡፡ የተሻሻለው የንግድ ሕግ ሦስት መጻሕፍት ታትመው ሥራ ላይ ውለዋል፡፡ ይህ የንግድ ሕግ ኢትዮጵያ ከወቅቱ ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ...