Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአሜሪካ ዲፕሎማቶችና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ስለተወሰዱ ጅምር የለውጥ ዕርምጃዎች ይናገራሉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአሜሪካው የንግድ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ጉብኝት ይጠበቃል

በኢትዮጵያ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ የአሜሪካ ኩባንያዎችና ዲፕሎማቶች በመንግሥት እንደሚወሰዱ ይፋ የተደረጉ የለውጥ ዕርምጃዎች ተስፋ እንዳሳደሩባቸው ገለጹ፡፡

በአሜሪካ ኤምባሲ አዘጋጅነት የተሰናዳው የንግድ ውይይት ሐሙስ፣ ሰኔ 14 ቀን 2010 ዓ.ም. በተካሄደበት ወቅት እንደተገለጸው መንግሥት ይፋ ያደረጋቸው የለውጥ ዕርምጃዎች ለአሜሪካ ኩባንያዎች ብቻም ሳይሆን፣ ለግሉ ዘርፍ ማደግ የሚያስፈልጉና ሲጠበቁ የነበሩ መሆናቸውን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይነር አስታውቀዋል፡፡

የመንግሥት የለውጥ ዕርምጃ እንደሚደገፍ፣ አሜሪካ ለረጅም ጊዜም ሐሳብ ስታቀርብበት እንደነበር የጠቀሱት አምባሳደር ሬይነር፣ በኢኮኖሚውና በንግዱ መስክ የአሜካ ኩባንያዎች ተሳትፎን ሊያሻሽል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ በውይይቱ ወቅት ተሞክሯቸውን ያቀረቡት ጄኔራል ኤሌክትሪክ (ጂኢ)፣ ፒቪኤች ኮርፖሬሽንና ዳው ኬሚካል በኢትዮጵያ ወደፊት ስለሚታያቸው ተስፋና በአሁኑ ወቅት በሚያደርጉት የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ስለሚገጥማቸው ችግርም ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ የጂኢ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ዳንኤል ኃይሉ፣ ላለፉት 20 ዓመታት በኢትዮጵያ ሲንቀሳቀስ የቆየው ይህ ኩባንያ፣ በአቪዬሽን መስክ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላን ሞተሮችን በማቅረብ፣ በኤሌክትሪክ ኢነርጂ መስክ በተለይም በታላቁ ህዳሴ ግድብ የሁለት ኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ሥራ ላይ በመሳተፍ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ በአገልግሎት መስክ በተለይም በድንገተኛ ጥገና ለመተሐራ ስኳር ፋብሪካ የሰጠው የማሽን ጥገናን በምሳሌነት ከጠቀሷቸው ውስጥ ይገኝበታል፡፡ መተሐራ ስኳር ፋብሪካ በቅርቡ ባጋጠመው የጎርፍ አደጋ ሳቢያ ላለፉት 50 ዓመታት ሲገለገልበት የቆየው የስቲም ተርባይን ማሽን የደረሰበትን አደጋ በመጠገን በኩል ጂኢ ተሳትፏል፡፡

በታዳሽ ኃይሎች የቴክኖሎጂ አቅርቦት መስክ፣ በጤና መስክ በተለይም የተለያዩ የሕክምና መሣሪያዎችን በማስመጣት፣ የላቦራቶሪ አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም በኮርፖሬት ኃላፊነት በኩል ስለሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎችም አቶ ዳንኤል ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ይሁንና ኩባንያው እስካሁን በነበሩት ሒደቶች ከግዥና ከጨረታ ሥርዓት አኳያ ችግሮች እየገጠሙት እንደሚገኝ፣ በክፍያ መዘግየትና እንደ አብዛኛው የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያም የውጭ ምንዛሪ ችግር እየተፈታተነው እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ይህም ሆኖ መንግሥት የግልና የመንግሥት የሽርክና አሠራር ሕግ ማውጣቱ ኩባንያው ተሳትፎ ማድረግ በሚፈልግባቸው መስኮች ላይ ለሚኖረው እንቅስቃሴ ትልቅ ተስፋ እንደሰጡት ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በመንግሥት ወደ ግል እንደሚዛሩ ከተጠቀሱት ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ውስጥ ተሳትፎ የማድረግ ፍላጎት እንዳለውም አስውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግና ከ40 ዓመታት ወዲህም የራሱን የማምረቻ ፋብሪካ በዓለም ደረጃ ሲከፍት የመጀመርያው እንደሆነ ያስታወቀው የአልባሳት አምራቹ ፒቪኤችም በኢትዮጵያ ያለውን ተሞክሮ ያቀረበ ሌላኛው የአሜሪካ ኩባንያ ነው፡፡ ፒቪኤች የሐዋሳ ኢንዱትሪ ፓርክ እንዲመሠረት መንግሥትን በማማከርና በአካባቢ ላይ ብክለት የማያስከትል የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓት እንዲዘረጋ በማገዝ በኩል ሚና እንደነበረው የገለጹት፣ በኩባንያው የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ዳይሬክተር ማት በትለር ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2014 ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ፋብሪካ ለመክፈት የወሰነው ፒቪኤች በዓለም ላይ ካለው የምርት ግዥና አቅርቦት ድርሻ ውስጥ 20 በመቶውን ወደ አፍሪካ ለማዞር ካለው ፍላጎት በመነሳት ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡

በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በ20 የውጭ ኢንቨስተሮች የተያዙ 52 የማምረቻ ሼዶች እንደተገነቡና በአሁኑ ወቅትም 17 ሺሕ ዜጎች የሥራ ዕድል እንዳገኙ ያብራሩት ሚስተር በትለር፣ በዚህ ዓመት ከፓርኩ ወደ ውጭ የተላኩ ምርቶች የ100 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንዳስገኙም አስታውሰዋል፡፡ በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥም ከሐዋሳ ኢንዱስትሪ ወደ ውጭ የሚላከው ምርት 500 ሚሊዮን ዶላር ሊያስገኝ እንደሚችል፣ አሁን የተፈጠረው የሥራ ዕድልም ወደ 60 ሺሕ ከፍ እንደሚል፣ በፓርኩ እሴት ተጨምሮባቸው የሚላኩ ምርቶች በአሁኑ ወቅት 82 በመቶ እንደሆኑና በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥም መቶ በመቶ በኢትዮጵያ የተመረቱ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በመንግሥት ኃላፊዎች ሲገለጽ በነበረው መሠረት የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ በጀመረ በዓመቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስገኝ ይጠበቅ ነበር፡፡ የሥራ ዕድል የሚያገኙትም 60 ሺሕ እንደሚሆኑ መነገሩም አይዘነጋም፡፡ 

ከዚህ ባሻገር ግን በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ሠራተኞች የሚከፈላቸው ደመወዝና የመደራጀት መብት ላይ ጥያቄዎች ሲነሱ ቆይቷል፡፡ ፒቪኤች እንዲህ ያሉ ጉዳዮች በተገቢው መንገድ ምላሽ እንዲያገኙ ፍላጎቱ መሆኑን፣ ነገር ግን አብዛኞቹ ሠራተኞች ከገጠሩ ክፍል የመጡና ስለፋብሪካ ብቻም ሳይሆን ስለከተማ አኗኗር ግንዛቤው ሳይኖራቸው የሚመጡ በመሆኑ፣ ከ85 በመቶ በላይ ሴቶች በመሆናቸውም እንዲህ ባሉት ጉዳዮች ላይ በማተኮር በሠራተኞቹ ደኅንነትና በመኖሪያ አቅርቦት ሥራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን የፒቪኤች ተወካይ ገልጸው፣ ኩባንያው ዓለም አቀፍ ብራንድና ስም ያተረፈ ግዙፍ ተቋም በመሆኑ ከሠራተኞች ክፍያና የመደራጀት መብት አኳያ የሚነሳውን ቅሬታ የዓለም የሥራ ድርጅት (አይኤልኦ) በሚሳተፍበት አግባብ እንደሚፈታው አስታውቀዋል፡፡

ዳው ኬሚካልም የአሜሪካ ትልቁና ዕድሜ ጠገቡ ኩባንያ ነው፡፡ በኢትዮጵያ መንቀሳቀስ ከጀመረ ወዲህ በተለይ በጤፍ አመራረት ሒደት ላይ ፓላስ 45 የተሰኘ ፀረ አረም ምርት በማምረትና በማቅረብ እየሠራ እንደሚገኝ የኩባንያው ተጠሪ ሚስ ሴሬና ቻፔሌቲ ጠቅሰው፣ በቅርቡም ለውኃ ብክነት መፍትሔ የሚሆንና ለኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ እንዲመች ተደርጎ የተዘጋጀ ምርት ለማቅረብ ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ በአገሪቱ የኬሚካል ዘርፍ ላይ ሰፊ የግንዛቤ ችግር እንደሚታይም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

የአሜሪካ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያላቸውን እንቅስቃሴና የሚገጥማቸውን ፈታኝ ሁኔታ ለማወቅ በሚል መነሻ የአሜሪካው የንግድ መሥሪያ ቤት ምክትል ሚኒስትር ጊልበርት ካፕላን በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የአሜሪካ ኤምባሲ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የባለሥልጣኑ ጉበኝት በአሜሪካ ፕሬዚዳንት አማካሪ ምክር ቤት አባላት ልዑካን እንደሚታጀብ የተገለጸ ሲሆን፣ በርካታ ኩባንያዎችም አብረው እንደሚመጡ ተጠቅሷል፡፡ ሚስተር ካፕላን በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ከባለሥልጣናት ጋር እንደሚነጋገሩ፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴርና ከሌሎችም ተቋማት ኃላፊዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነቶችን እንደሚፈርሙ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች