Wednesday, March 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የመንግሥት ባንኮች ወደ ግል እንዲዛወሩ ፖሊሲም እንዲቀየር የሚጠይቁ ሐሳቦች 

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት በለውጥ ሒደት ላይ ስለመሆናቸው ከሰሞኑ የተደረጉ የአመራሮች ለውጦች ወይም ሽግሽጎች አመላካች እየሆኑ ነው፡፡ የፋይናንስ ተቋማቱ የአመራር ለውጥ በአገሪቱ ዋና ዋና የሚባሉ ባንኮች ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡

የአመራር ለውጡ ባንኮቹን በበላይነት ይመሩ በነበሩ ግለሰቦች መነሳት ላይ ሳይወሰን፣ የተቋማቱንም አሠራሮች በአዳዲስ ለመተካት እንደተፈለገ ይነገራል፡፡ ከሰሞኑ ከተደረጉ የአመራር ለውጦች ውስጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ለ13 ዓመታት ሲመሩ የነበሩትን አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በፋይናንስ አማካሪነት በመመደብ በቦታቸው አዲስ ገዥ ተተክቷል፡፡ ከዚህ ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ዋና ኢኮኖሚስት የነበሩትን ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ወደ ኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተርነት እንዲዛወሩ መደረጉ ይታወሳል፡፡

ይህ የአመራሮች ለውጥ በብሔራዊ ባንክ ውስጥ በሚገኙ ቁልፍ የሥራ መደቦችም ውስጥ ሊቀጥል እንደሚችል በርካቶች እምነቱ አላቸው፡፡ የብሔራዊ ባንክ ቦርድ አመራር አባላትም በአዲስ እንደሚተኩ ይጠበቃል፡፡ በዘርፉ ሥር ነቀል ለውጥ ሊደረግ እንደሚችል የሪፖርተር ምንጮች የገለጹ ሲሆን፣ ከብሔራዊ ባንክ በተጨማሪ የአገሪቱ ትልቁ ባንክ በሆነው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በኢትዮጵያ ልማት ባንክም የአመራሮች ለውጥ ይደረጋል ብለዋል፡፡   

      ሦስቱም ባንኮች አዲስ የቦርድ አመራሮች ተሰይመውላቸው ወደ ሥራ እንደሚገቡ የሚጠቁመው መረጃ፣ በአዲስ ቦርድ ሰብሰባዎች እንደሚመሩም አመላክቷል፡፡ የሪፖርተር ምንጮች እንደሚጠቅሱት፣ የልማት ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር የነበሩትና የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ከሚመሯቸው የቦርድ አባላት ጭምር በአዲስ አመራርና የቦርድ አሠራር ይተካሉ፡፡ በብሔራዊ ባንክ ገዥነት የተመደቡት የቀድሞው የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽር ይናገር ደሴ (ዶ/ር)፣ በቦርድ ሰብሳቢነት ሲመሩት የነበረውን የንግድ ባንክ ቦርድ ለተተኪው የቦርድ አመራር አባላት ያስረክባሉ፡፡

      በፋይናንስ ተቅማት ውስጥ እንደሚተገበር የሚጠበቀው ሌላው ለውጥ፣ የየባንኮቹ የቦርድ አባላት ምርጫ ሒደትን የተመለከተው አሠራር ነው፡፡ እስካሁን በነበረው አሠራር ለባንኮቹ የሚሰየሙት የቦርድ አባላት የሚውጣጡት ከተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ሲሠሩ የነበሩ ባለሥልጣናት ናቸው፡፡ በሌላ አገላለጽ አብዛኞቹ የባንኮቹ አመራሮች የፖለቲካ ሹመኞች ነበሩ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በወሰኑት መሠረት፣ የእስከዛሬው አሠራር ተቀይሮ ባንኮቹን በቦርድ የሚመሩት የመንግሥት ባለሥልጣናት ብቻ መሆናቸው እንደሚቀር ይጠበቃል፡፡

 ለሦስቱ የመንግሥት ባንኮች የሚመደቡት የቦርድ አመራር አባላት፣ ከፋይናንስ ሥራ ጋር ተዛማጅ ትምህርትና ልምድ ያካበቱ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን እንደሚካተቱበት ይነገራል፡፡ በተጨማሪም በቦርዶቹ ውስጥ የንግድ ኅብረተሰቡን የሚወክሉ ግለሰቦችም እንዲካተቱ የምንጮቻችን መረጃ ይጠቁማል፡፡ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከንግድ ምክር ቤቶች ከሚወከሉት ባሻገር በፋይናንስ መስክ ልምድ ያላቸውና ከመንግሥት መዋቅር ውጪ የሆኑ ባለሙያዎችም ታሳቢ ተደርገዋል፡፡ ይህ አዲስ ጅምር ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በዚህ ውጥን መሠረት ብቁ የተባሉ ባለሙያዎች ለቦርድ አባልነት እየተመለመሉ ስለመሆኑም ተሰምቷል፡፡ የባንኮቹ የቦርድ ሰብሳቢዎች ግን የመንግሥት ከፍተኛ  ባለሥልጣናት ይሆናሉ፡፡ እየተደረገ ያለው ለውጥ ብቻውን በዘርፉ የሚታየውን ውስብስብ ችግር እንደማይቀርፈው ቢታመንም፣ ችግሩን ለማቃለል የሚረዳ ዕርምጃ ስለመሆኑ በርካቶች ይስማሙበታል፡፡  

ለውጥና ተፈላጊው ዕርምጃ

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች፣ የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ኃላፊዎች መነሳት ብሎም በተቋማቱ ውስጥ በሚደረገው ለውጥ አስፈላጊነት ላይ ይስማማሉ፡፡ በተለይ ብሔራዊ ባንክ ላይ የተደረገውና ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው የአመራር ለውጥ ተገቢ እንደሆነ በብርቱ ከሚስማሙበት መካከል የባንክ ባለሙያውና ፖለቲከኛው አቶ ሙሼ ሰሙ አንዱ ናቸው፡፡

አቶ ሙሼ እንደሚገልጹት፣ በብሔራዊ ባንክ ላይ የተጀመረው ለውጥ ተገቢ ብቻም ሳይሆን፣ መደረግ ከነበረበት አኳያ የዘገየ ዕርምጃ ነው፡፡ ‹‹የሚመጡትን ሰዎች ባላውቅም ለዚህ ተቋም መሪነት የሚመጡትን ሰዎች የሚመርጠው አካል በአግባቡ ሊመርጣቸው ይገባል፡፡ በተለመደው መንገድ የሚመጡ መሆን የለባቸውም፡፡ ኢኮኖሚውን በደንብ ለማንቀሳቀስ የሚችሉ፣ አቅም፣ ዕውቀትና ግንዛቤ ያላቸው መሆን ይኖርባቸዋል፤›› ብለዋል፡፡ እስከዛሬ የነበሩት አመራሮች ‹‹አይቻልም፣ አይፈቀድም፣ አይሆንም፣ አይደረግም፤›› የሚል አመለካከት እንደነበራቸው የጠቀሱት አቶ ሙሼ፣ እንዲህ ያለውን አመለካከት የሚያራምድ አመራር እንዲለወጥ መደረጉን በብርቱ ይስማሙበታል፡፡

      ‹‹ለእኔ ብሔራዊ ባንክ እንደ አገር መከተል ያለበት ነገር የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲዳብር የውጭ ኢንቨስተሮች የሚመጡበት መንገድ መቀየስ እንጂ ልክ ጠመንጃ ይዞ በር ላይ እንደሚቆም ወታደር አትገቡም አትወጡም የሚል መሆን የለበትም፤›› ያሉት አቶ ሙሼ፣ ‹‹ገንዘብ፣ ካፒታል ወይም የውጭ ምንዛሪ ብሔር፣ ድንበር፣ ሃይማኖት የለውም፡፡ በተመቸው ቦታ ሁሉ ያለማንም ጠያቂ ይመጣል፤›› በማለት ሁኔታው ከተመቻቸለት ከውስጥም ከውጭም እየመጣ ያሰበውን ሠርቶና ከኢኮኖሚው የሚፈልገውን አግኝቶ፣ አገርን አሳድጎ ራሱን የሚጠቅምበት አግባብ እንደሚስፋፋ አብራርተዋል፡፡ ይሁንና ብሔራዊ ባንክ ለረዥም ጊዜ በዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ባለመቃኘቱ ሳቢያ ይጓዝበት የነበረው አሠራር ከሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም ብዙም ፈቅ እንደማይል ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡

      አቶ ሙሼ ማብራራታቸውን ቀጥለዋል፡፡ የፋይናንስ ተቋማቱ ሲከተሏቸው የቆዩት ፖሊሲዎች እግር ከወርች ጠፍረው የሚይዙና የማያፈናፍኑ ከመሆናቸው ባሻገር፣  የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ላይ ኃላፊነት የሚሰማው ብሔራዊ ባንክ እንጂ ሌላው ደንታ እንደሌለው ተደርጎ መታሰቡም የችግሮች መንስዔ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም የአመራሮቹ መለወጥ አማራጭ የሌለው ቢሆንም፣ ዋናው ግን የፖሊሲ ለውጥ ማድረጉ ላይ እንደሆነ ያምኑበታል፡፡

በፋይናንስ ዘርፍ አንጋፋ ባለሙያ የሆኑት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉም፣ ብሔራዊ ባንክ የግል ባንኮችን አስሮ የያዘ ተቋም ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡ ገንዘባቸውን አዋጥተው የመሠረቷቸውንና ያቋቋሟቸውን ባንኮች ለብሔራዊ ባንክ ፈላጭ ቆራጭነት አሳልፎ ለመስጠት ሲገደዱ የቆዩበትን የእስካሁኑ የብሔራዊ ባንክ አሠራር ላይ ያላቸውን ጠንካራ ትችት ሰንዝረዋል፡፡

‹‹የባንክ ፕሬዚዳንቶች ድምፅ የላቸውም፡፡ የቦርድ ዳይሬክተሮች ድምፅ የላቸውም፡፡ እኛ ባንክ አቋቁመን ለብሔራዊ ባንክ ማይክሮ ማኔጅመንት ማስረከብ ነው ሥራችን፤›› ያሉት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ የገዥው ባንክ አሠራር ሁሉ መለወጥ እንዳለበት ይስማማሉ፡፡ ‹‹ጥሩ ከባቢ አዘጋጅተህ ትቆጣጠራለህ፡፡ የሕዝብና የአገር ጥቅም እንዳይጎዳ መጀመርያ ባንኮችን ሊያሠራ የሚችል ከባቢ ሁኔታ፣ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ በሥራ ላይ መዋል አለበት፤›› ይላሉ፡፡

የብሔራዊ ባንክ አመራር መለወጡ አግባብ የመሆኑን ያህል፣ የቀድሞዎቹን ተክተው በተመደቡት ኃላፊዎች ላይ ግን አስተያየት ለመስጠት እንደሚቸገሩ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ይገልጻሉ፡፡ ለብሔራዊ ባንክ ገዥነት የተሾሙት ኃላፊ የተማሩት ትምህርት እንዲመሩት ከተሾሙበት ተቋም ጋር የማይገጣጠም መሆኑ ሥጋት ማጫር ጀምሯል፡፡

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ይናገር ደሴ (ዶ/ር)፣ የአካባቢ ጉዳዮችን ከኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በማዛመድ በሚያጠናው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ዘርፍ ወይም በኢንቫይሮመንታል ኢኮኖሚክስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ስለመሥራታቸው የሚጠቁመውን መረጃ በመንተራስ፣ ‹‹በእርግጥ የአገሪቱን ማክሮ ኢኮኖሚ የሚመራ ትልቅ ተቋም እንዴት ሊመሩት ይችላሉ?›› የሚለውን ጥያቄ አቶ ኢየሱስ ወርቅም አንስተዋል፡፡ ‹‹የሚፈለገውን ለውጥ በትክክል ማምጣት ስለመቻላቸው ተግባራቸውን መጠበቅ ግድ ይላል፤›› ብለዋል፡፡ የባንኩ ገዥ የትምህርት ዝግጅት ይሁን ቢባል እንኳ፣ ብርቱና ጉምቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ከሥር ሊያግዟቸው እንደሚገባ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

ለአቶ ኢየሱስ ወርቅ ትልቁ ነገር የሰዎች መለዋወጥ ሳይሆን፣ የፖሊሲ ለውጥ መሆኑን በመግለጽ ከአቶ ሙሼ ጋር ተመሳሳይ ሐሳብ ተጋርተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ስለጀመሯቸው የለውጥ እንቅስቃሴዎች የጠቀሱት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ በአሁኑ ወቅት ለሰዎች የኃላፊነት ቦታ ሊሰጣቸው የሚገባው በችሎታቸው እንጂ በፖለቲካ ታማኝነታቸው እንዳልሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸውን አመላክተው፣ በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ ግን ይህን መሠረት ያደረገ አካሄድ ታይቷል ወይ? በማለት መጠየቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

 ብሔራዊ ባንክን ሲመሩ የቆዩት አመራሮች በዘርፉ ዕውቀቱ ሊኖራቸው ቢችልም፣ ሥጋት ወይም ሪስክ መውሰድ ከሚጠይቁ ውሳኔዎች ጋር ለመጋፈጥ አለመፈለጋቸው በዘርፉ በርካታ ችግሮች እንዲታዩ ምክንያት እንደሆኑ አቶ ሙሼ ገልጸዋል፡፡ በእስካሁኑ የመንግሥት ኃላፊነት ቦታ ላይ የሚመደበው ሹመኛ ልማድ መሠረት ‹‹አለመሥራት ስለማያስጠይቅ፣ በአንፃሩ መሥራትና በመሥራት ሒደት ውስጥ የሚፈጠር ችግር ተጠያቂ ስለሚያደርግ፣ ሁልጊዜ አይቻልም አይሆንም ማለት እየቀናቸው ብሔራዊ ባንክ ብዙ መሥራት የነበረበትን ሥራ ሳይሠራ እንዲቆይ አድርገውታል፤›› ያሉት አቶ ሙሼ፣ ለአብነት የውጭ ምንዛሪ ችግርን ለማቃለል የሚያስችሉ አሠራሮችን ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ በመውሰድ አለመተግበሩን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ 

ብሔራዊ ባንክ በተወሰነ ደረጃ ገለልተኛና ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር መሆን እንዳለበት የገለጹት አቶ ኢየሱስ ወርቅ በበኩላቸው፣ የአገሪቱን ፊሲካልም ሆነ ማክሮ ኢኮኖሚ በሰፊው የሚያይ ተቋም በመሆኑ ለብሔራዊ ባንክ ውሳኔ የሚያስተላልፉት ፖለቲከኞች መሆን እንደሌለባቸው ያሳስባሉ፡፡ ውሳኔ ሰጪዎቹ ማክሮ ኢኮኖሚስቶች መሆን እንዳለባቸውም ይመክራሉ፡፡ ‹‹ኢኮኖሚያችን ገበያ መር እስከሆነ ድረስ ይህ ለውጥ አስፈላጊ ነው፡፡ ጠንካራ ማክሮ ኢኮኖሚስቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ለዘርፉ ብቃት ያላቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች አገሪቱ እንዳሏት የሚያምኑት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ በመስኩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ዙሪያ ካሉ ሰዎች መካከል እንዲሁም በጡረታ ከተገለሉት እንደ አቶ ግርማ ብሩ ያሉ ባለሙያዎች ሊመደቡ ይገባቸው እንደነበር በመግለጽ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የግል ባንኮችና የውድድር ሜዳው

ከግል ባንኮች አንፃር ብሔራዊ ባንክ ያወጣቸው በርካታ የመቆጣጠሪያ ሕጎች ትችት ሲያስነሱበት ቆይተዋል፡፡ የባንክ ባለሙያዎች አላላውስ እንዳሏቸው የሚጠቅሷቸው መመርያዎች መብዛት፣ የግል ባንኮች ኢኮኖሚው ውስጥ መጫወት የሚገባቸውን ሚና እንዳይጫወቱ ገድቧቸዋል በማለት ሲወቅሱት ቆይቷል፡፡ ለውጥ ይደረጋል ከተባለም የገዥው ባንክ ሕጎች መታየት እንዳለባቸውም እየተጠቆመ ነው፡፡ አቶ ሙሼም ሆኑ አቶ ኢየሱስ ወርቅ እንዲህ ያለውን አስተያየት ቢጋሩትም፣ አጽንኦት ሰጥተው የገለጹት ግን የብሔራዊ ባንክ የተቆጣጣሪነት ሚናው ወሳኝና አስፈላጊ እንደሆነ ነው፡፡

አቶ ሙሼ በተለይ የግል ባንኮች ላይ ቁጥጥር መደረጉ አግባብ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ባንኮች የሚያስተዳድሩት የሕዝብ ሀብት በመሆኑ፣ ይህ ሀብት እንዳይባክን ክትትል መደረጉ አግባብ ነው፤ ጥበቃም ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡ ‹‹ስህተቱ እግር ከወርች የሚያስርና የማያፈናፍን ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡ ስህተቱ የተዛባ የውድድር ገበያ  እንዲኖር ያደረጉ መመርያዎች መተግበራቸው ነው፤›› ያሉት አቶ ሙሼ፣ ይህንን በምሳሌ የሚያስረዱት ንግድ ባንክ በውድድር የገበያ ሥርዓት የማይመራ ተቋም መሆኑን በማውሳት ነው፡፡

አብዛኞቹ የመንግሥት ተቋማት የገንዘብ ዝውውራቸውን የሚያንቀሳቅሱት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል መሆኑ፣ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዛቸው የሚከፈላቸው በንግድ ባንክ በኩል መሆኑ፣ ቀበሌዎች ወረዳዎች ሳይቀሩ በመንግሥታዊው ባንክ በኩል ብቻ እንዲጠቀሙ መገደዳቸው፣ የውድድር ሜዳው ሆን ተብሎ እንዲዛባ ለመደረጉ ማሳያዎች ናቸው ይላሉ፡፡ በዚህ ሳይገታ ወደ ቻይና የሚረገው የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄደው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ብቻ መሆኑም የፋይናንስ ዘርፉ የፖሊሲ ለውጥ እንዲደረግበት ከሚያስገድዱ አሠራሮች ውስጥ ጥቂቶቹ እንደሆኑ አቶ ሙሼ ይገልጻሉ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ለመንግሥት አገልግሎቶች ማለትም ለኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ የሚፈጸመው በንግድ ባንክ በኩል እንዲሆንና ተጠቃሚዎችም በባንኩ የሒሳብ መዝገብ እንዲከፍቱ እየተደረገ መሆኑ ሁሉ፣ የግል ባንኮች በጋራ በፈረጠሩት ጥምረት እንዲህ ያለውን አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ባካሄዱበት ወቅት የተደረገ መሆኑ በዘርፉ የውድድር መንፈስ ላለመኖሩ ማሳያ ነው የሚሉት አቶ ሙሼ፣ የመንግሥትም ሆኑ የልማት ድርጅቶች ለውድድር ክፍት መሆን እንደሚገባቸው ያሳስባሉ፡፡ በእሳቸው እምነት የግል ባንኮችን የበለጠ የጎዳቸው የቁጥጥር መመርያዎች ሳይሆኑ፣ ተገቢነት ያለው ውድድር አለመኖሩ ነው፡፡ ‹‹የመንግሥት ተቋማት ባንኮችን ሊመርጡ የሚገባቸው በሚሰጧቸው የአገልግሎት ቅልጥፍና፣ በቀላሉ ተደራሽ በመሆናቸው፣ በሚፈጥሯቸው አዳዲስ አገልግሎቶች ተወዳድረው የድርሻቸውን በማንሳት ነው፤›› ብለዋል፡፡  

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአንድ ባንክ ከፍተኛ ኃላፊ፣ የመንግሥትና የግል በማለት የሚከፋፈለው አሠራር መቆም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ውድድር ለፍፁማዊነት የቀረበ አሠራር ለማምጣት አንዱ መገለጫ ነው የሚሉት እኚህ ኃላፊ፣ የመጫወቻ ሜዳውና የመጫወቻው ሕግ ለሁሉም እኩል መሆን እንዳለበት ይጠይቃሉ፡፡

የመወዳደሪያ ሜዳው አድሏዊ ነው ለሚለው ወቀሳ ማሳያ ሆኖ የሚቀርበው ሌላው ነጥብ፣ የግል ባንኮች ከሚሰጡት ብድር ላይ 27 በመቶ ቀንሰው ለቦንድ ግዥ እንዲያውሉ የሚስያስገድደው መመርያ ነው፡፡ ይህ መመርያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የማይመለከተው ሲሆን፣ የውጭ ምንዛሪን የሚመለከቱ አሠራሮችም የንግድ ባንክ ነፃ እንዲሆን የሚያደርጉ መመርያዎች ሲተገበሩ መቆየታቸው ነው፡፡ የግል ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ለደንበኞቻቸው ሲሰጡ እንዲያሳውቁት የሚያስገድድ መመርያ ቢያወጣም፣ ንግድ ባንክ ላይ እንዳይተገበር ማድረጉም ሌላው ፍትሐዊ የውድድር ሜዳ እንዳይኖር ያደረገበት ማሳያ ሆኖ ቀርቧል፡፡

አገሪቱ ወደ ነፃ ኢኮኖሚ ወይም ወደ ሊበራሊዜሽን እያቀናች ነው የሚል እምነት ያላቸው የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ለዚህ ዓይነት ሥርዓት የሚመጥን ፖሊሲ እንደሚያስፈልጋት በመግለጽ የኢንዱስትሪው የሰዎች መለዋወጥ ብቻ ለውጥ እንደማያመጣ ያስረዳሉ፡፡ የፋይናንስ ተቋማቱ ሊበራል ለሆነው የኢኮኖሚ ምኅዳር የሚያገለግል አቋምና ቁመና ሊኖራቸው እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንትን ከአሁኑ የበለጠ ለመሳብም ተስማሚ የፋይናንስ ፖሊሲዎች እንደሚያስፈልጉ ከወዲሁ እየተጠየቀ ነው፡፡

ለውጡና የቦንድ ግዥ መመርያው

ይህ ቀመር የተሠራው በብሔራዊ ባንክ ሲሆን፣ ዋነኛ ዓላማውም ከባንኮቹ በቦንድ ግዥ የሚሰባሰበው የ27 በመቶ ገንዘብ ወደ ልማት ባንክ እንዲዛወር በማድረግ የአገሪቱ ቁልፍ የልማት ሥራዎች ፋይናንስ እንዲደረጉበት ታስቦ ነው፡፡

ይህ መመርያ ከጅምሩ አከራክሯል፡፡ የግል ባንኮች ቀደም ሲል የሰባት በመቶ ወለድ እየከፈሉ ከደንበኞቻቸው የሚያሰባስቡትን ገንዘብ ለቦንድ ግዥው ሲያውሉ የሚያገኙት ግን የሦስት በመቶ ወለድ መሆኑ እየጎዳቸው ነው፡፡ ይህ መመርያ ውሎ አድሮ ባንኮችን ይጎዳቸዋል የሚለው ሥጋት ተንፀባርቋል፡፡ በእርግጥ በዚህ አሠራር ሳቢያ የተፈራውን ያህል ችግር ባይከሰትም፣ ባንኮች ከአሁኑም የበለጠ አትራፊ ሊያደርጋቸው የሚችል ከፍተኛ ገንዘባቸው በልማት ሰበብ ተይዞባቸዋል፡፡

ከዚህ መመርያ ጋር ተያይዞ አግባብ ያልሆነው ነገር ብለው አቶ ሙሼ የጠቀሱት አንኳር ነጥብ፣ የቦንድ ግዥውን ሲፈጽሙ የሚታሰብላቸው የወለድ ምጣኔ አነስተኛ መሆኑ ነው፡፡ ‹‹ንጥቂያ፣ ዘረፋ ነው›› ብለውታል፡፡ ሌላው የባንክ ባለሙያም ባንኮች ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣታቸው ግድ እንደሆነ ቢስማሙበትም፣ የግል ባንኮች 27 በመቶ ለቦንድ ግዥ የሚያውሉት ገንዘብ ዕውን ለሚፈለገው ዓላማ በትክክል እየዋለ ነው ወይ የሚል ጥያቄ እያስነሳ በመሆኑ መንግሥት ተገቢ ምላሽ ሊሰጥበት ይገባል ብለዋል፡፡

ለዚህ አባባላቸው ምክንያታቸውን የጠቀሱት ባለሙያው፣ የግል ባንኮች በ27 በመቶ የቦንድ ግዥ አምስት ዓመት በማስቆጠሩ ገንዘባቸውን ከወሰዱት ባንኮች ውጪ እ.ኤ.አ. እስከ ማርች 2018 ድረስ የተሰበሰበው ገንዘብ 67 ቢሊዮን ብር ቢደርስም፣ ልማት ባንክ እስከ ማርች 2018 ድረስ ያበደረው  ገንዘብ መጠን 31 ቢሊዮን ብር ብቻ በመሆኑ፣ ‹‹ቀሪው ገንዘብ የት ገባ?›› በማለት ይጠይቃሉ፡፡  የግል ባንኮች አገራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ቢሆንም እንዲህ ያለውን ክፍተት መንግሥት መመርመር እንደሚገባው አመላካች ስለመሆኑ ተብራርቷል፡፡

ብሔራዊ ባንክ የማክሮ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት ከዚህ ቀደም ይከተል በነበረው የአሠራር ሥልት መቀጠል እንደሌለበት የሚመክሩ ምሁራንና ባለሙዎች፣  እስካሁን የነበረው የውጭ ምንዛሪ ላይ የተመሠረተ አሠራር መቀየር እንዳለበት ይጠይቃሉ፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚው የሚመራበት ፖሊሲ ውጤት ስላላመጣና አገሪቱም በውጭ ምንዛሪ ድርቅ እንድትመታ በማድረጉ አዲስ ፖሊሲ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡ አንዲት አገር ከሥጋት ነፃ የሚያሰኛት የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችቷ ከዓመታዊ የገቢ ንግዷ ውስጥ ለሦስት ወር ግዥ የሚበቃ መጠባበቂያ ሲኖራት እንደሆነ ዓለም አቀፍ አሠራሮች ያሳያሉ፡፡

ከዚህ ሥሌት አንፃር የኢትዮጵያ የገቢ ንግድ መጠን 16 ቢሊዮን ዶላር በመሆኑ አገሪቱ ሊኖራት የሚገባው የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ መጠን ወደ 3.9 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ያለው ሁኔታ ለአንድ ወር ከሁለት ሳምንት የሚበቃ መጠባበቂያ እንዳለ የሚያሳይ በመሆኑ፣ የውጭ ምንዛሪ ድርቁን ለመቅረፍ የሚያስችል ፖሊሲ ቀርጾ ሥራ ላይ ማዋልና ለውጥ የሚያመጣ የገንዘብ ፖሊሲ መተግበር እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎች እያሳሰቡ ነው፡፡

የመንግሥት ባንኮች ወደ ግል መዛወርና የዳያስፖራው ሚና

በቅርቡ በመንግሥት ይዞታ ሥር ያሉ ግዙፍ ተቋማትን በከፊል ፕራይቬታይዝ ለማድረግ ተወስኗል፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም  ፕራይቬታይዝ መደረግ አለበት የሚሉ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነው፡፡

በንግድ ባንክ ሥር የተጠቀለለውን የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክን ወደ ግል ለማዛወር መንግሥት ጨረታ አውጥቶ እንደነበር በማስታወስ፣ ንግድ ባንክም እንደ ቴሌና እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ግል እንዲዛወር ቢወሰን ይጠቅማል በማለት የሚከራከሩ አሉ፡፡ አቶ ሙሼም ይህንን ሐሳብ አጥብቀው ይደግፋሉ፡፡ ‹‹መንግሥት ለፖሊሲ ማስፈጸሚያው ልማት ባንክ አለው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን መሸጥ አለበት፤›› ያሉት አቶ ሙሼ፣ ኢትዮጵያዊ ሁሉ አክሲዮን ገዝቶ የንግድ ባንክ ባለቤት እንዲሆን መደረግ እንዳለበት፣ ንግድ ባንክ ከመደበኛ ባንኮች የሚለየው ነገር እንደሌለውና የግሉ ዘርፍ ባለድርሻዎች እንደማንኛውም ባንክ ሊመሩት እንደሚችሉ ይናገራሉ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የፋይናንስ ዘርፉ ለዳያስፖራዎች መፈቀድ አለበት የሚሉ አስተያየቶች ይሰጣሉ፡፡ አቶ ኢየሱስ ወርቅም በዚህ ሐሳብ ላይ ምን መደረግ እንደሚገባው ጭምር ማብራሪያ ሲሰጡበት ቆይተዋል፡፡

ይበጃል ያሉትንም ሐሳብ ለመንግሥት እስከማቅረብ ደርሰዋል፡፡ ዳያስፖራው በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ እንዲሳተፍ ቢያንስ 20 በመቶውን የግል ባንኮች የባለአክሲዮንነት ድርሻ በውጭ ምንዛሪ እንዲገዙ ቢደረግ፣ አገሪቱ ያለባትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሊቀርፈው ከመቻሉ ባሻገር፣ የባንኮቹን አቅም ከፍ እንደሚያደርገው፣ ለውድድርም እንዲዘጋጁ እንደሚያደርጋቸው ሲያሳስቡ ከርመዋል፡፡ ችግሩ ግን እንዲህ ያሉትን ሐሳቦች አዳምጦ ለአገር የሚበጅ ነገር ለማድረግ አለመቻል ነው ብለዋል፡፡ ስለዚህ አሁን በፋይናንስ ተቋማት ፖሊሲ ዙሪያ ለውጥ ይደረጋል ከተባለ አዳዲስ ሐሳቦች እንዲቀርቡና እንዲሠራባቸው መደረግ ይኖርበታል ያሉት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ አገሪቱ ዓለም የሚተገብረውን ጠቃሚ አሠራር በመውሰድ መጠቀም እንደሚገባት መክረዋል፡፡ ‹‹ዛሬ ላለንበት ችግር የተዳረግነው የእኔ ሐሳብ ብቻ ትክክል ነው ብሎ ራስን አጥሮ በማስቀመጥ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ዳያስፖራውን ለውጭ ምንዛሪ ችግራችን ብቻ መፈለጉ ተገቢ እንዳልሆነ የገለጹት አቶ ሙሼ፣ ‹‹በአንድ በኩል መጥታችሁ ኢንቨስት አድርጉ እየተባሉ በሌላ በኩል ግን የውጭ ምንዛሪያችሁን ነው የምንፈልገው ማለት አይቻልም፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹ኢትዮጵዊ ናችሁ ብለህ ካመንክ፣ በማንኛውም ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደረጉ መፍቀድ ያስፈልጋል፡፡ እንደ ቴሌ፣ አየር መንገድ ላይ የውጭ አገር ዜጎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ፈቅዶ ባንክ ላይ ሲሆን ግን ኢንቨስት አታድርጉ ብሎ መከልከል የተምታታ አሠራር ነው፤›› በማለት ዳያስፖራዎች በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥም ኢንቨስት ሊያደርጉ እንደሚገባ ሞግተዋል፡፡

የባንኮች ውህደት

 የአገሪቱ የግል ባንኮች አቅም አነስተኛ ነው በሚለው ድምዳሜ በርካቶች  ይስማማሉ፡፡ 16ቱ የግል ባንኮች ያላቸው ካፒታል ተደምሮ ከ30 ቢሊዮን ብር አይዘልም፡፡ ጠንካራ የፋይናንስ ተቋማት እንዲኖሩ ከሚሰጡ አስተያየቶች መካከል፣ ባንኮች እንዲዋሃዱ ማድረግ የሚለው ተጠቃሽ ነው፡፡ እንደ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ያሉ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በባንኮች ውህደት ያምናሉ፡፡ በዚህ ዙሪያ ከዚህ ቀደም ለሪፖርተር ሰጥተውት በነበረው ማብራሪያ፣ ባንኮች ካላቸው አቅም አንፃር ተጣምረው ጠንካራ ባንክ መፍጠር አለባቸው ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ይህንን ሐሳብ በርካቶች ይጋሯቸዋል፡፡ በሌሎች አገሮችም የተለመደ ነው ይላሉ፡፡ አሁን ያሉት ባንኮች ተዋህደው አምስት ስድስት ባንክ ቢፈጠር ጠንካራ ተወዳዳሪ ባንኮች ይኖራሉ ብለው ነበር፡፡ ይህ ሐሳብ ሲያነጋገር የቆየ ሲሆን፣ የቀድሞው የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉም የባንኮች የካፒታል አቅም ወደሚፈለገው ደረጃ ካልደረሰ ባንኮችን ማዋሃዱ ግድ እንደሚሆን ለሪፖርተር ገልጸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

እንዲህ ያለው አመለካከት አሁንም በተለየ መልክ ይንፀባረቃል፡፡ አቶ ሙሼ ግን የባንኮች ውህደት በፍላጎት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት የሚል ጠንካራ አቋም አላቸው፡፡ በግዴታ ሊሆን አይችልም፡፡ እኔ ገንዘብ ኢንቨስት ያደረኩበት ባንክ ከሌላ ባንክ ጋር እንዲዋሃድ የእኔ ይሁንታ መኖር አለበት የሚሉት አቶ ሙሼ፣ ዝም ብሎ ተነስቶ በአዋጅ ከእገሌ ጋር ተዋሃድ ሊባል አይችልም፡፡

ሌላው ደግሞ ገበያው ፈቅዶላቸው በዚህም ተጨባጭ ሁኔታ መሠራት ከቻለ በግዳጅ ለምን እንዲዋሃዱ ይደረጋል? ገበያው ፈቅዶ ትርፋማ ሆነውና አዋጥቷቸው እየሠሩ በመሆኑ፣ ተዋሃዱ መባሉ ትርጉም የሌለው ነገር ስለመሆኑም ይጠቅሳሉ፡፡ የአሜሪካን ልምድ ያስታወሱት አቶ ሙሼ፣ በአብዛኛው አንድ አካባቢ አንድ ስቴት ላይ የሚሠራ ባንክ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ባንኮች የተለያየ ሥልት ቀይሰው እኔ የሚያዋጣኝ ከዚህ አካባቢ ብሠራ ነው ሊል ይችላል ምክንያቱም እንዳቅሙና ተጨባጭ ሁኔታው ነው የሚሠራው፡፡ ስለዚህ አስገድዶ ለማዋሃድ መሞከር አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡ ዛሬ እነዚህ የግል ባንኮች የቀጨጩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአቅሙ በላይ በመወጣጠሩ እንደሆነ በመግለጽ ገበያው ለሁሉም ክፍት ቢሆን ኖሮ ባንኮች ከፍተኛ ካፒታል ያላቸውና ብዙ ቅርንጫፎች ሊኖሯቸው ይችል ነበር፡፡ ስለዚህ በእኔ ገንዘብ ተዋሃዱ ማለት የኮማንድ ኢኮኖሚ ሥርዓት በመሆኑ በግድ ተዋሃዱ ማለቱ ተገቢነት የለውም ብለዋል፡፡

በአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክና በሚቆጣጠራቸው ባንኮች መካከል ሊኖር የሚገባው ግንኙነት የከዚህ ቀደሙ ዓይነት መሆን እንደሌለበትም ባለሙያዎቹ ገልጸዋል፡፡ በጥቅል ሲታይ ግን የአገሪቱ አሁን ካለችበት ኢኮኖሚያዊ ችግር በተለይም የውጭ ምንዛሪ ችግር አንዱ ምክንያት እስካሁን ሲሠራበት የነበረ ፖሊሲ በመሆኑ፣ ይህንን ፖሊሲ መቀየር የግድ ስለመሆኑም ያስረዳሉ፡፡ ኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉት የባንክ ሰዎችም የፖሊሲ ለውጡ አካል ተደርጎ አማራጭ የሚሆኑ አሠራሮች ካልተተከሉ አሁንም ችግሩ ሊቀጥል እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ በተናጠል ባለሙያዎቹ ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ የበለጠ የባንኮች ማኅበርም የፖሊሲ አመንጪ አካል እንዲሆን ራሱን ማጠንከር ይኖርበታል ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ በመሆን ለበርካታ ዓመትት ያገለገሉት አቶ ተክለ ወልድ፣ በፋይናንስ ጉዳዮች አማካሪነት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከተመደቡ በኋላ፣ ለሁሉም የፋይናንስ ተቋማት የስንብት ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡ አገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ በማድረግ በኩል ባንኮች በጋራ መሥራታቸው የተገኘ ውጤት መሆኑንም በመግለጽ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ ከተተኪው የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ ጋር ተባብረው እንዲሠሩም ለባንኮች አደራ ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች