Sunday, April 14, 2024

ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ አዲስ ምዕራፍ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. የጠቅላይ ሚኒትርነት ሥልጣኑን የተቀበሉት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በበዓለ ሲመታቸው ላይ ካሰሙት አነቃቂ ንግግሮችና ሐሳቦች መካከል በዓብይነት ከተነሱት ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የኤርትራን ጉዳይ የተመለከተ ነበር፡፡

በዕለቱ ንግግራቸው፣ ‹‹ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለዓመታት ሰፍኖ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃ ከልብ እንፈልጋለን፡፡ የበኩላችንንም እንወጣለን፡፡ በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩ የሁለቱ አገር ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል፣ ልዩነታችንን በውይይት ለመፍታት ያለንን ዝግጁነት እየገለጽኩ የኤርትራ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም እንዲወስድ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ፤›› የሚል መልዕክት ለኤርትራ መንግሥት ማስተላለፋቸው ይታወሳል፡፡

ከኢትዮጵያ በኩል እንዲህ ዓይነት የሰላም ጥሪዎችና የእንደራደር ጉትጎታዎች ላለፉት ዓመታት ወደ ኤርትራ ወገን ሲላኩ የነበረ ቢሆንም፣ ከኤርትራ ወገን የሚሰጠው ምላሽ ተመሳሳይ ነበር፡፡ ይህም የአልጀርሱ ስምምነት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የማይተገበር ከሆነ መነጋገርም ሆነ መደራደር የማይቻል ነው የሚል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን የሰላም ጥሪ ተከትሎም ከኤርትራ ወገን የተገኘው ምላሽ ተመሳሳይ ነበር፡፡ የሁለቱ አገሮችን ሰላምና ወንድማማችነትን ለመመለስ የሚቻለው፣ ኢትዮጵያ የአልጀርስ ስምምነትን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ስትፈጽም ብቻ መሆኑን፣ የሰላሙ ኳስ ያለው ኢትዮጵያ እግር ውስጥ ነው የሚል የተለመደው ምላሽ ከኤርትራ ወገን ተሰጠ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ ተከትሎ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ምን ሊመስል ይችላል? ሊደራደሩባቸው የሚችሉ ነጥቦች ምን ሊሆኑ ይችላሉ? ለሚሉ ጥያቄዎች፣ ሁለቱ አገሮች በመካከላቸው ሰላም ማስፈን ከቻሉ በአጠቃላይ ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምና መረጋጋት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ የሚገልጹ የተለያዩ ባለሙያዎች አስተያየቶች መሰንዘር ጀምረው ነበር፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ አዲስ ምዕራፍ

 

ነገር ግን እንዲህ ያሉ አስተያየቶች፣ ጥያቄዎችና ትንተናዎች መዝለቅ የቻሉት ለተወሰኑ ቀናት ብቻ ነበር፡፡ ምክንያቱም የኤርትራ ምላሽ ያው እንደተለመደው የአልጀርስ ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሳይደረግ የሚኖርና ምንም ዓይነት ድርድር የለም የሚል በመሆኑ ነው፡፡

በዚህም ምክንያት በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያው ተንሰራፍተው የነበሩ የተስፋ ጭላንጭሎች ቀናት ሳያስቆጥሩ ከሰሙ፡፡ የሁለቱ አገሮች ግንኙነትም ከዚህ ቀደም ወደሚታወቅበት ጦርነትም ሰላምም የሌለበት ፍጥጫ ተመለሰ፡፡

ሁኔታው እንዲህ ባለ ሁኔታ እንደቀጠለ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. አስቸኳይ ስብሰባውን ያካሄደው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ የኢትዮ ኤርትራን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና የአልጀርሱን የሰላም ስምምነት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ እንደሚቀበል በመግለጽ፣ በሁለቱ አገሮች መካከል የሰፈነውን ጦርነትም ሰላምም የሌለበትን ሁኔታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሔ ለመስጠት መወሰኑን ይፋ አደረገ፡፡

ይህ ውሳኔ ይፋ ከሆነ በኋላ ከኢትዮጵያ ወገን ለሚነሱ ማናቸውም ዓይነት አስተያየቶች ፈጣን ምላሽና ትችት በመስጠት የሚታወቀው የኤርትራ መንግሥት ዝምታን መምረጡ፣ ጉዳዩን በቅርብ ለሚከታተሉ ተንታኞችም ሆነ ለአብዛኛው ሕዝብ እንግዳ ነገር ነበር፡፡

ረቡዕ ሰኔ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ማለዳ ግን በኢትዮጵያና በኤርትራ ቀጣይ ግንኙነቶች ላይ ከፍተኛ ድርሻ የሚኖረው ምላሽ ከኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተሰማ፡፡ ፕሬዚዳንቱ የኤርትራ የሰማዕታት መታሰቢያ ቀንን አስመልክቶ ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ኤርትራ በኢትዮጵያ ያለውን ለውጥ የሚገመግምና ወደ ፊት ሲኖሩ የሚችሉ ውይይቶችን የሚያመቻች የልዑክ ቡድን ወደ አዲስ አበባ ትልካለች፤›› ሲሉ የመንግሥታቸውን ዝምታ ሰበሩት፡፡

ይህንንም ተከትሎ በርካቶች የተለያዩ አስተያየቶችን እየሰጡ ነው፡፡ በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተላለፈው ውሳኔ በፓርቲው ታሪክ ብዙም ያልተለመደና ፓርቲው ከሚታወቅበት የዴሞክራሲዊ ማዕከላዊነት ባፈነገጠ መንገድ ሕወሓት ያለውን ቅሬታ አስታውቆ ነበር፡፡

ነገር ግን ከቀናት በኋላ ደግሞ ሰኔ 14 ቀን 2010 ዓ.ም. በትግራይ ሰማዕታት መታሰቢያ ቀን ዋዜማ መግለጫ የሰጡ የሕወሓት ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ ‹‹የአልጀርሱን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑ በሁለቱ አገሮች ድንበር መካከል የቆየውን ዝምታ የሰበረ ነው፤›› በማለት ውሳኔው መልካም እንደሆነ በመጥቀስ፣ በውሳኔው ላይ ያላቸውን አንድነት ገልጸዋል፡፡

በዚህ ሁሉ መሀል ኤርትራ የልዑካን ቡድን ወደ አዲስ አበባ እንደምትልክ መወሰኗን ካስታወቀች በኋላ በርካታ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ ኤርትራውያን በተለይ በማኀበራዊ ሚዲያው ደስታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ የተለየ ሐሳብ የሚያንፀባርቁ ዜጎችም እንደሁ በዚሁ የመገናኛ መድረክ ሐሳባቸውን እያጋሩ ይገኛሉ፡፡

የኤርትራ መንግሥት የልዑክ ቡድን እንደሚልክ መወሰኑ ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረላቸው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ወደ አዲስ አበበ የሚመጡትን ልዑካን ወንድማዊ በሆነ ታላቅ አክብሮት ተቀብለው ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግርኛ ባስተላለፉት መልዕክት የተሰማቸውን ጥልቅ ደስታ ከመግለጽ ባለፈ፣ የኤርትራ መንግሥት ይህን ውሳኔ ተቀብሎ ልዑክ ለመላክ መወሰኑ ለሁለቱ አገሮች ቀጣይ ወንድማማችነትና ሰላም የሚኖረውን ጠቀሜታም ጠቁመዋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የደስታ መልዕክት በተጨማሪም፣ ጉዳዩ በዓለም አቀፍ ተቋማትም ሆነ በኃያላን መንግሥታት ዘንድ ይሁንታንና አድናቆት ተችሮታል፡፡

በዚህም መሠረት ጉዳዩን አስመልክቶ መግለጫ ያወጣው የአሜሪካ መንግሥት ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት፣ ውሳኔው ከሁለቱ አገሮች ባለፈ በአጠቃላይ ለቀጣናው ሰለምና ደኅንነት መስፈን የሚኖረው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ለመቀበል መወሰኗን፣ እንዲሁም የኤርትራ ፕሬዚዳንት የኢትዮጵያ መንግሥትን ውሳኔ በመደገፍና የሰላም ጥረቱን ለማገዝ ከፍተኛ የአገራቸውን ልዑክ ወደ አዲስ አበባ ለመላክ መወሰናቸውን አድንቋል፡፡

በተመሳሳይ በሁለቱ አገሮች መካከል የተጀመረውን የመደራደርና የመወያየት ፍላጎት ያደነቁት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ ማህማት፣ የሁለቱን አገሮች ሰላም ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶችን እንደሚያግዙም ቃል ገብተዋል፡፡

በሁለቱ አገሮች መካከል የሚኖረው ዘላቂ ሰላም ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ለመላው አፍሪካ ሰላም መስፈን ከፍተኛ ተምሳሌታዊ አስተዋጽኦ እነደሚኖው ገልጸዋል፡፡            

የሁለቱን አገሮች መንግሥታት ውሳኔዎች ያደነቁት የተባበሩት መንግሥታት ድርጀት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ ሁለቱ አገሮች ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከርና ለማሻሻል ለጀመሩት ሥራ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ተመድ ዝግጁ መሆን አስታውቀዋል፡፡

የአውሮፓ ኅብረትም የሁለቱ አገሮችን ውሳኔ የደገፈ መሆኑን በመግለጽ፣ የሰላም ጅማሮው ተጠቃሚ የሚያደርገው ሁለቱን አገሮች ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ነው ብሏል፡፡ ኅብረቱ ወደፊት ለሚኖሩ የሰላም ሥራዎች የሚያስፈልጉ እንቅስቃሴዎችን እንደሚደግፍ ይፋ አድርጓል፡፡ 

ይህ በዓለም አቀፍ ተቋማትና በኃያላን መንግሥታት ከፍተኛ ሙገሳ የተቸረውን ስምምነት በአገር ውስጥ የሚገኙ ፖለቲካ ተንታኞች፣ ምሁራንና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የአዲስ ምዕራፍ የመጀመርያ መሆኑን ከመጥቀስ ባለፈና መልካም ውሳኔ መሆኑን ከመግለጽ በዘለለ፣ የኢትዮጵያ መሠረታዊ መብቶች በተለይም የባህር በር መብት ጉዳይን በተመለከተ ወደ አዲስ አበባ ከሚመጡት የኤርትራ መንግሥት ልዑካን ጋር መንግሥት ሊመክር እንዲሚገባ አሳስበዋል፡፡

ሁለቱ አገሮች በዚህ ደረጃ ለውይይት ዝግጁ መሆናቸውን፣ የኤርትራ መንግሥትም ልዑኩን ወደ አዲስ አበባ ለመላክ መወሰኑ መልካም ጅማሬ እንደሆነ የገለጹት ታዋቂው የሕግ ምሁርና ፖለቲከኛ፣ እንዲሁም ‹‹አሰብ የማናት?›› የሚለው መጽሐፍ ጸሐፊ ያዕቆብ ኃይለ ማርያም (ዶ/ር)፣ ነገር ግን ከተደራዳሪዎች ጋር የኢትዮጵያን ዘላቂ መብቶች ከግምት ያስገቡ ጉዳዮች ላይ መወያየት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

‹‹ወደ አዲስ አበባ ከሚመጡት ተደራዳሪዎች ጋር በሚኖረው ውይይት መነሳት ከሚኖርባቸው ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው መሆን የሚኖርበት፣ የኢትዮጵያ ወደ ባህር በር የመዝለቅ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ላይ ድርድርና ስምምነት መደረግ አለበት፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ለዚህም የሚሰጡት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ የኢትዮጵያ የባህር በር የመጠቀም መብት ጥያቄ ምላሽ የሚሻ በመሆኑ፣ በተለያዩ ጊዜያት ሊነሱ ከሚችሉ ጥያቄዎች ዋነኛው በመሆኑ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ማንም ኢትዮጵያዊ የሚዘለው ጉዳይ አይደለም፡፡ ዛሬ ባይነሳ ነገ መነሳቱ የማይቀር ጉዳይ ነው፤›› በማለት በዚህ ጉዳይ ላይ ዘለቄታዊ መፍትሔ ማበጀት ለሁለቱ አገሮች ቀጣይ ሰላም፣ ወንድማማችነትና አብሮ የማደግ ህልምና ውጥን የሚኖረውን የጎላ ሚና በመጥቀስ፣ የአሰብ ጉዳይ በአጀንዳነት መነሳት የሚኖርበትን ምክንያት አቅርበዋል፡፡

አዲስ የተቋቋመው የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ፓርቲ (ኢሃን) ሊቀመንበር አቶ ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር)፣ ጉዳዩ በዚህ ወቅት የተነሳው በሁለቱ አገሮች መሪዎች ለሰላም ፍላጎት ስላላቸው ሳይሆን፣ በውጭ ግፊት ምክንያት ነው በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በተለይም ደግሞ የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ተጠባባቂ ረዳት ጸሐፊ ዶናልድ ያማሞቶ በተደጋጋሚ ወደ ቀጣናው መምጣት፣ ሁለቱ አገሮችን ግፊት ውስጥ በመክተት ይህን እንዲፈጽሙ አስገድዷቸዋል በማለት፣ የሁለቱን አገሮች የሰላም ድርድር በጥርጣሬ ተመልክተውታል፡፡

አዲስ የተቋቋመው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)፣ በጉዳዩ ላይ ፓርቲያቸው አለመወያየቱንና አቋም አለመያዙን አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ ለመወያየትና ለመደራደር የሚያስችል አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ደርሰዋል፡፡ ይህ የታሪክ አጋጣሚ የሁለቱን ወንድማማች ሕዝቦች ጥቅምን ባስጠበቀ መንገድ መጠቀም፣ በአጠቃላይ ለቀጣናው የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነ በብዙዎች እየተገለጸ ነው፡፡ ቀጣይ ድርድሮች የሚያመጡትን ውጤት ደግሞ በጊዜ ሒደት የሚታይ በመሆኑ፣ የሁለቱ አገሮች ዳግም ግንኙነት ጅማሬ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -