የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በአዲስ አበባ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባደረገው ስብሰባ፣ የድርጅቱ ሊቀመንበር በመሆን ከየካቲት 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ከኃላፊነታቸው ለቀቁ፡፡
አቶ ሽፈራው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርና የደኢሕዴን ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ተክተው ነበር ወደ ሊቀመንበርነት የመጡት፡፡
አቶ ሽፈራው በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተዋቀረው አዲሱ ካቢኔ የግብርናና የእንስሳት ሀብት ልማት ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ይታወሳል፡፡
በቅርቡ በደቡብ ክልል በሐዋሳ፣ በወላይታ ሶዶና በወልቂጤ ከተሞች በተከሰቱ ግጭቶች በርካቶች በመሞታቸውና በመፈናቀላቸው ምክንያት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልሉ በተዋረድ ያሉ ባለሥልጣናት ከሥልጣናቸው በገዛ ፈቃዳቸው እንዲሰናበቱ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡