ቅዳሜ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተዘጋጀው የድጋፍና የምሥጋና ሥነ ሥርዓት ላይ በተፈጸመው የቦምብ ጥቃት ሕይወታቸው ላለፈ ወገኖች ሐዘናችንን እየገለጽን ለቤተሰቦች መፅናናትን፣ ጉዳት የደረሰባቸው ደግሞ በፍጥነት እንዲያገግሙ መልካም ምኞታችንን እንገልጻለን፡፡ ይህ ዓይነቱ የአውሬነት ድርጊት ዳግም እንዳይፈጸም በአፅንኦት እናሳስባለን፡፡ በወቅቱ በተፈጸመው የቦምብ ጥቃት ላይ ምርመራ ተጀምሯል፡፡ ምርመራው በኢትዮጵያዊያን የመስኩ ባለሙያዎችና በአሜሪካ የፌዴራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ጭምር እየተከናወነ ነው፡፡ የምርመራውን አጠቃላይ አፈጻጸም ለባለሙያዎች በመተው፣ ጥንቃቄ ላይ እናተኩራለን፡፡ የቅዳሜው የቦምብ ጥቃት የሚጠቁማቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱና ዋነኛው በዕለቱ ነበረ የተባለው የደኅንነት ክፍተት ነው፡፡ ይህ ክፍተት የተፈጠረው ሆን ተብሎ? በቸልተኝነት? ወይስ ለጥንቃቄ የተሰጠው ቦታ አናሳ በመሆኑ ነው? ሚሊዮኖች በተሰባሰቡበት ሥነ ሥርዓት ላይ የነበረው ፍተሻም ከዚህ በፊት ከነበሩት የላላ እንደነበር፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩና እንግዶች በነበሩበት መድረክና በሠልፉ ተሳታፊዎች መካከል የነበረው ርቀት በጣም የተቀራረበ ስለመሆኑ ብዙ ተብሏል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ቦምብን የሚያህል ነገር ተወርውሮ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ በበርካታ ዜጎች ላይ ግድያ ቢፈጸም ኖሮ ሊደርስ የሚችለው መጠነ ሰፊ ጥፋት ይዘገንናል፡፡ የጥንቃቄ ጉዳይ ትኩረት የሚያስፈልገው ለዚህ ነው፡፡
በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ የማይፈልጉና ጥቅማቸው እንደሚነካባቸው በሚሠጉ፣ ወይም ራሳቸውን የለውጡ አካል አስመስለው የተለየ ፍላጎት በሚያራምዱ፣ እንዲሁም ባኮረፉ አካላት ሳይቀር የተፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል መጠርጠር ይገባል፡፡ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር በአንድነት ቆሞ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፉን ሲገልጽ፣ የኢትዮጵያን አንድነትና ጥንካሬ የማይፈልጉ ኃይሎች ድርሻም መዘንጋት የለበትም፡፡ ሕዝቡን በብሔርና በእምነት ለመከፋፈል ከሚያሰፈስፉ ጀምሮ፣ ልዩነቶችን በማጦዝ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚተጉም እንዳሉ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ ወዳጅ ያሉት ጠላት እንደሚሆንም መገንዘብ ብልህነት ነው፡፡ የፀጥታና የደኅንነት ክፍተቱን በሚገባ የሚያውቁና የተጀመረውን ለውጥ ለማጨናገፍ የተለየ ዓላማ ያላቸው አይኖሩም ማለት ደግሞ የዋህነት ነው፡፡ አሁን ዋናው ጉዳይ ጥንቃቄን በተመለከተ መሆን አለበት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተቻለ መጠን በልዩ ልዩ ሥፍራዎች የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች ከአደጋ ነፃ ለማድረግ የፀጥታና የደኅንነት መዋቅሩን ማፅዳትና ማደራጀት፣ ለበለጠ አደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉ ክፍተቶችን በመድፈን የለውጥ ሥራዎች ላይ ማተኮር ይኖርባቸዋል፡፡ ጥንቃቄ በሌለበት አንድ ዕርምጃ መራመድም አይቻልምና፡፡
የበቀደሙ የቦምብ ጥቃት ከበስተጀርባው ብዙ ጥያቄዎች ይነሱበታል፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙት በተጠናከረ የምርመራ ሥልት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙዎችን ሥጋት ውስጥ ከሚከቱ የአደጋ ቀጣናዎች ራሳቸውን እየጠበቁ፣ አገሪቱን ወደ አደጋ ሊመልሱ የሚችሉ ድርጊቶች እንዳይከሰቱ ጥንቃቄ ቢያደርጉ ይመከራል፡፡ በውትድርናና በደኅንነት ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት አገልግሎት ለሰጠ ሰው ይኼንን አድርግ፣ ያንን አታድርግ ብሎ ማሳሰብ የዋህነት ወይም አላዋቂነት ቢመስልም፣ እያንዳንዱ ዕርምጃ በጥናትና በስክነት ሊከናወን እንደሚገባ ሐሳብ ማቅረብ ግን ተገቢ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍቅር እንደሚያሸንፍ በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡ ፍቅር ማሸነፍ የሚችለው ግን ጥንቃቄ ሲታከልበት ነው፡፡ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉም ሆነ ከሌሎች በምርመራ ወቅት የሚገኘው መረጃ ወይም ፍንጭ ለጥንቃቄ እጅግ በጣም ጠቃሚ ስለሚሆን፣ ለስሜታዊነት ክፍተት መስጠት ተገቢ አይደለም፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ ድጋፍ እየሰጡ ያሉ ወገኖችም ከስሜታዊነትና ከመላምቶች በመላቀቅ ጠቃሚ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የተጀመረው ለውጥ ስኬታማ የሚሆነው ማስተዋልና ማገናዘብ ገዥ ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡ ስሜታዊነትና ግብታዊነት ለውጡን ለማደናቀፍ ካልሆነ በስተቀር ፋይዳ የላቸውም፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡
እዚህ ላይ አፅንኦት ሊሰጠው የሚገባው መሠረታዊ ጉዳይ ለውጡ ያስፈለገበት ምክንያት ነው፡፡ እንደሚታወቀው በሺዎች ለሚቆጠሩ እስረኞች ክስ ማቋረጥ፣ የፀና የመጨረሻ የሞት ፍርድና ቅጣት የተወሰነባቸውን ወገኖች ጨምሮ ለብዙ ሺሕ ፍርደኞች ከእስር ቤት እንዲወጡ ማድረግ፣ እንዲሁም እየተረቀቀ ላለው አዲስ የምሕረት አዋጅ መውጣት መንስዔ የሆነው በኢትዮጵያ የሕግ፣ የፍትሕና የዳኝነት ሥርዓት ውስጥ የታየው የከፋ ፖለቲካዊ ገመና ነው፡፡ ሕግና ፍትሕ ለመንግሥታዊ አመፅ፣ በደልና የግፍ ዱላ ሆኖ በማገልገሉ ነው፡፡ እስራት፣ ክስና ፍርድ እንደ ልቦለድ እየተደረሰ የሚከናወን በመሆኑ ነው፡፡ ገለልተኛና ኢወገናዊ ያልሆነ የመንግሥት አውታር ባለመገንባቱ ነው፡፡ ከኢሕአዴግ ውስጥ የተፈለቀቀውና በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የሚመራው የለውጥ ኃይል፣ በተለይም የገዥው ፓርቲ ዋና ችግር የሆነውን ወደ ተፎካካሪነት የመለወጥና ይህ የሚጠይቀውን አስተሳሰብ፣ ምግባርና ጨዋነት ማስያዝና በሕግ ውስጥ ማጠር ደግሞ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት ጋር የተገናኘ ታላቅ ዕርምጃ ነው፡፡ የሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የድጋፍ ሠልፍም የዚህ መግለጫ ነበር፡፡ ይህንን የሕዝብ ፍላጎት ከግብ ለማድረስ ጥንቃቄ አስፈላጊ ነው፡፡
የቦምብ ጥቃቱ ይኼንን ተስፋ የሚቀናቀን መሆኑን በመገንዘብ፣ በጥቃቱ የተጠረጠሩ ሰዎች ጉዳይ አንዱ መፈተኛ ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር እስካሁን ድረስ በጥርጣሬና በጥላቻ የሚመራ ስድብና የሚዲያ ‹‹ዜና›› ብቻ በቂ ማስረጃ ሆኖ ያለ ጥፋት ሲበየን፣ እስራት ሲፈረድና ‹‹ጊዜ ቀጠሮ›› እየተባለ እንግልት ሲደርስ በስፋት ይታወቃል፡፡ የስሜት ፍርድ ያልተጫነው እውነተኛ የሕግ አግባብ ጠፍቶ ለጅምላ ውንጀላና ለጅምላ ይቅርታ ሲዳርግም እንዲሁ፡፡ ይህ በዚህ ጊዜ በጭራሽ መደገም የለበትም፡፡ የፍትሕና የዳኝነት ሥርዓቱ ነፃነቱ በአግባቡ ተጠብቆ ከነበረበት አረንቋ ውስጥ መውጣት አለበት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በተደጋጋሚ እንደገለጹት፣ ከዚህ ዓይነቱ ጨለማ ውስጥ በመውጣት ኢትዮጵያን ወደ ታላቅነቷ መመለስ ጊዜ የማይሰጠው ታላቅ ተግባር ነው፡፡ ለዚህም ሲባል ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ ‹‹አስተውሎ የሚራመድ ካሰበበት ይደርሳል›› እንደሚባለው፣ የለውጡ ጉዞ ስኬታማ መሆን የሚችለው ለጥንቃቄ ልዩ ትኩረት ሲሰጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች የነገዋን ባለ ተስፋ አገር መሠረት ለመጣል ሲሹ፣ ከስሜታዊነት ይልቅ ለምክንያታዊነት በቂ ሥፍራ መስጠት አለባቸው፡፡ የጥንቃቄ መነሻም ይኸው ነው፡፡
ዘወትር እንደምንለው ኢትዮጵያ በርካታ መልካም አጋጣሚዎች ያመለጧት ከጥንቃቄ ጉድለትና ከጥድፊያ ነው፡፡ ጥንቃቄ የጎደለው ዕርምጃ ጥድፊያ ሲታከልበት ውጤቱ ተያይዞ መውደቅ ነው፡፡ ሕዝብ ሰከን ብሎ መሪው በማስተዋልና በመረጋጋት ወደሚፈልገው እንዲወስደው ማገዝ አለበት፡፡ የአገር ግንባታውና ነፃ ማኅበረሰብ የመፍጠር ጉዞው እንዳይደናቀፍ ለጥንቃቄ ትልቅ ዋጋ መስጠት ይገባል፡፡ ባለፈው ቅዳሜ ምኑም ባለየለት ቅጽበታዊ የአደጋ ወቅት ለሕይወታቸው ሳይሳሱ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሕይወት ለመታደግ የተረባረቡ ወጣቶች፣ የነገዋ ኢትዮጵያ ስለምታስፈልጋቸው ነበር ያንን ወደር የሌለው ቁርጠኝነት ያሳዩት፡፡ የነገዋ የበለፀገችና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ዕውን መሆን የምትችለው ደግሞ በሕዝብ መካከል ቁርሾ እንዳይፈጠር በማድረግ፣ ከልዩነት ይልቅ አንድነትን በማፅናት፣ ስሜት ወለድ የሆኑ አሉባልታዎችንና ሐሜቶችን ከማሠራጨት በመቆጠብ፣ በአፍ ብቻ ሳይሆን በተግባር ጭምር አገር በመውደድና የፍትሕና የርትዕ ጠበቃ በመሆን ነው፡፡ ይኼንን ማሳካት ሲቻል ታላቅ አገርና ታላቅ ሕዝብ የመሆን ምኞት በተግባር ይረጋገጣል፡፡ ይህ ምኞት በገቢር እንዲታይ ከላይ እስከ ታች ጥንቃቄ ያስፈልጋል!