Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየደኢሕዴን ጽሕፈት ቤት ወደ ደቡብ ከተዛወረ አፈ ጉባዔዋ ከኃላፊነታቸው እንደሚለቁ ተጠቆመ

የደኢሕዴን ጽሕፈት ቤት ወደ ደቡብ ከተዛወረ አፈ ጉባዔዋ ከኃላፊነታቸው እንደሚለቁ ተጠቆመ

ቀን:

አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የለቀቁት በክልሉ ሕዝብ ተቃውሞ ነው ተባለ

የደኢሕዴን ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ለቀቁ

አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ጽሕፈት ቤት ወደ ክልሉ ከተዛወረ፣ ሰኞ ሰኔ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. የንቅናቄው ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ከኃላፊነታቸው ተነስተው ወደ ደቡብ ክልል እንደሚሄዱ ተጠቆመ፡፡

ከደኢሕዴን ሊቀመንበርት የለቀቁትን አቶ ሽፈራው ሽጉጤን በመተካት ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት አፈ ጉባዔ ሙፈሪያት ካሚል፣ የደኢሕዴን ጽሕፈት ቤት ወደ ክልሉ ከተዛወረ ሁለቱንም ኃላፊነት መወጣት ስለሚያስቸግራቸው እንደሚለቁ የሪፖርተር ምንጮች ተናግረዋል፡፡

ሁለቱም የሥራ ዘርፎች ማለትም የድርጅቱ ሊቀመንበርና የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ መሆን የሙሉ ጊዜ ሥራ በመሆናቸውና ደርቦ መሥራት ስለማይቻልና ኃላፊነታቸውን በብቃት ለመወጣት አዳጋች እንደሚሆንባቸው አክለዋል፡፡ ከሁለት አንዱን መልቀቅም ግድ ሊሆን እንደሚችል ምንጮች ትክክለኛ ነው ያሉትን ግምት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የግብርናና የእንስሳት ሀብት ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ ወጣትና አዲስ አመራር ተክቷቸው እንዲሠራ በሚል ምክንያት በራሳቸው ፈቃድ ከደኢሕዴን ሊቀመንበርነታቸው መልቀቃቸውን ሰኞ ሰኔ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. የገለጹ ቢሆንም፣ ሥልጣናቸውን የለቀቁት በክልሉ ሕዝብና በንቅናቄው አባላት በደረሰባቸው ተፅዕኖ መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደተናገሩት፣ የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ‹‹ፊቼ ጫምባላላ›› በዓል ላይና ከዚያም በፊት በወላይታና በሲዳማ ማኅበረሰቦች መካከል ግጭት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ከግጭቱ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የግጭቱን ምክንያት ለማወቅና በሁለቱ ማኅበረሰብ መካከል ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ከማኅበረሰቡና ከአካባቢው ሽማግሌዎች ጋር ለመነጋገር በክልሉ መገኘታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ የአገር ሽማግሌዎች የችግሩን መነሻ ለማወቅና የመፍትሔ ሐሳብ እንዲያቀርቡ ጥያቄ ሲያቀርቡላቸው፣ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ከኃላፊነታቸው እንዲለቁላቸው ጥያቄ ሲያነሱ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉንም የመገናኛ ብዙኃን ከአዳራሽ አስወጥተው ውይይቱ መካሄዱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የአገር ሽማግሌዎቹ ሁሉንም ችግር አንስተው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዳራቸውን በሲዳማ እንደሚያደርጉ የታወቀ ቢሆንም፣ ምንም ሳይሉ ወደ ሐዋሳ ተመልሰው በማግሥቱ ወደ ወልቂጤ ማምራታቸውንም ጠቁመዋል፡፡ በወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎችና በቀቤና ተወላጆች መካከል ተነስቶ ስለነበረው ግጭት ሲያወያዩ፣ ስለሲዳማና ወላይታ ግጭት ከአገር ሽማግሌዎች ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ባገኙት መረጃ መሠረት እንደ ኢሕአዴግ ሊቀመንበርነታቸው፣ ደኢሕዴን በማኀበረሰቡ መካከል ስለተነሳው ግጭት የየዞኖቹን አመራሮች አነጋግሮ፣ ከኃላፊነታቸው በፈቃዳቸው እንዲለቁ እንዲያደርግ ማሳሰቢያ መስጠታቸውንና ይለቃሉ የሚል እምነትም እንዳላቸው፣ የክልሉ ፕሬዚዳንትን እየጠቆሙ መናገራቸውን አስታውሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማሳሰቢያ መሠረት የደኢሕዴን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ስብሰባውን አድርጓል፡፡ በወቅቱ በተደረገ ውይይት የደኢሕዴን ጽሕፈት ቤት ከአዲስ አበባ ወደ ክልሉ መዛወር እንዳለበትና ሊቀመንበሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤም ሄደው እንዲሠሩ ጥያቄ መቅረቡን ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡ ምናልባትም አቶ ሽፈራው በፈቃዳቸው ለመልቀቅ የወሰኑት በዚህ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ አክለዋል፡፡

ከሁለት ወራት በፊት ንቅናቄው ባደረገው የማዕከላዊ ኮሚቴ እልህ አስጨራሽ ውይይት፣ አቶ ሽፈራው የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትርና የደኢሕዴን ሊቀመንበር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ተክተው መመረጣቸውን አስታውሰዋል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊቀመንበርነታቸውን ለቀውና ከሥራ አስፈጻሚነት ዝቅ  ብለው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በመሆን ለመሥራት መወሰናቸው፣ እሳቸው እንዳሉት ወጣቱን ወደ አመራርነት ለማምጣት ሳይሆን በተለያዩ ተፅዕኖዎች ምክንያት ውሳኔ ላይ ሳያደርሱ እንዳልቀረ ግምታቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡         

አቶ ሽፈራው ከደኢሕዴን ሊቀመንበርነታቸው በለቀቁ ማግሥት የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ፣ ከደኢሕዴን ምክትል ሊቀመንበርነታቸውን በፈቃዳቸው ለቀዋል፡፡ አቶ ሲራጅ በራሳቸው ፈቃድ ከመልቀቃቸው በስተቀር ለምንና በምን ምክንያት እንደሆነ ማብራሪያ አልተሰጠም፡፡

የደኢሕዴን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በአቶ ሲራጅ ምትክ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስን ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡ አቶ ሚሊዮን ከዚህ በፊት የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ፣ የሲዳማ ዞን አስተዳደሪና የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሆነው መሥራታቸው ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...